በወልድያ የፈሰሰው የወጣት ክርስቲያኖች ደም የእኛ ደም ነው! – ልሳነ ግፉዓን

Print Friendly, PDF & Email

ጥር 13/2010

በወልድያ የፈሰሰው የወጣት ክርስቲያኖች ደም የእኛ ደም ነው! (pdf)

የጥምቀት በዓል በመላው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አማኞች ዘንድ በየአመቱ ከጥር 10 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በከፍተኛ ድምቀት የሚከበርና በተለይም በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎና፣ በሰሜን ሸዋ ህዝብ ዘንድ ልዩ ክብርና ፍቅር የሚቸረው ሲሆን ይልቁንም የበአሉ መዝጊያ የሆነው የቃና ዘገሊላ እለት፣ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የተባለለትና ወጣቶች ለቅዱስ ሚካኤል ታቦት ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በጭፈራና በተለያዩ ተግባራት የሚገልፁበት፣ ከጭፍራ መልስ ለበአሉ በተዘጋጀው ድግስ ከወዳጅ ዘመድ ጋር የሚጫወቱበትና የሚደሰቱበት የአመቱ ቁንጮ በአል ነው።

ይህን ታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በአል ለማክበር አምረውና ተውበው ወደ አደባባይ በወጡ የወልዲያ ወጣት ክርስቲያኖች ላይ ቅዳሜ ጥር 12, 2010 ዓ.ም በፋሽስቱ የህወሃት ነብሰ ጋዳዮች የተፈፀመው ጭፍጨፍና ግድያ እጅግ ያስቆጣንና ሃዘናችንም መሪር አድርጎታል። በዚህ አጋጣሚ ድርጅታችን ለሳነ ግፉዓን ከመላው አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ለሟች ቤተሰቦች፣ ለወልድያና ለአካባቢው ህዝብ፣ ለህዝበ ክርስቲያኑና፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን በእጅጉ ይመኛል።

ህወሃት ተስፋ ቆርጧል! ትላንት በእሬቻ ዛሬ ደግሞ በጥምቀት በአል ላይ የንፁሃን አማኞችን ደም በግፍ በማፍሰስ አረጋግጦልናል። ከእንግዲህ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ መግዛት እንደማይቻል በተግባር የተረዳው ህወሃት፤ ይልቁንም በብሄር ተደራጅቶ አገርንና ህዝብን መዝረፍ፣ የአንድን አናሳ ብሄር የበላይነት በታላቅ ህዝብ ላይ መጫን፣ የቁም ቅዥት የሆነበት ህወሃት፤ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አምልኮውን በሚፈፅምባቸው ታላላቅ በአላት ላይ እየመሸገ የንፁሃንን ደም በጭካኔ የሚያፈሰው፣ መንግስታዊ ሽብር የሚፈጥረው፣ ህዝብንና ሃይማኖትን የሚያዋርደው።

የፋሽስቱ ህወሃት ህልውና እና አምባገነናዊ ከፋፋይ ስርዓት ያከተመው የጎንደር ህዝብ ሃምሌ 24, 2008 ዓ.ም ባደረገው ታሪካዊው መሬት አንቀጥቅጥ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ “በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም!” “አማራ ኢትዮጵያዊ ነው!”… ወዘተ እያለ ያወጃ ቀን ነው። ያኔ ህወሃት ዘራሹና መራሹ የጎሳ ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቀመቅ ወርዷል! “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው!” “የአፋሩ፣ የሱማሌው ደም ደሜ ነው!” “አማራና ቅማንት አንድ ነን!” ብሎ አደባባይ ሲወጣ ያኔ ኢትዮጵያ ዳግም በክብርና በአንድነት ተወልዳለች! እኮ ያኔ ነው ህወሃት መራሹ የዘር ፖለቲካና ድቡሽቱ ስርዓት የተገረሰሰው! ያኔ በይፋ ህዝባችን ላይ ለሩብ ክፍለ ዘመን የተጫነው የመከፋፈል ሴራ ወደ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተቀየረው!

ህዝባችን “እስክንድር ነጋ ይፈታ!” “ሃብታሙ አያሌው ህመምህ ህመማችን ነው!” “አንዷለም አራጌ ይፈታ!” “በቀለ ገርባ ይፈታ!” “አታላይ ዛፌ፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ የወልቃይት ኮሚቴዎች ይፈቱ!” “የሙስሊም ኮሚቴዎች በአስቸኳይ ይፈቱ”… ወዘተ ሲል እስረኛ ይፈታ እያለ አልነበረም፡ የጎንደር ህዝብ በዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያ እራሷ ወደ ህዝቦቿ እስርቤትነት እንደተቀየረች ጠንቅቆ ያውቃል።ያስረዳሃል። ይልቁንስ እያለ የነበረው መሪዎቼ እነ አንዷለም፣ እነ እስክንድር፣ እነ በቀለ … ወዘተ ናቸው ነው።

የጎንደር ህዝብ “የሻዕቢያ ተላላኪ ህወሃት እንጂ ወልቃይት አይደለም” “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይደረግ!” ”የህወሃት የበላይነት ይቁም!” በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ያንገሸገሸውን የህወሃት ዘረኝነትና አይን ያወጣ ዝርፊያን ሲያወግዝ በህወሃት በኩል ለውጥ ይመጣል ወይም መስፋፋቱና ወረራው ይቆማል ወይም ህዝብን ማሸበሩና መዝረፉ ይታገሳል በሚል የዋህነት አልነበረም፤ ይልቁንስ ነገ በማይቀረው ታሪካዊ የህዝብ ቁጣና ፍርድ ውስጥ ማለፍ አይቀሬ መሆኑ እያሳሳበ ነበር።

እኩዩና ፋሽቱ ህወሃት ዛሬ በህዝባችን መራራ ትግል መፈናፈኛ አጥቶና ታሪካዊ መቃብሩ ውስጥ ወርዶም ቢሆን የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ወዘተ…. በሚሉ ያረጁና ያፈጁ የማዘናጊያና የማደናገሪያ ግም-ገማዎችና መግለጫዎች ቢያሰለቸንም፣ “አንዳንድ” ወገኖችን ከእስር በመልቀቅ ለለውጥ የተዘጋጀ ለማስመሰል ቢሞክርም፣ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ፣ አመለኛው ወያኔ እስረኞች ተፈተውና ህዝብ ደስታው ገልፆ ሳምንት ሳይሞላ የንፁሃን ልጆቻችንን ደም በየአውደ አመቱ በማፈሰስ ተስፋ መቁረጡንና ማንም ቢመጣና ምንም ቢደረግ እንደማይለወጥና ከዘላለማዊ ሞት በስተቀር ከዚህ ፍሽስታዊ ባህሪው እንደማያድነው አረጋግጦልናል !

ህዝባዊ ትግሉም ሆነ ጥያቄው መሆን ያለበት ዛሬ በትግራይ የጨለማ እስር ቤቶች ሳይቀር ከኦሮሞ ልጆች ኦሮምኛን ከአማራ ልጆች ደግሞ አማርኛን ተምረው የስራ ቋንቋቸው ኦሮአማ እስኪያደርጉ የደረሱበት፣ ሴት ልጅ ጡቷ በኤሌክትሪክ እሳት እየተጠበሰ የምትሰቃይበት፣ የወንድ ልጅ ብልት እየተኮላሸ የሚመረመርበት፣ የወገኖቻችን የእግር ጥፍሮች በጉጠት ከሚነቀልበትና እርቃናቸውን ከሚዋረዱበት የህዋሃት ሰይጣናዊ ማሳቀያ ቤቶች የታጎሩት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ወገኖቻችን አንድም የሰው ዘር ሳይቀር እንዴት እናድናቸው ላይ ነው!

ህዝብ በጀምላ ለኢፍትሃዊ እስር፣ ስቃይና፣ ሞት የተዳረገበት ፍትሃዊ ጥያቄ ሳይመለስ ወይም ሳይፈታ፣ ህዝባችን መሪዎቼ ያላቸውንና የቀባቸውን፣ ጥያቄውንና ብሶቱን አደባባይ ይዘው እንዲወጡ የላካቸውን ሰላማዊ ልጆቹን በየማሰቃያ ካምፖች ተዘግቶባቸው፣ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ወጣት በዱር በገደሉ እየተዋደቀ፣ ሃገሪቱ ያፈራቻቸው እውነተኛ የህዝብ ልጆች ለፍትህ፣ ለእኩልነትና፣ ለነፃነት ትግል በስደት እየተንከራተቱ በሚገኙበት ሁኔታ ማንን ይዞ ነው ሃገራዊ መግባባት የሚባለው? የምን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት ነው?

ችግሩ ግልፅ እንደሆነው ሁሉ መፍትሄውም እንዲሁ ግልፅ ነው። ጥያቄው ህዝባዊ መንግስት በአስቸኳይ ይቋቋም ነው! ጥያቄው የጠባቦችና የአናሳዎች የበላይነት ይብቃ ነው! ጥያቄው ዘረኛውና አምባገነኑ ህወሃት መራሹ ስርዓት ይወገድ ነው! ጥያቄው በዘር የተከፋፈለችና የተዳከመች ኢትዮጵያን አንሻም ነው! እነንዚህን ህዝባችን የጠየቃቸውንና እየጠየቃቸው የሚገኙትን ህዝባዊ ጥያቄዎች አስመስሎና አጭበርብሮ ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ በፍጥነት ትክክለኛውን መለስ መስጥት መጭውን አደጋ በእጅጉ ይቀንሳል ብሎ ልሳነ ግፉዓን በፅኑ ያምናል።

ይሃውም፦

1ኛ. ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የህዝቧ እስር ቤትና የማሳቃያ ቦታ ሆና በምትገኝበት የህወሃት ዘመን እዚህና እዚያ ያሉ እስረኞች ይፈቱ ብሎ ልሳነ ግፉዓን አይጠይቅም። ከእስር መፈታት ያለበት 100 ሚሊየን የሚጠጋው መላው ህዝባችን ነው!

2ኛ. ህወሃት/ኢህአዴግ 100% ህዝብ መርጦኛል በማለት የያዘውን መንግስታዊ ስልጣን ሃሰተኛ መሆኑና ህዝብም ድጋፍና እውቅና እንዳልሰጠው ህዝባችን በይፋ ለአለፉት ሶስት አመታት ባሳየው ሃገራዊ ተቃውሞ አረጋግጧል። ስለዚ ህወሃት መራሹ መንግስት በሃይል የያዘውን የህዝብ ስልጣን በአስቸኳይ ለህዝብ መመለስ ይኖርበታል። ይሃውም ከሙያና የፆታ ማህበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለተወጣጣና፣ የዓለም ማህበረሰብ በታዛቢነት ለሚገኝበት የአደራ መንግስት ስልጣን ማስረከብ፣

3ኛ. የህወሃት ጦር ትጥቁን እንዲፈታና በምትኩም ከህዝብ የተወጣጣ ጊዚያዊ ጸጥታ አስከባሪ ሀይል እንዲቋቋም ማድረግ፣

4ኛ. የአደራው መንግስት በሚያዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በነፃ ህዝባዊ ምርጫ ህዝባዊ መንግስት መመስረት።

ህወሃት መራሹ ፋሽስት ቡድን በህዝብ ትግል ፍፁም ተንበርክኮ ይህ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ መላው ህዝባችን፦

1. በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ማንኛቸውንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች! በተለይም የኢትዮጵያም ህዝብ ሆነ ገለልተኛው የአለም ማህበረሰብ በማይጎበኛቸው፣ አድራሻቸው ስውር በሆኑትና “ባዶ ስድስት” ተብለው በሚታወቁት የትግራይ የማሰቃያ ጉድጓዶች ተጥለው ፍዳቸውን እያዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁኔታ ህዝባችን በንቃት እንዲከታተል እናሳስባለን፣

2. በሁሉም አቅጣጫ የተጀመረውና ተቀጣጥሎ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተጋድሎ እጅግ ከፍ ባለና በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበናል።

3. ማንኛውም ከእስር የተለቀቀ የፖለቲካ መሪም ሆነ የህዝብ ልጅ ከህወሃት ጎን ተሰልፎ ለቅስቀሳም ሆነ ህዝብን ለማረጋጋት በሚል ተልካሻ ምክንያት እንዳይሳተፍ አደራ እንላለን፣

4. ማንኛውም በህወሃት ጦር ውስጥ በተለያየ ምክንያት እያገለገለ የሚገኝ የህዝብ ልጅ በአገኘው አጋጣሚ የህዝብ አጋርነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ እናሳስባለን፣

5. ማንኛውም ኢትዮጵያው ምሁር፣ የሃገር ሽማግሌና፣ ፖለቲካ ድርጅት መሪ ዛሬ ነገ ሳይል በአደባባይ የሚደረገውን የህዝብ ትግል እንዲመራና እንዲያስተባብር በአክብሮት እንጠይቃለን!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የወልድያ ወጣት ክርስቲያኖች ደም የእኛም ደም ነው
ልሳነ ግፉዓን
ጥር 13 2010 ዓ.ም