ከአክሱም መልስ … (ሚኪያስ ጥላሁን)

Print Friendly, PDF & Email

ልጁ አሁንም – አሁንም ከሃሳብ ጋር ይባትላል። ያለፉትን የመከራ ቀናት ሲያስታውስ፣ ውስጡ በከባዱ ይረበሻል።

“… ሁኔታዎች ጥሩ አልነበሩም። በአንድ ምት(በብረት መመታት እንዳለ ለመግለፅ ነው።) ልትሞት ትችላለህ። ብቻ፤ ሁኔታዎች ለአንድ አማርኛ ተናጋሪ ወጣት ጥሩ አልነበሩም።”

Aksum University, Tigray

ጎፈር ጠጉሩን በየሰከንዱ ያምሳል፤ ዓይኑንም ወደኮርኒስ ይልካል።

“ይህን ብጥብጥ ያስነሱት የመቀሌና የኣዲግራት ልጆች ናቸው። ሁሉም በደቦ ይነጋገርና ‘አማራ ነው!’ የተባለን ሁሉ፣በአገኙት ነገር ያጠቃሉ። ግቢው ውስጥ ደግሞ ድንጋይ አይታጣም። ’ድንጋይ’ ስልህ-ይሄ የሚፈረከስ፣ የሚሰነጣጠቅ ድንጋይ እንዳይመስልህ! ባልጩት! ሲወረወር ከሩቅ ድምፁ ይሰማሃል። ፌሮ ብረትም በሽ ነው። ግቢው ውስጥ የህንፃ ግንባታ ስላለ፣ ፌሮና አርማታ ብረት በየቦታው ተበታትኖ ይገኛል። እንግዲህ ያጠቁን በ’ነዚህ ሁሉ ነው። እኛም ራሳችንን ለመጠበቅ ጩቤ ታጥቀን ነበር። ከጩቤው ሌላ፣ አልጋ ላይ የሚሰካውን የብረት መወጣጫ ነቅለን ይዘናል፤ ቢመጡ ለማበራየት!”

በረዥሙ ተነፈሰ፤ እጁ ላይ ሲያፍተለትለው የቆየውን ሪሞት ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠና ወጉን ቀጠለ፣

“እንደ አጋጣሚ፣ እኛ ብሎክ ላይ ያለ አማራ ተገድሎ ተገኘ። አሟሟቱ አልታወቀም። ‘ታንቆ ነው!’ ይባላል። ይህ ልጅ ከሞተ በኋላ፣ መጠንቀቅ ጀመርን። ሁላችንም አማራ ነበርን።

“… ለመተንኮስ ሰበብ ነው የሚፈልጉት። ለምሳሌ:- ካፌ ውስጥ የመመገቢያ ሳህኑን ይጥልና ወደ አንተ ዞሮ ‘ለምን ገፋኸኝ?’ ብሎ አምባጓሮ ሊያስነሳ ይችላል። ወይም ወጡን ልብሱ ላይ ያንጠባጥብና ‘ማናባህ ሆነህ ነው-ልብሴ ላይ ወጥ ያንጠባጠብከው?’ ብሎ ሊወቅጥህ ይችላል።

በሁሉም መንገድ ነገር ይፈልጉሃል፤ ይፈታተኑሃል።

በትምህርት፣ በስፖርት ስትበልጣቸው አይወዱም። ሊያጠፉህ ይታትራሉ። ፈተና ከአስሩ አስር ካመጣህ፣ በነጋታው ሊገድሉህ ይችላሉ። እነርሱን መብለጥ የማይታሰብ ነው። ለመግደል ፈጣን ናቸውና።”

ሪሞቱን አንስቶ “ቻናል” መቀያየር ጀመረ።

የአፍታ ፀጥታ ነገሰ!

ይህ ልጅ አንደኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነው። አክሱም ተፈጥሮ በነበረው ግጭት፣ አካባቢውን ለቅቆ ወደ ባህርዳር መጣ። ከግቢው የወጣው ዘበኞችን ሸውዶ ነው። በሽወዳ አልፎ፣ ጓዙንም በገሚሱ እዛው ትቶ በአይሮፕላን ወደ ጎንደር በረረ። ጎንደር ካረፈ በኋላ፣ በመኪና ወደ ባህር ዳር መጣ። ትንሽ ጉድል የሚመስለውን ጉዞ እንዲያስረዳኝ አልጠየቅኩትም፤ በውክቢያውና በጉዞው ምክንያት ተዳክሞ ነበርና።

የልጅዬው አባት እንዳጫወቱኝ ከሆነ፣ በዚህ ጉዳይ ብአዴን ቢሮ ድረስ፣ ከሌሎች ወላጆች ጋር ሄደው ነበር። የተሰጣቸው ምላሽ ግን አሳዛኝ ነው።

“በወታደር እየተጠበቁ ነው፤ ሰላም ሰፍኗል!” የሚል ምላሽ ከግልገል ኳድሪሌው ተሰጣቸው።

ሌሎች የባለስልጣን ልጆች “ኮሽ!” ባለ በነጋታው ከየዩኒቨርሲቲው ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል። ሌላው ሃብትም፣ ስልጣንም የሌለው ወላጅ ያሳደገው ተማሪ ግን እዚያው ዶርም ውስጥ ተከርችሞበት እንዲከርም ተፈርዶበታል።

አባት ወሬውን ከሰሙ በኋላ፣ በጣም ስሜታዊ ሆነው ነበር። እየተንተገተጉ ለ “ግልገሉ” የተናገሩት ከዚህ በመነሳት ነው። በአንድ ሃገር፣ ከዜጎችም ውስጥ ለነፍሶቻቸው የተለያየ ደረጃ ሲሰጥ ማየቱ፣ በጣም ያናድዳል።

“… ሁሉም ትግሬ እንደሌሎቹ አማራን ‘ይተነኩሳል’ ማለት አይደለም። ለምሳሌ:- አንድ የአድዋ ልጅ ከኛ ዶርም በጉርብትና ይኖራል። ችግር ለመፍጠር ሲዶልቱ፣ በቅርብ ርቀትም ቢሆን ይሰማል። ለኛ ‘ማታ ለእራት አትውጡ! ሁኔታው ጥሩ አይደለም!’ ብሎ ይነግረናል። እኛም ከዶርም አንወጣም። እርሱ እንዲህ ብሎ በነገረን ዕለት፣ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ነበሩ። ሌላ ቀን፣ አንድ ተማሪ ሲደበደብ፣ ይኸው የአድዋ ልጅ ይመለከታል። ሄዶ ከሰዎቹ እጅ ተማሪውን ባያስጥል ኖሮ፣ የልጁ ነፍስ ወደ ሰማይ አርጋ ነበር።

“የከተማው ህዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው። እኛንም ለተወሰነ ጊዜ ከነውጠኞቹ ሸሽጎናል። ችግሩን የፈጠሩት ተማሪዎቹ ናቸው፤ ቅድም እንዳልኩህ የመቀሌና የአዲግራት ልጆች ናቸው-ችግሩን የፈጠሩት። እነዚህ ልጆች ላይ እስከ አሁን እርምጃ አልተወሰደም። ለምን ይመስልሃል? የሃገር ልጆች ‘ለምን ተነኩ?’ ተብለው ስለሚወቀሱ!

ባለፈው ዓመት አንድ አማርኛ ተናጋሪ ተማሪ ከአንድ ትግሬ ተማሪ ጋር ይጣላል። በዚህ ምክንያት ሁለቱም እንዲባረሩ ተደረገ። አማርኛ-ተናጋሪው ወደ ሚመለስበት ተመለሰ። ትግሬውስ? በሰው-ሰው ሃላፊዎቹን ለምኖ ተሳካለትና ወደግቢ ተመለሰ። ይሄ የሚያሳየው ዘረኝነት እንዳለ ነው። ቆይ! … በምን ማስተማመኛ ተማምኜ፣ ወደ አክሱም የምመለሰው? ከፎቅ ተማሪን ከወረወረ ልጅ ጋር ወይም በፌሮ ብረት ተማሪን ከደበደበ ልጅ ጋር አጠገብ ለአጠገብ እየበላሁ፣ ‘አንተንማ እገድልሃለሁ!’ እያለኝ፣ በሰላም የምማር ይመስልሃል? በስጋት፣ በጭንቀት፣ ከአሁን-አሁን ‘ገደሉኝ’ እያልኩ እየፈራሁ፣ እንዴት በሰላም እማራለሁ? ትምህርቱ ከነፍሴ አይበልጥም!… አንድ ዓመት ባቃጥል ለኔ ምንም ማለት አይደለም፤ አውቃለሁ! ጊዜ ይባክናል። ነፍስስ? እንደትምህርት ሌላ ጊዜ ይገኛል? ትገዛዋለህ? አትገዛውም! ስለዚህ ባልማር ይሻላል።”

አንገቱን ደፍቶ፣ጎፈሬውን በጣቶቹ ማመስ ጀመረ።

የአብዛኞቹ ተማሪዎች እጣ ከመሞትና ከመቁሰል እንደማያልፍ እውነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነግሶ፣ ህዝብ ተፋቅሮ ይኖር በነበረበት ዘመን፣ ህወሃት የሚባል የአጋንንቶች ስብስብ መጣና ነገር-ዓለሙን ቀያየረው። ሰይጣናዊውንና አስፀያፊውን ዘረኝነት በየሰው ልቦና ላይ ረጨ። ይሄው! … የዘራውን እያጨደ ነው። ዳግማዊ-ሩዋንዳን ለመፍጠር ከዚህም በላይ እየሄደ ነው። ተሰጋሪ ፈረስ የሆነው ብአዴን “እወክለዋለሁ” ያለውን፣ የአማራን ህዝብ ከጥቃት ሊጠብቀው አልቻለም። ድሮስ ከጌታው ትዕዛዝን ከሚጠብቅ አሽከር፣ ምን ይገኛል?…

…ነገሩ እየከነከነኝ፣ ልጅና አባትን ተሰናብቼ ለመውጣት ተነሳሁ። አባትዬው በሃሳብ መሰልሰሉን አየሁ።

“ስንቱ አባት ይሆን በሃሳብ የሚባክነው?” ብዬ፣ራሴን ጠየቅኩ።

በሃሳብ እንደተያዝኩ፣ሁለቱንም ተሰናብቼ ወጣሁ።