ወያኔ የሰጠን ምርጫ ባርነትን ወይም ሞትን ነው! – መቅደላ – የዐኅኢአድ ልሣን ቅጽ ፩ ቁጥር ፬

Print Friendly, PDF & Email

ወያኔ የሰጠን ምርጫ ባርነትን ወይም ሞትን ነው!

መቅደላ – የዐኅኢአድ ልሣን ሓሙስ ታህሳስ ፲፯ ቀን ፪ሺ፲ ዓ.ም

ሟቹ የወያኔው አውራ የነበረውና በሙት መንፈሱ አገሪቱን እንመራታለን የተባለለት መለስ ዜናዊ፣ ለትግሬ-ወያኔ የበላይነት ጠብቆ ለመጓዝ ምን ያህል እንዳጎደለ ከሞቱ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት በወያኔዎቹ ፖለቲካዊ አመራር ዙሪያ የሚስተዋለው ድህነት የቱን ያህል የሠፋና የጠለቀ እንደሆነ ከተስተዋለ በኋላ ነው። መለስ ሥልጣኑን የተናዘዘለት እንደሆነ የሚነገርለት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከዐባይ ወልዱ ያልተሻለ ወደል መሃይም መሆኑን ከጅምሩ እየተስተዋለ ነው። «ጠላት ብርቁ» የሆነው የወቅቱ የትግሬ-ወያኔዎቹ «ራስ» ደብረጽዮን፣ የጎንደርን ሕዝብ እንደ ሕዝብ በጠላትነት ሲፈርጅ፣ ትናንት ምን ነበር? እንዴትስ ነበር? ነገስ ምን ሊያስከትል ይችላል? ብሎ የትናንቱን ከዛሬው፣ የዛሬውን ከነገው አዛምዶ ለማየት አልሞከረም። ትናንትን በቅጡ ያልተረዱ ዛሬን በትክልል ሊያውቁ አይችሉም፣ በዚህም በነርሱ ዘንድ ነገ ጥቅጥቅ ጨለማ ነው። ዛሬ በወያኔ ሠፈር የምናየው መጠላለፍና ዝብርቅርቅ ሁኔታ ከዚህ የታሪክና የፖለቲካ ድህነት የመነጨ መሆኑን እንገነዘባለን።

ትናንት በአንድ የመንግሥት ነው በተሰኘ ቴሌቪዥን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የተባለው ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ በአገሪቱ ውስጥ ስለተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታና በምስቅልቅሉ ስለተጎዱ፣ ስለተበደሉና ስለተገደሉና ንፁሕ ዜጎች ተጠያቂው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው በማለት በገለጸበት የደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ፣ አዲሱ የወያኔው ሊቀመንበር በዚያው ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ፣ «በርካታ ጠላቶች ተነስተውብናል፤ እነኚህን ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ኃይሎች የማያዳግም ትምህርት እንሰጣቸዋለን» ሲል መሰማቱ የቱን ያህል ሕዝቡን እንደናቀና ሊጨርሰውም እንደተዘጋጀ በግልጽ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ በአመራሩ መካከል አንድነት የሚባል ነገር የሌለ መሆኑን ያሳያል። በአገሪቱ ላይ የሰፈነው አመራር አንድ ወይስ ሁለት? ወይስ ሁለቱም የአንድ መንግሥት ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብሎ ለመጠየቅ መንገድ ይመራል። የነዚህ አንድነትና ልዩነት፣ አባቶቻችን እንደሚሉት ፤ «ሽልም እንደሆን ይገፋል፣ዱባም ከሆነ ይጠፋል» ማለትን እንመርጣለን።(Read more, pdf)