የሽግግር ጊዜ ሰነድ ጋጋታ! (አንዱዓለም ተፈራ)

Print Friendly, PDF & Email

ሁላችንም የትግሬዎች መንግሥት አይቀሬ መውደቂያው መቃረቡን እናምናለን። በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጥርም ሆነ ብዥታ የለም። ከዚያ በኋላ የሚከተለውን፤ ከዚያ በፊትም፤ ይሄ እንዴት ሊከሰት እንደሚገባውና እንደሚችል፤ የአንድነት ግንዛቤ መኖሩን ግን እጠራጠራለሁ። ጥቂት ግለሰቦች የሽግግር ጊዜ ሰነድ ረቂቅ በማዘጋጀት፤ ለአንባቢዎች አቅርበዋል። አንዳንድ ድርጅቶችም የሚቀርቧቸውን በማሰባሰብ፤ ድርጅታዊ የሽግግር ሰነድ አዘጋጅተው፤ አሰራጭተዋል። ይኼ የሁላችንም፤ የሽግግሩ ሰነድ አዘጋጅዎቹ፣ የታጋዮቹና የመላው ሕዝብ ጉዳይ ነው። ታዲያ፤ የሽግግር ሰነዱን ለማርቀቅ ከመሯሯጥ በፊት፤ ቢያንስ ብዙዎቹን ለማሰባሰብ ለምን ጥረት አልተደረገም? የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ይሄ ነው።

1991 London Conference: Left hanging: OLF leader Lencho Leta on the far left was left shafted by the negotiations, despite the intervention of Isaias Afewerki (second from left) and US Assistant Secretary of State for African Affairs, Herman J. Cohen (middle). Meles Zenawi (second from left) clearly came out on top (Image: Herman J. Cohen)

የሽግግር ሰነድ የሚዘጋጀው፤ ለሽግግር ወቅት ነው። ሽግግሩ ደግሞ፤ አንዱ ለቆ፣ ፈርሶ፣ ጠፍቶ፤ ሌላው በግሩ የሚተካበት ወቅትና ሁኔታ ነው። በርግጥ ባሁን ሰዓት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የትግሬዎቹን መንግሥት “በቃኝ አልገዛም!” ብሎ፤ የትግሬዎቹም መንግሥት መግዛት አቅቶት፤ ሀገራችን በትርምስ ላይ ለመሆኗ፤ ማስረጃ አያስፈልግም። ነገር ግን፤ ይህን ያበቃለትና የመጨረሻው አድርጎ ወስዶ፤ ለነገ ዝግጅት የሚደረገው ሩጫ፤ የዛሬውን የቤት ሥራ ያጓድለዋል። ዛሬን እንዲረዝም ያደርጋል። ለምን? ይህ ተገቢ ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በትግሉ ሂደት፤ ከማንኛውም ድርጅት በፊት ቀድሞና ከፊት በለፊት እየመራ፤ ይህ መንግሥት፤ እንደ እስካሁኑ መግዛት እንደማይችል አሳይቷል። ከዚያ ተርፎ፤ አድማጭ አጣ እንጂ፤ “እባካችሁ ተባበሩ!” “እባካችሁ ከዚህ ዘረኛ አምባገነን የወራሪ ቡድን የተሻለ አማራጭ ሆናችሁ ቅረቡልን!” እያለ በያገኘው አጋጣሚ ሁሉ፤ የማይሰለች ልመናውን፤ ቆጥሮ ለመዝለቅ በሚያሰለች ድግግሞሽ አስተላልፎልናል። በሶፋችን ላይ ተኮፍሰን፤ በኮምፒተራችን መስኮት ተደቅነን፤ “ሕዝቡ ለምን አይነሳም!” ለምንል የሳይቨር ታጋዮች፤ ዓይናችንን መክፈት ብቻ ነው ያለብን።

ከዚያ በመለስ፤ ትግላችን በሳይቨር ዙርያ ያጠነጠነ ነው። መግለጫ ማውጣቱን የተካኑበት አሉ። ማመልከቻ ማሰባሰቡን ሙያዬ ብለው የያዙ አሉ። በውጪ ሀገራት ዓይኖች መታየትንና የኛን የቤት ሥራ እንዲሠሩልን የምንለምን ጥቂቶች አይደለንም። ይህ ሁሉ የሚያሳየው፤ ከመካከላችን ምን ያህላችን ለዚህ ታሪካዊ ኃላፊነት፤ ሙሉ ቆራጥነትንና አስፈላጊውን መስዋዕትነትን ለመክፈል አለመዘጋጀታችንን ነው። በርግጥ ደርጋማውን የመንግሥቱ ኃይለማርያም አረመኔ መንግሥት በመጣልና የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ለንደን ላይ በመወሰን በኩል፤ ከሞላ ጎደል የውጪ ኃይሎች ወሳኞች ነበሩ። የተከተለውን ሁላችን እናውቀዋለን። አሁንም እኒህ ኃይሎች፤ በምንም መንገድ፤ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የማይፈለቅሉት ደንጋይ የለም። ትርፉ ግን ያው የጉልቻ መቀያየር ነው።

እርግጠኛ ነኝ፤ ብዙዎቻችን ይህ እንዲደገም አንፈልግም። የታጥቦ ጭቃ ሽክርክር ትግሉ እንዲቀጥል አንሻም። የውጪ መንግሥታትና ኃይሎች በኛ የወደፊት ሂደት፤ እጃቸውን እንዲያስገቡ አንሻም። ይህን ግን፤ ከኮምፒውተር መስኮት ፊት ሆነን፤ በመጻፍና በማንበብ የምንፈይድበት ኩናቴ የለም። የኛ ኃላፊነት መሆኑን አውቀን፤ ወደፊት ስንቀርብ ነው። “የኔ የግሌ ሳይሆን፤ የመላ ሕዝቡ ኃላፊነት ነው። ብቻየን!ና እኔ የምፈልገውን ብቻ! የምልበት ሳይሆን፤ “ከሌሎች ጋር ሆኜ፤ በብዙኀኑ ድምጽ እየተገዛሁ፤ የምችለውንና የሚገባኝን አደርጋለሁ!” ብለን ስንዘጋጅ ነው። እስኪ ወደ ተነሳሁበት ወደ የሽግግሩ ሰነድ ልመለስ።

የሽግግር ሰነዱን ማዘጋጀቱ መጥፎ አይደለም። ያሳሰበኝ ግን፤ ሁሉም በየኪሱ የሚይዘው የየራሱ የሽግግር ሰነድ ሲያዘጋጅ፤ ሌላ ተጨማሪ የቤት ሥራ ለራሳችን እየሠጠን መሆኑ አሳስቦኛል። በያንዳንዱ በተዘጋጀው የሽግግር ሰነድ ጀርባ፤ የተወሰኑ ደጋፊዎች አሉ። እኒህ ደግሞ ላዘጋጁት የሽግግር ሰነድ፤ ጦራቸውን ገትረው ይሟሟታሉ። ይህ ሌላ ክፍፍል አስከተለ ማለት ነው። የኔ ችግር ይሄ ነው። ተሯሩጦ ወደ ነገው መዝመቱ፤ የዛሬውን ሥራ ያመሰቃቅለዋል እንጂ፤ አያቀለውም። ከመዝናናት አንጻር ላየው፤ ምንም ችግር የለውም። ምክንያቱም፤ በዚህ ዕይታ አኳያ፤ ሁሉን አሰባስቦ ጥሩውን ለቃቅሞ፤ አዲስ ማውጣት ነው። ይህ ግን ላባባል የሚቀል፤ ቦታ የሌለው ለመሆኑ፤ የድርጅቶች መከፋፈል በቂ ምስክር ነው። ታዲያ ምን ይሻላል?

ድንቅ! ይህ የሽግግር ሰነድ፤ በሽግግሩ የሚሳተፉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የሚገዛ ነው። ስለዚህ፤ እኒህ ተሳታፊዎች በዝግጅቱ ያሉበት የሽግግር ሰነድ ነው የሚገዛቸው። “እኔ በማምንበት መንገድ፤ ለሁላችሁም ይሠራል ባልኩት ሁኔታ አዘጋጅቸዋለሁና፤ ችግር የለውም! የምታሻሽሉትን አሻሽሉት!” የሚለው አባባል፤ ንቀትን ያዘለ፤ ተቀባይነት የሌለው እብሪት ነው። ቅደም ተከተሉ፤ መሰባሰብ፤ ከዚያ አብሮ መሥራት ነው። አሁን በማዕከልነት ራሳቸውን ያሰለፉት፤ ሀገር ቤት ያሉት ሰላማዊ መንገድን የመረጡ ታጋዮች፤ በውጪ ደግሞ ሶስት ወይንም አራት የሆኑ ማዕከሎች አሉ። እኒህ አራቱ ማዕከል ሊሆኑ የሚሞክሩት ስብስቦች፤ መለያያ ጉዳያቸው፤ “እኔ የያዝኩት መንገድ ነው መሆን ያለበት!” የሚል ግትርነት ብቻ ነው።

እስኪ ተመልከቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የትግሬዎቹ መንግሥት ነው። የሁሉም በዳይ ይህና ይህ ብቻ ነው። ሁሉም የሚፈልጉት ይህ መንግሥት እንዲፈርስ ነው። ይህ መንግሥት “በምንም መንገድ መፍረስ አለበት!” የሚለውን ባንድ መንገድ ወይንም በሌላ፤ ሁሉም ይቀበላሉ። በመሠረቱ፤ ይህ “መንግሥት መፍረስ አለበት!” ያለ ክፍል፤ ይህን መንግሥት በዚህ ወይንም በዚያ መንገድ ለመጣል ከተሰለፉት ጋር ጠብ አይኖረውም። በሰላም አመጽም ይበል በትጥቅ አመጽ፤ ይህ መንግሥት መውደቅ አለበት ያለ ድርጅት፤ ከሌላው ጋር፤ በአወዳደቁ ሳይሆን፤ መከተል ባለበት ነው፤ መነጋገር ያለበት። እዚህ ላይ አውዳቂው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ስቼው አይደለም። ነገር ግን፤ ሁለቱም ክፍሎች ሊጣሉ የሚገባቸው፤ “በዚህ መንገድ መውደቅ አለበት!” ወይንም “በዚያ መንገድ!” በሚለው ሳይሆን፤ እንዴት ነው ተባብረን የምንጥለው በሚለው መሆን አለበት፤ ለማለት ነው።
ነገ ተጨማሪ የሽግግር ሰነዶች እንደሚቀርቡ ቅንጣት ታክል ብዥታ የለኝም። ይህ ደግሞ የበለጠ ትግሉን እንደሚያመሳቅለው አምናለሁ። ስለዚህ፤ እውነተኛ መፍትሔ እንዲገኝ የምንሻ ሁሉ፤ ካሁኑ፤ አብዛኛውን ክፍል ያጠቃለለ የሽግግር ጊዜ ሰነድ እንጂ፤ ሁሉም በየኪሱ የሚሸጉጠው ሰነድ እንዲያዘጋጅ የጋበዘውን የተበታተነ የትግል አባዜ፤ በተቻለ ፍጥነት ወደ አንድ በማምጣት፤ የምንችለውን ጥረት፤ እባካችሁ እናድርግ።

ይሄን በሚመለከት ሃሳብ ካላችሁ፤ በ eske.meche@yahoo.com ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።