በአማራ ሳይንት ከሚገኘው ተድባበ ማርያም ገዳም ጽላት ተሰረቀ

Print Friendly, PDF & Email

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2010)

በአማራ ሳይንት ከሚገኘው ተድባበ ማርያም ገዳም ጽላት መሰረቁን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

በዚህም የአካባቢው ምዕመናን የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በሌላም በኩል በምዕመናን ተቃውሞ ሲቀርብባቸው የቆየው የአዲስ አበባው ሳህሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደብደበው ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።

በደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ወረዳ የሚገኘው የጥንታዊው የተድባበ ማርያም ገዳም በስሩ ከሚገኙት 12 አብያተክርስቲያናት የአንደኛው የመድሃኒአለም ቤተክርስቲያን ጽላት መሰረቁ የታወቀው በቅርቡ ነው።

ሕዝቡም ጽላቱ እንዲመለስና የዘረፋትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

የገዳሙ አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ሃላፊ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ወደ ለንደን ከተጓዙም 5 ወራት ማስቆጠራቸው ታውቋል።

አስተዳዳሪው ማህተሙ ላይ ቆልፈው ወይንም ይዘው በመሄዳቸው ስራዎች ተስተጓጉለዋል የሚል ተቃውሞም በመቅረብ ላይ ይገኛል።

በጽላቱ መሰረቅ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ምዕመናኑ አስተዳዳሪውን በመጠየቅ ላይ ቢሆኑም አስተዳዳሪው ግን ከእንግሊዝ ለንደን አለመመለሳቸው ታውቋል።

ከአክሱም ጺዮን ገዳም ቀጥሎ ጥንታዊ የሚባለው የተድባበ ማርያም ገዳም ከአዲስ አበባ ከተማ በ612 ኪሎ ሜትር በደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ወረዳ የሚገኝ ጥንታዊ ገዳም ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የሳህሊተ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ከምዕመናን ጋር በፈጠሩት ውዝግብ ተደብድበው ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።

አስተዳዳሪው አባ ሩፋኤል የማነብርሃን ከምዕመናኑ ጋር በፈጠሩት ውዝግብ ለፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስ አቤቱታ መቅረቡንም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

በ12 አውቶቡሶች ተሳፍረው ወደ ፓትሪያርኩ ለአቤቱታ ሲጓዙ የነበሩ ምዕመናን ጉርድ ሾላ አካባቢ ሲደርሱ በፖሊሶች ጉዟቸውን ለመግታት የተደረገውን ሙከራ አልፈው ምዕመናኑ ለፓትሪያርኩ ያቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን ምዕመናኑ ገልጸዋል።

ውዝግቡ ሳይቋጭ እየተካረረ መሄዱን ተከትሎም አስተዳዳሪው በሳምንቱ መጀመሪያ በደረሰባቸው ድብደባ ሆስፒታል ገብተዋል።

ኢሳት ማረጋገጥ ባይችልም አስተዳዳሪው የተደበደቡት በምዕመናኑ ላይ ሽጉጥ ማውጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተገልጿል።