ከወልድያ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በሃራ ከተማ በህወሓት ንብረቶች ላይ ህዝባዊ እርምጃ ተወሰደ

Print Friendly, PDF & Email

በሃራ ከተማ በህወሓት ንብረቶች ላይ ህዝባዊ እርምጃ ተወሰደ

ከወልድያ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሃራ ከተማ ህዝባዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ታወቀ፡፡

ከከተማዋ በተለይ ለቢቢኤን የደረሰው መረጃ እንደጠቆመው፤ ትላንት እሁድ እና ዛሬ ሰኞ የህወሓት ንብረት በሆኑ የተለያዩ ቁሶች ላይ ህዝባዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡

ትላንት እሁድ ጥር 13 ቀን 2010 በሃራ ከተማ፣ ትግራይ ከሚገኘው የሲሚንቶ ፋብሪካ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሲሚንቶ የሚያመላልሱ ሁለት ከባድ የጭነት መኪኖች በእሳት እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡

የህወሓት ንብረት በሆኑት ሁለቱ መኪኖች ላይ ከተወሰደው እርምጃ በተጨማሪም፤ በተመሳሳይ ቀን ትላንት እሁድ በህዝብ ላይ ጥቃት የሚሰነዝር አንድ ፓትሮል የፖሊስ መኪና በሃራ ከተማ ነዋሪዎች እንዲቃጠል መደረጉን፣ ህዝባዊ እርምጃውን የተመለከቱ የዓይን እማኞች ለቢቢኤን ገልጸዋል፡፡

ከወልድያ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ፈንጠር ብላ በምትገኘው ሃራ ከተማ ትላንት የተጀመረው ህዝባዊ እርምጃ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን የገለጹት የዓይን እማኝ፤ በዛሬው ዕለት ሰኞ ጥር 14 ቀንም በፖሊስ ንብረቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን እማኞቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በከተማዋ ሁለት የፖሊስ ሞተሮች እና ሌላም አንድ የፖሊስ ባጃጅ እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ከእማኞቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በእሳት እንዲቃጠሉ የተደረጉት እነዚህ ንብረቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ ንጹሃን ዜጎችን እየገደለ ለሚገኘው የህወሓት አገዛዝ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆኑ፤ በሚከፍለው የገዛ ግብሩ በተሸመቱ ንብረቶች እየተገደለ የሚገኘው ህዝብ፤ ቁጣውን ለመግለጽ እንዲህ ያለ ህዝባዊ እርምጃ መውሰዱ አንዱ የትግል ስልት መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

በሃራ ከተማ እንዲህ ያለው ህዝባዊ እርምጃ ሊወሰድ የቻለው፤ በወልድያ ከተማ በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ሲሆን፤ ዛሬም በከተማዋ አለመረጋጋት ሰፍኖ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

የህወሓት ወታደሮች ቅዳሜ ጥር 12 ቀን 2010 ለጥምቀት በዓል አደባባይ በወጣው ህዝብ ላይ ተኩስ ከፍተው ብዙዎችን ማቁሰላቸው ይታወሳል፡፡

ወታደሮቹ በወሰዱት በዚህ የኃይል እርምጃም፣ ከአስር በላይ ሰዎች መገደላቸውን ዛሬ የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ከሟቾች በተጨማሪም ሌሎች በርካታ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ከመረጃዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በወልድያ በተፈጸመው በዚህ አስከፊ ጥቃት የተቆጣው የሃራ ከተማ ነዋሪ፤ የህወሓት ንብረት በሆኑ የተለያዩ ቁሶች ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡

ሃራ ከተማ ከወልድያ 20 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ከከተማዋ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የራሱ ትጥቅ (መሳሪያ) እንዳለው እማኞች ይገልጻሉ፡፡

ሃራ የአማራ ክልልን ከአፋር ክልል ጋር የምታዋስን የክልሉ የመጨረሻዋ ከተማ ናት፡፡

ቢቢኤን ጥር/14/2010