አባይ ለኛም የምግብ ዋስትናችን ነዉ

Print Friendly, PDF & Email

(በኢ/ር ብሩ ኢቲሣ)

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ዉሃ አመንጭ አገር ናት፡፡ በመሆኑም የአባይ ወንዝ የዉሃ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ የአባይ ወንዝ ድንብር ተሻጋሪ ወንዝ ነዉ፡፡ ስለሆነም የዉሃ አጠቃቀሙ የተፋሰሱን ግርጌ አገራት የዉሃ ፍላጎት ያገናዘበና በስምምነት መሆን ያለበት ነዉ፡፡ ይህ ማለት ግን አባይ የጋራ ሀብት ነዉ ማለት አይደለም፡፡ አባይ የኢትዮጵያ ሀብት ነዉ፡፡ ዉሃዉ የጋራ ሃብት ሊሆን የሚችለዉ አንዳንድ ምሁራን እነደሚያንፀባርቁት ወደፊት የተፋሰሱ አገራት ለበለጠ የጋራ ኢኮኖሚ እድገት እና ልማት ተጠቃሚ ለመሆን አሁን ያለዉን ሉኣላዊ ግዛታቸዉን በፍላጎታቸዉ ትተዉ ተፋሰሱን እንደ አንድ የሃይድሮሎጂ አሀድ በመዉሰድ በስምምነት አንድ የጋራ መንግስት ሲያቋቁሙ ብቻ ነዉ፡፡ ይኸ የወደፊት የእሩቅ ህልም ሊሆን ይችላል፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባሉበት አካባቢዎች ሁሉ በዉሃ አጠቃቀም ላይ ከጥንት ጀምሮ ዉዝግቦች፤ግጭቶች እና አልመግባባቶች ነበሩ፡፡

መጀመሪያ ላይ የየተፋሰሱ አገሮች በየወቅቱ ሲከሰቱ የነበሩትን ግጭቶች እና ዉዝግቦች ሲፈቱ የኖሩት በየአካቢያቸዉ ልማዳዊ ህጎች ላይ በመመርኮዝ ነበር፡፡ በኋላም ዓለም አቀፍ የዉሃ አጠቃቀም ህጎች ቀስ በቀስ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ከሄልሲንኪዉ 1966/እ.አ.አ/ ዓለም አቀፍ የዉሃ አጠቃቀም ህግ (the 1966 Helsinki Rules) ጀምሮ ፤ የ1997ቱን/እ.አ.አ/ የተባበሩት መንግስታት ስምምነትን (the 1997 UN Convention on International Water courses) አካቶ እሰከ 2004ቱ/እ.አ.አ/ የበርሊኑ ህግ (the 2004 Berlin Rules) ድረስ ዓለም አቀፉ የዉሃ ህጎች ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ ነዉ የመጡት፡፡ የሄልሲንኪዉ ሩልስና የተባበሩት መንግሰታቱ ኮንቬንሽን በዉሃ ‘’ፍትሃዊ አጠቃቀም‘’ እና ‘‘የማይጎዳ አጠቃቀም‘‘ አንቀፆቹ ላይ የደበዘዙ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል የበርሊኑ ሕግ በፍተሃዊ አጠቃቀም እና አንዱ ሌላዉን እነዳይጎዳ የታከሉት የዉሃ ክፍፍል አንቀፆች ላይ በትልቁ ተሻሽለዉ ተፅፈዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የዉሃ አጠቃቀም ድርድር የበርሊኑ ሩልስ የተሻለ እና ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ ነዉ ሚታየዉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ዓለም አቀፍ የዉሃ አጠቃቀም ህጎችን ዶ/ር አሮን ተስፋዬ The Political Economy of the Nile Basin Regime in the Twentieth Century በሚለዉ መጽሀፋቸዉ ዉስጥ በስፋት ተንትነዋል፡፡

በቅርቡ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብፆች በዝግ ስበስባ ሲዶልቱብንና ሲፎክሩብን የነበረዉ አምልጦ ወጥቶ አለም ሰምቶታል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ሲያካሄዱብን የነበረዉ ደባቸዉና ተንኮላቸዉ ተጋለጧል፡፡ ወደፊት ከግብፅ ጋር የሚደረጉ ንግግሮችም ሆኑ ድርድሮች ኃይል ማመንጨትን ብቻ ሳይሆን መስኖ ልማትንም ያካተቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የህዳሴዉ ግድብ በዉሃዉ በኩል ሙሉ በሙሉ ግብፅን እና ሱዳንን የሚጠቅም ሲሆን፤ በኢነርጂ ብኩል በከፊል ሁለቱንም የሚጠቅም ነዉ፡፡

በአባይ ሸለቆ ዉሰጥ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እ.አ.አ ከ1958 መጀመሪያ አንስቶ እስከ ጁን 30 1963 ድረስ በአሜሪካ ዓለም አቀፍልማት ድርጅት እርዳታ በተከናወነዉ ጥናት 33 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተለይተዉ ታዉቀዋል፡፡ ከዚህም ዉስጥ 8ቱ ሁለገብ (ለመስኖ እና ኃይል ማመንጫ)፤14ቱ ለመስኖ ብቻ፤ እና 11ዱ ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ ናቸዉ፡፡ ሪፖርቱ የተጠናቀቀዉ እ.አ.አ ጁን 30 ቀን 1964 ሲሆን ለኢትዮጵያ መንግሰት የተላከዉ እ.አ.አ ኦገስት 7 ቀን 1964 ነዉ፡፡ የአሜሪካኖቹ ጥናት

መስኖን በተመለከተ እስከ 433,754 ሄከታር ሊለማ እንደሚችል ሲያመለክቱ፤ በኋላ በተደረጉ ጥናቶች ግን ከ 1 ሚልዮን ሄከታር በላይ፡ ለማልማት እንደሚቻል ታዉቋል፡፡ ኃይል ማመንጫን በተመለከተ አምሪካኖቹ ያመለከቱት ወደ 7,000 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚቻል ነበር፡፡ በኋላ ግን ወደ 9,000 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚቻል ነዉ የታወቀዉ፡፡ እነኚህን ልማቶች መተግበር የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ማለት ይሆናል፡፡አጠቃላዩን ኢትዮጵያ ዉሰጥ ከ 3.6 ሚልዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል እና በዉሃ ኃይልም በኩል ከ 30,000 – 45,000 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚቻል አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በአባይ ሸለቆ ዉስጥ በአሜሪካ መንግስት እርዳታ በተደረገዉ ጥናት መሰረት ከላይ ከተዘረዘሩት ሁለገብ ፕሮጀከቶች ዉሰጥ ኢትዮጵያ እሰከዛሬ ልትገነባ የቻለችዉ ፍንጫኣን እና የጣና ሐይቅ ዉሃ ወደ አባይ በሚገባበት ቦታ ላይ የዉሃ ልቀት የመቆጣጠርያ ግድብ በመስራት የጣናን ዉሃ ከፍታ በ2.5 ሜትር በመጨር የሐይቁን ዉሃ በምእራብ በኩል ወደ ላይኛዉ ብር ሸለቆ ራስጌ በመቀልበስ የሐይቁን ዉሃ ለሃይል ማመንጫ እና ለመስኖ ልማት ማዋልን ብቻ ነዉ፡፡

የጣና ሐይቅ ዉሃ ልቀት መቆጣጠርያ ግድብ የተጀመረዉ በ1975 ዓ.ም አካባቢ በደርግ ዘመን ነዉ፡፡ግድቡን ጀምረን ግድቡ በሚያርፈት ቦታ ዉሃ በግድቡ ሥር እነዳይሰርግ ለመከላከል በግድቡ መሠረት ሥር ያሉትን ክፈተቶች በሲሚንቶ የመድፈን ሥራ (Grouting) ጀምረን በማጣደፍ ላይ እያለን አንድ ቀን በድንገት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጓድ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ብዙ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን አስከትለዉ ከተፍ አሉ፡፡ስለፕሮጀከቱ በቦታዉ ላይ በሥዕል በተደገፈ ከሥራ ጓዶቼ ጋር ገለፃ አደረግንላቸዉ፡፡እርሳቸዉም ስለፕሮጀከቱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ከጠየቁ በኋላ ዉሃዉን የምታመቻቹት ለታሪከ ጠላቶቻችን ጥቅም ስለሆነ ብለዉ አሉና፤ ፕሮጀክቱ እንዲቆም አዘዙ፡፡እኔም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን ብቻ የምጠቅም መሆኑን እና ከጣና የሚወጣዉ ዉሃ ሱዳን ጠረፍ የሚደርሰዉ እጅግ በጣም አነስተኛ መጠን ያለዉ (minimal)) መሆኑንና ይህም ፈፅሞ ጉልህ ጥቅም ለሱዳንም ሆነ ለግብፅ እንደማይሰጥ ገልጬ፤ በአባይ ተፋሰስ ተለይተዉ ከታወቁት 33 ትላልቅ ፕሮጀክቶች የፊንጫኣን ሁለገብ ፕሮጀክት ብቻ በመሆኑና በሌላ በኩል ግብፆች የመስኖ ልማታቸዉን በከፍተኛ ደረጃ እያራመዱ በመሆኑ እኛም ቶሎ ቶሎ ብለን የዉሃ ተጠቃሚነታችንን ካለረጋገጥን በአባይ ዉሃ ላይ ያለንን መብታችንን እያጣን ስለምንሄድ፤ይህች ግድብ ትንሽ ብትመስልም ጠቀሜቷ የጣናን የዉሃ ልቀት ዓመቱን ሙሉ በመቆጣጠር የጢስ አባይን ኃይል ማመንጫ ዓመቱን ሙሉ ይመነጭ ከነበረዉ 8 ሜጋ ዋት በአስተማማኝ ወደ 12 ሜጋ ዋት ከፍ እዲል ስለምታደርግና በምእራቡም በኩል የሐይቁ ዉሃ ወደ ላይኛዉ በለስ ራስጌ ለመቀልበስ የምታስችልና 200 ሜጋ ዋት ለማመንጨትና 63,000 ሄከታር መሬት በመስኖ ለማልመት ስለምታስችል የግድቡ ሥራ ቢቀጥል የሚሻል መሆኑን ለማሳመን ሞከርኩ፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለዉ ዉሃ ወደ አባይ የሚገባዉ ከጣና ግርጌ ከሚገኙት መጋቢ ወንዞች እንጂ ከጣና አለመሆኑን ጭምር ገለፅኩላቻዉ፡፡

መከራከሩን ስቀጥል ጠቅላይ ሚኒሰተሩ ትንሽ ቆጣ ማለት ሲጀምሩ የወቅቱ የኮንስትራክሽን ሚኒሰትር የነበሩት ጓድ ካሣ ገብሬ በእግራቸዉ ነካ አደረጉኝ፡፡ ተዉ ማለታቸዉ ገባኝ፡፡ እኔም ዛሬ ባንሠራ ወደፊት አንድ ቀን መሥራታችን አይቀርም፤የጀመርነዉን grouting ሥራ እንኳ እንድንጨርስ ይፈቀድልን አልኩና ዝም አልኩኝ፡፡ ነገሩ በዚሕ ቆመና ባለሥልጣኖቹ መመለስ ሲጀምሩ ጓድ ካሣ ወደ ኋላ ቀረት አሉና grouting ሥራዉን ቀስ ብዬ አሰፈቅጄ እደውልልሃለዉና አሁን የፕሮጀከቱን ሥራ አቁም ብለዉኝ ሄዱ፡፡ አዲስ አበባም እንደ ደረሱ በስልክ ገራዉቲንግ ጨርስና ፕሮጀክቱን ዘግተህ ወደ አዲስ አበባ ተመለስ አሉኝ፤ እኔም የግራዉቲንጉን ሥራ አስጨርሼ ፕሮጀከቱን ዘግቼ ወደ አዲሰ አበባ ተመለስኩ፡፡ የሚገርመዉ ጓድ ፍቅረሥላሴን ካጀቡት ዉስጥ ከጓድ ካሣ በስተቀር እኔን በመደገፍ ሆነ በመቃወም ትንፍሽ ያለ አንድም ባለሥልጣን አልነበረም፡፡ በተመሳሳይ፤ ከአባይ ጋር ግንኙነት ስለሌላቸዉ እዚህ አላነሳም እነጂ በከተሞች መጠጥ

ዉሃ ዙሪያም በአሰብ፤ በጂጂጋ፤ በአሶሳ፤ በአስመራ፤ በምፅዋ፤ በመቀሌ፤ በአዳማ፤ በጊኒር እንዲሁም በሌሎች፤ ብዙ ተመሳሳይ ገጠመኞች አሉኝ፡፡

እንዳጋጣሚም፤ እንዳልኩት ሆነና ኢሕአዴግ እንደገባ ሥራዉን ጀምሮ አስጨረሰዉ፡፡ ይሁን እንጂ እዚሕም ላይ አንድ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የግድቡ ሥራ ጨረታ ወጥቶ ጨረታዉን አንድ የግብፅ ኩባንያ በ 5 ሚልዮን ዶላር አሸነፈ ተባለ፡፡ ግራ ገባኝ፤ ጥርጣሬም ገባኝ፡፡ 5 ሚልዮን ዶላር የመሃንዲሶች ግምት ነበር፡፡ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስተራክሽን ጀምሮት ከነበረዉ ከጣና በለስ ፕሮጀከት ጋር በማያያዝ፤ ጥናቱንና የምሕንድስና የዋጋ ግምቱን ያዘጋጀዉ የጣሊያኑ Studio Peter Angeli ነዉ፡፡ የኢንጂሪንግ ሪፖርቱንና የዋጋ ግምቱን ለግብፆች አሳልፈዉ ይሰጣሉ ብዬ ከግብፆች ጋር የቅርብ ግንኙንት የነበራቸዉን ሁለት ሰዎች ጠረጠርኩ፡፡ ስማቸዉን እዚህ መጥቀሱ አስፈላጊ አይሆንም፤ በአሁኑ ጊዜም በህይወት የሉም፡፡ ወድያዉ ከአቶ ጊድዮን አስፋዉ፤ በወቅቱ የተፈጥሮ ሀብት ሚኒሰቴር የዉሃ ዘርፍ ምክትል ሚኒሰትር ከነበሩ ጋር ተነጋገርንና አቶ ጊድዮንም ሁኔታዉን ለአቶ ታምራት ላይኔ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒሰትር ለነበሩት አስረድተዉ ጨረታዉ ሁለተኛ ለወጣዉ ለበርታ ኩባንያ በ 6 ሚልዮን ዶላር እንዲሰጥ ተደረገና ግብፆች ጣና አባይ ምንጭ እንዳይገቡ ተደረገ፡፡ በዚህም ተገላገልናቸዉ፡፡

እላይ ከተጠቀሱት ፍንጫኣና ላይኛዉ በለስ ፕሮጀከቶች በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ጣና ሐይቅ ዙርያ የርብ፤የጉማራ እና የምእራብ መገጭ የመስኖ ልማት ሥራዎች በጎርጎራ በኩል ተጀምረዋል፡፡ እነኚህ ፕሮጀከቶች ሳይጀመሩ ይኸን ያህል ረጅም ጊዜ መቆታቸዉ ብዙ ምክንያቶች መዘርዘር ይቻላል፤ አንዱ ግን የዉጭ ብድር እንዳናገኝ የግብፅ ተፅእኖ ነዉ፡፡ ግብፆች ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ከፍተኛ ኤከስፐርቶችዋን በኢንተርናሽል ፋይናንስ ተቋማት፤ በተባበሩት መንግሰታት ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ተቋማትና፤ እንዲሁም በሌሎች ልዩ ልዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ዉሰጥ በአላማ ስታሰማራ፤ ኢትዮጵያ በተቃራኒዉ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸዉ ዜጎቿ በተመሳሳይ በራሳቸዉ ጥረት ለአለም አቀፍ ሥራዎች ቢታጩ፤ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ፤ የመንግስት ድጋፍ አያገኙም፡፡ ለወደፊቱ ግን ይህንን ጉዳይ መንግሰት በደንብ ሊያስብበት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ለይ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚደንትነት ታጭተዉ መንግሰት ድጋፍ ስለነፈጋቸዉ ብቻ ለፕሬዚደንትነቱ ቦታ ሳይመረጡ ለቀሩት የአቶ ተካልኝ ገዳሙን ጉዳይ ነዉ፡፡ አያይዤ አንባቢያንን የምጠይቀዉ ፅሁፌ ዉሰጥ ከላይና ከዚህ በታች በስም የጠቀስኳቸዉ ባለሥለጣናትና ከፍተኛ ፕሮፌሽናል ግለሰብ፤ በበጎ መልኩ መሆኑን እንዲረዱልኝ ነዉ፡፡ በኔ በኩል እነኝህ ሰዎች ሁሉም አገር ወዳድ ናቸዉ፡፡

በተመሳሳይም ግብፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ዙሪያም ሆነ በምእራባዉያንና በምስራቃዉያን አገሮች ዘንድ በተፈጥሮ አቀማመጧ በሱኤዝ ካናል እና በቀይ ባህር ምክንያት ተፅእኖ ለማሳደር የምትችል አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ግን ዛሬ ቀይ ባህርን ስላጣች በፊት መፍጠር ትችል የነበረዉን ተፅእኖ ዛሬ መፍጠር አትችልም፡፡ በዚህ ዙሪያም ልትፈጥር ትችል በነበረዉ ተፅእኖ ልታገኝ ትችል የነበረዉን ጥቅም አስቀርቶባታል እንደማለት ነዉ፡፡ በተዘዋዋሪ አባይ ዙሪያ ማሰባሰብ ይቻል የነበረዉን ድጋፍ ይቀንስባታል፡፡ ይኸ ለወደ ፊቱ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል፡፡

በሌላም በኩል ግብፅ የዉሃ ባለሞያዎቿ ናይል ተፋሰስ ዉሰጥ ተወልድዉ፤ ናይል ሥራ ላይ ተቀጥረዉ፤ ብዙ ልምድና እዉቀት ካካበቱ በኋላ በጡረታ እድሜአቸዉ በናይል ተፋሰስ ዉስጥ ከተቋቋሙት በርካታ ልዩ ልዩ የናይል ዉሃና ተፋሰስ ምርምር ተቋማት ዉስጥ ተመድበዉ እሰክ ዕለተ ሞታቸዉ ድረስ እንዲያገለግሉ ይደረጋል እነጂ ከሥራ በቀላሉ አይሰናበቱም፡፡ በኛ በኩል ያችዉ ያለችንን

የሰዉ ኃይል በየምክነያቱ በትነን ስለ ሰለጠነ ሰዉ ኃይል እጥረት እናወራለን፡፡እስከ አሁን ከተሾሙት የኢሕአዴግ የዉሃ ሚኒስትሮች፤ አቶ ሺፈራዉ ጃርሶ ብቻ ነበሩ ልምድ ያካበቱ የክፍለ ኢኮኖሚዉን ፕሮፌሽናሎች በየጊዜዉ አሰባስበዉ በልዩ ልዩ የዉሃ ጉዳች ላይ እነዲመክሩ ሲያደርጉ የነበሩ፡፡

እንዲሁም ግብፅ የአባይንም ሆነ የናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ስልጣን የኔ ብቻ ነው እያለች ነው፡፡ አልፋ ተርፋም በናይልም ሆነ በአባይ ውሃ መጋቢ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን (veto power) አለኝ ለማለት ይዳዳታል፡፡ አያይዛም የናይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ቦታ ለኔ ይገባል እያልች ነዉ፡፡ የተፋሰስ አገራቱ ለኮሚሽነርነቱ ቦታ ምርጫ የራሳቸዉ መለኪያ ይኖራቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ትልቁ መለኪያ ወደ ናይል የሚያመነጩት የዉሃ መጠን ከፍተኛ የመለኪያ ነጥብ ሊሰጠዉ ይገባል፡፡

በርሷ አባባል የርሷ (veto power) የሚመነጨው የናይልን ውሃ ለመጠቀም የሚያስችል እ አ አ በ1929 እና 1959 ዓ.ም የተደረጉ ስምምነቶች ናቸው፡፡ እ አ አ በ1929 የተፈረመው ስምምነት በእንግሊዝና በግብፅ መሐከል ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ግብፅ በአመት 48 ቢሊዮን ሚኩ ውሃ ታገኛለች፡፡ ሱዳን በአመት 4 ቢሊዮን ሚኩ ውሃ ይደርሳታል፡፡ እንግሊዝ በወቅቱ ከግብፅ ጋር የፈረመችው በቅኝ ትገዛቸው የነበሩትን ኡጋንዳን ኪንያን ታንዛንያን እና ሱዳንን በመወከል ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነኝህ አገራት ለእንግሊዝ ውክልና በይፋ መስጠታቸው አይታወቅም፡፡

እ.አ.አ. በ1959 የተፈረመው ስምምነት በግብፅና ሱዳን መሃከል ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረትም ግስፅ በአመት 55.5 ቢሊዮን ሚኩ ውሀ ድርሻ ታገኛለት፡፡ ሱዳን በአመት 18.5 ቢሊዮን ሚኩ ድርሻ ተስጥቶታል፡፡

ኢትዩጵያ የተባሉትን ሁለቱንም ስምምነቶች ስለማታውቃቸውና ስለአልፈረመቻቸው የሚመለከትዋት አይደሉም ፡፡ በማታውቃቸውና ባልፈረመቻቸው ውሎች ልትገዛም አትችልም፡፡ የተባሉት ሁለቱም ስምምነቶች የተፋሰሱን የራስጌ አገራትን የውሃ ፍላጐት ከግንዛቤ ያላስገቡ ነበር፡፡ የሚገርመው፤ የራስጌ አገራቱ የውሃ አመንጭ አገራት ናቸው፡፡

ግብፅ በናይል ዉሃ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ ነኝ የምትለዉን አመለካከትዋን አቁማ አሁኑኑ በናይል ውሃ አጠቃቀም ከተቀሩት የተፋሰሱ አገራት ጋር ካልተባበረችና ካልተስማማች ወደፊት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላት ይችላል፡፡ ከግዜዉ ጋር እራሷን ማስተካከል የሚበጃት ይሆናል ፡፡ ግርጌ አገራት ዉሃዉን ለህዝባቸዉ ጥቅም ልማት ላይ ለማዋል በየግዜዉ ለሚያድረጉት ጥረት ጦርነት አዉጃለሁ ማለት በፍጹም አያዋጣትም፡፡ ኢትዮጵያን እወጋለሁ ማለት መላዉን የተፋሰሱን የራስጌ አገራት እውጋለሁ እንደማልት ነዉ፡፡

ይልቁንስ እ አ አ በ1999 ዓ. ም ከተቋቋመው ከናይል ተፋሰስ እንሺዬቲሸ (Nile Basin Initiative) ለጥቆ እ አ አ በ May 2007 የተቋቋመዉን የናይል ተፋሰስ ኮሚሸን ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ፈርሞ ዉሃ አጠቃቀሙን ሚዛናዊና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተደራድሮ ልማት ማካሄድ ተቀባይነት ያለው አማራጭ ነው፡፡

የተፋሰሱ አገራት በአሁኑ ጊዜ 11 ሲሆኑ የናይል ተፋሰስ ኢንሺዬቲቨ አባል አገራት ኤርትራ ስትቀር 1ዐ ናቸው፡፡ በናይል ኮሚሽን የተዘጋጀዉን የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት /CFA/ የፈረሙት 6 አገራት ናቸው፡፡ እነሱም ኢትዩጵያ ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ የኮንጐ

ዲሞክራትክ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ለመፈረም ቃል እነደገቡ ተነግሯል፡፡

ሱዳንንና ግብፅ የትብብር ማእቀፉን ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ካልፈረሙ ሁለቱም አገራት ተጐጂ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሱዳን የትብብር ማእቀፉን ባትፈርምም በአሁኑ ጊዜ የህዳሴዉን ግድብ እየደገፈች ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳን አቋሟን በየግዜዉ ስለምትቀያይር በጥንቃቄ መታየት ይገባል፡፡

የተፋሰሱ የግርጌ አገራት የውሃ ፍላጐት እየጨመረ ወሳኝ ቦታ ላይ እየደረሰ ነው ፡፡ በመሆኑም ግብፅ አሁን በናይል ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን በበላይነት የመቆጣጠር ስልጣን ተገዳ እንድትለውጥ የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህም ግብፅ በውሃ አጠቃቀሙ የሁሉንም የተፋሰሱ አገራትን የውሃ ፍላጐት ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተዳድር አዲስ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ የግድ ይላል፡፡ ለዚህም የጊዜ ገደብ ሊሰጣት ይገባል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ወደ ስምምነቱ ካልገባች አማራጩ እሷን ማግለል ነው፡፡ ይኸ ሱዳንንም ይመልከታል፡፡ እዚህ ላይ የራስጌ ተፋሰስ አገራት ጠንከር ብለዉ ቆራጥ አቋም መያዝ ይገባቸዋል፡፡ ቢሆንም ለድርድር በራቸዉን ምንጊዜም ክፍት ማድረጉ ይመረጣል፡፡

ሁለቱም – ግብፅና ሱዳን – ተገልለዉ ጉዳቱን ካዩት በኃላ ወደ አዲሱ ስምምነት ለመግባት የተፋሰሱን አገራት የሚለምኑበት ጊዜ ረጅም አይሆንም፡፡ ግብፅ እስከዛሬ እንደምትለፍፈው የናይልን ውሃ ሙሉ በሙሉ እኔ ካልተቆጣጠርኩና ካልተጠቀምኩበት ወደ ጦርነት እሄዳለሁ የምትለው አባባል አይሰራምም አትችልምም፡፡ ግብፅ ልማትን እንደምትፈልግ ሁሉ ሌሎችም የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ልማቱን ይፈልጋሉና፡፡

በተጨማሪም እላይ እንደተገለጸዉ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የውሃ አጠቃቀም ሁኔታ በተመለከተ የድሮ አስተሳሰቦች ተቀይረዉ በተፋሰሱ አገሮች ስምምነትና ትብብር ላይ በተመረኮዘ አቀራረብ በሚደረጉ ትብብሮችና ስምምነቶች እየተተኩ መሆኑ ግልፅ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ይህንኑን አዝማሚያ እየደገፈ በመምጣት ላይ ነው፡፡ ጊዜዉ ባለፈበት አስተሳሰብ ተመርኩዞ መጓዝ አያስኬድም፡፡ ስምምነትና ትብብር ካለ ግን ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በቂ ውሃ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል ፡፡ በውሃ ችግርም የተነሳ ጦርነት ሊነሳም አይችልም፡፡ ተቀባይነት ያለዉ የዉሃ አስተዳደር ከተዘረጋና ተግባራዊ ከሆነ የዉሃ እጥረትን ለመከላከል ይቻላል፡፡ይሁን እንጂ መዘናጋት ሳያስፈልግ ልማትን ለማስጠበቅና ለመከላከል ብቃት ያለው ኃይል አደራጃቶ መገኘት ተገቢ ይሆናል ፡፡ ይህንኑ በተመለከተ እ.አ.አ ኖቬምበር 1 ቀን 1997 ለዉሃ ልማት ሚኒሰቴር አዘጋጅቼ ባቀረብኩት ቴክንካዊ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከግብፅ ተፅእኖ የተነሳ ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ ድርጅቶች ለአባይ ሸለቆ ልማት ብድር ስለማታገኝ የአገር ዉስጥ ፈንድ በማቋቋ ልማቶችን ፋናንስ ማድረግና ማካሄድ አስፈላጊ እንደሚሆንና ልማቶቹንም ከዉጭ ጥቃት ብቃት ባለዉ ወታደራዊ ኃይል በተለይ የአየር ኃይሉን በብቃት በማደራጀት መጠበቅና መከላከል አስፈላጊ እነደሚሆን ገልጬ ነበር፡፡

ለማንኛዉም ቁም ነገሩ ኃይል ሳይሆን ስምምነትና ትብብር እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ስምምነትና ትብብር እስካለ፤ የውሃ አስተዳደሩ በብቃትና በትክክል እስከተዘረጋ፤ ውሃን ከተፈጥሮ ምንጩ በብቃትና በዘላቂነት እነዲኖር በማድረግና በማስገኘት፤ እንዲሁም የውሃ አጠቃቀሙ ከብክነት ነፃ (water use efficient) ከሆነ ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ለልማታቸው በቂ ውሃ ለማቅረብ ይቻላል ፡፡ አሁን ባለዉ ሁኔታ ግብፅ ዉሃ እንደምታባክን ነዉ፡፡ እርሷ ግን አላባክንም እያለች ነዉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እሰራኤል የዉሃ ብክነት እነዳይኖር ከፍተኛ ጥነቃቄ የምታደርግ አገር ናት፡፡ ይኸንን ለማየት እ.አ.አ በ1986 እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ግብፅንም እ.አ.አ በጃንዋሪ 1991 በግብፅ መንግስት ተጋብዤ ከአሰዋን

ግድብ ጀምሮ እሰከ ሜዲቴራኒያን ደልታ (Mediterranean Delta) በምእራቡ እሰከ አሌክዛንድሪያ ድረስ፤ ከዚያም በሱዌዝ ካናል በኩል እሰከ ኢስማኤሊያ (Ismailia) ድረስ ወስደዉ አስጎብኝተዉኛል፡፡ እንደተገለፀልኝም ግብፅ እስከዚያን ወቅት እንኳ እስከ 3.5 ሚልዮን ሄክታር አልምታ ነበር፡፡ የናይል ዉሃም በሱዌዝ ካናል ሥር በሳይፎን (Syphone) ወደ ሲና በረሃ በመሻገር ላይ ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ የዉሃ ልማት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ፡፡

ግብፅ አባይ ውሃ ላይ ብቻ ለዘላለም ሙዝዝ ማለት የለባትም፡፡ ኢትዮጵያም የራሷ የዉሃ ልማት እስተራቴጂ እና የትግበራ ፕሮገራም እንዳላት ግብፅ ማወቅ ይገባታል፡፡ አባይ ለኛም የምግብ ዋስትናችን መሆኑን አምና መቀበል ይኖርባታል፡፡ እርሷ መኖር እንደምትፈልግ ሁሉ እኛም መኖር እንፈልጋለን፡፡ እኛ ወንዛችንን ሙሉ በሙሉ አሳልፈን ሰጥተን፤ እርሷ በወንዛችን አልምታ ስትበላ፤ እኛ እየተራብን ጧፍ አብርተን ቆመን ልናበላት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ግብፅ የራሷንም አማራጮች መፈለግ የግድ ይላል፡፡ይህም፤ የከርሰ ምድርንና የገፀ ምድርን ውሃ አጠቃቀምን ማጤንን፣ ውሃ መቆጠብን፣ ዝናብ በሰዉ ሠራሽ ዘዴ የማዘነብንና ለዚህም የእሰራኤልንና የአዉሰተራልያን ልምድ መፈተሸ፣ የባህር ውሃ የማጣራትንና በከፍተኛ ደረጃ የውሃ መጠንን የሚፈልጉ ሰብሎችንና ተክሎችን፤ ለምሳሌም ሩዝን፤ ስንዴንና ሸንኮራ አገዳን እንደገና ማጤንና ከውጭ እስከማስገባት ያሉትን አማራጮች ማየት ያስፈልጋል፡፡ የሰብሎቹ የዉሃ ፍጆታ ብቻ ሰይሆን የመስኖ የዉሃ አጠቃቀሙ ዘዴ እራሱ ለብክነት የየተጋለጠ ነዉ፡፡ እኔ በጎበኘሁበት ወቅት የቦይና (Furrow irrigation) የጎርፍ (Flood irrigation) መስኖ በብዛት አይቻለሁ፡፡ ይህም ሲካሄድ የነበረዉ በገበሬዎች ይዞታ መስኖ ሥራ ላይ ነበር፡፡ እተሸከረከሩ የመስኖ ዉሃ የሚረጩ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ የግል ሰፋፊ መስኖ ልማቶችንም አይቻለሁ፡፡

በሌላም በኩል ግብፅ ቀድማ አልምታ ለመገኘትና ተጨማሪ የውሃ ፍላጐቷን ለማስከበር ባላት ምኞት የናይልን ውሃ ከተፈጥሯዊዉ ፍሰት አቅጣጫው አስወጥታ ትላልቅ የመስኖ እርሻዎችን ማልማት ጀምራለች፡፡ በምዕራቡ የግብፅ በረሃ በኩል ቶሽካ ኘሮጀክት ወይንም አዲሱ ሸለቆ ፕሮጀከት በመባል በሚጠሩ በቶሽካ ሰርጓዳ ስፍራ ውስጥ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች ጀምራለች፡፡ ፕሮጀከቱ የተጀመረዉ እ. አ.አ በ1997 ነዉ፡፡ ዕቅዱ 238,000 ሄክታር (2340 km2) ለማልማትና ግብፅን የመስኖ እረሻ 10% ለመጨር እና 3,000,000 ህዝብ በሸለቆዉ ለማስፈር ነበር፡፡ የመስኖ ዉሃዉ በሞተር የሚሳበዉ ከአስዋን ግድብ የሙባረክ Pumping Station ተብሎ ከተሰየመዉ ጣቢያ ሲሆን ዉሃዉን የሚያጉዘዉ የመስኖ ካናሉ ከአስዋን ግድብ በስተምእራብ አቅጣጫ እሰከ ዳርብ-ኤል-አረበኢን መስመር አድርጎ አቀጣጫዉን ወደ ሰሜን አዙሮ በጠቅላላዉ 310 ኪሜ ተጉዞ ባሪስ ኦኤሲዝ ድረስ ይደርሳል፡፡ የሙባረክ Pumping Station የተመረቀዉ እ.አ.አ በ2005 ዓ.ም ነዉ፡፡እ.አ.አ እስከ 2020 ወደ 238,000 ሄክታር (2340 km2) ለማልማት ነዉ የታቀደዉ፡፡ ይሁንና ፕሮጀክቱ እንደታሰበዉ ሆኖ አለተገኘም፡፡ የሸክላ አፈር በጥልቀት ስለሚገኝ የመስኖ ዉሃዉን የሚረጨዉ መሣሪያ በጭቃ እየሰመጠ መሽከርከር አልቻለም፡፡አካባቢዉ በጣም ጨዉማ ስለሆነ ግብፆች የሚደብቁትን የኑቢያን ከርሰ ምድር ዉሃ እየበከለባቸዉ ከጥቅም ዉጪ እያደረገባቸዉ ነዉ ፡፡

በዚህም ምክንያት የመስኖዉ እርሻ እነደታሰበዉ አልተሳካላቸዉም ፡፡ የካናል ሥራዉን እ.አ.አ 2012 ድረስ 250 ኪ.ሜ አጠናቀዋል፡፡ በአዲሱ ሸለቆ ፕሮጀከት፤ መጀመሪያ የታሰበዉ እሰከ 1.5 ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት ነበር ይባላል፡፡

በሰሜን ምስራቅም የናይልን ውሃ በሱዌዝ ካናል ስር አሻግራ ከ168,ዐዐዐ ሂክታር በላይ የመስኖ ስራ በሲና በርሃ ውስጥ ማልማት ጀምራለች፡፡በእቅዱም መጨረሻ እሰከ 260,400 ሄክታር ለማልማት ነዉ፡፡በሱዌዝ ካናል በስተሰሜን ምዕራብ ሌላ የመስኖ ኘሮጀክት ጀምራለች፡፡ እነኝህ ሁለት ትላልቅ ኘሮጀክቶች ከናይል ሸለቆ ውጪ ተጨማሪ ውሃ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ግብፅ ይህንን ስታደርግ የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች አላማከረችም፡፡ ተጨማሪ የውሃ ፍላጐት እንደሚያስከትል ታውቃለች፡፡ ኢትዩጵያ

በተደጋጋሚ ግብፅ የናይል ውሃን ከተፈጥሮአዊው ሸለቆ አስወጥታ አቅጣጫ በማስቀየሯ ተቃውሞዋን ደጋግማ አሰምታለች፡፡
በሌላ በኩል በምዕራቡ በረሃ የሚገኘውን የኑቢያን ከርሰ ምድር ውሃ በድብቅ ይዛ ስለናይል ውሃ ፍላጓቷ ብቻ ትጮሃለች፡፡ ይኸ ግልፅነትና ቅንነት የጐደለው አካሄድ ነው፡፡ በእርግጥ የኑቢያ ከርሰምድር ዉሃ (Fossil Water) በመሆኑ አላቂ በመሆኑ በዝናብ በቀላሉ የሚተካ አይደለም፡፡ የኑቢያ ከርሰ ምድር ስፋት 826,ዐዐዐ ኪ.ሜ ካሬ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የሚገኘውም በምዕራቡ የግብፅ በረሃ ነው ፡፡ ማለትም ከናይል ወንዝ በስተምዕራብ ከደቡቡ ጫፍ እሰከ ሰሜን ጫፍ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ምእራብ በኩል ባሪሰ ኦኤሲዝ አካባቢ፤ በግል ይዞታ መስኖ እርሻ፤ እሰከ 10,000 ሄክታር፤ በዓመት እስከ 1.ዐ29 ቢልዮን ሚ ኩ ውሃ በሞተር ከጉደጓድ እየሳቡ በመጠቀም ላይ ናቸዉ፡፡

ግብፅ በዓመት ከግዛቷ የምታገኘዉ ወደ ናይል የሚፈስ የገፀ-ምድር ዉሃ ወደ 0.5 ቢልዮን ሚኩ የሚጠጋ ነዉ፡፡ በአንፃሩ ከኢትዮጵያ ወደ ናይል በዓመት የሚፈሰዉ የዉሃ መጠን እንደሚከተለዉ ነዉ፡-

1) ከአባይ ተፋሰስ ወደ……………….52.62 ቢልዮን ሚኩ
2) ከባሮ አኮቦ ተፋሰስ ወደ…………..11.81 ቢልዮን ሚኩ
3) ከተከዜ ተፋሰስ ወደ………………. 7.63 ቢልዮን ሚኩ
4) ከመረብ ጋሽ ተፋሰስ ወደ………… 0.88 ቢልዮን ሚኩ
ጠቅላላ ወደ…………………….72.94 ቢልዮን ሚኩ

የናይል ተፋሰስ የዓመት ጠቅላላ የወሃ ሀብት 84.00 ቢልዮን ሚኩ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወደ ናይል የሚፈሰዉ ዉሃ መጠን በዓመት ወደ 73 ቢልዮን ሚኩ ወይንም ወደ 87 % ነዉ፡፡ አንዳንድ የምዕራብ አገሮች በተለይ እንግሊዝ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ ዉሃ መጠን ስለአላት እላይ ከተጠቀሱት 4ቱ የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ወደ ናይል የሚፈሰዉን ወደ 73 ቢልዮን ሚኩ የሚጠጋ ዉሃ ለግብፅ ትተዉላቸዉ የሚል አቋም አላቸዉ፡፡ ይኸን አቋማቸዉን እንግሊዞች ባገኙት ዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ ሲያነፀባርቁ ታይተዋል፡፡ እ.አ.አ በኤፕሪል 1991 የዓለም አቀፍ የመስኖና ፍሳሽ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ኮሚቲ ሰብሳቢነቴ (Chairman of the Ethiopian National Committee of the ICID / International Commission on Irrigation and Drainage/) ቻይና ቤጂንግ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክዬ በተገኘሁበት ወቅት ከግብፆች በላይ እንግሊዞች ነበሩ ሽንጣቸዉን ገትረዉ ለግብፅ ሲከራከሩኝ የነበሩት፡፡ እንግሊዞች አሁንም ይኸን ስሜታቸዉን የተዉዉ አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ የእንግሊዝ መንግስት ይኸ የመንግስት አቋም ሳይሆን የግለሰቦች ነዉ ሊል ይችላል፡፡ በተጨማሪም ግብፅ በአረብ አገሮች ዘንድ ባላት ተደማጭነትና እንዲሁም በሱኤዝ ካናልና በቀይ ባሕር ምክንያት ከምእራቡ ዓለም በተለይ ከአሜሪካ ጋር ያላት Strategic Partnership የበለጠ ድጋፍ ያስገኝላታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የግብፅ የዉሃ ፍላጎት በዓመት ከ 50-55 ቢልዮን ሚኩ እነደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ የአስዋን ግድብ 150 ቢልዮን ሚኩ ዉሃ ነዉ የሚይዘዉ፡፡ ከረጅሙ ጊዜ የዉሃ ፍላጎቷ አንፃር የግብፅን ስጋት ለማሰወገድ፤ ውሃ ኢትዩጵያ ውስጥ ተጠራቅሞ በሚፈለገው መጠን ለግብፅና ሱዳን ሊለቀቅ ይችላል፡፡ ዋናው መስማማትና መተባበር ነው፡፡ ዉሃ ማጠራቀሙ በሌሎችም የተፋሰሱ አገራት ዉሰጥ በተለይም ዩጋንዳ ዉሰጥ ሊከናወን ይችላል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የሚከተሉትን እርምጃዎች በጋራ ተባብሮ በስምምነት መሥራት እና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ግብፅ ለራሷ ጥቅም ብላ መሪ እና ጉልህ ሚና ልትጫወት ይገባል፡፡ አስፈለጊዉንም የገንዘብ መዋጮ ማድረግ እና የማስተባበር ሚና በቀዳሚነት መዉሰድ ይኖርባታል፡፡

የዉሃ መጠን ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች፡-
1) ውሃ መቆጠብ፤
2) በዘለቄታዊነት የዝናብ ውሃ እንዲኖርና እንዲጨምር፤ ወበቅና እርጥበት በስፋት እንዲፈጠር ማድረግ፤
ለዚህም ፡-
• የተናጋውን የአካባቢ ተፈጥሮ ወደነበረበት መልሶ ለማቋቋም ጥረት ማድረግ፤
• ደኖችን ማልማት እና መንከባከብ፤

በኢ/ር ብሩ ኢቲሣ

Email: birru_i@hotmail.com