መልስ ለድንበሩ ደግነቱ – ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ)

Print Friendly, PDF & Email

(To download and read the PDF, click here)

ጸሃፊው ከታዘብኩት ትችታዊ አጣጣሉ የግንቦት 7 ደጋፊ አንደሆነ እገምታለሁ። “የኦሮሞ ደም የኔ ደም ነው!“ ማለት የሱማሌውም፥ የትግሬውም፥ የጋምቤላውም፥ የሱርማውም ወዘተ የኔ ነው ማለት አይደለምን? (ድንበሩ ደግነቱ) በሚል ርዕስ የተጻፈ ትችት የግንቦት 7 አቀንቃኝ ሚዲያ በሆነው “አባይ ሚዲያ” በተባለው ድረገጽ የተለጠፈው ከላይ የተጠቀሰው ርዕስ፤ ስለ አማራ እና ስለ ፕሮፌሰር አስራት የተቸበትን ጉዳይ ላወያያችሁ።

ከላይ የቀረበው ጽሑፍ የተመለከትኩት በየድረገፆች ከመዞር ያዳነንን በየድረገፆች የሚለጠፉትን ዜናዎችን ባጭር፤ ባጭር ርዕሶቹን ብቻ አሰባስቦ ከነምንጫቸው በመጠቆም በየቀኑ ወደ ኢመይሌ የሚልክልኝን እኔ በአክብሮትና በምስጋና “ሸጋ” (ቢዩቲፉል) ብየ የምጠራው EthioExplorer.com ድረግጽ ላይ ነው ነው ጽሑፉን የተመለከትኩት። ምንጩ abbaymedia.com http://amharic.abbaymedia.com/archives/38460 የተባለው ድረገጽ ሲሆን፤ የትችቱ ዓላማ የሚመሰገን ቢሆንም፤ ከመስመር የተዛነፉ ትችቶች ስላነበብኩ ሁለት ነገሮችን በመጥቀስ በዚህ ልሂድበት።

በመጀመሪያው ነጥብ ፀሐፊው እንዲህ ይላል

<< ፕሮፌሰር አሥራት የአማራ መጨፍጨፍ ዛሬ ከቆመ ነገ መዐሕድን አፈርሠዋለሁ ይሉ ነበረ። ዛሬም ለዐማራ ድርጅት መፈጠር የሚባዝኑት የዐማርኛ ተናጋሪው ተለይቶ መጨፍጨፍ ነው ምክንያታቸው። ግን ባሁኑ ጊዜ ያልተጨፈጨፈ ወይም በመጨፍጨፍ ላይ የሌለ ኢትዮጵያዊ የኅብረተሰብ ክፍል አለመኖሩ ነው ቅራኔው። >> ይላል ጸሃፊው።

በሥርዓት ላይ የተቀመጠው የትግሬዎቹ ፋሺስታዊ ስርዓት ከመነሻው በሦስት የዘመናት እርከኖች ጀምሮ (ዘርዝሩን እና ደራጃዎቹ በቪኦኤ ትግርኛ አስመልክቼ ያቀረብኩላችሁ ትንተና ጽሑፍ ተመለክቱ) “ኦርዮን” የተባለው የጦቢያ መጽሄት የዜና ዘጋቢ፤ ‘መጽሄቱ’ ድሮ አገር ውስጥ ሲታተም በሚገባ እንዳስቀመጠውና እኔም በመጽሐፍቶቼ እንዳብራራሁት በአንድ ዘር ላይ (ነገድ ላይ) ያነጣጠረ ጥቃት ከመነሻው የትግሉ መነሻና ምክንያት አድርጎ የተንቀሳቃሰው የትግሬዎቹ ብሔረተኛው ቀኝ አክራሪው ቡድን “ያነጣጠረው” በአማራ ላይ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ገልጸናል። በጸሀፊው ደካማ መከራከሪያ ጊዜየን ላጠፋ አልፈልግም (ያደከም ጉዳይ ነው)። የተቀሩት ዜጎች የሚጨፈጨፉት “በቅርቡ” (ለ26 አመት ሳይሆን ‘በቅርቡ’ ይህን ቃል አትርሱ) በቅርቡ የተነሳ የበቃኝ አልገዛም ባይነት ‘በጨቋኝ እና በተጨቋኝ” መሃል የተነሳው እንቅስቃሴ ያስከተለው ጭፍጨፋ እንጂ-፡ ጸሃፊው አንደሚለው “ሁሉንም” ነገዶች እንደ አማራው “ቀንደኛ ጠላት” ብሎ ፈርጆ የጨፈጨፈው አለ የሚለው መከራከያ ካለው ጸሃፊው የማሳመን ሐላፊነት ይጠበቅበታል። እንዲህ ዓይነት እምነት ያለችሁ ዜጎችም ሌላ ማሳመኛ ካላችሁ ንገሩን። የቅርቡ ኦሮሞና ሶማሌ ብለህ ምሳሌ እንዳታቀርቡ ግን እሰጋለሁ። ያ የሚያዛልቅ መልስ ሊሆን አይችልም። የነዚህ ክስተትና አማራው ለየብቻ ነው። የታየው መገዳደልና የመባረር ክስተት ምክንያቱን ስትፈትሹት ‘እርስበርስ በማጋጨት’ ስርዓቱ ያስከተለው ‘የኤትኖ ፌዴራሊሰት አፓርታይድ” አደረጃጀት ያስከተለው ውጤት እንጂ እንደ ሩዋንዳው ሁቱ እና ቱሲ፤ እንደ ኢትዮጵያው “ትግሬና አማራ” በሚል በፕሮግራም የተቀረጸ ዕልቂት ስላልሆነ ሌላ መከራከያ ፈልጎ ቢያስረዳኝ ይመረጣል።

እባክህን ውድ ጸሃፊም ሆንክ ሌሎቹ የምትጋሩት ሁሉ፤ “ወልቃይቶች/ጎንደሬዎች፤ ወሎዎች፤ ጎጃሜዎች፤ ሸዋዎች እና በመላው አገሪቱ ተበትነው ከመኖርያቸው እና አገራቸው ውጡ እየተባሉ ለ36 አመት ፍዳ የተፈጸመባቸው አማራዎች አንዳይሰሙዋችሁ ታቀቡ። ለፖሊቲካችሁም፤ ለታሪካችሁም እና ለድርጅታችሁም የሚጎዳ ነው። የናንትን አመለካከት አማራዎቹ “እስኪ ጊዜው ቢያልፍ እያሉ” ፤ “አገር እንዳይፈርስ” እያሉ ልብ አወፍረውም ይሁን ወይንም የናንተው አጉል መከራከያ ይዘው (አላውቅም) እራሳቸውም ቤተሶቦቻቸው ከነ ነብሰቸው ወደ ኡንቁፍቱ ገደል ሲገፈተሩ ለ20 አመት ዝም ብለው ‘ሲያመነቱ’ ነበር የቆዩት። በመጨረሻ እባካችሁ ብለን ገፍተን ገፋፍትን ‘በእነሱም በእናንተም” እየተሰደብን አሁን ወደ አለው ደረጃ እና ሰነዶችን፤ መጻህፍሮችን ተደብቀው የነበሩ ምስጢሮችን (አውዲዮዎች/ቪዲዮዎች/ደብዳቤዎች….) እራሳቸው በመሳተፍ ይፋ አድርገው በዘር ማጥፋት የሚጠየቁ ወንጀለኞች ለሕግ አዋቂዎች (ለታሪክ ጸሃፊዎች “ታሪክ ተመራማሪዎች/ሕግ አዋቂዎች/ ጥሪውን የሚቀበሉ ከሆነ – ግን ምቾት ሸፍኖኣቸዋልና የሚያደምጡት አይመስለኝም)! ሰነዶች አዘጋጅተው ጊዜ እስኪመች ድረስ እያመቻቹ ይገኛሉ። እናንተ ያልሰራችሁት እነሱ በመደራጀታቸው ባጭር ጊዜ አመርቂ ሥራ ሰርተዋል ማለት ነው!!።

“አማራ ብቻ አይደለም- ሁሉም ተጠቅቷል” ባዮች አማራዎቹ ከመደራጀታቸው በፊት፤ እናንተ ለአማራው አስባችሁ የዘገባችኋቸው ሰነዶች፤ መጽሐፍቶች፤ ምርመራዎች፤ ክርክሮች… ካለ አሳዩን። ግን ምንም ያደረጋችሁት ነገር የለም! አይደለም እንዴ? ስትጠየቁ መልስ ስጡ! ንገሩን እንጂ! ስለ ጋዜጠኞች መታሰር እና መሸለም አልነበርም ወይ 25 አመት ስትዘግቡና ስትጽፉ ስትሟገቱ ጥብቅና ቆማችሁ የነበረው? አማራው ሲጨፈጨፍ እናንት የት ነበራችሁ!? እንዲህ ያሉ ያሉ ጸሃፊዎች ናቸው አማራ ለ26 አመት ሲጨፈጨፍ ተኝተው ቆይተው፤ አማራዎች ተነሱ ብለን በመከራ አስነስተናቸው ሲነሱ እንደገና አፋቸው እንዲዘጉ በመወትወት ላይ ይገኛሉ።

የግንቦት 7 አባሎችና ጸሃፊዎች ለድርጅታቸውና ለታጋዮቻቸው ገንዘብና ምክር ሲለግሱ፤ እኛ ነን ከጭፍጨፋው ነፃ የምናወጣችሁ እና አማራዎች ለድርጅታቸው ገንዘብና ምክር አትለግሱ ይላሉ። ምን የሚሉት ፖለቲካ እንደሆነ ምንም አይገባኝም። ግንቦት 7 የተባለው አስቂኝ ስብስብ አማራውን ነፃ ሊያወጣ ቀርቶ እራሱ ከታሸገበት ከሻዕቢያው ኮለኔል ፍጹምና ከኢሳያስ ትዕዛዝ ውጭ ፍንክች እንደማይል መሪዎቹ (ጀሌዎቹ ሳይሆኑ) መሪዎቹ ያውቁታል። ቢክዱትም እኔ በበቂ ማስረጃ አለኝ; በበቂ! ከውስጥ ከራሳቸው ከሻዕቢያዎች!!!! ያም ሆነ ይህ አማራው እራሱን ከማዳን የማይመለስ መሆኑን ፖለቲካ የሚያውቁ ሰዎች የሚያውቁት ነው። ይህ ሃቅ ምንም ቢሆን የሚለወጥ አይሆንም። አሁን በጣም ረዢም መንገድ ተጉዟል። ይህ ‘የፖለቲካ-ከብትነት’ እና ጸረ-አማራ ድርጅት ዘመቻ መክፍት ጭራሽ ያለመብሰልና የባሰ ውጥረት መፍጠር ነው። ስለዚህ ስራችሁን ብቻ አትኩሩና አሳዩን። ያ በቂ ነው።

ጸሃፊው ስለ ኢደፓው ጎረምሳ (የወያኔው ጎረምሳ) ልደቱ አያሌው በትንሹ ነካክቶ በማጋለጥ ያለፈው ትችት እስማማለሁ። በትንሹ መተቸቱ ግን አልወደድኩት (ሆኖም ርዕሱ ስላልሆነ ከጸሐፊው ጋር እስማማለሁኝ)።

ስለ ልደቱ እጽፋለሁ ስል ነው ረስቼው አሁን ያሳታወስኩት። ልደቱን በሚመለከት አንዲት ዩ ቱብ ላይ ያየኋት ወጣት ኢትዮጵያዊት ሁሌም የልደቱ መገለጫ የሆነውን ስሙን “ክህደቱ’ ብላ ስትጠራው ወጣቶች እየነቁ መምጣታቸው ደስ አለኝ። ቁጭቷ እና ወቀሳዋ ያነጣጠረው ‘ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ” በማለት በኢትዮጵያ ምድር ቁጭ ብሎ በአማርኛ የሚስተናገድ ዝግጅትን በእንግሊዝኛ ርዕስ ተሰጥቶት ለሚያቀርብ አዘጋጅ ‘ልደቱን” እንደ እንግዳ መጋበዙን በመቃወም ባሰማቺው ላይ ነው “ክደቱ’ ስትል ደጋግማ የተቸቺው። ልደቱን ማነሳቴ ላልቀረ፤ አንድ ነገር ልብልና ወደ ሌላው ልሸጋገር። ልደቱ ከተናገራቸው አሳፋሪ ወያኔአዊ ፕሮፓጋንዳው ሁሌም የሚገርመኝ በሰፊው ለወደፊቱ የምተንትንበት ንግግሩ እንዲህ የሚለውን እንደነጥብ ያዙልኝ። ልደቱ እንዲህ የሚለውን ንግግሩ ሁሌም የማልረሳው ነው፤-

“ተቃዋሚዎች፤ በሽግግሩ መንግሥት የተከሉትን አስተሳሰብ እስካሁን ድረስ ሊቀይሩት አልቻሉም።ይህ ሁሉ ልማት እየሰራ ኢሕአዴግ እዚህ የመጣው አገር ለማፍረስ ነው፤አገር ለማጥፋት ነው ብሎ እንደ አንድ ውጪአዊ ሃይል ይፈርጁታል። ይህ አስተሳሰባቸው አብሮ ለመስራት፤ለመመካከር ትልቅ እንቅፋት የሆነውን መለወጥ አልቻሉም። መንገዱን እየሄዱበት ህንፃውን እየኖሩበት ኢህአዴግ የሚሰራውን በጎ ጎን ማየት አልቻሉም። ማን በሰራላቸው ጎዳና እና ህንጻ ነው እየኖሩና እየሄዱበት ያሉት?

ሲል ልረሳው የማልችል አስገራሚ የሆነ የካድሬነቱ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ አድመጬአለሁ። ልደቱ አንድም የአንግሊዝ ሊበራሎች ስለ (ኢንትርናል ኮሎኒያሊዝም) ፖለቲካ አላስተማሩትም (ያስተማሩት ሌላ የቤት ሥራ ሊሆን ይችላል?) ወይንም ሆን ብሎ ወያኔአዊ ስራውን እየሰራ ነው፤ ወይንም የወያኔ ትክለሰውነት ምንነት አላወቀውም ማለት ነው። ለዚህም ነው ላንቃው እስኪደርቅ ድረስ “በማን ጎዳና እና ማን በገነባላችሁ ህንጻ ነው እየተኛችሁ ያላችሁት የሚለው።

ተቃወሚዎቹ ስለ ድሃ ሕዝብ እየወከሉና እየተናገሩ፤እየታሰሩ፤እየሞቱ፤እያተሰሩ ለሕዝብ ሲሉ መሆኑን ረስቶታል። ድሃውን የሚተኛበት ቤት አጥቶ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ክምሮች እየተኛ ፤ የቆሻሻ ናዳ በላዩ ላይ እየተናደበት “የኢትዮጵያን ድሃው ሕዝብ” የምትኖሩት ህንጻና የምትራመዱበት ጎዳና የሰሩላችሁ ወያኔዎችን አመስግኑ! በማለት ባለ ጊዜው ልደቱ አያሌው “ንግግር ያውቃል” የሚባልልት ሙገሳ ጭንቅላቱ ላይ ወጥቶ በክርክር ምርጫ ወቅት ያለ ምንም ሚዛን በሕብ ኑሮ ሲያፌዝ አድመጬዋለሁ። ይገርማል።
ለመለስ ዜናዊና ለአጋዚ አልሞ ገዳዮች ዱላና ጠመንጃ የያዙ ወታደሮች የሚሽሞኖሞኑበትን ጎዳናና አደባባይ ፤ “ለሰላማዊያን ተቃዋሚ ሰልፈኞች” የሚከለከሉበት፤የሚደበደቡበትና የሚረሸኑበትን ጎዳናንን ነው ወያኔዎች ገንብተውላችኋልና መሪያቸውን ‘መለስ ዜናዊን’ አመስግኑ እያለ በሕዝብ ህይወት ላይ የተመጻደቀው። ‘መለስ በሕዝብ መተላለፊያ ሲያልፍ’ በወታደራዊ ታንኮችና አልሞ ተኳሾች አጥር የሚከለከል ጎዳናንን ማመስገን ቀርቶ፤ ተቃዋሚው ለውይይት ሕዝብ ጠርቶ ሆቴል ሲከራይ፤ እንዲሁም ቴዲ አፍሮ የመሳሰሉ ታላላቅ ዜጎች ለሙዚቃ ምረቃ /አዳራሽ/ ሲከራዩ የሚታገደውን ታሪክ ነው ምስጋና ይገባዋል ለኢሕአዴግ (ወያኔ) የሚለን። ስለ ልደቱ እዚህ ላቁም፡ብዙ ሄድኩኝ።

ሁለተኛው እና አስገራሚው ጸሃፊው ያነሳው ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‘አማራ የለም” መፈክር እና መከራከያ ነው።

እርግጠኛ ነኝ ይህ ያሰለቻችሁ ወገኖች እንዳላችሁ አምናለሁ። በዘመነ ውቤ የደነቆረ “በውቤ አምላክ” እያለ ይጮሃል የሚባል የትግሬዎች አባባል አለ። አንድ ዘፈን እየዘፈኑ ያውም “የሚደብር” “አማራ የለም አሉ ፕሮፌሰር መስፍን” የሚለው።

እንደገና ወደ አሰለቸን መከራከያ እንግባ “ሳንወድ!!”።

ጸሃፊው እንዲህ ይላል።

“አጥብቀን ማስገንዘብ የምንፈልገው ነገር መደራጀት መብት መሆኑን ብንቀበልም፤ የአማራን ድርጅት ፈጥረን ለኢትዮጵያ አንድነት እንታገላለን የሚለውን ገለፃ፥ ከራሣችን ቁስል የተማርን በመሆኑ አናምንምና አታላግጡብን። ይሄ ከመለስ ዶክትሪን ይቃረናል። የአማራ ብሄርን የፈጠረውና ብሔርተኝነቱንም ያጠናከረው፥ ለኤርትራውያን አገር ሠጥቶ ኢትዮጵያን እንደነሣቸው ሁሉ፥ ለአማራም ክልል ሠጥቶት ከኢትዮጵያን ሊነቅለው ፈልጎ ነው።”

አያችሁ ማሾፍ ማለት? አማራን ለማዳን እራሳቸውን ለመከላከል የተደራጁትን ነው “አታላግጡብን” የሚለው። አንባቢዎቼ- ሌሎቻችሁ በዚህ ግፉበት ስለዚህ ሰውዬ መተቸት ምርር ስላለኝ ከመግፋት ላቁም እና ስለ ፕሮፌሰር መስፍን አማራ የለም እያለ የሚደግፋቸውን አባባሉን እንቀጥል እና ልዝጋ።

ጸሐፊው አማራ የሚባል የለም ያሉትን የፕሮፌሰሩን ንግግር ሲደግፍ ፤ ሳይታወቀው ልክ ፕሮፌሰሩ ሳይታወቃቸው እንዳዳለጣቸውና መልስ ያጡበት ንግግራቸውና ጹሑፋቸው (ወደኋላ እናያለን) እንደገና እሱ አማራ የሚባል መኖሩን ሳይታወቀው ድንገት ሲያምን እንዲህ ይላል፡ “አማራነት ወንጀል እንዳልሆነው ሁሉ” በማለት አማራ የሚባል እንዳለ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ምላሱ አዳልጦት አማራነት የሚባል እንዳለ ነግሮናል። አማራ ከሌለ አማራነት ቃሉም ስነሉቦናውም እራሱ ከየት ይፈለሰፋል? ይገርማል!

ስለ ፕሮፌሰሩ እና መለስ ዜናዊ እንዲህ ይላል፤-

<<“በዘር ዘር መለከፍ (የወዲ ዜናዊ-መንግድ-መለከፍ) መለስ ዜናዊ ከታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፥ ፕሮፈሠር መሥፍን ጋር ባደረገው የመጀመሪያም የመጨረሻ ውይይት፥ ፕሮፈሠር “የአማራ ብሔርተኝነት የለም ምርምር አድርጌ ነው እዚህ የደረስኩት ግን አንተ ልትፈጥረው ትችል ይሆናል።” ብለውት ነበር። መለስ አላዋቂነቱን ለመደበቅ በዕለቱ ቢዘላብድም የፕሮፌሠርን ምክር ለምን ክፉ ዓላማ ሊጠቀምበት እንደሚችል እያሰላሰለ ነው ከዛ መድረክ የተሰናበተው። ከውይይታቸው በሁዋላ፥ ብዙም አልቆየ “የአማራ ብሔርተኝነት ይጠንክር!” የሚል መፈክር በየአደባባዩ እንዲሠቀል ተደረገ።”>>

አያችሁልኝ የኛ ምሁራን/የጻሀፊው/ ትንታኔ? መለስ ዜናዊ ከደደቢት በረሃ ሲነሳ አማራን ለማጥፋት እንዳልተነሳና፤ አማራው በሽግግሩ ወቅት ሲጨፈጨፍ፤ሲባረር ““የአማራ ብሔርተኝነት ይጠንክር!” የሚል መፈክር በየአደባባዩ እንዲሠቀል ተደረገ።” ሲል የአማራዎችን ቁጭት፤ ንዴት እና ትውስታ “በብሔረተኛነት” የሚወነጅሉ እንዲህ የመሳሰሉ በክህደትና በግብዝነት የሚጽፉ በክህደት የሰከሩ በአማራ ማሕበረሰብ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል “በየቁንድፍቱ ገደል” ህጻንት ሲታረዱና ሲገፈተሩ ፤ አማራው ገበሬና ሰራተኛ የሚከላከልለት አጥቶ እራሱን ለመከላከል ሲጥር፤ በሽግግሩ ወቅት የወረደው “ምጽአተ አማራ” አስፈሪ እልቂት ማስታወሱ እራሱ ይዘገንናል፤ ያስጨንቃል፤ ያስፈራል። እንዲያም ሆኖ ዛሬም እራሱን እንዳይከላከል አማራ “ብሔረተኛ” ሆኗል እያሉ የሚከሱ ሰዎች ‘መጽሐፍ ቅዱስ/ቁርዓን’ ይዘው ተምበርክክው የአማራን ሕዝብ እናቶችና አባቶች ‘ይቅርታ መጠየቅ’ አላባቸው።

የደብረብርሃን፤ የወልቃይት አማራዎች ስብሰባና እሮሮ በወያኔ ሹማምንት ላይ በየአዳራሹ እስከዛሬ ድረስ ምን እያሉ እንደተናገሩ ለጸሃፊው እንዲያየው በዩ-ቱብ የተለጠፈውን “እየኖርን ነው ወይስ አያኗኗርን?’ የሚለውን እንዲመለከት እጋብዘዋለ። ምጽአተ አማራ የሚለው ሞረሽ ወገኔ ያሳተመው መጽሀፍም እንድያነበው እጋብዘዋለሁ። ቢያንስ ኦሮሞዎች እንኳ ¾ ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ምድር ባለቤቶች ናችሁ ተብለው ተሰጥቷቸዋል። አማራው የነበረቺውን ትንሽየው “ክልል (?)” ከወሎም ከጎንደርም ለም መሬቶች ተቆርሰው ለሱዳን፤ለትግሬዎች፤ለጉምዞች…. መኖሪያና ምርት ባብቀያ ተድረጓል። እንዴት ነው ሁሉም አንድ ነው የተጨፈጨፉት የሚባል ቋንቋ? አልገባኝም እኔ! ይህ ፍትህ አትቶ ኩፉኛ የተጨፈጨፈን ሕዝብ እሮሮ አሳንሶ ማየት አቁሙ!

ያሰለቸን የሞኞች ማጣቀሻ ክርክር የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አማራ የለም ወደ እሚለው ልሂድና ልደምድም።

ጸሃፊው እንዲህ ይላል፦

መለስ ዜናዊ ከታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ፥ ፕሮፈሠር መሥፍን ጋር ባደረገው የመጀመሪያም የመጨረሻ ውይይት፥ ፕሮፉሰሩ “የአማራ ብሔርተኝነት የለም ምርምር አድርጌ ነው እዚህ የደረስኩት ግን አንተ ልትፈጥረው ትችል ይሆናል።” ብለውት ነበር።” ይለናል።

ለዚህ አሰልቺና ደካማ መከራከሪያ የሚሆን መልስ በሞረሽ ሊቀመንበር በክቡር አቶ ተክሌ የሻው የቀረበውን ልጥቀስ።

-አቶ ተክሌ የሻው ፕሮፌሰር መስፍን ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ የጻፉትን ጥቅስ መነሻ ያደረጉትን ልነሳ፡

<<ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደማርያም፦ «ሥልጣን፣ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካዊ ምርጫ» በሚል ርዕስ በ2003 ባሳተሙት መጽሐፈዎ ገጽ 120 ላይ እንዲህ ብለዋል። «ኅዳር 1951 ዓም ከአጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ባለሥልጣኖች ባሰራጨሁት የጥናት ጽሑፍ ስለኦጋዴን የሚከተለውን ብየ ነበር። «በጠቅላላው የአማሮቹና የሱማሌዎቹን ግንኙነት ላስተዋለው፣ አማራዎቹ የሚያሳዩት የበላይነት መንፈስና በሱማሌዎቹ ላይ ያላቸው ንቀት፤ ሱማሌዎቹ በበኩላቸው ያላቸው ኩራት በአማራዎቹ ንቀት እየተነካባቸው የሚሰማቸው ስሜት በአንዴ ይታወቃል። “ቆሻሻ ሱማሌ“በያለበት የሚሰማ ነው። በዕድሜም ሆነ በክብር ከፍ ያሉትን ሱማሌዎች እርሰዎ እያለ የሚያነጋግራቸው በቁጥር ነው።—እንደዚህ ዓይነቱ የሌለውን የአማራ የበላይነትና የሱማሌ የበታችነት በግልጽም በድብቅም የሚያሳይ መንፈስ የሱማሌዎቹን ልብ በጣም እንደሚያሞክረው የሚያጠራጥር አይደለም። ሱማሌዎቹ ልክ እንደአማራዎቹ መሆናቸውን ሁሉ የተገነዘቡት አይመስሉም፤ ሱማሌዎቹም ሁሉ የሚውቁት አይደለም።» ………………………………………………>> ( መስፍን ወ/ማርያም «ሥልጣን፣ ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካዊ ምርጫ» በሚል ርዕስ በ2003 ባሳተሙት መጽሐፈዎ ገጽ 120)

አቶ ተክሌ እንዳሉት አማራ የሚባል ካልነበረ <<አማራዎች የሚያሳዩት በላይነት መንፈስና ሶማሌዎች ላይ ያላቸው ንቀት……>> እያሉ አማራ ከሌለ ‘ፕሮፌሰር መስፍን’ ከየት አግኝተውት ነው “አማራ” የሚባል ነገድ እየጠቀሱ መጽሐፋቸው ላይ የወነጀሉት? ውንጀላው እኮ ልክ እንደ ጣሊያኖቹ እና ጭንቅላቱ በማርክሲዝም የተበወዘው “ፌክ ኢትዮጵያ እና አማራ ሱፕረማሲ የሚለውን” እንደ ዋለልኝ መኮንን የመሳሰሉት ጸረ አማራዎች…….. ከሶማሌዎች ጋር ያናክሱት እንዳይበቃ እርስዎ ደግሞ ያውም በታሪክ የማይለቅ በመጽሐፍ ውስጥ ጽፈው እኮ ነው ክቡር ፕሮፌሰር ሆይ ተጨማሪ ዱላ አቀባይ የሆኑት!!!!!!! ምን እሚሉት ወንጀልና ክፋት ነው?

ታዲያ አማራ ከሌለ በመጽሐፎ አማራ እያሉ ለመጻፍ የበቁት ከየት ፈልስፈውት ነው? አሁን አማራው በገፍ እየተገደለ ባለበት ጊዜ እውን ከአንድ ምሁር የሚጠበቅ ነው? አማራው ብትር በበዛበት ሰዓት መወንጀሉ ጥቅሙ ምንድ ነው? በአማራው ሕብረተሰብ ላይ ያነጣጠረ የተቀነባባረ ጥቃት ልክ አንደ እነ “ታምራት ላይኔ” ንግግር ለዛሬው ግፍ የእርስዎ ምስክርነት ተጨማሪ ብትር አላቀበልኩም ሊሉ ይችላሉ? ለመሆኑ አማራ የሚለው ከየት አመጡት አማራ የለም ካሉ? መልሱን እርስዎም አማራ መኖሩን እያወቁ ‘ለክፋት መጠቀሚያ ሲሆን ብቻ *አለ* የሚሉ እርስዎ እና የእርስዎ ትምህርት ቀስመው አማራ የለም የሚሉ ተከራካሪዎች መልስ እንዲሰጡኝ እጠብቃለሁ። አበቃሁ። የኼ በስሜት የሚንጋጋው ጀሌ እንዴት ማዳን እንደሚቻል ለኔ ግራ ገብቶኛል።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ getachre@aol.com