የዋልድባ መነኮሳት በእስር ቤት የደረሰባቸው ስቃይ

Print Friendly, PDF & Email

(ከቂሊንጦ እስር ቤት የተላከ)

መነኮሳቱ ዋልድባ ገዳም መታረስ የለበትም፣ የእግዚያብሔር ቤት ነው በማለት ከ2004 ዓም ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ በመሄድ ለእምነታቸው ሲታገሉ ቆይተዋል። ከ4ቱ የገዳሙ ተወካይ መነኮሳት አንዱ የሆኑት አባ ገ/ እየሱስ ኪ/ማርያም ይህን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ በመጠየቃቸው ለእስር ተዳርገዋል። ከአባ ገ/ እየሱስ ኪ/ማርያም በተጨማሪ አባ ገ/ስላሴ ወልደ ሀይማኖትም ያለ ምንም ማስረጃ በሀሰት ተከሰው በስቃይ ላይ ይገኛሉ።

የዋልድባ ገዳም መፍረስ የለበትም በማለታቸው ብቻ የግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው በ”ሽብር” ተከሰዋል። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ መነኮሳት በ”ሽብር” የተከሰሱበት ወቅት ነው።

ያለ በቂ መረጃ እና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩት መነኮሳቱ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። አሁን ደግሞ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን 5 በሚባል ጨለማ ቤት ተወርውረዋል። የምንኩስና ልብሳቸውን እና ቆባቸውን አውልቁ፣ ካላወለቃችሁ ፍርድ ቤት አንወስዳችሁም ተብለዋል። በየጊዜው ድብደባ እየተፈፀመባቸው ታፍነው ይገኛሉ።

መነኮሳቱ ልብሳችን የእምነታችን መገለጫ ስለሆነ አናወልቅም፣ እምነታችን የሚያዘንን እንጅ ሌላ አናደርግም፣ የቃል ኪዳን ልብሳችን ነው በማለት በፅናት እየታገሉ ይገኛሉ።

በፆምና በፀሎት የደከሙትን መነኮሳት ሜዳ ላይ እያንከባለሉ ስለደበደቧቸው ለህመም ተዳርገዋል። የታሰሩበት ጨለማ ቤት በመሆኑ የተነሳ አይናቸው ተጎድቷል። ህክምና ማግኘት ስላልቻሉ በተለይ አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም በከፍተኛ ስቃይ ላይ ይገኛሉ። በእስር ላይ ያሉትን መነኮሳት ለመጠየቅ ከዋልድባ ገዳም የሚመጡ አባቶች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ነው።