የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት 3ኛ ጉባዔ የአቋም መግለጫ!

Print Friendly, PDF & Email

የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት 3ኛ ጉባዔ የአቋም መግለጫ! (pdf)

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ቅዳሜ ጥር ፭ ቀን ፪ሺህ፲ዓ.ም.

እኛ የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት 3ኛ ጉባዔ ተሳታፊዎች ጥር 5 ቀን 2010 ዓም ባደረግለው ጉባዔ፣ ድርጅቱ ባለፉት 5 ዓመታት ያከናወናቸውን የተለያዩ ተግባሮች በማዕከላዊ ምክር ቤቱ በቀረበው ዝርዝር ሪፖርት፣ በቁጥጥርና ፍተሻ ኮሚቴ የገንዘብ አወጣጥና አጠቃቀም እንዲሁም የመመሪያዎች አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት አዳምጠን ባደገርነው ሠፊ ውይይት ፣በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ የሚስተካከሉትን እንዲስተካከሉ፣ የሚጨመሩ እንዲጨመሩ ሀሳብ በማቅረብ ሪፖርቶቹ የድርጅቱ ቋሚ ሰነዶች ሆነው እንዲያዙ በሙሉ ድምፅ በመወነስ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል።

1. ጉባዔው ዐማራውና ኢትዮጵያ የገጠሟቸውን ችግሮች፣ በአንክሮ መርምሯል። አገሪቱ በአሁኑ ሁኔታ ከቀጠለች የመፈራረስ ዕጣዋ ሠፊ መሆኑን አጢኗል። ይህ እንዳይሆን፣ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በበኩሉ ማከናወን ያለበትን ዐማራውን የማደራጀትና የማንቃት ሥራ በአገር ቤትና በውጭ አጠናክሮ ከመቀጠል ባሻገር፣ በኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ በግለሰብ ነፃነትና በሕግ የበላይነት ከሚያምኑ ድርጅቶች፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች ጋር በመመካከር፣ ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን እንደ አገር የመቀጠል ያለመቻል የመበታተን አደጋ ገፎ፣ ወደ ነባሩ የአባቶቻችን የአብሮነትና የመቻቻል ግንኙነት እንድንመለስ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና መሰል ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ አጽንዖት ሰጥቶ ተወያይቷል። ለዚህ ተግባራዊነትም የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት አካላትና አባላት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ ባሉባቸው ባህላዊና ማኅበራዊ ስብስቦች ውስጥ የአሰባሳቢነት፣ የመልካም ዐማራዊ ኢትዮጵያዊነት ምሳሌዎች በመሆን፣ የአብሮነቱን ስሜት እንዲጎለብት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ጉባዔው አሳስቧል።

2. ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የተመሠረተበትን መሠረታዊ ዓላማዎች ባለፉት አምስት ዓመታት ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ያደረገውን ጥረትና የተገኘውን ውጤት በሪፖርቱ በሚገባ ከመረዳታችንም በላይ፣ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፣ የዐማራው ድምፅ ከመሆን አልፎ፣ ዐማራው በኢትዮጵያ ምድር የሚመጥነውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታውን ማስጠበቅና ለኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ መዝለቅ የሚታገል ፣«የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት» የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት እንዲመሠረት መደረጉ ተገቢ እና የሚያኮራ መሆኑን አጢነን፣የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዓላማ የተሳካ እንዲሆን የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት አካላትና አባላት ማናቸውንም ድጋፍ ለመስጠት ቃል እንገባለን።

3. ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ባለፉት ዓመታት ያስጠናው «የፍትሕ አፈላላጊ ፕሮጀክት» ቀጣይ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ በዐማራ ወገናችን ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ለፍትሕ እንዲቀርቡ የማድረጉን ሥራ በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ያልተቆጠበ ጥረታችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናደርጋለን።

4. ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የዐማራው ድምፅ በዓለም ዙሪያ እንዲሰማና ዐማራው የማይገፋ ኃይል ሆኖ እንዲቆም ለማስቻል ያቋቋመው የዐማራ ድምፅ ራዲዮ፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማድረግ በተጓዳኝ፣ ወደ ቴሌቪዥን ለማሸጋገር የተያዘው ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን የዐማራ ድምፅ ራዲዮ ድጋፍ ኮሚቴዎችን በማጠናከር የማያቋርጥ የገቢ ምንጭ በመፍጠር፤ ዐማራውን የማደራጀት፣ የማንቃትና የማሳወቅ ተግባር በተከታታይ እንዲሠራ የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የመረጃና የሰው ኃይል ለማቅረብ ቃላችን እናድሳለን።

5. የዐማራው ኅልውናም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊጠበቅ የሚችለው የአገር ውስጥ ያለው የሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ወጥ አደረጃጀትና አመለካከት ይዞ በተደራጀ መንገድ ሲመራ ስለሆነ፣ ይህ የተቀናጀ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት እስካሁን ያደርግ የነበረውን ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል እናደርጋለን።

6. ለሁሉም አቋሞቻችን መሠረቱ የአባላት በዓይነትና በመጠን መጠናከር እለሆነ፣ በንኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ዐማራሮችንና የዐማራ ወዳጆችን በመለየት ትግሉን እንዲቀላቀሉ የማድረጉን ሥራ አጠናክረን እንገፋበታለን!

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገአሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!