“ከዘፈንሽ ባላሳፈርሽ” – መግለጫውን ወደ ተግባር ከለወጠው፤ የኢህአዴግ የመጀመሪያ ዙር እርምጃ መልካም ነው።

Print Friendly, PDF & Email

ከአክሎግ ቢራራ (ዶር)

እኛ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን መሰረታዊ ችግሮች በራሳችን ውይይትና ድርድር፤ በቀና፤ በመልካምና ማንንም በማያገል አስተሳሰብና የፖለቲካ ሂደት ለመፍታት እንችላለን። ይህ የቅንነት ብሄራዊ አመለካከትና ሂደት የሚጠይቃቸው አስኳል ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ከድርጅት፤ ከብሄርና ከኃይማኖት፤ ከግልና ከቡድን የኢኮኖሚ ጥቅሞች በላይ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማስቀደምን ይጠይቃሉ። ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም መቆም የተቀደሰ ተልእኮና ተግባር ነው። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፤ ህወሓት በበላይነት ሲያስተዳድረው የቆየው የኢህአዴግ አገዛዝ የሕዝብ የፖለቲካ ስልጣንንና የኢኮኖሚ ጥቅሞች አግባብነትን ወደ ጎን አስቀምጦ ራሱን አገልግሎበታል።

ይህ ለሕዝብ ታዛዢና አገልጋይ ለመሆን ያልቻለና ያልፈቀደ አገዛዝ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ የበላይነቱን ይዞ ለመግዛት እንደማይችል የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ እምቢተኛነቱን መስዋእት እየከፈለ አስመክሯል። ታላቁን የተሃድሶን ግድብ በሕዝብ ባጀት የሚሰራው አገዛዝ ሕዝብን ለማነጋገር፤ የሕዝብን ድምጽ ለመስማት፤ የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት ምንም ፈቃደኛነት አያሳይም፤ ብቃትም የለውም። ሕዝብን፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ ለማነጋገር የማይችልበት ዋና ምክንያት ይህን ትውልድ ስለሚፈራው ብቻ ነው። ሌላ ምክንያት ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም። ሕዝብን የሚፈራ አገዛዝ ደሞ፤ ከሕዝብ የሚፈራው ነገር አለ ማለት ነው። ስለሆነም፤ የአገዛዝ ለውጥ አስፈላጊ ነው።

ባለፉት ሳምንታት በብዙ ድህረ ገጾች የተሰራጨውና በአገር ቤት ጋዜጣ ታትሞ ሕዝብ የሚነጋገርበት “የኢህአዴግ ኑዛዜ ወይንስ የለውጥ አቅጣጫ? —አማራጩ ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት ማድረግ ብቻ ነው” የሚለው ትንተና ይዘት፤ መግለጫው የየትኛው ኢህአዴግ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር። በአጭሩ እንዲህ ይላል።

“በህወሓት የበላይነት የሚገዛው የኢህአዴግ የስራ አስኪያጅና አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ የሕዝብን ባጀት ተጠቅሞ፤ ለሶስት ሳምንታት ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች ካላዘነ በኋላ መግለጫ አውጥቶ ሕዝብን እያነጋገረ ነው። ይህ የምስጢር ጉባኤ የተካሄደው የህወሓት የስራ አስፈጻሚ ቡድን ለሳምንታት በመቀሌ የዝግ ችሎት አድርጎ ራሱን በአዲስ መልክ አወቅሬአለሁ ካለ በኋላ ነው። ቡድኑ አጠናክሮ የወጣው አሁንም ራሱን የስልጣን መአከል አድርጎ እንዴት የበላይ ሆኘ እገዛለሁ በሚል የህወሓቶችን ቀጣይነት የሚያሳይ ስልት መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የኢህአዴግ አመራር ክብደት የሰጠው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስልጣን ሳይሆን ለአዲሱ የህወሓት አመራር የበላይነት መሆኑ በግልጽ ይታያል። ….  (Read More, pdf)