“ኡፍ! እባካችሁ እንተኛበት!” በወያነ ትግራይ መሪዎች ለተጻፈለት ደብዳቤ …

Print Friendly, PDF & Email

“ኡፍ! እባካችሁ እንተኛበት!” በወያነ ትግራይ መሪዎች ለተጻፈለት ደብዳቤ አንድ የትግራይ ምሁር የሰጠው መልስ

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ)  (To read the article with PDF, click here)

ከሻዕቢያ ጋር ብንጣላም ‘ኤርትራን የሚተናኮል’ ክፍል ካለ ህወሓት ዛሬም ቢሆን ከኤርትራ ጎን ቆማ የኤርትራ ጠላቶችን ትወጋለች’ ሲል የነገረን ከኢሳያስ አፈወርቂ ጎን በስተግራ በኩል እጁን በአክብሮት ወደ ኋሊት አዙሮ የቆመው ስብሓት ነጋ ነው።

ወደ ርዕሴ ከመግባቴ በፊት ፤በመጀመሪያ እስካሁን ድረስ ለሳምንታት ያክል ወያኔዎችን የሚወጥሩ በርካታ ሰነዶችን ያላንዳች “ሴንሰር” እና የቃላት “ስረዛ” እንዲታተሙ በመፍቀዱ ለዓይጋ ድረገጽ አመሰግናለሁ። አንባቢዎቼን ላስገነዝብ የምፈልገው፤ ዘሐበሻ (ሳተናው) የተባለ ጸረ ኢትዮጵያ ግምባሮች እንዲጨፍሩበት የሚፈቅድ ድረገጽ ባለፈው ወር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ ልኬለት “አንተ/እሱ” ብለህ የጻፍከው “እሳቸው/እርስዎ” በሚል ቃል ካልለወጥከው ለሕዝብ አላቀርበውም ሲል ክርክሬ ለሕብ እንዳይነበብ አግዶታል።

እንደዚህ ያሉ ሚዲያዎች በተቃወሚ ስም ቆመው ወያኔን የመናገርና የመጻፍ መብታችን አገደን ሲሉ፤ በነጻ ለመጻፍና ለመናገር የምንሻ ነጻ ዜጎች ግን በገንዘብ የሚደጉሟቸው (ለምሳሌ ሻዕቢያ/ኢሳያስን/ብርሃኑን) እና የፖለቲካ መሪዎቻቸው መንካት ያስኮንናል። አይፈቀድም። አሲምባ የተባለው ድረገጽም “ዋለልኝ መኮንን’’ እና ኢሕአፓን ተቸህ ብለው ጽሑፌ ለሕዝብ አንዳይነበብ አግደውት፤ እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ጸበኞች ነን። ኢትኦ-ሚዲያ ወዘተ…ወዘተ… ሁሉም አንድ ባህሪ አላቸው። ሆኖም ኢትዮ-ፓትርዮትስ እና ወልቃይት.ካም የተባሉ አገር ወዳድ አውነተኛ ሚዲያዎች እስካሁን ድረስ ሃሳቤን በነጻ እንድጽፍ ፈቅደውልኝ እስካሁን ድረስ ከሕዝብ ጋር እነጋገራለሁ። እነሱንም አጅግ አመሰግናለሁ። ሚዲያ ሲያፍንህ፤ ሕዝብ አይማርም። መረጃ የሌለው ሕዝብ ደግሞ፤ የመጣ ገዢ የሚሰይፈው “የመስዋእሰት በግ” ነው። በቅርቡ ዓይጋ የጀመረው “ዲመክራቲክ- ጀስተር” (አዲስ መስተንግዶ) ወያኔን “ፋሺስት’ ነው ብየ ብከራከርም ያለ ምንም ሴንሰር ሌሎች እንዲሞጉቱኝ በነፃ እንድጽፍ መፍቀዱ በጣም አመሰግናለሁ። ዘሐበሻ (ሳተናው) እና ኢትዮ-ሚዲያ የመሳሰሉ ከዚህ እንደሚማሩ ተስፋ አለኝ (ግን አይማሩም)። አፋኝ የዜና ማሰራጪያዎች በአፈና ባሕሪ ሲጓዙ ሕዝብ/አንባቢ ካልተቃወማቸው አፋኝ መሪዎችን የማንገስ ችሎታ ያላቸው መሆን ብቻ ሳይሆን ሳይመረጡ እራሳቸው ወደ መድረክ ብቅ ብለው ያልተመረጡ የሃሳብ ነፃነት አፋኝ አምባገነን ንጉሶች ወደ መሆን ይሸጋገራሉ።

ሌላው ደግሞ- ሰሞኑን ኤርትራን አስመልክቼ በጻፍኩት በርካታ ሰዎች በግል ኢመይል ጽፈውልኛል። በተለይ አንድ በዕድሜ ክልል ወጣት ነኝ ብሎ የጻፈልኝ በስድብ ክምር የታጀበ የአንድ ኤርትራዊ ደብዳቤ ደርሶኛል። ካስገረመኝ ውስጥ ስድቡ ሳይሆን “ትግሬዎች እኛን ኤርትራኖችን ወንድሞቻችን ናችሁ ስትሉን ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ነው። ከናንተው ጋር ምንም ዝምድና የለንም። ት/ቤትም ቢሆን ይህንኑ ነው የተማርኩት፡ አባቴም ቢሆን ሁሌም ስለ ትግሬዎች ሲነሳ “ከትግሬዎች ጋር ቋንቋ” እንጂ ምንም የሚያገናኝን ነገረ የለም፤ለምን ወንድማማቾች ነን እንደሚሉን አልገባኝም፤ ከነሱ ጋር የምንዛመደው ነገር የለም፡ ብሎ ስለነገረኝ ፤ እባካችሁ ትግሬዎች ወንድማማቾች ነን እያላችሁ “አታደንቁሩን” ብሎ የጻፈልኝ ሳስታውስ የነቀዙ የኤርትራ ምሁራን እና በክህደት ባሕር ለበርከታ አመታት እየዋኙ ያሉት የወያኔ መሪዎች ለኤርትራ ወጣቶች ሕሊና መበላሸት አስተዋጿቸው ምን ያህል እንደተጓዘ በዚህ ወጣት ሕሊና ማየት ችያለሁ።

አሁን ወደ ርዕሳችን እንግባ።

ጀግና ሰዎች የተናገሩት ወደ ብርሃን ይዘውት የሚመጡ ሌሎች ጀግኖች አሉ። ልሳን ሊታፈን ይችላል፡ ከተቀበረበት ቦርቡረው እንዲደመጥ የሚያደርጉ ሰዎችም ‘በተዘዋዋሪ’ የነዚያ ጀግኖች አካሎች የሚሆኑበት ጌዘ አለ። አስቀድሜ እላይ እንደገለጽኩት ስለ ኤርትራ ሰፋ ያለ ሰነድ አቅርቤ ነበር። ይህ ጽሑፍ የዚያ አካል ነውና በዚህ ልደምድም።

አንድ የትግራይ ምሁር ከወያኔ መሪዎች የተጻፈለትን የአብረኸን ታገል የጥሪ ደብዳቤ የሰጠው አስገራሚና የማይረሳ የጥቅስ መልስ እንፈትሻለን። በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ እራሳቸውን በነፃ አውጪነት በመሰየም ብዙ ዜጎች እንዲያልቁ ካደረጉት እስካሁን ድረስ ለፍርድ ያልቀረቡ የወያኔ መሪዎች (ፋሺስቶች) እና የኢሕአፓ (ኮሚኒሰት) መሪዎች ናቸው። ወያኔዎች በትግራይ ተወላጆች ላይም ይሁን በመላ አገሪቱ ያደረሱት አገራዊ ወንጀል፤ የህይወት የንብረት እና የቤተሰብ መፍረስ ወንጀል እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ ለፍርድ አልቀረቡም። ለምሳሌ በትግራይ ተወላጆች ላይ የተሓህት መሪዎች፤ካድሬዎች ፤የሕዝብ ክፍሎች፤ክርቢቶች፤ሰላዮች፤የሓለዋ ወያኔ ሓላፊዎችና መርማሪዎች “በማን ይጠይቀኛል” ተነሳስተው ያለ ሕጋዊ ፍርድ በሕዝብ ህይወት ውሳኔ በማሳለፍ ድብደባና ግድያ፤አፋና እና የንብረት ነጠቃ ወንጀል የፈጸሙ የ‘ተሓህት’ ታጋይ አባሎች “ለፍርድ እንዲቀርቡ” በወቅቱ የትግራይ አስተዳዳሪ ለነበረው ለነ ገብሩ አስራት በርከት ያሉ ወደ 500 የሚጠጉ የትግራይ ኗሪዎች ፍትህ እንዲያገኙ ጥያቄ ቢያቀርቡም “በረሃ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ካለ ለአብዮቱ ተብሎ የተደረገ ስለሆነ አንጠየቅበትም” ብሎ እንደመለሳቸው “ወያኔዎች በ7ጥይት ደብድበው ሞቷል ብለው ጫካ ላይ ጥለውኝ ሄዱ” በሚል ርዕስ በኢጦብና በኔው መጽሀፍ “የወያኔ ገበና ማህደር” ላይ ድያቆን ገብረህይወት ባደረገው ቃለ መጠይቅ ነግሮናል።

እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ፡ ጠያቂዎቹ የጠየቁት አጭርና ግልጽ ጥያቄ ነበር። “ደርግ በዜጎች ህይወት ጭፍጨፋ ፈጽሟል ብላችሁ ልዩ ፍርድ ቤት ካቋቋማችሁ፤ እናንተም እውነት ወንጀል አልፈጸምንም ብላችሁ ሌሎችን ወንጀለኞች ቀጪዎችና ፈራጆች ከሆናችሁ፤ እኛም በናንተ ላይ ያለንን ክስ ለማቅረብ ዕድል ስጡን እና የእናንትን ገበና የሚመረምር ልዩ ፍርድ ቤትም አብራችሁ ክፍቱና ንጹሃን ከሆናችሁ እሰየው፤ ካልሆነም ቅጣታችሁ እንድታገኙ ፍትህ ስጡን” ነበር ግልጽ የሆነችዋ ጥያቄአቸው። ሆኖም “ምን ያለበት ዝላይ አይወድም” እንደሚባለው ፤ ይኸው እስካሁን ራሳቸው ከሳሾች፤ራሳቸው ምስክሮች፤ ራሳቸው ዳኞች፤ ራሳቸው የታሪክ ጸሓፊዎች ሆነው በሌሎች ላይ ሲተቹ፤ ሲፈርዱና ሲቀጡ 26 አመት ሆናቸው።

ለወያኔ ድብዳቤ የተሰጠ ይህ የአንድ የትግራይ ተወላጅ ምሁር አስገራሚ መልስ ያነበብኩት “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” ከሚለው በገበሩ አስራት የተጻፈ ታሪካዊ መጽሐፍ ይዤአችሁ ከመግባቴ በፊት፤ ስለ ገብሩ አስራት መጽሐፍ ይቅርታ ተጨምሮበት መጋለጥ የነበረባቸው ይፋ ያልሆኑ የድርጅቱ ወንጀሎችና ምስጢሮች ያለማካተቱ የተቸሁበትን እንደተጠበቀ ሆኖ በመልካም እይታ በተከታታይ ትችቶች የተቸሁበት ይህ መጽሓፍ፤የዳግማይ ወያነ መሪ የነበረው መለስ ዜናዊና ድርጅቱ በሉዓላዊነታችን ያደረሰው ኪሳራ በርካታ ሰነዶች የያዙ ለጀሮአችን አዳዲስ ምስጢሮችን የያዘ የታሪክ መጽሀፍ ሲሆን፤ ትንናንት ማታ ዓይጋ ድረገጽ ስጎበኝ ካሳ ሃይለማርያም ረዳ ስለ አባቱ ብላታ ሃይለማርያም ረዳ ህይወት እና እሳቸው የመሩት “የቀዳማይ ወያነ” (እኔ የትግሬ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው የጥላቻ መነሻ ምንድነው? በሚለው አዲስ መጽሐፌ ውስጥ የተቸሁዋቸው፤ ለወደፊቱም ልጃቸው የጻፈውን አዲስ መጽሐፍ አንብቤ ለመተቸት እየጠበቅኩኝ ነኝ። ካደመጥኩት የራሱ ቃለመጠይቅም ሆነ ተናገሩት ከተባለው ንግግራቸው ካሁን በፊት ለተቸሁዋቸው ጉዳዮች የሚያያዙ እና የሚያስረግጡልኝ ንግግሮቻቸው ስለሆኑ ያንን በጊዜው የምናየው ይሆናል።) ይህ በላ 500 ገጽ የሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፈቃድጅነት የታተመው በትግርኛ የተጻፈ አዲስ መጽሐፍ፤ ለየትምህርት ቤቱ መማርያ እንደሚሆን ተነገሯል። ይህንን አስምልክቶ ያደመጥኩት ነገር ያስገረመኝን ሳልጠቅስ ወደ ርዕሴ አልገባም።

በመጽሐፉ የምረቃው ድግስ አዳራሽ ውስጥ የመድረክ አስተናጋጅ ሆኖ ከነበረው (በዕድሜ ወጣት ይመስለኛል) አክራሪ ትግራዊ ብሔረተኛነቱን የሚያስተጋባው ንግግሩ እንዳለ ሆኖ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብላታ ሃይለማርያም ልጅ የካሳ ሃይለማርያም ረዳ መጽሐፍ ማሳተሙን በከፍተኛ ጭብጨባ እና የትግራይ ሕዝብ ዩኒቨርሲቲውን እንዲያመሰግን አዳራሹን ከጠየቀ በኋላ፤ እንዲህ ይላል።

<<ይህ አዳረሽ ለታሪክና ለስነ ጽሑፍ ደራሲያን ምን ጊዜም ክፍት ነው>> ይላል።

ይህ ከሃቅ የራቀ “ሽወዳ” ነው። መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በወያኔ ካድሬዎችና ሰላዮች መያዙን እዛው ሲያስተምሩ የነበሩት መምህራን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ለማወቅ ችለናል) ምርምርና ጥናት (?) የተያዘው በወያኔ አቀንቃኝ ግለሰቦች (ደ/ር) መሪነት ስለሚካሄድ፤ ወያኔዎችና የወያኔ ትግሬ አባሎች ስለ ድርጅታቸው የሚያቀርቡት ታሪክና የሚፈልጉትን ሰነድ ማግኘትና በቀላሉ ለሕትምት ምቹ እንደሚሆን መገመት ይቻላል (ሰነዶችም የተበላሹም “ፎርጅድ” (የተፈበረኩ) ይሁኑም አይሁኑም ለማወቅ ያስቸግረናል። እንደጠቃሚነታቸው መጠቀም ይቻል ይሆናል)። ለእነ ገብሩ አስራት ግን ዩኒቨርሲቲው ሊፈቅድ አይችልም። ምክንያቱ ግልጽ ነው።

ሆኖም ልጁ የሚናገረው <ይህ አዳራሽ ለታሪክና ለስነ ጽሑፍ ደራሲያን ምን ጊዜም ክፍት ነው> ሲል በገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” ስለ ዳግማይ ወያነ ገበና እና የድርጅቱ የህይወት ታሪክ፤ከሌሎች ድርጅቶች የነበረው ግንኙነትና ጦርነቶች የድርጅቱ ቁመና በሚገርም ሁኔታ አስመልክቶ የጻፈው መጽሐፍ < ያ አዳራሽ ለታሪክና ለስነ ጽሑፍ ደራሲያን ምን ጊዜም ክፍት ነው> የሚለው ቅጥፈት ለአስገደ ገብረስላሴም ሆነ ለገብሩ አስራት ለመሳሰሉት የሚያስተናግድ መድረክ እንዳልሆነ አስምሬ ወደ ርዕሱ እንሂድ።

ገብሩ በግሩም አቀራራብ በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ይላል፡

<<ተሓሕት በክልሉ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውን የሕዝብ ድርጅት ሓላፊዎችም ለማደራጀት ሞክሯል። ለምሳሌ ያህል ኢንጂነር ታደሰ በዛብህንና መቶ አለቃ ደስታ ታደሰን (የትግራይ ክ/ሀገር የሕ.ድ ዋና ሓለፊና ከጅብ በላይ የሚፈራ፤ደም የጠማው ደብዳቢና ነብሰ-ገዳይ የነበረውን ነው ገብሩ “ደስታ ታደሰ” ስም ከላይ የጠቀሰው) ለመመልምል ሙከራ አድርጎ ነበር። ኢንጂኔር ታደሰ በተሓሕት የምዕራብ ግምባር የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው የመለስ በዛብህ ወንድም መሆኑን ተገንዝበን በህቡእ አባልነት ልንመለምለው በወንድሙ በኩል መልእክት ልከንለት ነበር። በአውሮጳ የድሮ ተማሪዎች ማህበር እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበረው ኢንጂኔር ታደሰም አባላችሁ የምሆነው የድርጅቱ ፕሮግራም ትክክለኛ ከሆነ ብቻ ነው የሚል መልስ ላከ።

ይህን መልስ የሰጠን በግሉ ይሁን ከደርግ ባለሥልጣናት ጋር ተማክሮ ይሁን ባይታወቅም የተሓህትን ፕሮግራም ቅጂና ሰፊ ማብራሪያ ልከንለት እሱም ሰፊ መልስ ጽፎልን ነበር።

በነዚህ ጉዳዮች ዙርያ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንደሆነችና ችግሩ መፈታት ያለበት በኢትዮጵያ አንድነት ማዕቀፍ መሆኑን ሲገልጽ የመገንጠል መብት ብሎ ነበር እንደሌለም በአጽንኦት ገልጾልናል። ኢንጂኔር ታደሰ የተሓህትን ፕሮግራም እንደማይቀበል ካሳወቀን በኋላ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ <<ኡፍ! እባካችሁ እንተኛበት!> የሚል የምጸት ሐረግ ማስፈሩ እጅግ ቢያስቀንም በአንድ በኩል ደግሞ የማይሆን ነገር እያስነሣችሁ እትወትውቱን፤ አትረብሹን፤ በቃችሁ፤ የሚል መልእክት እያስተላለፈ እንደነበር ገብቶን ነበር።>>

በማለት ገብሩ በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረውን አንድ የትግራይ ምሁር ለተሓህት መሪዎች የሰጠው በታሪክ የማይረሳ መልስ ተመርኩዤ፤ እኔም ኤርትራ ኤርትራ እያላችሁ ሌት ተቀን የምትወተውቱን የኤርትራ አፈቀላጤዎች እነ ሻለቃ ዳዊቶች፤ካሳ ከበደዎች፤ ግንቦት 7 ቶች፤ ተሓህቶች እንዲሁም ተከታዮቻቸው እኔም እንደ ኢንጂኔር ታደሰ “ኡፍ! እባካችሁ እንተኛበት!” በማለት ስለ ኤርትራ የለኝን ትችት ደመደምኩ። በሌላ ርዕስ እንገናኝ!

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ- ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) getachre@aol.com