“አማራና ትግሬ ደርግን ሲታገሉ ጎን ለጎን ወድቀዋል —” ላሉት ለህወሃቷ ወይዘሮና ካድሬ ጥያቄ አለኝ!

Print Friendly, PDF & Email

(ከትንታጉ ዘወሎ)

“አማራና ትግሬ ደርግን ሲታገሉ ጎን ለጎን ወድቀዋል —” በማለት የሁለቱን ብሔረሰቦች አንድነት አልፋና ኦሜጋ የህወሓት ትግል እንደሆነ አስመስለው ለተናገሩት ህወሓታዊት ወይዘሮ ጥያቄ አለኝ

የትግራዩ ህወሓት በአማራ ስም ከአደራጀው ክንፉ ብአዴን/ኢህዴን ጋር ባደረገው በካድሬዎች በተሞላው “የሰላም ኮንፈረንስ” ስብሰባ ላይ የተናገሩ ሲቪል ለባሽ ህወሓታዊት ወይዜሮ ትግሬውና አማራው አንድ መሆኑ በእሳቸውና በህወሓት በኩል የምንሰማው እጅ ያልነካው፣ ትኩስ እውነት እንደሆነ አድርገው ማቅረባቸው፣ የሁለቱ ብሔረሰቦች ትስስር የህወሓትና የሱ ፍጡር ብአዴን ትስስር ያመጣው እንደሆነ አድርገው መናገራቸው፣ ከትግራይ የመጡ የህወሓት አንጋቾች ጉና ላይ በመሞታቸው ወይም አማርኛ ተናጋርወች በትግራይ ምድር መሞታቸው የሁለቱ ብሔረሰቦች አንድነት አንጡራ መገለጫ አድርገው መውሰዳቸው እንደ ህወሃታዊ እመቤትነታቸው የሚጠበቅ ነው።

የትግሬ ወያኔ መሪዎች ስለ አማራ ሕዝብ ከተናገሩት በከፊል የተወሰደ

ጉና ላይ የሞቱት የአገው ልጆች፣ የኦሮሞ፣ የወላይታ — ብሄረሰብ ተወላጆችም እንዳሉ፣ ጥንትም አድዋ ላይ ተነባብረው የወደቁ፣ ማይጨው ላይ ተጋድለው የተሰው፣ ኦጋዴን ላይ ሀገራቸውን ከወራሪ ጠላት ሲከላከሉ የወደቁ —- የኦሮሞ፣ የአማራና ትግራይ —- ብሄረሰብ አባላት እንደነበሩ ካድሬዋ ወይዘሮ በህወሓት የካድሬ ስልጠና ወቅት ባይሰሙት ወይም ይህን ማንሳቱ የኢትዮጵያን አንድነት ማንሳትም በመሆኑ ህወሃታዊ ጸላዔ -ኢትዮጵያ ባህርያቸው አልፈቅደው ብሎ — አይታወቅም ወይዘሮዋ እውቅና ነፍገውታል። የህወሃታዊ ወይዘሮዋን ጉዳይ ለጊዜው ትተን ወደ አንድ ተያያዥ ጉዳይ እንለፍ።

ህወሓት ታግየላችኋለሁና አታግያችኋለሁ ሲል፣ በተለይ አማራውን አንዴ ድል አድርጌያችኋለሁ፣ ሌላ ጊዜ ድል አደረግሁላችሁ ሲል፣ ተራራ አንቀጠቀጥኩ እያለ ሲፎልል፣ ሲያቅራራና ሲዘፍን፣ አንዴ እንድናደንቀውና እንድናጨበጭብለት ሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲንፈራውና ያለውን፣ ያደረገውን ሁሉ በይሁንታ እንድንቀበል የሥነልቡና ጫና ለመፍጠር ሲሞክር — ኖሯል።

ይሁንና እኔም ሆንኩ ሌላው ዜጋ በዚህ ዙሩያ ህወሃቶችን የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች በሽ ናቸው። ህወሓት በጧት በማታ የሚያላዝንበትና “ውለታ ስለዋልኩላችሁ እንደልቤና እድሜ ልኬን ልግዛችሁ” የሚልበት ትግል ለማን ያደረገው ነው? ህወሓት ኢትዮጵያ ወጋት ወይስ ተዋጋላት? ለሞቱና በሕይወት ላሉት የህወሓት መሪወችና አንጋቾች እናልቅስ ወይስ እነሱን ለመመከት ተሰልፈው ለተሰዉት የቀድሞ ሰራዊት አባላት፣ ለኢሕአፓ፣ ኢድዩ፣ ተሃትና ከፋኝ የአርበኞች ንቅናቄ አባላት እናንባ? ለጨቋኙ ነገር ግን በሀገርና ሕዝብ አንድነት ጉዳይ ለማያወላውለው፣ ለረጋጩ ነገር ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋር ሕልውናው ማክተሙ ለማያጠራጥረው ለደርግ ስርዓት መውደቅ እናልቅስ ወይስ “ደርግን ብቻዬን ታግዬ፣ ጥዬ ሱር ታጠቅሁበት” ለሚለውና የጎሳ ፍጅት፣ ብተናን፣ ጭቆናንና ጭፍጨፋን፣ የዘር መድልዎንና የሀገር ምዝበራን ደርቦ ደራርቦ ለተከናነበው ለህወሓት አድናቆታችንን እንግለጽ? ህወሓት የታገለው ደርግን ወይስ አማራን?—- የሚሉት ካሉን የብዙወቻችን ሽህ ጥያቄዎች የተወሰኑት ይመስለኛል።

ህወሓት ለማን ታገለ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ምን እንደሆነ ከነባራዊው ሁኔታ የኢትዮጵያም ሆነ የአለም ህዝብ እያየው ያለሁ ሁኔታ ነው። ማን በባዶ እግሩ መጥቶ አሁን በዘመናዊ መኪና እንደሚንፈላሰስ፣ ማን ከደሳሳ ጎጆ ወጥቶ በአጭር ጊዜ ባለ ብዙ ፎቆች ባለበት እንደሆነ፣— የየትኛው ጎሳ መሬት እንደተቀማ፣ ሃብቱን እንደተዘረፈና ያ ሀብት ለየትኛው ጎሳ በአድልዎ እንደሚያገለግል፣ የትኞቹ ብሔረሰቦች እንደሚፈናቀሉና የትኞቹ ባለ ብዙ ሺ ሄክታር መሬት ባለቤት ሆነው በዘመናዊ ነፍጠኝነት እንደተሰማሩ፣ የየትኞቹ ብሄረሰብ አባላት በህንድ ውቅያኖስ፣ ቀይ ባህርና ሜድትራንያን ባህር ወለል እንደተረፈረፉና ከሊቢያ እስኬ ደቡብ አፍሪካ ያሉትን እስር ቤቶች እንዳጨናነቁ፣ የማን ልጆች ውጭ አገር በብዙ የሀገር ሀብት እየተመዘበረ ወደ ውጭ ለከፈትኛ ለትምህርት እንደምላኩና የትኞቹ አረብ አገር በግድ ግርድና እንደምማቅቁ፣ እነማን ጨፍጫፊ ፣ አሳሪና ገራፊ የትኞቹ ደግሞ ሙትና ቁስለኛ፣ ዎፌ ኢላላ ተዘቅዛቂና በአሰያፍ ዘረኛ ስድብ ተዋራጅ— እንደሆኑ ሁሉም ያውቀዋል።

ዛሬ ገዢ የትግሬ የጎሳ መደብ የለም ብሎ የሚያምን አንጡራ ኢትዮጵያዊ አይገኝም። እናም ህወሓት የአማራም ሆነ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆችን ይዞ ታገለ፣ ጉናም ይሙት ናቅፋ የታገለው በዋናነት ለመርዎቹና ለጋሻጃግረወቻቸው ጥቅም፣ አልፎም ለትግርኛ ተናጋሪው ነው። ይህ ትግርኛ ተናጋሪው ፈለገውም አልፈለገውም ያለ እውነታ ነው።

የህውሃቷ ካድሬ አብረን ወድቀናል በማለት የሌለ አንጀት ልትበላ መነሳቷ እጅግ ያበሽቃል። ሳያውቁ ለህወሓትና ለጠባብ አላማው የሞቱ የአማራም ሆነ ሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ኢትዮጵያውያን የሚያዩአቸው ሞተው ከአመጡት ግፍና በደል፣ ገድለው ለአመጡት አይን ያወጣ የዘር መድልዎ፣ ጭፍጨፋና መፈናቀል፣ አፈናና ጭቆና ነው። መሞት በራሱ ግብ አይደለም። ለወራሪው የሶማሊያ ጦር ተሰልፈው የሞቱ የኦጋዴን፣ የገሪና ገርባ ጎሳ ተወላጆች ነበሩ። ለጣልያን ያደሩ የኤርትራና የትግራይ፣ የአማራና ኦሮሞ ሹምባሾችም ነበሩ (የመለስ ዜናዊን ባንዳ ዘርማንዘር መጥቀሱ እዚህ ላይ ላያስፈልግ ይችላል)። ጸረ ኢትዮጵያው ኃይል የጣልያን ጦር ተባለ የዚያድ ባረ፣ የሻብያ ተባለ የህወሓት አንጋች ጸረ ሕዝብ ባንዳ እንጂ አርበኛ አይደለም። እናም ጉና ላይ ሞተ ሌላ ተራራ ላይ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ ማንም ከንፈር አይመጥለትምና የወይዘሮዋ ትረካ ፋይዳ የለውም።

ጉና የሞቱት የአማራ ልጆችን ነጥዬ ባነሳ ለአማራው ያመጡለት ነገር ቢኖር መሬቱ በህወሓት እንድነጠቅ፣ ታርዶ እንቁፍቱ እንዲጣል፣ ቤት ተዘግቶበት ቤቱ ውስጥ እንዲቃጠል፣ አሶሳ ላይ በሰልፍ እንዲረሸን፣ አንገቱ በጎራዴ እንዲቀላ —-ዝርዝሩ ረጅም ነው። እናም ለህወሓት የሞተ አማራ፣ ለጸረ ኢትዮጵያ ቡድን አንግቶ የተሰየፈ ባንዳ እንጂ ሌላ አይደለም።

ኢህድን የህወሃትን አላማ ከግብ ለማድረስ “የአማራ ድርጅት “ ሳይደረግ በኢህድንነት ተሰይሞ ጉናና ሌላ ቦታ መዋጋቱ በጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ የሰከሩትና የጸረ አማራ ዘፈን በእየለቱ የሚደልቁት የህወሓት አባላት መሳሪያ እንዳያዞሩበት ጭምር እንደነበረ የህወሓት ሁነኛ መሪወች ኋላ ላይ ብቅ ያደረጉት እውነታ ነው። የትግራይ ነጻ አውጭ ጉናና ደብረታቦር ላይ ሲመታ “የምንዋጋው ለትግራይ እንጅ ለአማራ ስላልሆነ እዚህ መሞታችን ፍትሃዊ አይደለም” ብሎ ጉዞውን ወደ ትግራይ ያደረገው የህወሓት ጦር ጉዳይ ለእዚች ስብል ለባሽ ህወሃታዊ ወይዘሮ አዲስ ዜና ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ። ደርግ ወደቀና ሁሉም ሲያበቃ በህወሓት አመራር ውሳኔ የአማራ ክንፍ ሆኖ ያገለግል ዘንድ ከኢህድንነት ወደ ብአዴንነት በአንድ ቀን ወርዶ፣ ከኢትዮጵያዊ ድርጅትነት ወደ ጎጥና ጎሳ ድርጅትነት ተተንሾ ባህር ዳር ተሰየመ። አባላቱ የነበሩት እነ አባዱላና ካሱ ኢላላ የብሔር ስር፣ ግንዳቸው ተጠንቶ የየጎሳቸው አባወራ ተብለው ከኢህድን የተለዩት የዚያኑ ሰሞን እንደነበር ሁሉም ያስታውሳል። ነባር የኢሕድን ታጋዮች ተመንጥረው ህወሃትን ቆቦ ላይ የተቀላቀሉት የድል አጥብያ አርበኞች እነ አለምነው መኮነን ለህወሓት ያላቸው ተአማኝነት ብቻ ሚዛን ደፍ ሆኖ እራሳቸው ለሀጫቸውን ለአለቃቸው ለህወሃት እያዝረበረቡ አማራውን “ልሀጫም” በማለት በልሳነ ህወሓት ዘለፉት። አማራው “ይወከላል” የሚባለው እንግዲህ በነዚህ ነው።

የህወሃትና የብአዴንን ስብሰባ አስመልክቶ አንድ ወዳጀ ሲናገር “ህወሓት ከህወሓት ጋር ተሰበሰበ” ብሎታል። ለምን ህወሓት ተሰበሰበ እንዳላለ ስጠይቀው “ያንማ መቀሌ ላይ ብቻውን አድርጎታል፣ ህወሓት አንድም ትንድም የሆነ ሕልም´ውና አለው። የራሱን ህልውና ይዞ ሲሰበሰብ ‘ህወሓት ሰሰበሰበ’ ይባላል። በሌሎች ላይ ሕልው የሆነው ህወሓት ከራሱ ህልውና ካለው ጋር ሲሰበሰብ ‘ህውሃትና ህወሓት ተሰበሠቡ ወይም ህወሃቶች ተሰበሰቡ ሊባል ይችላል” አለኝ። ገብቶናልም። አልገባኝምም።