ጎንደሬው፤ “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” አለ! –የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት ይከበር

Print Friendly, PDF & Email

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

(To read the article in PDF, click here)

የኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ የጣናን ኃይቅ አደገኛ ሁኔታ ሲመለከት ወገኖቹ የጎጃምና የጎንደር ዐማራ ወጣቶች የሚሰሩትን ታሪካዊ የመከላከል ትግል በማድነቅ “ጣና ኬኛ” ብሎ ሲንቀሳቀስ የተሰማኝ ደስታ ከመጠን ያለፈ ነው። የጣና ኃይቅ የመላው ኢትዮጵያዊያን ኃይቅ፤ የመላው ኢትዮጱያዊያን የተፈጥሮ ኃብት ነው። ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት መስዋእት የሆነውን የኦሮሞውን ሕዝብ ያገባዋል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በጣና ላይ ትልቅ ስህተት ሰርተዋል። ማንም ሃላፊነት የሚሰማው “መንግሥት ነኝ ባይ ቡድን ግዙፍ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ሊወገድ በሚችል “እምቦጭ” በተባለ ወራሪ እየጠፋ ወደጎን ቁሞ አያይም። ይኼ ከሌላ አገር የመጣ ወረርሽኝ (Hyacinth) የተባለ አረም በአፍሪካ የቪክቶሪያን ኃይቅ ሊያጠፋው ነበር። ሰማንያ በመቶ (80 percent of the lake was infected). የኡጋንዳ ሳይንቲስቶች ከመንግሥታቸው ጋር ተባብረው ችግሩን ለመፍታት ችለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የት ነበር? ከማለት አልፎ ፍጥነት የሚያሳየው ምን ሁኔታ ሲከሰት ነው ወደሚለው ጥያቄ ይወስደናል። የጣና ኃይቅ ሊወገድ በሚችል ወራሪ ከጠፋ የተሃድሶ ግድብም የውሃ ሽታ ሊሆን ይችላል። ገዢው ፓርቲ ለምን ሃላፊነቱም አልተወጣም ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ፤ መልሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚያውቀው አልፈዋለሁ።

የጣና የተፈጥሮ ኃብት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ህይወት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ መሻሻል፤ ለአገራችን ኢኮኖሚ እድገት፤ በተለይ ለሃገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት፤ ለመብራት ኃይልና ለመስኖ ግድቦች መጋቢ ነው። ለሕዝብ የሚቀርብ የመብራት አገልግሎት መስፋፋት፤ በምግብ በኩል አስተማማኝ ለሆነ የምግብ አቅርቦት ውጤት ወሳኝ ነው። የተሃድሶ ግድብ ብዙ ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ተደርጎበት ለዓባይ ወንዝ ዋናው መጋቢ የሆነው ጣና ቢደርቅ ምን ሊሆን ነው? ይህ የተፈጥሮ ኃብት ከወርቅና ከእንቁ የበለጠ ጥሪት ነው። የተገላቢጦሽ ሆነና ወጣቱ ትውልድ የክልልና የፌደራል መንግሥት ሃላፊዎችን እያስተማረ ነው።

ስለሆነም፤ የተሃድሶን ግድብ ለመስራት የወሰነው ገዢ ፓርቲ የጣናን ኃይቅ የመታደግ ሃላፊንት አለበት። ኃይቁን ለመታደግ የሚደክመው ወጣት ትውልድ መመስገን አለበት። ሆኖም “አባይን በጭልፋ” እንዲሉ ይህን ግዙፍ የእምቦጭ (Hyacinth) ወረራ በፍጥነት ማጥፋት ያለበት መንግሥት ነው። የኢትዮጵያ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ባለሞያዎች ጥረቱን መደገፍ ግዴታቸው መሆኑን ያውቃሉ፤ ጥረት ያደርጋሉ። ባለሞያዎቹ ይኼ አደጋ ጊዜ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም ይላሉ። በኃይቁ ዙሪያ የሚገለገለው፤ አሳ አጥማጁ፤ ከብት አርቢው፤ ገበሬው፤ ኢንዱስትሪውና ሌላው የሚመካበት ኃይቅ እንደ ተራ ነገር መታየት የለበትም። ቢያንስ የሁለት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ኑሮና ህይወት በቸልተኝነት ምክንያት ተቃውሷል። ሃላፊነት የሚሰማው ባለሥልጣን ሁሉ ይኼን ችግር ሄዶ መጎብኘትና መፍትሄ መፈለግ አለበት።

ጣና ኬኛ” የሚለው የኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን መፈክር አግባብ አለው። ወቅታዊ ነው። ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ያቀራርባል። የኢትዮጵያዊነታችን መስፈርትና መንፈስ ተምሳሌት ነው። ይኼ አስደናቂ ወገን ለወገኑ የመነሳትና የመደጋገፍ ባህል ባለፉት ሁለት ዓመታት እያበበ ሄዷል። ህወሓት/ኢህአዴግ ወጣቱን ትውልድ በብሄር በመከፋፈል፤ በጥርጣሬ እንዲኖርና እንዳይተማመን በማድረግ፤ በማይመለስበት ደረጃ ጠባብ ብሄርተኛ አድርጌ ጠምቄዋለሁ ወደሚል የተሳሳተና አጥፊ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር። ይህ በህወሓቶች መንፈስና እርዮት ታንጿል ያሉት ወጣት ትውልድ የጠባብ ብሄርተኝነትና ጎጠኝነትን የሚያንጸባርቅ፤ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ሕዝብ የሆነውን የጠባብ ብሄርተኝነት፤ በጭቁን ሕዝብ ስም ራስን አገልጋይነትን የሚያንጸባርቅ የፖለቲካ ባህልን ወጣቱ ትውልድ አደገኛ ነው በሚል ምሬት እያገለለው ሄዷል። ይህ አዲስ ትውልድ ልክ እንደ አያቶቹና ቅድመ አያቶቹ አዲስ ታሪክ እየሰራ በራሱ ህይወት ላይ የተጫነውን ቀንበር እያናጋው ይታያል።

ለማሳሰብ የምመኘው አስኳል ጉዳይ፤ ይኼ ሁሉ ጥረትና ትብብር እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሮሮች ሊቀረፉ ትየሚችሉት በጥገናዊ ለውጥ አይደለም። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቸውም በበለጠ ደረጃ መሰረታዊ የሆነ ወይንም ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። ሕዝብን የስልጣኑ ባለቤት የሚያደርግ ዲሞክራሳዊ ለውጥ ማለቴ ነው። ይህም ከቡድን፤ ከኃይማኖት፤ ከጎሳ፤ ከራስ ጥቅም በላይ አገርንና ሕዝብን ማስቀደምን፤ መተባበርን፤ መቻቻልን፤ የአመራር ብልሃትን፤ አርቆ አስተዋይነትን ይጠይቃል።

ባለፈው ሕዝባዊ አመጽ አፍላ ጎንደሬው፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ “የኦሮሞው ደም ደማችን ነው፤ በቀለ ገርባ መሪያችን ነው” ወዘተርፈ ብሎ በተነሳበት ወቅት ይህ ብሂል ታሪክ ሊለውጥ ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ። የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ይኼው የኦሮሞው ወጣት ኢትዮጵያዊይም “ጣና ኬኛ” ሲል እኔንም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ያገባኛል ማለቱ ነው። ጣና የኔ ነው ከሚለው በላይ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የሚመሰገን ታሪክ እየሰራ ነው። ህወሓቶች ከጅምሩ ሲነሱ የተነሱበት እርዮትና መፈክር “የአማራው ሕዝብ ጠላታችን ነው” ብለው ነው። ከዚህ አቋማቸው አንድም ስንዝር ወደኋላ አላሉም። እንዲያውም ሁኔታውን በማባባስ፤ በጎንደር ሕዝቡን “አማራና ቅማንት” ብለው እየከፋፈሉት ነው። የጎንደሪውን ኢትዮጵያዊ መሬት ለወዳጃቸው ለሱዳን መንግሥት መርተውታል።

ህወሓቶች ይኽ መከረኛና ድሃ የአማራ ሕዝብ እንዲጋለጥ፤ እንዲጨፈጨፍ፤ ከጋምቤላ፤ ከቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ ከኦሮምያ፤ ከደቡብ ክልል እንዲሰደድ፤ እንዲፈናቀል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች እንዲታረድ፤ እንዲዋረድ፤ መሬቱን እንዲነጠቅ፤ በጠላቶች እንዲከበብ አጋለጡት። ዛሬም በጀርባ ሆነው ግድያውን ወይንም ሌላውን ግፍ “እኔ አላደረግሁትም” የሚል ጩኸት ቢያሰሙም የሚሉትን ለማመን የሚያስችል መረጃ አናገኝም። በአማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደውን ጭካኔ በጎንደር የሚካሄደው የመሬት ነጠቃና የትግራይ ክልል ተስፋፊነት ዋናው መረጃችን ሊሆን ይችላል። ህወሓት ከአማራው ሕዝብ–ክወሎ፤ ከጎጃምና ከጎንደር እየነጠቀ ወደ ትግራይ ክልል ማጠቃለሉ የአማራውን ሕዝብ የኢኮኖሚ መሰረት ነጥቆ ለማደህየት ነው። የዚህ ሕዝብ ጉረሮ ከታነቀ ለከታታይ ትውልድ የሚያስከትለውን ችግር ለመገመት ሮኬት ሳይንስ አይደለም። ወጣቱ ትውልድ መኖሪያ ከሌለው የሚኖረው አማራጭ ረሃብና ስደት ይሆናል ማለት ነው። የጎንደርና ሌላው የአማራና የኦሮሞ ወጣት በገፍ ከሃገሩ እየተሰደደ የሳይናይ፤ የየመን፤ የሳሃራ በረሃና የሊቢያ ስለባ መሆኑ ቀጥሏል። ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ወጣቶች በሊቢያ ይሰቃያሉ። ወገኖቻቸውን ድረሱልን ይላሉ። በገፍ ከአገር እየተሰደዱ በኬንያ ጠረፍ አድርገው ወደሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚሰደዱት በብዙ መቶ የሚገመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በእስር ቤቶች ይማቅቃሉ። የስደቱ ዋናው ምክንያት የስራ እድል አለመኖሩ መሆኑ ቢታወቅም፤ ከዚህ ጀርባ ለስደቱ መሰረት የሆነው የአገዛዙ አድሏዊነት፤ ኢሰብአዊነትና ጸረ-ሕዝብነት ነው። ለዚህ ነው ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል የምለው።

ይህ አገርን ትቶ መሰደድና ሰለባ መሆን ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም። ለዚህ የሚበጀው መፍትሄ በኢትዮጵያዊያን እጅ ነው። ይኼውም የሕዝቡ፤ በተለይ የወጣቱ ትውልድ መደራጀትና ለአንድ አገር፤ ለአንድ የተሳሰረ ሕዝብ ዲሞክራሳዊ ስርዓት ምስረታና የመንግሥት ለውጥ መታገል ነው። ለዚህ ኃላፊነቱ የወደቀው በደካማዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ብቻ መሆን የለበትም። የተቻላቸውን አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው። ዋናው የትግሉ መሰረት ሕዝቡ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ነው። ይኼን በሚመለከት ወጣቱ የጎንደር፤ የባህር ዳር፤ የኦሮሞና ሌላው ወጣት ትውልድ የጀመረው ተጋድሎ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የዚህን ወጣት ትውልድ ጥሪ ማክበርና መደገፍ አለባቸው። አለያ፤ ብሄራዊና ማህበረሰባዊ ሚና አይኖራቸውም። በአጭር ጊዜ ደግሞ ከአስራ አመስት ሚሊየን በላይ ይሆናል ተብሎ የሚገመተው ከአማራው ክልል ውጭ የሚኖረው የአማራው ሕዝብ ግድያና ሌላ ግፍ እንዳይደርበት በኦሮሞያና በሌሎች ክልሎች ባለሥልጣናት ነን የሚሉ ቡድኖች፤ በተለይ ነዋሪዎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ተጨማሪ ግፍ እንዳይደርባቸው የመከላከል ግዴታ አለባቸው። የህወሓታን ሌሎች ስርጎ ገቦች ወንዳማማቹን የኦሮምና የአማራ፤ የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝና የአማራ፤ የአኟክና የአማራ፤ የሶማሌው ኢትዮጵያዊና የኦሮሞው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይጋደል መከታ መሆን የፖለቲካ ለውጡ አንዱ መስፈርት መሆን አለበት። ይህን ለማድረግ የተለየ ብቃትና ችሎታ ያለው ተራው ነዋሪው ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ነው። ሕዝብና ሕዝብ ሲቀራረብና ሲተባበር ከፋፋዮችና ጠባብ ብሄርተኞች ይረበሻሉ፤ አሁን እንደሆነው።

ለምሳሌ፤ በቅርቡ የባህር ዳር ወጣቶች ለመላው የአማራ ወጣት ትውልድ ያቀርቡት ብሄራዊ የትግል ጥሪ አግባብ አለው። እነዚህ ወጣቶች ለቆሙበት የፍትህ-ርትህ፤ የስር ነቀል ለውጥ ጥያቄ ስኬታማ ውጤት ሳያገኙ ራሳቸውን ለአልሞ ተኳሾች ሲሰጡ የሚኖሩ አይመስለኝም። እነዚህ ወጣቶች ቀስ በቀስ አገራቸው ኢትዮጵያ በአያትና በቅድመ አያት ወገኖቻቸው መስዋእትነት የቆየች መሆኗን እያስመሰከሩ ነው። ይኼ ሲባል ደሞ የሁሉም ብሄሮችና ኃይማኖቶች ተባብሮ አገርን የማዳን ተጋድሎ ውጤት መሆኑን በማወቅ ላይ ናቸው። በጎንደር፤ በደብረ ታቦር፤ በባህር ዳር፤ በደሴ፤ በመላው ኦሮምያ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደው በገፍ የተጨፈጨፉት እነሱ ናቸው። በሽህዎች የታሰሩት፤ እንዲሰወሩና እንዲሰደዱ የተፈረደባቸው እነሱ ናቸው። ይህ ሁሉ ግፍና በደል ደርሶባቸው በጥገና ለውጥ ይመለሳሉ ብሎ መገመት አይቻልም። ወጣቶቹ፤ ከዚህ አሰቃቂ ሁኔታ የተማሩት ክስተት አለ። ይኼውም፤ በተናጠል የሚደረግ ድርጅት፤ የሚደረግ ትግልና የሚከፈል መስዋእት የትም እንደማያደርስ ነው። የወቅቱ ጣያቄ መተባበር ነው የምለው ለዚህ ነው፤ ሌላ አማራጭ የለንም።

ወጣቱ ትውልድ አገር አቀፍ የሆነ ከብሄረሰብና ከቡድን በላይ የሆነ፤ ማለትም የተቀነባበረ ሕዝባዊ አመጽ ወይንም እምቢተኛነት መጀመር አለበት። በኦሮምያ የተካሄደው ሕዝባዊ እምቢተኛነት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። የባህር ዳር ወጣቶች ጥሪ ይኼን የተቀነባበረ ትግል የሚያንጸባርቅ ጥሪ አድርገዋል።
የአማራው ወጣት ትውልድ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚካሄደው ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል እንዲሆን በማሰብ የባህር ዳር ወጣቶች ወቅታዊ የትብብር ጥሪ አቅርበዋል፤

■ ያልተነሳው ወጣት ትውልድ ወደጎን መቆሙን ትቶ ለፍትህ፤ ለዲሞክራሲ፤ ለእውነተኛ እኩልነት እንዲነሳ ጥሪ አቅርቧል፤
■ በተናጠል የታገለውና በለጋ እድሜው በገፍ የተጨፈጨፈው፤ እናቶቹን፤ እህቶቹን፤ አባቶቹን፤ ዘመዶቹን ያስለቀሰው ወጣት ትውልድ በከንቱ መስዋእት እንዳልሆነ ለማሳየት የሚቻለው የእነዚህን ሰማእታት አርአያነት ተከትሎ ለፍትህ-ርትህ፤ ለነጻነት፤ ለእኩልነትና ለዲሞክራሳዊ ትግል የሚደረገውን የትግል አድማስ ማስፋፋት መሆኑን ወጣቶቹ አመልክተዋል፤
■ ዛሬም እንደበፊቱ፤ ህወሓት የአማራውን ሕዝብ በጠላትነት ከሶና አውግዞ በአለበት ሁሉ እንዲገደል፤ እንዲሰድድና እንዲዋረድ የሚያደርግበት ዋናው ምክንያት ለራሱ ቡድን የፖለቲካ የበላይነትና ለራሱ ቡድን የኢኮኖሚ ምዝበራ ለማመቻቸት መሆኑን ወጣቱ ትውልድ በሚገባ አስተውሎታል፤
■ አሁንም እንደተለመደው ፡ኦሮሞውን አማራው መጣብህ፤ አማራውን ኦሮሞው መጣብህ” በሚሉ ማዘናጊያዎች ሕዝብን ለሕዝብ ለመከፋፈል የተቀነባበረ ፕሮፓጋንዳ እንደሚካሄድ ወጣቱ ትውልድ ደርሶበታል፤
■ ይህን ስል ላሰምርበት የምፈልገው፤ በአማራውና በኦሮሞው፤ በአማራውና በትግራዩ፤ በአማራውና በአኟኩ፤ በአማራውና በአፋሩ፤ በአማራውና በወላይታው፤ በአማራውና በሌላው ተራ ሕዝብ ማከከል ስር የሰደደ ጥላቻ አለመኖሩን ለማሳየት ጭምር ነው፤
■ ሰው ስራሽ ጥላቻንና አለመተማመንን በብልሃት ለማሸነፍ ይቻላል፤
■ አብሮና ተጋብቶ የሚኖረውን ሕዝብ ለጥላቻ፤ ለቂም ተበቃይነት፤ ለግድያ፤ ለዘር ማጥፋት (Ethnic cleansing) ለስደት፤ ለውርደት ወዘተ የዳረገው ቡድን ህወሓትና በራሱ የጠባብ ብሄርተኝነት እርዮት የፈጠራቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው፤
■ እነዚህ በህወሓት የመርዝ ፖለቲካ የተበከሉ ግለሰቦች አማራ፤ ኦሮሞ፤ ወላይታ፤ ሶማሌል፤ አኟክ ወዘተ ተብለው አይለዩም፤ ከሁሉም ብሄሮችና ኃይማኖቶች የተወጣጡ፤ በብልሃት የታነጹ ናቸው፤
■ የአማራው ወጣት ትውልድ በተወለደበትና በሚኖርበት “ክልል” (በወሎ፤ በጎንደር-ቤጌምድር፤ በጎጃም) መውጫና መግቢያ፤ መስሪያና መጦሪያ መሬት እንዳይኖረው፤ መሬቱን ነጥቆ ወደ ትግራይ ያቀላቀለው ህወሓት ነው፤
■ የጎንደሬውን መሬት ነጥቆ ለሱዳን መንግሥት ያስተላለፈው ህወሓት ነው፤
■ አማራና ቅማንት ብሎ ጎንደሬውን በብሄር የከፋፈለው ህወሓት ነው፤
■ የአማራውን ሕዝብ ከትግራዩ ሕዝብ ጋር እንዲጋጭ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቂም የፈጠረው ህወሓት ነው፤
■ ተራውን አርሶና አርብቶ አደር እያስወገደ የአገሪቱን ለም መሬት ለውጭ ኢንቬስተሮችና ለምርጥ የትግራይ ተወላጆች ያስተላለፈው ህወሓት ነው፤
■ አማራውና ኦሮሞው እርስ በርሱ እንዲጨራረስ ሁለቱ ብሄሮች “እሳትና ጭድ ናቸው” ብሎ ጠብ የጫረው ህወሓት ነው፤
■ የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጠላትነት የፈረጀው ህወሓት ነው፤
■ የባህር ዳር ወጣቶች የትግል ጥሪ እነዚህንና ሌሎችን አሰቃቂ ሁኔታዎች በማጤን ወጣቱ ትውልድ በተናጠል እንዳይጨፈጨፍ ከፈለገ ያለ አንድነት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለው አስምሮበታል።

እኔ የምጨምረው ግን፤ መተባበር ያለበት የአማራው ብሄር ወጣት ትውልድ ብቻ አይደለም የሚለውን ነው። የአማራው ወጣት ትውልድ መተባበር ወሳኝነት እንዳለ ሆኖ–ምክንያቱም ችግሩ የህልውና፤ ማለትም ራስን ከእልቂት የማዳን ጉዳይ ስለሆነ—ከአሁን በኋላ የሚኖረው የፖለቲካ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል መሆን አለበት የሚል ነው። ትግሉ የአማራው፤ የኦሮሞው፤ የትግራዩ፤ የወላይታው፤ የሶማሌው፤ የአኟኩ ወዘተ፤ ማለትም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው።

በሌላ በኩል ወደኋላ የሚጎትት ክስተት በማህበረሰባዊ ሜድያ ይናፈሳል። አንዳንድ ተመልካቾች ጎንደሬውም፤ ኦሮሞውም የሚለውን አንቀበልም ይሉናል። ምክንያቱም በጀርባ የምዶለት ነገር አለ የሚል ጥርጣሬ ስር ስለሰደደ ነው። ማንን ታምናላችሁ፤ ማን የሚለውን ትቀበላላችሁ ተብለው ቢጠየቁ ግን አጥጋቢ መልስ አይሰጡም። ጎንደሬው በጎንደሬው ላይ ይተቻል። አማራው በሌላው አማራ ላይ ይተቻል። ትግራዩ በሁለቱም ላይ ይተቻል ወዘተ። ይኼ እኔ ሌላውን አላምንም የሚለው ባህል ለማንም “ተቃዋሚ ነኝ” ባይ አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው የከፋፍለህ ግዛውን አለቆች ብቻ ነው። ህወሓቶች “የኦሮሞውና የዐማራው ሕዝብ እሳትና ጭድ ናቸው” ብለው ሲቀሰቅሱ አብሮ፤ ተጋብቶና ተዋልዶ፤ አገሩን ከወራሪዎች ተከላክሎ የኖረውን ታላቁን የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ አጋጭተውና እንዲገዳደል አድርገው በፈለጉት ደረጃ፤ ለፈለጉት ጊዜ እንዲገዙና እንዲበዘብዙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጋጭ ብሎ የተናገረበት ጊዜ የለም፤ ምንም መረጃ የለንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የቋንቋ፤ የኃይማኖት፤ የባህል፤ የታሪክና ሌሎች ልዩነቶችን እንደ ጸጋ፤ እንደ በረከት ተቀብሎ የኖረ ሕዝብ ነው። እነዚህን ከስብጥር ሕዝቦች (Diversity) የሚከሰቱ ልዩነቶች ጤናማ ናቸው። ህወሕትና በራሱ አመለካከት፤ “የማይታረቁ ልዩነቶች ናቸው” በሚል ስልት፤ ለራሱ የኢኮኖሚ ጥቅምና የፖለቲካ የበላይነት በሚጠቅም ብልሃት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ሲያጋጨው ቆይቷል። ህወሓቶች እንዳሉት የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ “እሳትና ጭድ” እንዲሆን አንቀበልም ብሎ መከራከርና መታገል ያለበት የሁለቱም ብሄሮች ወጣት ትውልድ ናቸው። ሌሎቻችን “እሳትና ጭድ” የሚለውን ከፈቀድን ተጠቂዎች መሆናችን አይቀርም።

የብሄር ጥላቻው ሊወገድ የሚችለው በኦሮሞውና በአማራው ሕዝብ መካከል ያለውን የሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር፤ አንዱ ብሄር ለሌላው ብሄር መብት መከበር በመታገል ነው። ስር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በሁለቱና በሌሎች ብሄሮች መካከል እንደ ብረት ጠንካራ የሆነ ትብብር እንዲፈጠር በመታገልና በማስተጋባት ነው። ይህ ሲሆን ግን የአማራውና የኦሮሞው ሕዝብ ሌሎችን ኢትዮጵያዊያን አግልሎ አይደለም። ጥላቻን በጥላቻ ለመተካት አይቻልም፤ ጎጅ ነው። ሌላውን ሕዝብ ማግለል ለኢትዮጵያ አያዋጣም። ተቀራርቦ ማቀራረብ አስፈላጊ ነው። የሁለቱ ምሰሶ ብሄሮች ምሁራንና ልሂቃን ታሪካዊ ግዴታ በዜግነት መብቶች ላይ የተመሰረተ የማህበረሰብ ግንኙነትና የፖለቲካ ባህል እንዲፈጠር ማድረግ ነው። አንድነት ስለ ተመኘነው ብቻ ስኬታማ እንደማይሆን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አይተናል። የሚያቀራርቡ መሪዎች፤ ልሂቃን፤ ምሁራንና ድርጅቶች ያስፈልጋሉ።

ከጀርባ ያለው የተለመደው የኢትዮጵያዊያን ጥርጣሬ አጥጋቢ መልስ አለማግኘቱ ቢታወቅም፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማቆራኘት ጉዞውን በሚመለከት ወጣቱ የኦሮሞ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ የሚናገራቸውና የሚሰራቸው ተሳፋ ይሰጣሉ። ወጣቱን ትውልድ ይስባሉ። በፕሬዝደንቱ የሚመራው የኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን የልዑካን ቡድን ወደ ባህር ዳር ከተማ ሄዶ የተደረገለት አቀባበል የኢትዮጱያዊያንን የቆየ ፍቅር፤ የማስተናገድ ችሎታ፤ ጨዋነት፤ ተፈላላጊነት፤ የህብረት እምቅ ችሎታ ወዘተ ያሳያል። ህዝብን ከሕዝብ ጋር ለማቀራረብ የሚደረግ ጥረት ሁሉ የኢትዮጵያዊያንን ጨዋነት ብቻ የሚያሳይ አይደለም። “ኢትዮጵያዊነት እንደ ሱስ ነው” አለ ይኼ ኢትዮጵያዊ። እውነትም የማይሰለችና የማይረሳ “ሱስ” ነው። ኢትዮጵያዊያንን የሚያያቀራርባቸው ማህበረሰባዊ፤ ታሪካዊ፤ ባህላዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ኃይማኖታዊና መንፈሳዊ ወዘተ እሴቶች ከሚለያዩአቸው የላቁ መሆናቸው እየጠነከረ የሚሄድ መሆኑን ያመለክታል። “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው!! ጣና ኬኛ” እና “ኢትዮጵያዊነት እንደ ሱስ ነው” ትርጉማቸው ይኼው ነው። መለያየት በቃ ቢባልስ?

በእኔ ግምት ይኼ ጅምር በመሬት ላይ ብዙ ለውጦችን ይጠይቃል፤ ይኼ ገና አልተሰራም። ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያዊነት መመሪያችን ከሆነ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመኖር፤ ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ ወዘተ መብት የትም ቦታ መከበር አለበት።

የኢትዮጵያ ምሁራን “የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ዘመን ያስቆጠረ ትስስር፤ አንድነት እና ወንድማማችነት” እንዳላቸው አስተምረውን ነበር። በተጻራሪው፤ ህወሓቶችና ተመሳሳይ ኃይሎች ያስተማሩትና አሁንም የሚሰብኩት ጠባብ ብሄርተኝነትን፤ ስግብግብነትን፤ ጥላቻንና መለያየትን ነው።

በእኔ እምነት ሕዝብና ሕዝብ ተገናኝቶ መወያየቱ ብስለትን የሚያሳይና የሚፈለግ የፖለቲካ ሂደትና ስራ ነው። የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ ያለበት ታሪካዊ ግዴታ የጠባብ ብሄርተኛነትን አጥር አስወግዶ የሕዝብን አንድነት ማጠናከር ነው። እነዚህ የኢትዮጵያ ምሰሶዎች በአድዋና በሌሎች ቦታዎች በጋራ ሆነው አገራቸውን ከውጭ ጠላቶች ተከላክለው ለእኛ ትውል አስተላልፈዋል። አሁንም እነዚህ ምሰሶዎች ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብረውና ተመካክረው አፋኙን፤ ጸረ-ፍትህ-ርትሁን፤ ጠባብ ብሄርተኛውንና ሙሰኛውን አገዛዝ ለማዳከምና ለመተካት የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር እምቅ አቅም አላቸው። እነዚህ ምሰሶዎች ከሌላው ሕዝብ ጋር ሆነው፤ ሕዝብ ወሳኝና የፖለቲካ ስልጣን ማእከል መሆኑን ተቀብለው የስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል እምቅ አቅም አላቸው። እነዚህ ሁለት ምሰሶዎች ድልድይ ሆነው፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለማመቻቸት የሚችል ብሄራዊ የአንድነት የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ሕዝባዊ ድጋፍ ለመስጠት ከቆረጡ አፋኙ አገዛዝ አለቀለት ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የሁለቱ ሕዝቦች ከሌላው ሕዝብ ጋር ሆነው በአንድ ድምጽ መናገር፤ በአንድነት ከዳር እስከዳር መነሳት የአፋኙና የከፋፋዩ አገዛዝ እድሜ የተወሰነ ነው። ሆኖም፤ ድልድዩ ተሰራ ማለት ስርዓቱ ተሻሻለ ማለት አይደለም። ስር ነቀል ለውጥ በህወሓት ፈቃድ ሊመሰረት አይችልም።

የአቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ልኡካንን ይዞ ወደ ባህር ዳር መሄድ ምን ፋይዳ አለው? የሚለው ጥያቄ አግባብ እንዳለው እቀበላለሁ። ጠለቅ ብየ ስመራመረው ተስፋ የሚሰጡ የአመለካከት ለውጦች ይታያሉ። አቶ ለማ በተከታታይ በመድረኮች ወጥቶ በሰጣቸው ንግግሮች የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት አስፈላጊነት ደጋግሞ አስምሮበታል። በባህር ዳር ከተማም የሰጠው ንግግር ብሄራዊ አንድነት ወሳኝ መሆኑን ያንጸባርቃል። የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች እንግዳውን የልኡካን ቡድን በደመቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፤ መስተንግዶና አቀባበል ያስተናገደበት ዋና ምክንያት ቀደም ብየ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሁሉ ኢትዮጵያ አገራችን የሁላችንም መሆኗን አምነው ብሄራዊ ጥሪ ለማድረግና ስር ነቀል ለውጥ ወሳኝ መሆኑን ለማስመር ስለፈለጉ ነው። ቀደም ሲል የኦሮሞ ወጣቶች “ጣና ኬኛ” የሚል መፈክር ይዘው ወደ ባህር ዳር ሲሄዱም የተደረገላቸው የክብር አቀባበል ይሔን የሕዝብ ግንኙነትና አንድነት የሚያንጸባርቅ ነበር። የፖለቲካ መሪዎችን ወጣቱ ትውልድ የሚለውን በማዳመጥ አመለካከታቸውን ከለወጡ ለምን እንደምንቃወማቸው ሊገባኝ አልቻለም። ወሳኙ የወደፊቱ የፖለቲካ አማራጭ ነው። ይኼ አማራጭ በጋራና በአንድነት፤ አንደ ሰብሳቢ ሰነድ (Political Platform or Framework) ይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብ ድርጅቶችና የታወቁ ግለሰቦች ጉባኤ የሚወስነው መሆን አለበት። ይህ ስራ ጊዜ አይሰጥም።

ጉብኝቱ “ለማዘናጋት ነው” የሚለው ብሂል

በአሁኑ ወቅት ህወሓቶች ብዙ የማዘናጊያ ስራዎችን ይሰራሉ። ከእነዚህ መካከል በአሜሪካ ምክር ቤት H.R. 128 & S.R. 168 የተባሉት በአሜሪካ የታችና የበላይ ምክር ቤት አባላት ስለ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት፤ የሁሉን አቀፍ አገዛዝና የዲሞክራሲ ስርዓትን አስፈላጊነት የሚጠቁሙ የሕግ ውሳኔዎችን ለማቆም የሚድረገው አቤቱታ ነው። ህወሓቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ የውጭ ምንዛሬ እየተጠቀሙ የአሜሪካን ባለሥልጣናት ማባበልና ማስፈራራት ጀምረዋል። አንዱ በትራቸው እናንተ ይኼን ሕግ ካወጣችሁ አልሸባብን ለመከላከል የምናደርገውን ወታደራዊ አገልግሎት ፈጽሞ እናቆማለን የሚል ነው። በዚህም መሰረት የህወሓት መንግሥት ብዙ ሽህ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ልኳል። ይኼ “ታማኝ አገልጋይ ነኝ” የሚል መልእክት የኢትዮጵያ ተራ ወታደሮች የህወሓት አገልጋይ ሆነው እንዲሞቱ ያጋልጣቸዋል እንጅ በዘላቂነት ሲታይ የሶማሌን ችግር ሊፈታው አይችልም። በዚህ የታማኝነት ዘመቻ የሚጠቀሙት አንዱ ህወሓት ሲሆን ሌላው ተጠቃሚ የአሜሪካ የመከላከያ ኃይልና የደህንነት ክፍሉ ናቸው። ይህ ታማኝነት ለኢትዮጱያ ሕዝብ የሚያስከትለው መዘዝ፤ በጸረ-ሽብርተኛነት ዘመቻ አሳቦ አፈናውና ግዳያው ፍጹም በባሰ ደረጃ እንዲካሄድ የሚረዳ ይሆናል። ይህ ያልተጠበቀ የህወሓት ዘመቻ ከላይ የጠቀስኳቸው ህጎች እንዳይሳኩ በሚያስችል ደረጃ አሁንም “ለአሜሪካ ታማኝ ነን” የሚል ምልክት መሆኑ አያከራክርም። ይኼ ነው አንዱ የማዘናጋት ዘመቻው።

ሌላው የተቀናጀ ማዘናጊያ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨት ነው። ባለፉት ወራቶች ብቻ ከአምስት መቶ ሽህ ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል። ህወሓት ችግሩን ለመፍታት ባለመቻሉ ሁኔታውን አባብሶታል። ማንኛውም ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ አውጇል። በመገናኛ ብዙሃን በኩል የሚታየው አፈና ተጠናክሩል (Freedom House: Ethiopia’s Freedom on the Net 2017 Status NOT FREE). ሕዝብ ነጻነት ይላል፤ ገዢው ፓርቲ የባርነት ሰንሰለቶችን አጠናክሯል። ይኼም ነው ስር ነቀል ለውጥ ከሌለ አደጋው ይባባሳል የሚያስብለኝ። ተራው ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት ሁሉ ግጭትና አፈና ካስመረረው እርጋታና እድገት ሊኖር አይችልም። የኑሮ ውድነት እየተባባሰ ይሄዳል። ስደቱ ይቀጥላል።

ከጀርባ ያለው መሰረታዊ ዘመቻ የተካሄደበት ዋና ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደገና የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ ያስከተለው መሽበር፤ አገዛዙን ወደ ፍርሃት ወሥዶታል። እዚህ ላይ መጠንቀቅ አለብን። ምክንያቱም፤ ህወሓት በበላይነት የሚያስተዳድረው አገዛዝ ተንገዳገደ እንጅ አልፈረሰም። የመከላከያና የደህነት ክፍል አሁንም በህወሓት እጅ ነው። ባጀቱ፤ በተለይ መሳሪያ ለመግዛት የሚያስቸለው የውጭ ምንዛሬ በህወሓት እጅ ነው። ገና ብዙ ስራዎች ከፊታችን ላይ ተደቅነው ተባበሩ የሚል ጥሪ አቅርበውልናል። ሕዝባዊው አመጽ አገር አቀፍና ከብሄር በላይ መሆን አለበት። ጅምሩ ጎንደሬው የተናገረው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ያለው፤ የኦሮሞው ወጣት በቅርቡ “ጣና ኬኛ” ያለው እንዳለ ሆኖ፤ ወደማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ አንድነት ለመሸጋገር መደረግ ያለበት ውይይትና ድርድር ገና አለመካሄዱ ትልቁ ተግዳሮት ነው።

ስለሆነም፤ ይህ ለጋራ ዓላማ በጋራና በአንድነት የመወያየትና የመደራደር ስራ በአስቸኳይ መካሄድ አለበት። ቃላቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ከፈቃደኝነትና ከቆራጥነት ሌላ የቀረን ነገር የለም። የአማራው፤ የትግራዩን ሆነ የኦሮሞውንና ሌላውን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉት ፓርቲዎች የሕዝብን እሮሮ ካዳመጡና ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ከህሊናው እንዳያወጣቸው ከፈለጉ አሁን የተከሰተውን እድል በመጠቀም፤ የስልጣን ሽሚያውን ወደ ጎን ትተው ለኢትዮጵያና ለመላው 105 ሚሊየን ሕዝቧ በፍጥነት ብሩህ የሆነ ሁሉን አቀፍ አማራጭ ማቅረብ አለባቸው። የባህር ዳሩ ውይይት መነሻ እንጅ መድረሻ አይደለም። መድረሻው ስር ነቀል ለውጥ ነው።

በጎጥ፤ በብሄር፤ በኃይማኖትና በግልና በቡድን ጥቅም መደራጀቱ አያዋጣም ብለን አሁን ለመነሳት ካልቻልን አፋኙና አሰቃቂው አገዛዝ ለተከታታይ ዓመታት ይቀጥላል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአሰቃቂው አገዛዝ ለማላቀቅና እውነተኛ ዲሞክራሳዊ ስርዓት እንዲመሰረት ከተፈለገ ጠባብ ብሄርተኝነትን ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህ ተግባር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ብቻ አይደለም። የማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የመንፈሳዊ አባቶች፤ የሴቶች፤ የወጣቶች፤ የምሁራን፤ የልሂቃን፤ የባለሞያዎች፤ የባለኃብቶችና የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።

በጠባብ ብሄርተኝነት አጥር ውስጥ ታጉረን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳን አንችልም (We cannot save Ethiopia from Balkanization if we continue to adhere to the failed state phenomenon of ethnic enclaves). በጠባብ ብሄርተኝነት በሽታ ተበክለን የአማራው ሕዝብ ዛሬ ሲጨፈጨፍ፤ ነገ የአኟኩ፤ ከነገወዲያ የኦሮሞው ወዘተ ሲጨፈጨፍ “ማነህ ባለሳምንት” እያልን እልቂቱን ልንታደገው አንችልም። “ማነህ ባለሳምንት” ማለታችን ይቁም፤ ሁላችንም በትሩን ቀምሰነዋል በቃን ብለን የምንተባበርበት ጊዜ ዛሬ ነው። ስለትናላንቱ እልቂት፤ ስለትላንቱ ጥፋትና ውርደት የምነወያይበት ጊዜ ይመጣል። አቶ ለማ መገርሳ በባህር ዳር እንዳሳሰበው፤ አሁን ያለንበት ጊዜ የሚጠይቀው አንድነትን፤ ኢትዮጵያዊነትን ነው። አሁን ከፊታችን የተደቀነው ጥሪ ኢትዮጵያን ከመፈራስ፤ ሕዝቧን ከእልቂት ማዳን ነው። ይህ ጥሪ የአመራር ብልሃትን፤ መቻቻልን፤ አርቆ ማስተዋልን፤ ለሕሊና መገዛትን ይጠይቃል። አገርንና ሕዝብን ከቡድን፤ ከጎሳ፤ ከራስ ጥቅም በላይ ማስቀደምን ይጠይቃል። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ማገናኘትን፤ ማስታረቅን፤ ማቆራኘትን ይጠይቃል። ይኼ ደሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።

እስካሁን የአማራውና የኦሮሞው ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ራሱን ለህወሓቶች አልሞ ተኳሾች እያጋለጠ መስዋእት ሆኗል። ባለፉት ሳምንታት ግን ሌላ ሕዝብ ማወቅ ያለበት ሕዝባዊ አመጽ በመቀሌ ተካሂዹል። ይኼ በአሬና ፓርቲ የተቀነባበረው ሕዝባዊ እምቢተኛነት እየሰፋ መሄዱን ያመለክታል። አንድ ተመልካች እንደገለጹት፤ አሬና “ከብዙ ኣመታት በኋላ ግን የትግራይም ሕዝብ ከኣብራኩ ህዝብ የወጣ ለሃገራችን አንድነት እና እኩልነት፤ ሉኣላዊነት ለማስከበር መታገያ ፕሮግራም ነድፎ የአፈናን ምሽግ ሰብሮ መስዋእት ከፍሏል። ኣባላቱ ታርደዋል፤ በእስር ተሰቃይተዋል፤ በሽብር ተፈርጀዋል።” ይኼን ከጻፉ በኋላ ያሳሰቡት አንድ መሰረታዊ ምክር አለ። ይኼውም “ታድያ ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ እንዴት ብሎ ነው አንድ ናቸው የሚባለው ? ይህን ሌሎቻችን ልናስብበት ይገባል። ሁላችንም የምንፈልገው የኢትዮጵያን ቀጣይነት፤ ግዛታዊ አንደነት፤ ሉዐላዊነትና የመላው ሕዝቧን አንድነት ስለሆነ የትግራይም ሕዝብ በጨቋኙ በህወሓት ላይ እንዲነሳ ማበረታታት አለብን።” ይኼን ጥሪ በተደጋጋሚ ማስተጋባት ያለበት የትግራይ ሕዝብም ጭምር ነው፤ ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጎን መቆም ግዴታው ነው።

እኒህ አገር ወዳድ እንዳሉት፤ “በኣማራ ፣ በኦሮሞ ፣በሱማሌ ፣በጋንቤላ ፣ በጉሙዝ ፣ በደቡብ ፣በኣፋር ላነሱት ጥያቄ መልሱ ጥይት ተሰጥቶዋቸዋል፤ ሆን ተብሎ ሃብት ወድሟል ። ይህ ሁሉ ሞትና ውድመት ሲከሰት በየኣካባቢ የነበሩና ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥናት በተሞላበት መልክ ቢመሩ ኖሮ ይህን ግሪዚያኒ መሰል ስርኣት ያጋልጡት ነበር።” ይህ ትክክል ነው። ግን የትግራይ ተወላጆች ድምጽና ተሳትፎ የት ላይ ነው? እነሱም እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት አለባቸው። እርግጥ ነው፤ የእኛ መበታተን ለህወሓት የበላይነትና አፋኝነት ዋናው ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

የአማራው፤ የጉራጌው፤ የወላይታው፤ የአፋሩ፤ የሶማሌው፤ የአኟኩ፤ የትግራዩ፤ የኦሮምው፤ የሃዲያው፤ የዳውሮውና የሌላው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ መብትና ጥቅም ሊከበር የሚችለው የሁሉም ጥቅም ሲከበር ብቻ ነው። የጎንደሬዎቹ ወጣቶች፤ የባህር ዳሮቹ ወጣቶች፤ የኦሮሞዎቹ ወጣቶች የሚቀሰቅሱት ለአንድ አገርና ለአንድ ሕዝብ መብትና ጥቅም ነው። እነሱና ሌሎቻችን የምንለው የሁሉንም ጥቅም ለማስከበር የሚቻለው በተናጠል አይደለም፤ በአንድነት ነው። የኢትዮጵያ ነጻነት ተከብሮ የቆየው በሁሉም ሕዝቦቿ አንድነትና መስዋእት መሆኑን ስንቀበል፤ በተመሳሳይ መቀበል ያለብን የወደፊት እድላችንም የሚወሰነው ለጋራ አገር የጋራ ጥቅም ያስፈልጋል በሚለው መርህ ስናምን ነው። ስር ነቀል ለውጥ የሁላችንም ፍላጎት ስለሆነ የሁላችንንም አስተዋፆ ይጠይቃል። አለያ፤ ለውጥም ቢመጣ፤ የኦሮሞውና የአማራው ሕዝብ ቢወያይም፤ ከአለፈው አድሏዊ አገዛዝ ለመላቀቅ አይቻልም፤ አፋኙን ስርዓት በሌላ አፋኝ ብንተካው ችግሩ ይቀጥላል።

ላማጠቃለል፤ አስፈላጊው ስርነቀል የሆነ የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው።፤ ይህ ሊሆን የሚችለው አንዱ ሌላውን በመጠራጠር አይደለም። በመቀራረብ፤ በመነጋገር፤ በመወያየት፤ በመተማመን፤ በመደጋገፍ፤ በመቻቻል፤ በመወያየት፤ በመነጋገርና በመደራደር ነው። ጠባብ ብሄርተኝነት የፈጠረውን መርዝ፤ ልዩነትና አጥር ሁሉ እንደገና በማፈራረስ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በአስተዳደር በደል ተበክላለች፤ ተመዝብራለች፤ ታፍናለች፤ ተከፋፍላለች ወዘተርፈ እንላለን። ይህንን ራሱ ገዢው ፓርቲም አምኗል። ጊዜ ይወስዳል እንጅ እያንዳንዱ ወንጀለኛ ይጋለጣል፤ እያንዳንዱ ሙሰኛ ይታሰራል። በግልጽ እንደሚታየው ሁሉ፤ ህወሓት ያላመነው ነገር ቢኖር፤ ራሱ የፈጠረው የብሄር ተኮር አስተዳደርና አመራር አጥር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮና ተሳስቦ የገጠመውን ችግር ሁሉ ለመወጣት አቅሙን ያደከመው መሆኑን ነው። ይህ አጥር የሶማሌው ኢትዮጵያዊ ከወንድሞቹ ከኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንዲጋጭ፤ የአማራው ሕዝብ ከትግራይ ወንድሞቹ ጋር እንዲጋጭ፤ የአማራው ሕዝብ ከቤኒ ሻንጉል ኢትዮጵዊያን ጋር እርስ በርሱ እንዲጋጭ፤ ሰላምና እርጋታ እንዲበከል አድርጎታል። የዛሬው ጥላቻና ግጭት ለተከታታይ ትውልድ እንደሚተላለፍ ያላጤኑት ክስተት ነው ለማለት አልችልም። ህወሓቶች አውቀውና ሆነ ብለው የሚያደርጉት የአገዛዝ ስልት ነው።

ለዚህ የሚበጀው ምን እንደሆነ የመመራመርና አማራጮችን የማቅረብ ግዴታ ያለብን በኢትዮጵያ ቀጣይብነትና ሉዐላዊነት፤ በሕዝቧ አንድነት ሙሉ እምነት ያለንና ለመላው ሕዝቧ የኑሮ መሻሻል የምንቆረቆረው አገሪቱ ያስተማረችን ልጆቿ ነን። ኢትዮጵያ የሰዎች መካን ናት ካላልን በስተቀር የጠባብ ብሄርተኝነት
ያስከተለውን አደጋ በግልጽ ማጋለጥና የተሻለ አማራጭ ማቅረብ ያለብን እኛው ራሳችን ነን። ይኼን ፈረንጆች አያደርጉልንም፤ ግዴታቸውም አይደለም። ይኼን ካላደረግን ታሪክ ይወቅሰናል ማለት ነው።

የአማራው፤ የኦሮሞው፤ ቀስ በቀስ የትግራዩ ወጣትና ሌላው ትውልድ ስርዓቱን ለመለወጥ ተነስቷል። በአገር ቤትና በስደት የምንኖረው የሌሎቻችን ታሪካዊ ግዴታ በአገር ቤት የሚካሄደውን ሕዝባዊ ትግል፤ በተለይ ወጣቱን ትውልድ ማበረታታት፤ መደገፍና፤ አቅጣጫ እንዳይስት ማድረግ፤ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር
እንዲገናኝና አንድነቱን እንዲያጠናክር ማመቻቸትና ብሩህ የሆኑ አማራጮችን በቅንነት ማቅረብ ነው።

የኢትዮጵያ ቀጣይነትና የመላው ሕዝቧ ብሄራዊ አንድነት የሚጠቅመው ለሁሉም ብሄሮች መሆኑን ወጣቱ ትውልድ እያስመሰከረ ነው።

November 14,, 2017