ሦስት አጀንዳዎች – የዐማሮች መከራ፣ ትግሬዎች እየተሳደዱ ነው ስለመባሉ እና የመቱ ዩኒቨርሲቲው ችግር

Print Friendly, PDF & Email

(ሙሉቀን ተስፋው)

(ሀ.) ስለ ዐማሮች መከራ እንዳንጮህ ለምትፈልጉ …

አንድ በተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ያለው የማከብረው ሰው የመቱ ዩኒቨርሲቲውን ችግር ጠቅሶ “ሙሉቀን አደራህን የዐማራንና የኦሮሞን አንድነት የሚጎዳ ዜና እንዳትዘግብ” ብሎ ወተወተኝ። ከሌሎችም በጣም በርካታ ሰዎች ተመሳሳይ አስተያየትና ውትወታ ደረሰኝ፤ በጣም ብዙ!!!

የዐማሮች መሞትና መሳደድ ዜና ሆኖ እንዳይዘገብ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከዚህ በፊት አገር ቤት እያለሁም ሆነ ከአገር ከወጣሁ በኋላ ስለወገኖቼ ስለዐማሮች መሞትና መሳደድ በምጽፍባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍ ያለ ውርጅብኝ ወርዶብኝ ያውቃል። ቤንሻንጉል ጉምዝ ላይ፣ ጉራ ፈርዳ ላይ፣ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አመያና ሌሎች ቦታዎች ላይ ዐማሮች ሲገደሉ በስፍራው እየተገኘሁ በመዘገቤ ያስተንገድኩት ስድብ ለሰሚው የሚከብድ ነው። በሌሎች የዐማራ ልጆች ላይም ተመሳሳይ ውግዘት ደርሶባቸዋል፤ እየደረሰባቸውም ነው። ግን ለምን? ከሚገደሉት ወገኖቻችን ይልቅ “ተገደሉ” ተብሎ መዘገቡ ለምን አጀንዳ ይሆናል?

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በዐማራ ሕዝብ ላይ ስለሚደርሰው ውርጅብኝ እንዳንዘግብ አጥብቀው ከሚከለክሉን መካከል የሁለቱን ሕዝቦች ኅብረት ያሻክራል፣ በዚህም ምክንያት ፀረ ወያኔ ትግሉ ይጎዳል ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ።

በእነዚህ ወገኖች እምነት ኦሮሚያ ክልል ውስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በዐማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግጭት የሚያቀነባብረውና የሚመራው ወያኔ ነው። ስለሆነም ሁሉም ሰው በወያኔ ላይ ብቻ ነው መረባረብ ያለበት።
እኛም እንደእነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱትን ግጭቶች ላይ ያለው፣ በተለይ ደግሞ በዐማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል በግንባር ቀደምትነት የሚያቀነባብረው ወያኔ ነው እንላለን። በዚህ መሠረታዊ ሃቅ ላይ ልዩነት የለንም።

ይሁን እንጂ በእኛ በኩል ከወያኔ በተጨማሪ በዐማራ ሕዝብ ላይ የከፋ ጥላቻ ያላቸው ኅይሎች አሉ፤ እነዚህ ፀረ ዐማራ ኀይሎችም ከወያኔ ባልተናነሰ መልኩ በሕዝባችን ላይ ሲዘምቱ ኖረዋል፤ ዛሬም ነገም በህዝባችን ላይ ይነሳሉ የሚል የማያወላውል አቋም አለን። ልዩነታችን ይህ ነው። ጠላት ሳይሆን ጠላቶች ናቸው ያሉን ነው የምንለው። የሚጠሉን፣ የእኛን መኖር የማይፈልጉ በርካታ ፀረ ዐማራ ኀይሎች አሉ። ይሄ እኮ ሃቅ ነው፤ ያገጠጠ ያፈጠጠ ሃቅ!!!

ለመሆኑ ወያኔ “ዐማሮችን በሏቸው” ብሎ ትእዘዝ በሚሰጥበት ጊዜ ሁሉ ትእዛዙን እጥፍ ድርብ አድርጎ የሚያስፈፅም ፀረ ዐማራ ባይኖር የወያኔ ተልእኮ እንዴት ይሳካ ነበር? ለመሆኑ ወያኔ የዐማራ ሕዝብ በሌሎች ሕዝቦች ላይ እንዲዘምት ቢቀሰቅስ የሚሰማው ዐማራ አለን? በጭራሽ!!!

በእኛ በዐማራ ልጆች እምነት በህዝባችን ላይ የሚደርሰው ውርጅብኝ በወያኔ ውድቀት ማግስት የሚቆም አይደለም። ተደራጅተን እራሳችንን እስካልጠበቀን ድረስ ዛሬም ነገም እንሞታለን።

ስለሆነም እኛ በሕዝባችን ላይ የሚደርሰው የማያቋርጥ መከራ የሚንገበግበን የዐማራ ልጆች ስለሕዝባችን በደል እንጮሃለን፤ በምንችለው ሁሉ ለሕዝባችን እንታገላለን፤ ትግላችን ሕዝባችንን ከተደቀነበት ፈተና ነጻ ለማውጣት እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣን ውጊያ በፅናት እንቋቋመዋለን።

(ለ.) ትግሬዎች እየተሳደዱ ነው ስለመባሉ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወያኔና ጀሌዎቹ በአገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ መሳል የፈለጉት ስዕል አለ። ይኸውም “ትግሬዎች በያለበት እየታደኑ ነው” የሚል ነው። ነገሩ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንደሚሉት ነው። ባለፈው ዓመት ጎንደር ላይ በወያኔ የደህንነት ተቋም በተዘጋጀው ድራማ ትግሬዎች እየተሳደዱ ነው ብለው በአልጀዚራ ቴሌቪዥን (ለዘጋቢ ገንዘብ ከፍለው) ሳይቀር ዘገባ አሰርተው እንደነበር የሚታወስ ነው። እውነታው ግን፣ ዐማራ ክልል ውስጥ አንድም ትግሬ በትግሬነቱ ያልተነካ መሆኑ ነው።

አሁንም ቢሆን ትግሬዎች ተለይተው እየተጠቁ ነው የሚል ምስል ለመፍጠር የማይዳክሩት መዳከር የለም። እኛም (እኔን ጨምሮ) ይህን የወያኔን ትርክት እየተቀበልን ስናስተገባ እንውላለን፤ በዚህም የእነሱ አጀንዳ አስፈጻሚዎች ሆነናል።

ሃቁ ከዚህ የተለየ ነው። ሃቁ ዐማሮች ላለፉት 26 ዐመታት ሲሳደዱና ሲገደሉ መኖራቸው ነው። መራሩ ሃቅ የሚያሳየን የዐማሮች ሞት ለማንም የማይገደው እየሆነ መምጣቱን፣ በአንጻሩ የአንድ ትግሬ መሞት አገሪቱን በአንድ እግሯ የሚያቆማት መሆኑ ነው። ከዚህ አስቀያሚ እውነታ ላይ ነው ያለነው!!!

(ሐ.) ስለመቱ ዩኒቨርሲቲው ችግር በጣም ባጭሩ

መቱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልክ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ በተለይ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዳሉት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎች ተሳቀው ነው የሚኖሩት። ልክ በሌሎች ዩኒቨርሰቲዎች እንዳለው ሁሉ መቱ ውስጥም በትግሬና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል ችግር አለ። ነገር ግን እንደሁልጊዜውም የትግሬ ተማሪዎች የሚጠብቃቸው (custodian) ስላላቸው ምንም አይሆኑም፤ እልሆኑምም።

በዚህ መካከል ልክ እንደሁልጊዜው በሌሉበት ጠብ የጦስ ዶሮ የሚሆኑት የዐማራ ልጆች ናቸው። መቱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሆነውም ይኸው ነው። የአካባቢው ሽማግሌዎች ነገሩን ለማስተካከል እየሞከሩ ቢሆንም አሁንም ልጆቻችን ምን ይደርስብን ይሆን ብለው በከፍተኛ መሳቀቅ ውስጥ ነው ያሉት። ይህን ተከታትሎ መዘገብና መላው የዐማራ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ የእኛ ፋንታ ነው።