ኢሳት በመዐሕድ ላይ ለምን የመንደር – አሉባልታ ዘመቻ ከፈተ?

Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዷለም)

የኢሳት ጌቶች በተዘዋዋሪ “መዐሕድን ይዛችሁ ነገር ግን አማራነታችሁን ጥላችሁ ከጎጥ ማህበራት፣ ግለሰቦችና የመሳሰሉት ጋር ተጨፍልቃችሁ ወደ አገራዊ ንቅናቄ ግቡ” አሉ። እኛ “አላማችን አገራዊ ንቅናቄ ሳይሆን የአማራ ነጻነት ነው” አልናቸው። የጎጥ ማህበራትና ሌሎች ግን ወደአንድ አማራነት ድርጅት የሚጠቃለሉ ከሆነ መብታቸው ነው፤ ነገር ግን የሚከተለውን ማድረግ እዳለባቸው በስነስርአት ጽፈን ላክንላቸው። ሆኖም ሊቀበሉት አልወደዱም። ድምጻቸውን አጥፍተው ከርመው የመንደር አሉባልታ በመቀራረም የአማራን እንቅስቃሴ ለመጉዳት እና ድርጅታችንን መጥፎ ጥላሸት ለመቀባት ሞከሩ። በዚህ አጋጣሚ አመራሮቻችንን “ኑና ስለድርጅታችሁ ለህዝብ አሳውቁ ብሎ በራሱ ጥያቄ ነው” ለቃለመጠይቅ ያቀረባቸው። ያው የእነሱ ጥረት ወጥመድ ቢሆንም አልተሳካላቸውም።

በነገራችን ላይ ኢሳት እንዲህ ተራና ርካሽ ስራ በመስራቱ ሊያፍር ይገባዋል።

መልካም ንባብ።
—————-

መስከረም 11 2010 ዓ.ም.
ለአማራ ፖለቲካ ድርጅቶች አቀራራቢና አመቻች ኮሚቴ

መግቢያ
አቀራራቢ ኮሚቴዉ የጀመረው የማቀራረብ ሥራና የሄደበት ርቀት የሚያስመሰግነዉ ነው። ድርጅታችን መዐሕድም መስከረም 7/2017 ዓ.ም በተካሄደዉ የመጀመሪያዉ የማቀራረብ ስብሰባ ተወካዮቹን ልኮ ተሳትፏል። ስለሆነም በእናንተ በኩል የተላከልንን ሰነድ ተመልክተን በስብሰባው ድርጅታችንን የወከሉ አራት አመራሮች የቀረበልንን ሪፖርት አድምጠናል። በዚህም መሰረት የሚከተሉትን ዝርዝር ሁኔታዎች ተወያይተን የግምገማችን ዉጤትና አማራጭ የመቀራረቢያ ሰነድ አዘጋጅተን ልከናል።

በአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች አቀራራቢና አመቻች ኮሚቴ ሰነድ ላይ ያለን አቋም እንደሚከተለዉ ይሆናል፦

1ኛ) ሰነዱ በጅምላ የፖለቲካ መነጽር አማራዉ የተጋረጠበትን የህልዉና አደጋ ተገቢ በሆነ መልኩ ያላገናዘበ እና ዘላቂ ጥቅሞቹን ያላካተተ ሆኖ ስላገኝነዉ በዚህም ከድርጅታችን ዋና አላማ ጋር እጅጉን የተፋታ ሆኖ በመገኝቱ ድርጅታችን ያልተቀበለዉ መሆኑን ስንገልጽ ከአክብሮት ጋር ነዉ ።

2ኛ) በስብሰባዉ ላይ በተወካዮቻችን የተንጸባረቁ ሃሳቦችና በነበሩት ተሳታፊዎች ስምምነት የተደረሰባቸዉ ጉዳዮች በቃለ- ጉባኤዉ እንዳይካተቱ መደረጋቸው ሂደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረን አድርጓል።

3ኛ. በመጨረሻም በድርጅታችን ተወካዮች በቀረበልን ሪፖርት እንደተረዳነዉ በዋናነት በሰነዱ ይዘት ላይ ይደረጋል ተብሎ የነበረዉ ዉይይት በቂ ጊዜ ሳይሰጠዉ ተድበስብሶ እንዲያልፍ ተደርጓል። ስለሆነም የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከዚህ በታች የቀረበውን ተለዋጭ ምክረ-ሃሳብ አስቀምጧል።

———————–
ከአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለሚደረጉ የትብብር/ ጥምረት/ ህብረት/ ግንባር/ ዉህደት
ከመዐሕድ የተሰጠ ተለዋጭ ምክረ ሃሳብ
——
ይህ ሰነድ የተዘጋጀው መዐሕድ በሚያደርገው የትግል ጉዞ በአማራ ሕዝብ ልጆች ከተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚኖረውን የወደፊት የመቀራረቢያና የመደራደሪያ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ነው። የዚህ ሰነድ ዋነኛ መርህ መዐሕድ የተቋቋመበትን ራዕይና ዓላማ የሚጋሩ፤ ካላቸው ራዕይ ጋር የሚመሳሰልና ያንንም ለማሳካት በሙሉ ልብ ቆርጠው ከተነሱ አምሳያ ድርጅቶች ጋር ዉይይት ለመጀመር የሚያስችሉትን መርሆዎችና ምልከታዎች በጥቅሉ ለማመላከት ሲሆን ድርድሩ የሚከናወነው በተደራዳሪ ወይም ተቀራራቢ ድርጅቶች ቀጥተኛ ተወካዮቻቸው ይሆናል። መዐሕድ ከትብብር እስከ ዉህደት ባሉት ደረጃዎች ለሚያደርጋቸዉ ድርድሮች ሁሉ ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የተደራዳሪ ድርጅቶችን የፖለቲካ መርሃ-ግብርና የመተዳደሪያ ደንብ ሰነዶቻቸውን ብቻ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ረጅም የታሪክ ዘመን በስልጣኔና በዝመና እንዲሁም በሥርዓተ መንግሥታት ምስረታና እድገት ሂደት ውስጥ ሁሉም የኢትዮጵያዊ ብሄር ብሄረሰቦች አስተዋጽኦ ያለበት ቢሆንም የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ አበርክቶት ግን እጅግ የጎላና ደማቅ ለመሆኑ ማስረጃ የሚያሻው አይደለም። ስለሆነም ራሱ የመሰረታትን አገር ሲንከባከብ በዉጩ ጠላት የመጠቃት ስሜት ሲያናዉዘዉ በውስጡ ደግሞ በበታችነት ስሜት ሌሎች የአማራን ሕዝብ በስውርና ፊት ለፊት ሲያጠቁት ኖረዋል። ለምሳሌ ያክል በውጭ ጠላትነት ፋሽስት ጣልያንን በአገር ዉስጥ ደግሞ የትግሬ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅትን መጥቀስ ይቻላል። ይህም ጥቃት ለሰማንያ አመታት ገደማ የዘለቀ ስለሆነ የአማራ ህዝብ አንድ ማህበረሰብ ሊጠፋ ሲል የመጨረሻ ህልውናዊ ትግል የሚያደርገውን የሞት ሽረት ትግል ባልተደራጀ መልኩም ቢሆን ጀምሮታል። የተጀመረውን ያልተደራጀ ትግል ደግሞ ጫፍ ለማድረስ ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች ለየብቻ ከሚያደርጉት ትግል ይልቅ በጋራ ቢታገሉ ውጤት እንደሚያመጡ መዐሕድ ያምናል።

በመሆኑም ከመዐሕድ ጋር ለሚደረጉ የትብብር፣ ጥምረት፣ ህብረት፣ ግንባር ወይም ውህደት የውይይት መሰረታዊ ጽንሰ-ሃሳብ ማዕቀፍ እንደሚከተለው ተዘርዝሯል።

1ኛ) የአማራ ሕዝብ እስካሁን ማንነቱን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደደረሰበት ሙሉ በሙሉ የሚቀበሉና፤ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ በትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር መሪነት እየደረሰበት ያለው ጥቃት ዘርን መሰረት ያደረገ መሆኑን አምነው የተቀበሉ መሆን አለባቸው።

2ኛ) ባለፉት 26 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሶ የመኖር፤ ሀብትና ንብረት የማፍራት መብቱ መነፈጉን፤ የማንነት ክብሩና ልእልናው መረገጡን፤ እንዲሁም ከሌሎች ብሄር ብሔረሰቦች ጋር በእኩልነት የሚኖርበት መብቱ ተደፍጥጦ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቹ መነጠቁንና ታሪካዊ ማንነቱ ሆን ተብሎ መጠልሸቱን የሚያምኑና ይህን ለመቀልበስ ሙሉ ለሙሉ የሚታገሉ ድርጅቶች መሆን አለባቸው።

3ኛ) የአማራ ሕዝብ ለደረሰበት የሰብአዊና የስነ ልቦና ቁስል ተገቢውን ፍትህ ለማግኘትና በሰላምና በእኩልነት በአገሩ ላይ ተከብሮ ለመኖር እንዲችል በአማራነት መደራጀትና መታገል አስፈላጊ ነው ብለዉ የሚያምኑ ድርጅቶች መሆን አለባቸው።

4ኛ) ከመዐሕድ ጋር በትብብር፣ ጥምረት፣ ህብረት፣ ግንባርና ውህደት ድረስ መወያየትና መደራደር የሚችሉ ድርጅቶች በአማራነት የተደራጁ ብቻ ሲሆኑ ከዛ ዉጭ ባሉ የብሄር፣ ክፍለ ሀገራዊና የአንድነት ድርጅቶች ጋር በትብብር ብቻ የተወሰነ ይሆናል።

5ኛ) መዐሕድ ከአማራ ሕዝብ ሲቪክ ማህበራት፣ ማሕበረሰብና የሙያ ማህበራት ጋር ሁለንተናዊ የሆነ የድጋፍና ትብብር ስራዎችን በጋራ ይሰራል። መዐሕድ ከእነዚህ መሰል ማህበራት ጋር በድጋፍና ትብብር ማዕቆፎች ከመስራት ባሻገር ጥምረትም ሆነ ውህደት ለማድረግ አይችልም። መዐሕድ ጥምረት፣ ግንባር ወይም ውህደት ሊፈጥር የሚችለው ተመሳሳይ የፖለቲካ አላማ ከሚያራምዱ ድርጅቶች ጋር ብቻ ነው።

6ኛ) መዐሕድ በአማራነት ተደራጅቶ ከሚደረገው ትግል ጎን ጎን ማንነት ግንባታን ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው። ይሄውም የማንነት ግንባታ የአማራ ህዝብ ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ስነልቡናዊ ትስስር ማዳበሩ በአንድ ልብ ለመታገል ያስችለዋል ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። መዐሕድ ይሄንን የማንነት ግንባታ ከሚቀበል የአማራ ድርጅት ጋር ሊጣመር፣ ግንባር ሊፈጥር ወይም ሊዋሀድ ይችላል።

መዐሕድ ከምንም በላይ ለአማራውና ለአማራ ብሄርተኝነት ቅድሚያ የሚሰጥ እና በህዝባችን ህልውና ላይ የማይደራደር ድርጅት ነው። ድርጅታችን የሕዝባችን ደህንነት እና ብሄራዊ ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ ማንኛውንም አይነት የትግል ስልት እና የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ያስተናግዳል። የመዐሕድ ዓላማ በዐማራ ሕዝብ ህልውናና የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ያጠላውን አደጋ በመቀልበስ የወደፊቱን መፃኢ ዕድላችን ባስተማማኝ ሁኔታ ላይ ይገኝ ዘንድ አፋጣኝ ሁለንተናዊ መልስ ሊሰጥ የሚችል ድርጅት መገንባትና መታገል ነው። በዚህ ዓላማ እምነት ካላቸው የዐማራ ስብስቦች ጋር ለመነጋገርና ለመስራት ፈቃደኛ ነው።

ድል ለዐማራ ሕዝብ
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት