ሀገርን እንደ ሀገር ዜጎችን እንደ ግለሰብ አይቶ ትንታኔ የሚሰጥ አመራር ያጣሁበት ግንቦት 7 የሚባል ድርጅት

Print Friendly, PDF & Email

ሀገርን እንደ ሀገር ዜጎችን እንደ ግለሰብ አይቶ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ አመራር ያጣሁበት ድርጅት ከገዥው መንግስት ባልተናነሰ መልኩ ግንቦት 7 ነው።

(በወይንሸት ሞላ – የሰማያዊ ፓርቲ አባል)

ግንቦት ሰባት በብሔር ፖለቲካ አናምንም እያለ ሲከራከር የነበረውን ምን አደርሶት ነው? አሁን አዲስ አበባ የአንዱ ሆኖ ሌላው መጤ ነው የሚለው? እንዲህ እንደ ዛሬው ዘር ቆጠራ ፋሽን ሳይሆን የግንቦት ሰባት አመራሮች ዘረኝነት እና የዝቅተኝነት መንፈስ ክፉኛ በተጠናወተው ልባቸው የሚናገሩትንና የሚፅፍትን መመልከት ከጀመርን አመታት አልፎናል:: አጠቃላይ ሀገርን እንደ ሀገር ዜጎችን እንደ ግለሰብ አይቶ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ አመራር ያጣሁበት ድርጅት ከገዥው መንግስት ባልተናነሰ መልኩ ግንቦት 7 ነው።

አዲስ አበባ የነማን መሆን እንደሚገባት የሚወስነው ግንቦት ሰባት ከአስር አመት በፊት ባራክ ኦባማ ሲመረጥ በድርጅታቸው ልሳን ላይ “በአገራችን በኢትዬጵያም ለአስርተ-መቶዎች አመታት እየተፈራረቀ ሲገዛ የኖረው የትግሬና የአማራ ልሂቅ .. ቦታውን ለደቡቡም ለኦሮሞውም ለአኝዋኩም የማይለቅበት ምንም ምክንያት የለውም” የሚል እንድምታ ያለው ፅሁፍ አስነብበውን ነበር:: ይህ በነሱ እሳቤ ጉዳዩ የተረኝነት እንጅ የዜግነት እንዳልሆነ በግልጥ ያሳያል:: ሌላው ቢቀር በግንቦት ሰባት ብሄራዊ ምክር ቤት ከኢትዬጵያዊነት ባሻገር ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ከሌላው አባል ተመራጭ እንደሚያስደርግ ደንባቸው ይደነግጋል:: አሁን ለምሳሌ እኔ አማርኛ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ ነኝ:: ስለዚህ መስፈርቱን ከኔ በላይ ሊያሟላ የሚችል ሌላም ቋንቋ ተናጋሪ አባል ካለ ምንም በእውቀት በክህሎት እና በተለያዩ ነገሮች ብበልጥም ላልመረጥ እችላለሁ ማለት ነው::

ለነገሩ ግንቦት ሰባት ዜጎችን በእኩል መነጥር የሚመለከት ብሄራዊ ፓርቲ ነው ብየ አላምንም:: እንዴውም አማራ-ጠል ድርጅት ለመሆኑ ከዚ በላይም ማስረጃ መጥቀስ እችላለሁ::

ለማንኛውም የሚሰማ ሰው ካለ አዲስ አበባ ከኢትዬጵያውያን ተርፋ የአፍሪካ መዲና ናት ስትባል ዶክተር ታደሰ አዲስ አበባ የአንድ ብሔረሰብ ንብረት መሆኗን ለማሳየት መሞከራቸው ህዝብን የሚያጣላ እንጂ የሚያፋቅር አይደለም። በተጨማሪም አመለካከታችሁም ቢሆን ህወሃት ጫካ ውስጥ ከፃፈችው ማኒፌስቶ ጋር ልዩነት የለውም:: ድርጊታችሁ ለትችት እና ለቅያሜ የሚያጋልጥ ነው:: የኢትዬጵያ ህዝብ የሰለጠነ ስለሆነ እንጂ እንደነዚ አይነት “አዋቂዎች” ትልቅ ቀውስ ይፈጥሩ ነበረ።

እኔ እንደ ዜጋ ሁሉንም ዜጎች በእኩል መነጥር የሚመለከት ድርጅት ከእናንተ እጠብቃለሁ:: ሀገሬም ዜግነትን ዋልታና ማገር አድርጋ ለዘለአለም የምትኖር ሀገር እንድትሆን እፈልጋለሁ:: ትችትን በአግባቡ ተቀብላችሁ ወደፊት መሄድ የማይቻል ከሆነ በግሌ ዝምታየ ነገ ሊያስጠቃኝ እንደሚችል አስባለሁ::

ግልባጭ:- ስድብ ትጥቁ ለሆናችሁ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች

ጉዳዩ የህልውናም ጭምር ነው:: ነገ የግንቦት ሰባት ኢትዬጵያ በቋንቋዬ አድሎ ቢያደርግብኝ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ቢለኝ ትናንት ምን ስሰራ እንደነበር የሚጠይቅ ህሊና አለኝ::
ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅ!!!

ዶ/ር ታደሰ ብሩ ስለ አዲስ አበባ የሰራውን ፕሮግራም ሙሉውን ከዚህ በታች ይመልከቱ።