በኢትዮጵያዊነት የታበተው የአማራ ህዝብ ጥያቄ

Print Friendly, PDF & Email

ቴዎድሮሥ ኃይለማርያም (ዶ/ር)

መግቢያ

ሰሞኑን ከግንባር ዜና የማይጠፉት ዳኛ ዘርዓይ ፣ በተከበረው የችሎት ወንበራቸው ተሰይመው በፍርደኞቻቸው ላይ የሚሰነዝሩት ትችት ለማመን የሚቸግረን አንጠፋም። ተራ ሽምግልና እንኳን ያስነወረውን ዘረኝነት ፣ በህገ መንግሥታዊ የመናገር መብት ተግኖ ለማራመድ ሃፍረት የሌለው ዳኝነት ከጤንነት የመነጨ ነውን? ዳኛ ዘርዓይ ከስራ ሃላፊነታቸው አንፃር የጥቅም ግጭት ትዝብት ላይ ይጥላቸው ካልሆነ ፣ የፃፉትም ሆነ የተናገሩት አዲስ ነገር አይደለም። ምናልባት ልብ ብለን ስናስብ የሚያስደነግጠን ፣ እኚህ ግለሰብ አንድ የታመመ ሥርዓት በተተኪነት ያፈራቸው ወራሾቹ ናሙና መሆናቸው ነው። በተለይ እናት ድርጅታቸው የመገባቸው በአማራው ህዝብ ላይ የተቋጠረ ደመኝነትና የዘረኝነት መንፈስ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ለማሳየት የሚረዳ ይመስለኛል።

ባለፉት ሃምሣ ዓመታት ሀገራችንን ክፉኛ ያናወጠው የፖለቲካ አዙሪት ፣ የጥያቄዎች ሁሉ አውራ ከሆነው የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ጋር እንድንጋፈጥ አስገድዶናል። ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? ኢትዮጵያዊስ ማነው? በኢትዮጵያዊነታችንና በዘውጌነታችን መካከል ያለው አንድነትና ልዩነትስ? ብሄር ግንባታ የማያቋርጥ ሂደት በመሆኑ ፣ የትኛውም ብሄራዊ ማህበረሰብ በዚህ ተፈጥሮአዊ ተጠየቅ ውስጥ ያልፋል። ስለዚህም ፖለቲካችን ጤናማ ቢሆን ኖሮ ፣ ሊያስጨንቀን የሚገባው ከሂደቱ የምናተርፈውና የምናጣው ሚዛን ጉዳይ ነበር።

የተጓዝንበት መንገድ አትራፊ ነውን? ቢሆንማ ዛሬ ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ አንያዝም ነበር። በኔ ግምት ቅንነት ፣ አስተዋይነትና ፍትሃዊነት የሌለበት ጎዳና ምንጊዜም አክሳሪ ነው። በአጠቃላይ የውድቀታችን ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ፣ ቀንደኛው ጠላታችን በጎሰኝነት የቆሸሸ ፖለቲካችን መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም። በአፍለኝነት የተገፋው ‹‹የብሄረሰቦች ጥያቄ›› ከግማሽ ምዕት ውጣ ውረድ በኋላ የዳኛ ዘርዓይን ትውልድ አበረከተልን። ብሄራዊ ራዕይ አልባ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትን ክፉኛ ተፈታተነ። የብሄረሰቦች ነፃ አውጭነቱ ቀርቶ ፣ ሀገሪቱን ገሃዳዊ ‹‹የብሄረሰቦች ገሃነም›› አደረጋት።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ባለፈው ግማሽ ምዕት ብሄራዊ ህልውናችንን ባስጨነቅንበት የነፍስ ብርበራ ሂደት መሃል ተዘንግቶ ፣ ተድበስብሶ ወይም ተቀብሮ የቀረ አንድ አብይ ጉዳይ አለ። የአማራው ህዝብ ጥያቄ! ‹‹ደሞ አማራ ምን ጥያቄ አለው?›› ፣ ‹‹አማራ ተጠያቂ እንጂ ጠያቂ ያደረገው ማነው?›› ከናካቴው ‹‹አማራው አለ አንዴ?›› የሚሉት አፀፋዎች በተለይ በዳኛ ዘርዓይ እድሜ የተለመዱ ናቸው። ነገር ግን ተወደደም ተጠላም አማራው አለ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ የግሉ የመብትና የማንነት ጥያቄዎች አሉት። እንዲያውም ከሌሎች ወንድሞቹ በተለየ ፣ በአማራው ህዝብ ላይ የተደቀነበት ተግዳሮት ከማንነቱ ጉዳይ ጋር የተቆራኘ ነው። እንዴት?

ጥርስ የገባ ህዝብ

የአማራው ህዝብ የቅርብ ታሪክ የኢትዮጵያ ዝንጉርጉር እጣፈንታ ሁነኛው ማሳያ ነው። የአማራ ፍዳ ጠንሳሾች ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ህልማቸው ከአንዴም ሁለቴ የከሸፈባቸው ጣልያኖች ናቸው። ጣልያኖች አድዋ ላይ ከደረሰባቸው ውርደት በኋላ ፣ አማራውን የዚህ ቀንደኛ ጦስ አድርገው ጥርስ ነከሱበት። በአውራጃ ፣ በሃይማኖትና በመደብ እንዲከፋፈል ፣ በወንድሞቹ አይን እንዲጠላና የጥቃት ኢላማ እንዲሆን ፣ አቅም እንዲያጣና በዝግታ እንዲጠፋ በረዥሙ ተደገሰለት።

ጣልያኖች ይህ ሴራቸው በሁለተኛው ወረራቸው ወቅት (1928 – 1933 ዓ.ም) ፍሬ አፍርቶ ፣ የረባ ውጊያ ሳይገጥማቸው ኢትዮጵያ ከእጃቸው ወደቀች። አሁን ለአማራው ጥያቄ የማያዳግም ፋሽስታዊ መፍትሄ ለመስጠት ፣ በዓለም ህዝብ ፊት ሰፊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካሄዱበት። ግራዚያኒ በአንደበቱ ‹‹አማራውን አርደን መፍጀት ግዴታችን ነው›› አለ። ጀግናው የአማራ ህዝብ ለሀገሩ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ህልውና ለአምስት መራራ ዓመታት ለመፋለም ተገደደ። እዚህ ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው።

የአማራ ግለ-ታሪክ ባንዲራ ከተመለሰ በኋላ ይጀምራል። ጣልያን ቢነቀልም በመላ ሀገሪቱ ላይ የተከለው አማራውን የመነጠል መርዝ መረቀዘ። አማራው ጠላት ካደረሰበት ከፍተኛ ስብራት የሚያገግምበት ፋታ እንኳን አላገኘም። ለሀገሩ ነፃነት ያንን ሁሉ ሃሳር መቀበሉና ደሙ መዘንበሉ ከቁም ነገር የማይጣፍለት አመድ አፋሽ ሆነ። እንደ ወጋችን ለይሉኝታ እንኳ ከንፈር የሚመጥለት አጣ። ጭራሽ ለሀገሪቱ ችግር ሁሉ ተወቃሽ ተከሳሽ ሆኖ አረፈ። ከመሃሉ ያሉ ወንድሞቹም ፣ ከአብራኩ የወጡ ገዥዎቹም ፣ ጥሬ ቆርጥሞ ያስተማራቸው ልጆቹም በጠላትነት ወይ በብትር አቀባይነት ተነባብረው የማርያም ጠላት አደረጉት።

የአማራው ህዝብ በፍትህ ፣ በእኩልነት ፣ በአብዮት ፣ በብሄር ብሄረሰቦች ስም ባይተዋር ሆነ ፣ ህልውናው ተካደ። ራሱን እንዳያውቅ ፣ ማንነቱን እንዲጠላና አንገቱን እንዲደፋ ተገደደ። ጉልቻ ቢለዋወጥም ለዚህ ህዝብ የሚበጀው አልተገኘም። በገዛ ሀገሩ የዜግነት መብቱን ተነጥቆ የመከራ ህይወት እንዲገፋ ተፈረደበት። አማራን መዝረፍ ፣ ማፈናቀልና መግደል የታማኝነት አብነት ፣ ለታላቅ ሹመት ለብዙ ሽልማት የሚያሳጭ ሆነ። ብሄራዊ ድርሻውን ከመነፈግ በላይ ፣ የራስህ ነው በተባለው ግዛት እንኳን የጌታ ፊት አይቶ አዳሪ ሆነ። ሲከፋው ውጭ ሀገር ቢሰደድ ፣ አማራነቱ እየተከተለ ጥገኝነት ይነፍገው ደረሰ። አማራው የአልፎ ሂያጅ መዛበቻ ፣ የጎሳ ፈላስፎች መራቀቂያ የመሆን እጣ ወደቀበት። የአማራ ገዥ መደብ ፣ የአማራ ትምክህት ፣ የአማራ ለሃጭ ፣ የአማራ ሆድ ፣ የአማራ ሳይኮሎጂ ፣ የአማራ ልሂቃን !

ጎበዝ ልክ አላለፈም እንዴ? ምንድነው የዚህ ህዝብ ሃጢአቱ? የትኛውንም ደበሎ ለብሶ ቢመጣ ፣ ትናንትም ዛሬም የአማራው ዋነኛው ሃጢያቱ ኢትዮጵያዊነቱ ነው። የቀን ፊት ሳያይ በኢትዮጵያዊነቱ መፅናቱ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ማተቡ ማድረጉ ነው። ከጠላት አብረው ቢወጉት በይቅርታ እጁን ዘርግቶ ፣ ትንሹም ትልቁም ቢገፋው አንገቱን ደፍቶ ፣ ገመናውን በሀገር ፍቅር ከትቶ መኖሩ ነው። አማራው በስመ ኢትዮጵያ የሚታረደው እስከ መቼ ነው? ዳኛ ዘርዓይ ‹‹ህገ መንግሥታዊ መብታቸውን›› ተጠቅመው ያስገነዘቡን ፣ የአማራው ማንነትና ህልውና ፈተና የደረሰበትን አደገኛ ደረጃ ይመስለኛል። በአጭሩ አማራው ለሁለተኛ ጊዜ ለራሱም ለሀገሩም ህልውና የሚቆምበት ግዴታ ውስጥ ገብቷል።

አማራነትና ኢትዮጵያዊነት

‹‹አማራ የሚባል ብሄረሰብ አለ ወይስ የለም?››። በግርድፉ የጅል ጥያቄ ማለት ይሄ ነው። በዓይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ህልውና ያለው ህዝብ ጥያቄ የሚነሳበት እንዴት ተደርጎ ነው? የዚህ ከገሃዱ ዓለም የተጣላ ጠርጣራነት ዋና መንስኤ ፣ በቅንነትም ይሁን በመሰሪነት የአማራው ማንነት ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር መምታታቱ ነው። የውዥንብሩ ሁለት ታሪካዊ መሰረቶች ደግሞ ፣ አማራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዒላማ በመሆን ያለፈባቸው የጣልያን ወረራ (1928 – 1933) እና የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ (1960ዎቹ) ናቸው። በአማራው ረገድ በቅርፅ እንጂ በይዘት የማይለያዩ ፣ እስካሁንም ጦሳቸው ከአማራው ራስ ያልወረደ እናትና ልጅ አስተሳሰቦች ናቸው።

ቅድም እንዳልኩት የአማራው ጉዳይ ማንም ተነስቶ እንደ ዝንባሌውና ጥቅሙ የሚመፃደቅበት ክፍት ርዕሰ ነው። ነገር ግን ባለፉት መቶ ዓመታት እንደ ህዝብ የአማራውን ውስጣዊ ማንነት ከምር ለመመርመር የሞከረ አንድ እንኳን ኢትዮጵያዊ መቁጠር አንችልም (ዘላለም ቁምላቸው ሳይዘነጋ)። ስለዚህም በአማራው ማንነት ላይ የሚሰነዘሩ እሳቤዎች ፣ ብሄረሰቡን ከጥራዝ ነጠቅ ንድፈሃሳቦች አንፃር ጅምላ ወደ መፈረጅ ያዘነበሉ ናቸው። ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው የልሂቃን ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ዝንባሌዎች ነፀብራቆች ናቸው። ይሁን እንጂ በደምሳሳው ‹‹አማራ አለ ወይስ የለም›› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡትን መልሶች ከሁለት አቅጣጫ ልንመለከታቸው እንችላለን። አንደኛው ከአማራ ህዝብ ማህበራዊ ህልውና አኳያ ፣ ሌላው ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ህልውና አኳያ።

ሀ. ከአማራ ህዝብ አኳያ

ከላይ እንደጠቆምኩት በአማራ ህልውና ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ዘለግ ያለ ታሪካዊ እድሜ ቢኖራቸውም ፣ እንደ አብይ ፖለቲካዊና ንድፈ ሃሳባዊ አጀንዳ የወጡት ከ1960ዎቹ የተማሪው ንቅናቄ ጀምሮ ነው። ነገር ግን በዘመነ ኢህአዴግ መባቻ አማራን ‹‹አለ ወይስ የለም›› ብለው በቴሌቪዥን መስኮት በመሟገት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቁት ሁለት ግለሰቦች ናቸው። ስለዚህም በአጠቃላይ በዚህ ርዕስ ስር የተንፀባረቁ ተቃራኒ አመለካከቶችን ፣ በአስተዋዋቂዎቹ ስም ‹‹የመስፍን መላምት›› እና ‹‹የመለስ መላምት›› ብለን ልንጠራቸው እንችላለን።

የመስፍን መላምት ፤ ‹‹አማራ የለም !››

‹‹አማራ የለም!›› የለዘብተኛ ፖለቲካ ፍልስፍና ቃና ያለውና ብዙውን ጊዜ ራሳቸውንም ብሄረሰቡንም ከ‹‹አማራ›› ይልቅ ‹‹አማርኛ ተናጋሪ›› ብለው ከሚጠሩ ወገን የሚሰነዘር ነው። እንደምናስታውሰው ፕሮፌሰር መስፍንን ትዝብት ላይ የጣላቸው ወለምታ ነበር። ምናልባት በመጥፎ ወቅት የተሰነዘረ ቀና አስተያየት ይሆናል። ነገር ግን አንዳንዶች ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› ብለውታል። መስፍን ከዚያ ታሪካዊ ክርክር በኋላ ሃሳባቸውን ያሻሽሉት ወይስ በዚያው ይፅኑ አላውቅም። አንዳንዴ ግን የትችት አለንጋቸውን ወይ የአማራ ህዝብ ላይ ወይ የአማራ ልሂቅ ላይ መሰንዘር ስለሚቀናቸው ፣ መቼም የሌለ ህዝብ አይተቹም የሚል እምነት አለኝ።

እንደዛ ከሆነ ደግሞ መስፍን አማራ እንደ ህዝብ የለም ማለታቸው አይሆንም። ብሄር የሚያሰኝ ወጥ ታሪካዊ ፣ ማህበራዊና ሥነልቡናዊ ማንነትና ስብእና የለውም እንጂ። እዚህ ላይ ፕሮፌሰሩ ባይናገሩትም ፣ የብሄር ስብእና መስፈርቶችን የምንተነትን ከሆነ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለብሄርነት የሚበቁ ህዝቦች አናገኝም። የጋራ ቋንቋ ፣ ታሪክ ፣ ባህል ፣ እምነት ፣ አሰፋፈር ፣ ኤኮኖሚ (ለስታሊኒስቶቹ) ፣ ሥነልቡና ፣ ወዘተ በነጠላም ሆነ በጥምረት ያላቸውን ሚና ካሰብን በኋላ ፣ የብሄርነት መቋጠሪያ የሚሆነውን ጉዳይ መወሰን ይቸግረናል።

ምናልባት የጋራ ሥነልቡና በሌሎቹ ላይ ተመርኩዞ የሚፈጠርና የሚዳብር በመሆኑ ከሁሉ የተሻለው የብሄርነት መስፈርት ቢሆንም ፣ በረቂቅና የማይጨበጥ ተፈጥሮው ምክንያት አገልግሎቱ ይጓደላል። በተጨማሪ ስሜቱ ውስጣዊ ይሁን እንጂ ፣ የሚጠብቅና የሚላላው በውጫዊ መስተጋብሮች ነው። በ‹‹ነኝ›› እና ‹‹ነህ›› ወይም በ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነርሱ›› መካከል ያለው አንድምታ ፣ በዘፈቀደ ምርጫ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ዘር ፣ ደም ፣ ቋንቋና ማንነት የይስሙላ ሥነ-ህይወታዊና ዘላለማዊ ቃና ቢኖራቸውም ቅሉ ታሪካዊ ፣ ተለዋዋጭና (ማህበረ)-ሰው ሰራሽ ናቸው።

የመስፍን ለዘብተኛ የብሄርተኝነት አመለካከት ፣ ከማህበረሰቦች ተፈጥሮአዊ የለውጥ ሂደት ጋር የሚስማማ ነው። ምክንያቱም ብሄርተኝነት ዝንጉርጉርነትና አሃድነትን አደላድሎ ስለሚይዝ ፣ በማህበረሰቦች መካከል ያለው ድንበር ደብዛዛ ፣ የተወሳሰበና ዋዣቂ ነው። የጋራ ማንነት ያለው አንድ ህዝብ በሂደት ተከፋፍሎ የተለያዩ ብሄረሰቦችን ሊፈጥር ፣ ከሌሎች ጋር ተቃይጦ መልኩን ሊለውጥ ፣ ወይም ከናካቴው ሊዋጥና ደብዛው ሊጠፋ ጭምር ይችላል። በሌላ በኩል የየራሳቸው ማንነት ያላቸው ህዝቦችም ፣ በሂደት ልዕለ-ነገዳዊ ብሄራዊ ማንነት ሊያዳብሩ ይችላሉ። በዚህ አካሄድ ደግሞ የመስፍን ‹‹ክህደት›› ለኦሮሞውም ፣ ለትግሬውም ፣ ለጋሞውም ፣ ለጉራጌውም ለሁሉም ነገዶችና ብሄረሰቦች ‹‹ይጋባል››። በከፊል ለዚህ ይመስለኛል መለስ የተቃወማቸው።

የመለስ መላምት ፤ ‹‹አማራ ከሌለ የለንም !››

‹‹አማራ ከሌለ እኛም የለንም!›› ፣ የአክራሪ (ዘውጌ) ብሄርተኝነት ቃና ያለው አመለካከት ነው። አማራ አለ ፤ ባይኖርም የግድ መፈጠር አለበት። እንጀራቸውን በአማራ ባላንጣነት ላይ የመሰረቱ ፣ የየብሄረሰቡ ጠበቆች የሚያራምዱት ነው። አማራ ከሌለ የነሱም ህልምና ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ያምናሉ። አማራ ከሌለ በብሄረሰብ ጭቆናና ሽኩቻ ላይ የተዋቀረው ርዕዮተ ዓለማቸው ይፈርሳል። የታሪክን እድፍ የሚሸከም ይጠፋል። ከፊሎቹ እንደ ባህሪ አባቶቻቸው ጣልያኖች ፣ አማራውን አከርካሪውን ከሰበርነው ኢትዮጵያን ሰጥለጥ አድርገን እንገዛለን የሚል ቀመር አላቸው። ለዚህም የደመኝነት ማኒፌስቶዎች ቀርፀው ፣ በጦርም በርዕዮትም ሜዳ ተፋልመው ለድል የበቁበት ጉዳይ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ዘውጌ ብሄርተኝነት ፣ ፖለቲካዊ ይዘቱ የሚያመዝን አመለካከትና ንቅናቄ ነው። በመሆኑም የብሄረሰቦችን ባህሪ ደመነፍሳዊና ተፈጥሯዊ በማስመሰል ፣ በአንድ ወይም በጥቂት ዘርፎቹ (በተለይ በቋንቋ) ይገድበዋል። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሌለ አንድነት ይፈጥራል። በአንጻሩ ከሌሎች ጋር ልዩነትን አለቅጥ ያጋንናል። ይህ የመጨፍለቅ ድርጊቱ በዛሬና በነገ አይወሰንም። ወደኋላ ሄዶ ታሪክንም ከመከለስ ይደርሳል። ስለዚህ ብሄረሰብን መቼም እስከመቼም ያለና የነበረ ፣ የማይለወጥና የተዘጋ ማህበረሰብ ያደርገዋል።

ለ. ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አኳያ

በዚህ ምድብ ‹‹አማራ አለ ወይስ የለም›› የሚለው በከፊል ታሪክ ጠቀስ ጥያቄ ነው። መልሱም የሚሰነዘረው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነትና ህልውና አኳያ ነው። አማራና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ አሃዶች ናቸው። ይህ አመለካከት በጣም ሰፊና በእምነትም በአላማም የየቅል የሆኑ ቡድኖች በየዓይነቱ የተሰለፉበት ነው። ከላይ የጠቀስናቸውም ሁለት መላምቶችም ይካተቱበታል። ነገር ግን ስለአማራ ህልውና የሚሰነዘሩትን አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ምላሾች በሁለት አበይት መላምቶች ስር ልናጠቃልላቸው እንችላለን።

የዋለልኝ መላምት ፤ ‹‹የአማራ ኢትዮጵያ !››

‹‹የአማራ ኢትዮጵያ!›› ፣ ኢትዮጵያን ለአማራ የሰጠ አመለካከት ነው። አማራ አለ። ኢትዮጵያ ግን የራሷ ተጨባጭ ህልውና የላትም። አማራው ሌሎችን ብሄረሰቦች ረግጦ ለመግዛት የፈጠራት ማታለያ ናት። የዚህ አስተሳሰብ ጠንሳሾች የጣልያን ቅኝ ገዥዎች ቢሆኑም ፣ ገራገር ኮሚኒስት አብዮተኞችም ፣ ኢትዮጵያን በክፉ መንፈስ ለማፍረስ የተነሱ አክራሪ ብሄርተኞችም ይጋሩታል። ግራዚያኒም ፣ ዋለልኝም ፣ መለስም በተለያየ መንገድ አራምደውታል። ፅንፈኞቹ አማራውን በመምታት ኢትዮጵያን ለመውረስ ወይም ለማፍረስ ሲተጉ ፣ ለዘብተኞቹ ደግሞ አማራን በመምታት ‹‹የሁላችንን ኢትዮጵያ እንፍጠር›› የሚል አቋም ያራምዳሉ።

አማራ ያልሆኑ ልሂቃን የአማራ ተቺዎችና ባለጋራዎችን በከፊል የሚያስተሳስራቸው ክር የበታችነት ስሜት ነው። ከአማራው በነፃ ሜዳ ተፎካክረው የሚያሸንፉ ስለማይመስላቸው ፣ በታሪክ ተጠቂነት ከለላ ልዩ ጥቅም ለማግኘት ይመኛሉ። አማራውን ያለአንዳች ልዩነት በአጥቂነት ፈርጀው ከእኩልነትና ከፍትህ ማዕድ ያገልሉታል። ስውርም ሆነ ግልፅ ጥቃት ይከፍቱበታል ፣ አለበለዚያም ጥቃትና መገለሉን በምንቸገረኝ ያልፉታል።

በዚህ ቡድን ውስጥ አለስፍራቸው የተቀመጡ የሚመስሉት በአማራው ላይ የሚነሱ አማሮች ናቸው። ይህን ተፈጥሮአዊ የማይመስል ነገር አንዳንዶች ‹‹ከጥፋተኝነት ህሊና የሚመነጭ›› (መሣይ 2008) አድርገው ይቆጥሩታል። እንደኔ ግን እንደ ዋለልኝ መኮንንና የብአዴን ተከታዮቹ ያሉት መጢቃ አብዮተኞች ፣ ለአማራው የሚያሳዩት ንቀትና ጥላቻ ከፍትህና እኩልነት ህልም የመነጨ ሳይሆን ፣ ጣልያን የዘራው አማራውን የማጥላላት ሴራ በትውልዳቸው ፍሬ አፍርቶ ካሳደረባቸው በራስ የመተማመን እጦት ለመዳን የሚደረግ ጥረት ይመስለኛል። እነዚህም ቢሆኑ እንዳባቶቻቸው ከሁለት ያጣ ወፍ ናቸው።

ኢትዮጵያን ያቀናት አማራ ብቻውን ነው። በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነው አማራ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ባህል የአማራ ነው። ዛሬ ፍሬው የጎመራው ይህ መርዘኛ አስተሳሰብ ፣ በአንድ በኩል የሌሎችን ኢትዮጵያውያን ውለታና ብሄራዊ ድርሻ ሸምጥጦ ይክዳል። አማራውን ብቸኛ የኢትዮጵያ ባለቤትና ባለርስት ፣ ሌላውን ደግሞ ደባልና ጭሰኛ ያደርጋል። ኢትዮጵያን የፈጠራትም ፣ ያኖራትም ፣ የተጠቀመባትም አማራው በመሆኑ ፣ ማንኛውንም ጦስ መቀበል ግዴታው ነው ይላል በተዘዋዋሪ። ከላይ እንደጠቀስኩት ይህ ብልሃት የኢትዮጵያ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶች አማራውን ነጥሎ ለማጥቃት የሚያራምዱት ነው።

የብሄረ ኢትዮጵያ መላምት ፤ ‹‹የኢትዮጵያ አማራ !››

‹‹የኢትዮጵያ አማራ!›› ፣ አማራን ለኢትዮጵያዊነት የሰጠ አስተሳሰብ ነው። አማራ የለም! ምክንያቱም አማራውን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማሰብ አይቻልም። ይህ ረዥም ታሪካዊ መሰረት ያለው የብሄረ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ፣ በብቸኝነት ለአማራው ነገድ ልሂቃን የተወሰነ አይደለም። ነገር ግን ትኩረታችን አማራው ስለሆነ ፣ የመላምቱ አራማጆች አማራው በሀገር ግንባታ የጎላ ታሪካዊ ሚና በመጫወቱ ከኢትዮጵያዊነት የተለየ የብሄር መታወቂያ የለውም የሚሉ ልሂቃን ናቸው። አንዳንዶች አማራ የሚለው ስም ራሱ የብሄረሰብ መጠሪያነት ታሪክ የለውም ፤ አማራም በአውራጃዊነቱና በኢትዮጵያዊነቱ መሃል ማንነት የለውም ብለውም ይከራከራሉ። እንደ ዘርዓይ ያሉት በከፍተኛ በቁጭት።

አምናም አንድ በውጭ ሀገር የሚኖር ጠበቃ ፣ ‹‹በአማራነት መደራጀት ፀረ-ኢትዮጵያዊ ሃሳብ ነው›› የሚል ከታሪክም ፣ ከአመክንዮም ፣ ከፍትህም የተጣላ ፅሁፍ አስነብቦ አስታውሳለሁ። የዚህ አስተሳሰብ የጀርባ አጥንት ፣ አማራው በነገዱ ከተሰባሰበና ከተደራጀ ፣ ለሌሎች ክፉ ተምሳሌት በመሆን ሀገራችንን ያፈርሳታል ፣ ኢትዮጵያ ትጠፋለች የሚል ስጋት ሊሆን ይችላል። ለአንዳንዶች ደግሞ ነገዳቸውን ማጉላት ኢትዮጵያዊነታቸውን ከመካድ አልፎ ፣ ከብሄራዊ ልዕልና ወደ ጎሠኝነት አዘቅት እንደመውደቅ ይቆጠራል። በታሪክ መቼት ውስጥ ካላስገባነው በስተቀር ፣ እንዲህ ዓይነቱ ቀኖናዊ አስተሳሰብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

አማርነት የግል ኢትዮጵያዊነት የጋራ !

‹‹አማርነት የግል ኢትዮጵያዊነት የጋራ!›› ፣ ምናልባት ሟቹን ፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ በርካታ የአማራ ልሂቃን ያለውድ በግዴታ የገቡበት እሳቤ ይመስለኛል። አማራው ከኢትዮጵያ ውጭ ነገዳዊ ማንነቱን ለማሰብ አለመፍቀድ ዝንባሌው ፣ በታሪክ ተሞክሮዎች የሚወሰን እንጂ በዘረመሉ የተቆራኘው አይደለም። ክፉም ይሁን ደግ ታሪክ የብሄርነት መፈጠሪያው ማህፀን ነው። አማራው ህዝብ ባለፉት መቶ ዓመታት በጋራ ከደረሰበት መገፋትና የህልውና ፈተና ፣ ብሄረሰባዊ ማንነቱን ለማስተዋል እንደተገደደ መካድ አይቻልም።

ይሁን እንጂ አማራው እስካሁን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ በነገዳዊ ማንነቱ የመታገያ ጠንካራ ስልት አላዳበረም። የአማራ ልሂቃን ስስ ብልት ስለአማርነታቸው በቅጡ የታሰበበትና የተደራጀ ግንዛቤና ልምድ እጦት ነው። ይህም ብሄረሰቡን ለዘርፈ ብዙ ጥቃት አጋልጦታል። የአማራው ህዝብ ራሱን እንዴት ማሰንበት የሚችልበትን የተሻለ መላ እስካላቀረብንለት ድረስ ፣ ይሙት በቃ በፈረድንበት ታሪክ ይጠይቀናል። አሁንም አማራው በማንነቱ የሚደርስበትን ጥቃት በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ሊመክተው አልቻለም። ስለዚህ በነገዳዊ ማንነቱ ድጋፍ መፍጠር ፣ ራሱንም ኢትዮጵያንም ለማዳን ያለው የተሻለው አማራጭ ነው። ከታሪክና ተሞክሮ የምንማር ከሆነ ፣ አማራው ሲደራጅ ሀገር ትደረጃለች እንጂ አትፈርስም።

አማራው ዛሬን ህልውናውን ከማትረፍ በተጨማሪ ፣ እግረ መንገዱንም ከታሪክ እዳ ከፋይነት የሚያላቅቀውን መንገድ መመልከት አለበት። ከእንግዲህ በኢትዮጵያዊነት ባላ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ፣ እርሱን በማታውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ እየማቀቀ መኖር ይበቃዋል። ልጆቹና የልጅ ልጆቹም በአማራነታቸውም በኢትዮጵያዊነታቸውም ኮርተው የሚኖሩባት እንጂ ፣ ዝንተዓለም ተሸማቀው መከራ የሚገፉባት ሀገር ማውረስ ታሪክ ከጣለበት ሃላፊነት መሸሽ ይሆናል። ስለዚህ በአማራነት መደራጀት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው።

ዳኛ ዘርዓይ ባደጉበት የአክራሪ ዘውጌ አስተምህሮ ፣ የማንነት አልፋና ኦሜጋ ነገድ ነው። ከትግሬነት ከፍም ዝቅም ማለት ሃጢአት ነው። ሌላውንም ዓለማቸውን የሚተረጉሙት በዚህችው አንድ ዓይና መነፅራቸው ነው። ነገር ግን በተግባር የሰው ልጅ ድርብርብ ማህበራዊ ማንነቶች ባለቤት ነው። ቢፈልግ ኢትዮጵያዊነቱን ፣ ወይም ዘውጉን አለያም እምነቱን ወይም አውራጃውን እንደየአገባቡ ጎላና ፈዘዝ በማድረግ ለእለት ኑሮው ይጠቀማል።

አማራውም ከዚህ ማህበራዊ ባህሪ የተለየ ተፈጥሮ የለውም። ከብሄራዊ መንግሥቱ ምስረታ ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት ፣ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀድም እንጂ መቼም ቢሆን አማራነቱን አልካደም። አይቻልማ!! የነዚህን መንታ ማንነቶች አንድነትና ልዩነት ግን በቅጡ ማጤን ተገቢ ነው። አማራነትና ኢትዮጵያዊነት ከጥንት በተዋረድ አብረው ተከባብረው ኖረዋል። አማራው ከኢትዮጵያ ቤተሰብ ነገዶች አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም። ልክ እንደቤተሰብ አባል ከማህበሩ ጋር የሚጋራውም ፣ ደግሞ ከሌሎች አባላቱ የሚለየውም ስብዕና አለው።

አማራው በማንነቱ ለመደራጀትም እንግዳ አይደለም። ጥንትም ዛሬም አብዛኛው አማራ በየአውራጃና በየጎጡ ተደራጅቶ ፣ የተወሰነው ደግሞ ከቀሪ ወንድሞቹ በአሰፋፈርም ፣ በባህልም ፣ በሥነልቡናም ተቃይጦ ፣ በኢትዮጵያዊነቱም በአማራነቱም ኮርቶ የኖረ ህዝብ ነው። ፋሽስት ጣልያን ህልውናውን በፈተነችው ሰዓትም ፣ በየጎጡ ተደራጅቶ በጎበዝ አለቃው ተመርቶ ራሱንም ሀገሩንም ታድጓል።

የጎሳ ፖለቲካን መፀየፍ ይቻላል። ማውገዝም ያስፈልጋል። ነገር ግን አማራው ቢደራጅ ወያኔ ሰመረለት እያሉ ፣ ወያኔ የፈጠረው ማስመሰልና ስብእናውንና መብቱን መካድ ፣ ወይ ተንኮል አለያም ድንቁርና ነው። ቁምነገሩ ‹‹አማራ ለምን መደራጀት አስፈለገው?›› እንጂ ‹‹እንዴት ሲባል ይደራጃል?›› አይደለም። ለፖለቲካ ስልጣን ባይሆን እንኳን ባህልን ፣ ታሪክን ፣ ቅርስን ለመጠበቅና ለማጎልበትም መደራጀት የግድ መሆኑንም አንዘንጋ። ደጋግሜ እንደገለፅኩት ከሁሉም በላይ የአማራን መደራጀት አንገብጋቢ ያደረገው የህልውና ጥያቄ ነው። ለአንድ ምዕት ግልጽና ስውር ጥቃት ሲወርድበት ፣ ሰባራ ሰንካላ ምክንያቶች በመደርደር ፣ ለአማራው ከምር ተቆርቁሮ የተነሳ አላየንም። ሲሻን ህልውናውን ከናካቴው እየካድን ፣ ወይም ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር እያምታታን ፣ ሳይሆን ደግሞ በታሪክ ባለእዳነት እየተጠቃቀስን ፍዳውን እንዲቀበል ትተነዋል።

በተለይም ለ26 ዓመታት ክፉኛ የተገዳደረውን ውርደት ፣ ስደትና ሞት አማራው ዝንተዓለም በፀጋ መቀበል አለበት የምንል ከሆነ ፍርደ ገምድልነት ነው። ይህን ታሪክ ይቅር የማይለውን ዳተኝነት በመፍቀሬ ኢትዮጵያዊነት ልናመካኝ አንችልም። የአማራ ልጆች ለመላው ኢትዮጵያ ሲታገሉ እንደኖሩ ፣ ዛሬ የዚህን ህዝብ ሰቆቃ የሚታደጉ አማሮች ቢነሱ ሊገርመንና እንደውርደት ልንቆጥረው አይገባም። በተራቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ለአማራው በተናጠልም በጋራም ቢቆሙለት ለምን እንደማንለው ሁሉ።

ስለዚህ አማራው ቢፈልግ በዘውጉ ፣ ቢሻው ደግሞ በብሄራዊ አመለካከቱ ፣ አለያም በሁለቱም እየተደራጀ እንዳመቸው ራሱን ሊከላከልና ሊታገል ይችላል። ማንም የማይሰጠው ፣ ማንም የማይነፍገው ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው። ዲያስፖራው ስለተንጫጫ ወይም ዘርዓይ ደሙ ስለተንተከተከ የማይቀር ፣ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለሌሎች ወንድሞቹ የፈቅድነውን ለአማራው በተለይ የምንነፍገው ከሆነ ፍትህ እናጓድልበታለን።

ብሄራዊ ኢትዮጵያዊነትና ነገዳዊ አማራነት የየፊናቸው ስፍራና ግልጋሎት አላቸው። በአግባቡ እስከተያዙ ድረስ ፣ ያንዱ ህልውና ሌላውን አያሰጋውም። ‹‹የደም›› አማራነት ፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ጣውንት አይደሉም። በፍጹም አይቀናቀኑም አይጣሉም። ልክ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት ፣ ጋሞነትና ኢትዮጵያዊነት ፣ ጉራጌነትና ኢትዮጵያዊነት ፣ ወዘተርፈ እንደማይቃረኑት ማለት ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ አማራነት የግላችን ፣ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የጋራ ሃብታችን መሆኑን እንገንዘብ። ነገር ግን ሁልጊዜም ኢትዮጵያዊነታችን የነገድ ማንነታችንን የሚመራበት እድል እንስጠው።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!