አቤ ቶኪቻውና ኢሳት (ግንቦት ሰባት)

Print Friendly, PDF & Email

በተለያዩ ወቅታዊና አንገብጋቢ የአገር ጉዳዮች ላይ በተዋዛና በስላቅ መልክ እጅግ ጠቃሚ መልዕክቶችን ለረዥም ዓመታት ሲያስተላልፍ የነበረውና በተለይም “ዋዛና ቁምነገር” የተባለውን መርሃ ግብር በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ጋዜጠኛ አበበ ቶላ ከኢሳት ጋር ያለውን ግንኙነቱን ማቋረጡን በለቀቀው ቪዲዮ አስታውቋል። አቤ ቶኪቻው ለዚህም የሰጠው ምክንያት አርበኛ ዘመነ ካሴ ለረዥም ዓመታት ኤርትራ ውስጥ በግንቦት ሰባት ተዋጊነትና አመራርነት ጭምር ሲሳተፍ ኖሮ አሁን በአውሮፓ ውስጥ በስደት እንደሚገኝና ይህንን አስመልክቶ ኢሳት ምንም ዓይነት ዘገባ አለማቅረቡና ይህም ትክክል አለመሆኑን አስመልክቶ ከኢሳት እራሱን ማግለሉን አስረድቷል። አቤ ቶኪቻው ይህንን በማድረጉ ታላቅ የመርህ ሰው መሆኑና አመለካከቱን በጥቅም ሊለውጥ የማይችል ጠንካራ ኢትዮጵያዊና ለሌሎችም ምሳሌ መሆኑን አስመስክሯል።

ግንቦት ሰባት በሻቢያ እርዳታ የትጥቅ ትግል አካሄዳለሁ እያለ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲያላግጥ 10 ዓመታት አልፎታል። አስር ዓመት ሙሉ የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ እያለ አንድ ስንዝር መሬት ከወያኔ ቁጥጥር ነጻ ያላወጣ ከመሆኑም በላይ አንዳችም የወታደራዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ አድርጎ አያውቅም። ግንቦት ሰባት 10 ዓመት ሙሉ ቱልቱላ መንፋትና በህዝብ ተስፋና ስሜት ላይ ከማላገጡም በላይ ከአገር ወዳድ ወገኖች ለሚቀርብለት ጥያቄ ዓይናችሁን ጨፍኑ የሚል የቁጭበሉዎች የሽወዳ ምላሹ ብዙዎችን አሳዝኗል። በነገራችን ላይ 10 ዓመት ሙሉ የጦር መሳሪያ ጨብጫለሁ ብሎ አንስቶ አንድ ስንዝር መሬት ባለማስለቀቅ እስከዛሬ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የለውም። በዚህም “ጊኒስ ቡክ” Guinness Book of World Records ውስጥ መመዝገብ ይገባዋል እላለሁ።

አቤ ቶኪቻው እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው አገር ወዳድ ወገኖች የሚሰራቸውን ተግባሮች የሚደግፉለትና የሚወዱለት አሉት። ግንቦት ሰባት ለሚቅርብለት ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄ ያቀረቡለት ግለሰቦች ላይ ስም የማጥፋትና ያልተናገሩትን ተናገሩ ብሎ ማደናገር ስራዬ ብሎ ያያዘው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ኢሳት ውስጥ የሚያገለግሉ ጋዜጠኞች አቤ ቶኪቻው ያቀረበውን ትክክለኛና በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለማግኘት የሚፈልጉን መልስ አቶ ዘመነ ካሴን ካለበት ቦታ ፈልገው ቃለ ምልልስ ማድረግ አላባቸው። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሻቢያና በግንቦት ሰባት የሚሰራው ደባና አሻጥር በዝርዝር መጋለጡ አይቀርም። ለደሞዝ ሲባል በህዝብ ደም ላይ ማላገጥ ከአንድ “የህዝብ ዓይንና ጆሮ” ነኝ ከሚል የዜና ማሰራጫ የሚጠበቅ አይደለም።

ኢሳት እውነተኛ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ከሆነ ዘመነ ካሴን በተመለተና ሌሎችም አፍነዋቸው ያሉትን ዜናዎች ለህዝብ ግልጽ ማድረግ አለባቸው። ይህንንስ ካላደረጉ ከወያኔ ጋዜጠኞች፣ ከፋና ብሮድካስቲንግ፣ከሚሚ ስብሐቱ፣ ከዘሪሁን ተሾመ፣ ከዳዊት ከበደ፣ ከንጉሴ ወልደ ማርያም፣ ከሰላም ሬዲዮ፣ ከኢትዮ ዲያስፖራ ራዲዮና ከሌሎችም በምን ይለያሉ? በሚከፈላቸው ደምወዝ አንደበታቸውን የለጎሙ የኢሳት ጋዜጠኞች መረጃ ማፈናቸው የተሸረበ ተንኮል እንዳለ የሚያረጋግጥ ነው።

አቶ ዘመነ ካሴ እድሉ ተሰጥቶት ቃለ ምልልስ ቢደረግለት የግንቦት ሰባት ጉድ ስለሚጋለጥና ማታለሉና ቅጥፈቱ እንዲሁ ከአገር ወዳዶች የሚዘረፈው ገንዘብ ስለሚቆም እንዲሁም የሻቢያን የኢትዮጵያ ጠላትነት ለማያውቁና ለረሱ ሰዎች ጥሩ ትምህርት ስለሚሰጥ የኢሳት ጋዘጠኞች ለህዝብ ጥቅም ይህንን ደባ ሰብረው መውጣት አለባቸው።

ካልሆነም ደግሞ ጨክነው እንደ አቤ ቶኪቻው እራሳቸውን ከኢሳት ማግለል አለባቸው። የኢሳት ጋዜጠኞች አሜሪካን አገር አገር ተቀምጠው እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ ወብሸት ታዬና ሌሎችም ወያኔ አፍንጫ ስር መስዋዕትነት እየከፈሉበት የሚገኘውን የሙያ ኃላፊነትና የአገር አለኝታነት መወጣት ሊያዳግታቸው አይችልም፣ አይገባምም።

አበጀ በለው (ዋሽንግተን ዲሲ)