ከባህር ዳሩ የኦህዴድና ብአዴን ውይይት ጀርባ የተደበቁ እውነታዎችና ስጋቶች!

Print Friendly, PDF & Email

(አያሌው መንበር)

በባህር ዳር የኦሮሞ ባህል ማዕከል ግንባታ ለማከናወን ከመፍቀድና ኦሮምኛን ለማስተማር ከመወሰን በፊት ቅድሚያ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ አማራዎች መብት ሊከበር ይገባል!!

በመንግስት የCSA 2007 መረጃ መሰረት ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ኦሮሞዎች በአማራ ክልል ውስጥ ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሰሞኑን በተደረገው ስብሰባ ከ250 በላይ ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በኦሮሚፋ እንደሚማሩ ተረጋግጧል።የራሳቸው የአስተዳደር ምክር ቤትና አመራርም አላቸው።

የብሄረሰብ ዞኑን መቀመጫውን ከሚሴ ላይ ያደረገው የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ባህሉን እና ቋንቋውን እንዲንከባከብ ሁሉ በጀት ከአማራ ክልል ይበጀትለታል። ይህ እውነታ አማራ ክልል አለ።

በጥቅል ግምት መረጃ ከ15 ሚሊዮን በላይ አማራ ከክልሉ ውጭ እንደሚኖሩ ይገመታል። ከእነዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮን ገደማ በኦሮሚያ ይኖራሉ። እነዚህን በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማራዎችን ስንመለከት የራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ታሪክ የሚያሳድጉበትና የሚንከባከቡበት የአስተዳደር ስርዓት አልተዘረጋም። በጀትም አይበጀትላቸውም።አንድም የአማራ “የብሄረሰብ” ዞን አልያም ወረዳ አልተቋቋመም።

አማራ ከቀሪው ህዝብ ቀንሶ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ኦሮሞዎች ልዩ አስተዳደርና በጀት ሲበጅት ኦሮሚያ ይህንን ከአስር ሚሊዮን በላይ አማራ ሊደግፍ የሚችል ልዩ የአስተዳደር ስርዓትና በጀት አይመድብም። እንዲያውም አማራዎች በሀገራቸው እንደ መጤና ሰፋሪ እየተቆጠሩ ሀብት ንብረታቸው ይቀማል፣ ይቃጠላል፣ ይሳደዳሉ፣ የስነ ልቦና ጫና ይደርስባቸዋል፣ የራሳቸው አስተዳደር ዞን ወይም ወረዳ ስለሌላቸው ለማን አቤት እንደሚሉም አያውቁም። ከበደኖው እስከ ሰሞኑ ኢሊባቡር ያለውን ማንሳት ይቻላል። የደብረዘይና ናዝሬት አማራዎች እና ከሁለቱም ብሄር የተወለዱ ወገኖች የሚደርስባቸውን የስራ ቅጥር ማግለልና መድሎ የሚያውቅ ያውቀዋል። በጥቅሉ ወደ ህግ ሲሄዱ በቋንቋቸውም አማርኛ እንኳን አይዳኙም። ይህ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አብዛኛው ቦታ ያለ እውነታ ነው።

እናም ሰሞኑን ወደ ባህር ዳር ያቀኑት የኦህዴድ አመራሮችና “ከህዝብ ተወከሉ” የተባሉት አባገዳዎች በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሲወያዩ ተመልክተናል። ውይይቱን ማንም ያዘጋጀው ማን መልካም ጎኑን መውሰድ ጥሩ ነው። ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ብዙ ተነግሯል።

ሆኖም እዚህ መደረክ ላይ ብዙ ይነሳሉ ብየ የጠበቅኳቸው ጉዳዮች ሳይነሱ ተለባብሰው ቀርተዋል።በአንፃሩ ያልጠበቅኳቸው ጉዳዮችን ዘግይቸ ሰምቻለው። ብዙ ካስገረመኝ ውስጥ ኦህዴድ የአማራን ፀጥታ አለማመኑና ሆቴሎች ሳይቀር በኦሮሚያ ፖሊሶችና ልዩ ሀይል መጠበቃቸው ግርምትን አጭሮብኛል።አቫንቲ ሆቴልን ማንሳት ይቻላል። ከተማዋ በርካታ የኦሮሚያ ፖሊሶች ይታዩ እንደነበር በፎቶም ሳይቀር ደርሶን ነበር። ይህ ትርጉሙ የአማራን ልዩ ሀይልና ፖሊስ አለማመን አልያም የተሻለ ሀይል አለን የሚል መልዕክት ይኖረዋል። ይህ ለደህንነታቸው የበለጠ እፎይታም ስጋትም ይፈጥራል ብየ እገምታለው። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የመጣው የፀጥታ ሀይል ቦዲ ጋርድ ሳይሆን ሙሉ ስኳድ ነው። በበጎው ስንመለከተው ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ለኦህዴድና ኦሮሞ ህዝብ ይቆማል የአማራ ግን የህወሃትን ቀጥተኛ ትዕዝዛ ስለሚያስፈፅም ምናልባት ህወሃት አደጋ ሊያደርስ ቢያቅድ (በእርግጥም ታቅዶ ነበር ይባላል) የአማራ ፖሊሥ የአደጋው ተባባሪ ወይም ጉልበት አልባ ይሆናል ከሚል ይመስለኛል። ለማንኛውም ግን ምዕራብ ዕዝ ከጎኑ በሚገኝ ከተማ ፖሊስ ከናዝሬት ማምጣት ትርጉሙ ሌላ ነው።

ሁለተኛውና ያልጠበቅኩት ነገር የኦሮሞ ባህል ማዕከልን በባህር ዳር ለመገንባት የተደረገው የቦታ ርክክብ ነው።በዚህ ላይ በቂ መረጃ ስላልነበረኝ ዝምታን መርጨ የሰነበትኩ የነበረ ቢሆንም ዘግይቶ ግን ይህም ተረጋግጧል። ለማ መገርሳ ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቦታ ተረክቧል ተብሏል። የሀምሳ ሚሊዮን የአማራ ህዝብ ባህል ማዕከል የሌለው አማራ ክልል ለግማሽ ሚሊዮን ኦሮሞ የባህል ማዕከል ግንባታ ለማከናወን መሞከር በኦሮሞ አስተዳደር ቅኝ እንግዛችሁ ከማለት አይተናነስ። በሌላ በኩል አማራው ታሪክ የለውም ወይም እንክብካቤ አይሻም የሚል ፖለቲካዊ ትርጓሜ ይሰጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተዋልዶና ተጋብቶ የሚኖረው የበርካታ ታሪክና ባህል ባለቤቱ አማራስ በዛው አካባቢ የራሱ ባህል ማዕከል ግንባታን ለማከናወን ቃል ተገብቷል ወይ? ሀላፊነት የወሰደ ወገን አለ ወይ? የሚል ወሳኝ ጥያቄም ያስነሳል።

በኦሮሚያ ክልል አማራው እንኳን ባህሉን ለማክበር የሚያስችል አሰራር ስርዓት ሊዘረጋለት ቀርቶ ሲወጣ ሲገባ እንዲሸማቀቅ “አያቶችህ ጡት ቆርጠዋል” እየተባለ በውሸት ታሪክ የጥላቻ ሀውልት ተገንብቶበት ለመኖር እንኳን እየተሳቀቀ ባለበት በዚህ ወቅት በቀየው የኦሮሞው ባህል ማዕከል ሊገነባ ነው ሲባል የሚደርስበትን የስነ ልቦና ስብራትም ይህ ውሳኔ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም። እናም የኦሮሞን ባህል ማዕከል ባህር ዳር ላይ ከመገንባት በፊት የጥላቻ ሀውልት ማፍረሱ ሊቀድም ይገባል፤ እንዲሁም አቻ የአማራ ባህል ማዕከል ግንባታም በናዝሬት ሊከናወን ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። የህዝብ ለህዝብ ውይይትና አቻ ድርድር ከሆነ መፍትሄው ለመብለጥ መሮጥ ሳይሆን በእኩልነት እና ፍትሃዊነት ለመጠቀመ መሻት ነው።

ሶስተኛው ጉዳይ እና ገና ያልተረጋገጠው “ኦሮምኛን በአማራ ክልል ለማስተማር” ተነሳ እና ቃል ተገባ የተባለው ጉዳይ ነው።የአንድን ሀገር ቋንቋ ማወቅ ጥቅሙ ለህዝቡ ቢሆንም ከ80 ሚሊዮን በላይ ተናጋሪ ያለው አማርኛን ከ10ኛ ክፍል በላይ ማንም እንዳይማረው የከለከለ መንግስት፣ ከ15 ሚሊዮን በላይ አማራዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት እድላቸው ተነፍጎ፣ በሌላ ቋንቋ እንዲማሩና አስተርጉመው እንዲመጡ እየተገደዱ ባሉበት ሁኔታ ከ30 ሚሊዮን በላይ አማራ በሚኖርበት ክልል ውስጥ የሚኖርን ህዝብ ኦሮምኛ ተማር ማለትም በህዝብ ላይ ሌላ ሸክም መጨመር ነው። ሌላኛው ይህ ጉዳይ ይሁን ቢባል እንኳን ኦሮምኛን አሁን አዲስ መጤ በሚባለው ፊደል ነው ወይስ ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት በነበረው?የሚማሩት የሚለውም አልተመለሰም። ይህ መጀመሪያ ሊጤን፣ህዝቡ ሊወያይበትና ምሁራን አስተያየት ሊሰጡበት የሚገባና ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ነው።

አራተኛው የአማራ ክልል ለአማራ ህዝብ ኦሮምኛን ከማስተማር በፊት አገውኛ፣ ግዕዝን እና የመሳሰሉ አማራዊ ቋንቋዎችን ማስተማር አይቀድም ወይ? የሚለውም ምላሽ አላገኝም። እኔ እንደ አንድ የአማራ ወጣት ከኦሮምኛ በፊት የእኔን ቀደምት ታሪክ ለማጥናትና አብረውኝ ካሉት ወንድሞቸ ጋር የምግባባበትን አገውኛና/ህምጠኛ እና መሰል ቋንቋን መማርን እመርጣለው። እናም መጀመሪያ ይህ ሊታሰብበት ይገባል። የዚህ ቋንቋ ፊደል አማርኛ መሆኑና ልሳኑም ቀላል መሆኑ ይህ ለአማራ ህፃናት ብዙ አይከብዳቸውም። ይህ ማለት ኦሮምኛ አይሰጥ ማለት አይደለም። ከኦሮምኛ በፊት አገውኛ ይቅደም። ኦሮምኛ ከመታሰቡ በፊት አማርኛ ላይ የተጣለው አገር አቀፍ ማዕቀብ ይነሳ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማራዎች መብት ይከበር ከሚል ቀናነት የመነጨ ሀሳብ ነው። አማርኛ ከታሪካዊና ከነባራዊ አንፃር የመላ ኢትዮጵያ ቋንቋ ነው። ይህ የፖለቲካ መደለያና መደራደሪያ ሳይሆን የህዝብ ሀብት ነው።ይህንን ቋንቋ የመንከባከብ ሀላፊነት የሁሉም ሊሆን ይገባል።

እናም ሲጠቃለል፥

1. የሰሞኑ ውይይት ላይ ስለ ኦሮሞ ባህል ማእከልና ኦሮምኛ ቋንቋ የተወሰነው ስህተት ነው።

2. ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማራዎች ጥያቄ አልተዳሰሰም፤ልዩ ትኩረትም ይሻል

3. ከፍቅር ቃላት በላይ መሬት የነካ ተግባር ስራ ይሻል ማለት ነው። ቃል የሚገባውም በሰላም ስለሚኖሩት ኦሮሞዎች ሳይሆን በስጋት ውስጥ ስለሚኖሩት አማራዎች ሊሆን ይገባል።

መልካም ጊዜ።