የታሪካዊ አገር ህልዉና ምንድን ነዉ?

Print Friendly, PDF & Email

(ተስፋዬ ደምመላሽ)  

(To read the article in PDF, click here)

ይህ ርዕስ ያነሳዉን እምብዛም ያልተለመደ ግን መሠረታዊ የአገር መኖር/አለመኖር ጥያቄ በኢትዮጵያ አገባቡ በይበልጥ ትኩረት እንደሚከተለዉ መቅረጽ ይቻላል። የአገራችን ብዙሃን ነገዳዊ/ባህላዊ ማህበረሰቦች በጥርቅም ብቻ ሙሉ አገር ስላልነበሩ፣ ዛሬም ስላልሆኑ፣ የጋራ ብሔራዊ ሕይወታቸዉ እምን ላይ ነዉ? በቅርቡና በቀጥታ ተጨባጭ ከሆኑ የአገራዊነት መገለጫዎች (ለምሳሌ ከመሬት ወይም ከግዛታዊ ሉአላዊነት) ባሻገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ህላዌ የሚገለጸዉ እንዴት ነዉ?

ጥያቄዎቹ ራሳቸዉ፣ ማለትም ገና ወደ መልሳቸዉ ሳንሄድ፣ አንድ ዋና ግንዛቤ ይጠቁማሉ። ይኸዉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የወል ብሔራዊ ሕይወት ከነገድ ማህበረሰቦችና አካባቢዎች የቁጥር ድምር ያለፈና ጭብጥ ሁኔታዎችንም ተሻጋሪ መሆኑን ነዉ። እንደምገነዘበዉ፣ በኢትዮጵያዊነት የጋራ ብሔራዊ ሕይወት አለን ማለት ህብረተሰባዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ለዉጥና እድገት እያኪያሄድንም ቢሆን፣ ብዙሃንነታችንን ትልቅ ዋጋ ሰጥተን እያከበርንም ቢሆን፣ እንደ ሕዝብ ራሳችንን በአንድነትና በሉአላዊነት የመጠበቅና የማንቀሳቀስ እዉንም እምቅም አቅም አለን ማለት ነዉ።

የአገራዊ ህልዉናችን መገለጫ እንግዲህ የአገሪቱ አካላት የሆኑ ማህበረሰቦችን ልዩነቶች አምኖ መቀበል ብቻ ወይም ማንነቶቻቸዉን በተናጠልም ሆነ በድምር ማረጋገጥ ወይም ደግሞ በየአካባቢዎቻቸዉ ተወስኖ ብቻ የወያኔን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መታገል አንዳለሆነ ብዙዎቻችን እናዉቃለን። ሌላ ነገር፣ ማለትም አካላቱን ይበልጥ አገናኝቶና አስተባብሮ በአገራዊ አንድነት የሚያንቀሳቅስ ነገር ያስፈልጋል። ግን ይህ አገራዊ ነገር በቅጩ ምንድን ነዉ? ማለትም ከታሪካዊ የማህበረሰቦች ትስስር ወይም ከወቅታዊ የፖለቲካ ስልት፣ አመራርና ትግል ባሻገር።
ለዚህ ወሰብሰብ ያለ ጥያቄ ቀላልና ዝግጁ መልስ የለኝም። ሆኖም ለመልሱ በመጠኑም ቢሆን አስተዋጽዎ ያደርጋሉ ብዬ የምገምታቸዉን ጥቂት ሃሳቦች እዚህ ባጭሩ ላቅርብ። ጉዳዩን ትንሽ ቀለል አድርጐ ለመጨበጥ አገራዊ ህልዉናን ከሰዉ ሕይወት (ከመኖር/አለመኖር) ጋር አመሳስሎ ማየት ይረዳል።

የአንድን ሰዉ በሕይወት መኖር የምንገለጸዉ የሥጋዊ ሰዉኑቱን የተለያዩ ክፍሎች ወይም ሥርዓቶች (እንበል የመተንፈሻ፣ የስሜት ሕዋሳት፣ የደም ዝዉዉር አካላቱን) በመዘርዘር አይደለም። የነዚህ አካላት ሥራዎች በአንጻር ልዩ የሆነ ሥርዓታዊነት ቢኖራቸዉም ለሰዉዬዉ ሕይወት የሚሰጡት በተናጠል አሠራራቸዉ እንዳልሆነ እናዉቃለን። ግለሰቡ በሕይወት መኖሩ ዝምብሎ የተለያዩ የሰዉነት ክፍሎቹ ድምር ሳይሆን የአካላቱ ኅብረተ ህላዌ ወይም መረባዊ አንድነት ነዉ። የሰዉነት ክፍሎቹ መገናኘት፣ መናበብ፣ ተጽዕኖ መለዋወጥና መደጋገፍ ዉጤት ነዉ። በዚህ መልክ የሥጋ አካላትን ግንኙነቶችና ትስስሮች ጠቅላላ መረብ መረዳት ለሰዉ ሕይወት ግንዛቤያችን ቁልፍ ነዉ።

የአገር ህልዉናንም፣ ማለትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሕይወት፣ ከዝህ ምስስል አንጻር ማየቱ ይጠማል። የአገሪቱ አካላት የሆኑት ማህበረሰቦች እንደያካባቢ ሁኔታዎቻቸዉ ባንፃር የየቅል የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የነገዳዊ ማንነት ልዩነቶችን ያንጸባርቃሉ። ነገር ግን የሚጋሩት አገራዊ ህልዉና ምንድነዉ ብለን ስንጠይቅ ወይም ስንፈልግ የምናገኘዉ ጥልቅ ታሪካዊ መሠረት ያለዉ ከማንኛዉም አገር ተለይቶ ባህላዊ ብዙሃንነትንም አንድነትንም ያካተተ ኢትዮጵያዊ ማንነት ነዉ።

ይህ ብሔራዊ ራስነት በታሪካዊ ስልጣኔዉና በዘመናዊ እድገቱ እንከን የለሽ ባይሆንም የተለያዩ ማህበረሰባዊና አካባባዊ ግብአቶችን (አካላትን) በሂደት ያቀራረበ፣ ያገናኘ፣ ያዛመደና አንድ ያደረገ ነዉ። ስለዚህ ግብአቶቹ በግንኙነታቸዉ፣ በትስስራቸዉና በተጽዕኖ ልዉዉጣቸዉ ያዳበሩትን ሙሉ አገራዊ ሕይወት ሳያዩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ህልዉና ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ጥርቅም ወይም ድምር ጋር እኩል አድርጐ መረዳት በጥልቅ የተሳሳተ ግንዛቤ ነዉ። ዛሬ አገሪቱ ካለችበት አስጊ የመኖር/ያለመኖር አኳኋን አንጻር ስናየዉ ግንዛቤዉ አደገኛም ነዉ። አደገኛነቱ ለአንድነታችን ብቻ ሳይሆን ለአካባባዊና ባህላዊ ማህበረሰቦች ደህንነትም ጭምር ነዉ።

ሕይወት ያለዉ ነገር ሁሉ ሊሞት ስለሚችል የሰዉና የአገር መኖር ምስስሉ የአለመኖር ሁኔታንም እንዲሁ ለማየት ይረዳናል። አንድ ሰዉ ሲሞት ከሃይማኖታዊ እምነት ተነስተን ነፍሱ ከሥጋዉ ተለየች እንላለን። በቅርቡ ያረፈ ግለሰብ ሥጋዊ ሰዉነት ልክ በሕይወቱ ሳለ የነበረዉ አምሳል አለዉ፣ ግን ግለሰቡ ሕያዉ አይደለም። ስለዚህ ተጨባጭ ሰዉነቱ (አንድነቱ) ብዙ ሳይቆይ ይፈርሳል፤ አካላቱ ይለያያሉ። እንዳልነበረ ይሆናል። የሰዉ ልጅ ሕይወት እንግዲህ የቁሳዊ/ሥጋዊ ንጥረ ነገሮችን ጥርቅም ያለፈ ምንጭ ወይም ምንነት አለዉ ማለት ነዉ።

ምንነቱ ከሥጋዊ ሰዉነት በፍጹም የተለየ ነዉ ከሚል ጥብቅ ሃይማኖታዊ አመኔታ በተገለለ ላላ ያለ አቀራረብም ቢሆን “ነፍስ” ወይም “መንፈስ”፣ በተለይ ደግሞ “ሃይል” (“energy”) ሊባል የሚችል ነዉ። ሕይወት ያለዉ ፍጡር ሁሉ ራሱን (ማንነቱን) አደራጅቶ ለመኖርና በቀጣይነት ለመጠበቅ የሃይል ፍሰት ያስፈልገዋል፤ የለት ተለት ኑሮዉ እዚህ ሕይወት ሰጪ ፍሰት ዉስጥ መሰካት አለበት።

የህልዉናዉ አንቀሳቃሽ ከሆነ ዉስጣዊና አካባባዊ ሃይል ከተለየ ወይም ከራቀ ራሱን ለቀዉስና ለፍርሰት አደጋ ያጋልጣል። ሕይወቱ ጠፋ ማለት እንቅስቃሴዎቹን፣ ድርጊቶቹንና ባህሪዉን በአንድነት የሚነዳበትን ሃይል አጣ ማለት ነዉ። እንግዲህ የሰዉን ሕይወት መጥፋት ሁልጊዜ በቀጥታና ባንዳፍታ ከሥጋዊ አካሉ ፍርሰት ጋር እኩል አርጐ ማየት አካቶ ትክክል እንዳልሆነ እንረዳለን። ለመንፈስ ጥፋት መዳረግ ወይም የቁም ሞት መሞት እንዳለም አይዘነጋም።

ታሪካዊ ማንነት ባለዉ አገር ደረጃም እንዲሁ ነዉ። ኢትዮጵያ እንደ ዳር ድንበሯና የማህበረሰቦቿ ትስስር ያሉ በቀጥታና በቅርቡ ተጨባጭ ከሆኑ የመኖሯ/ያለመኖሯ መገለጫዎች ባሻገር መንፈሳዊ ኑሮን፣ አለማዊ እዉቀትንና ብሔራዊ ንቃተህሊናን ያካተተ ሕያዉ የራስነት ሃይል ያላት አገር ናት። ይህ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ ተላላፊ የሆነ ተንቀሳቃሽ አገራዊ ሃይል (kinetic national energy) ከዉስጥ ጠልቆ የሚሰማንና የምንኖረዉ ብሔራዊ ልምድ ዋና አካል ስለሆነ ከኢትዮጵያዊነት ጨርሶ ሊለይ የሚችል አይደለም።

ይሁን እንጂ ዛሬ አገራችን ጤና ተጓድሎባት የተዳከመችዉ፣ ለፍርሰት አደጋ የተጋለጠችዉ፣ ባመዛኙ ከዝህ ሕይወት ሰጪ ሃይሏ ወይም መንፈሷ ስለራቀች ነዉ። ይህ ሁኔታዋ በተለይ የአገሪቱን ምሁራን በተቆራኘዉ ግራ የሚያጋባ ያፍዝ ያደንዝዝ ይገለጻል። ማለትም በምሀራኑ የምሁራዊ ሃይልና ንቅናቄ እጦት ይከሰታል። በአገር አድን ትግሉ ከሃሳቦች አቅርቦት አኳያ በከፍተኛ ደረጃ የተማረዉ መደብ በሚያሳየዉ ቸልተኛነት ወይም ወደኋላ ማፈግፈግ ይታያል።

ብርቱዉ ጉዳይ እንግዲህ ኢትዮጵያ ከቁም ሞት እንድትድን፣ ለመላ ዜጐቿና ባህላዊ ማህበረሰቦቿ በሚበጅ መልክም ብሔራዊ ነፍስ እንድትዘራ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ነዉ። ይህ ሰፊና ወስብስብ ጥያቄ በተለያዩ ረድፎችና ደረጃዎች አከራካሪ ሊሆን ይችላል። በጉዳዩ አቀራረጽ ራሱ መስማማት ቀላል አይሆን ይሆናል። መፍትሔዉን ማግኘት ደግሞ ይበልጥ ያዳግታል።

ሆኖም በአብዮቱና ድህረ አብዮቱ ዘመን፣ በተለይ አሁን ባለንበት የዚያ ዘመን ተረፈ ዉጤቶችና ርዝራጅ ሃሳቦች ባልተለየዉ ጊዜ፣ የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችን ወደ ጥፋት የተመራባቸዉን መንገዶች ጠለቅ ብሎ በግልጽ መገንዘቡ ለመፍትሔ ፍለጋዉ ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ይመስለኛል። ከያዝናቸዉ የጥፋት ጐዳናዎች ዉስጥ በዋናነት የሚጠቀሰዉ መጠንም ጥልቀትም የለሽ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነዉ። የፖለቲካዉን አገር አሰናካይነት ባጭሩ በሦስት የተዛመዱ ዋና ዋና ገጽታዎቹ ማየት ይቻላል።

1. ፖለቲካዉ በቅጥ የለሽ ተስፋፊነት አገርን፣ ነገዶችንና ኅብተሰብን አጥለቅላቂነቱ፦

እንደ አገር ዛሬ የምንገኝበት አስከፊና አስጊ ሁኔታ ቅርብ ምክንያት ወይም ምንጭ እርግጥ የሕወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነዉ። ይሁን እንጂ ሁኔታዉን በሥርዓታዊ ጐንና ስፋቱ ስናየዉ ከጠቅላላ ተራማጅ የተባለ ፓርቲና ጐሣ ዘለል የፖለቲካ ባህል የመነጨ መሆኑ ምንም ያህል ስዉር አይደለም። ባህሉ በተማሪዉ ንቅናቄ ተጸንስሶ፣ በደርግና ዉያኔ “አብዮታዊ” አገዛዞችም በተቃዋሚ ወገኖችም አማካኝነት ከሞላ ጐደል ቀጣይ እንደሆነ ይታወቃል።

የፖለቲካ ባህሉ ዉስጣዊ ተቃርኖ ባለዉ አኪያሄድ ነዉ ለሕዝብ ምንም ተጠያቂነት የሌለዉ ፖለቲካ የሚያራምደዉ። በአንድ በኩል ፖለቲካን በፈላጭ ቆራጭነት አስፋፍቶና ከአገርና ሕዝብ በላይ ዋጋ ሰጥቶ በጅምላም በዝርዝርም ቀርጿል፣ አዋቅሯል። በዚህ መልክ አገራዊ ተቋማትን፣ ክፍለ ሃገራትንና ነገዳዊ ማህበረሰቦችን አጥለቅልቆ በመከፋፈል የአንድ ጠባብ ወገን ተቀጥላና ተገዥ አድርጓል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይኸዉ አኪያሄድ ፖለቲካ ራሱን በመርሃዊና ተቋማዊ ሃቀኝነት ጠብቆ የኢትዮጵያን ስቪል ህብረተሰብ አገልጋይ ሥርዓትና መሣሪያ እንዳይሆን ያደረገ ነዉ። ማለትም፣ ፖለቲካዉ ሁሉ ቦታ ሰርጐም ተሽሎክልኮም ስለሚገባ ይህ ነዉ የሚባል የራሱ ሃቀኛ ሕገመንግሥታዊ መሠረት የለዉም። ስለዚህ ባንፃር ነፃ ሆኖ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተፈላጊነትና ተቀባይነት ላላቸዉ የመስተዳደር እሴቶች፣ መርሆች፣ መብቶችና ፖሊሲዎች አፍላቂ ሊሆን አይችልም። ባጭሩ፣ ነባርና ወቅታዊ “አብዮታዊ” ፖለቲካ ተንሰራፍቶ ሁሉም ቦታ አለ፣ ግን በገድብ ወይም በበጐ ሥርዓታዊ እዉንነት የትም የለም።

አገር ጐጂዉ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር ባህል ብሔራዊ ሕይወታችንን ያቃወሰዉ እንግዲህ በጠባብ ወገንተኛ/ዘረኛ ይዘቱ ብቻ አይደለም። በተጨማሪ በለከት የለሽ ተስፋፊነቱም ነዉ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ዜጐችና ማህበረሰቦች ጉዳይ አለሁበት ማለቱ፣ ሁሉን የአገር እሴትና ጸጋ፣ የባህል ማህበረሰቦችን ብዙሃንነት ሳይቀር፣ አልሚም አጥፊም እኔ ነኝ ባይነቱ ነዉ።

2. በታሪክ ሂደት የዳበረ ተጨባጭ የአገር ህልዉናን በመካድ/በማጣጣል “አዲስ” ዘር ተኮር ኢትዮጵያ ትፈጠር ባይነቱ፦

የተለያዩ ፓርቲዎች፣ ስብስቦችና አገዛዞች ለአስርተ አመታት መነታረኪያ፣ መጠፋፊያና መለጣጠፊያ ያደረጉት “ተራማጅ” ፖለቲካ (በተለይ በወያኔ፣ በሻቢያና በኦነግ ቅጂዎቹ) የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችንን በጅምላ እንደ ችግር ያየ ነዉ።

አይቶም ኢትዮጵያዊ ንቃተ ህሊናን ወይም ብሔርተኝነትን አባይ (እዉን ያልሆነ፣ የሐሰት) ነዉ ብሎ የፈረጀ፣ የነገዶች ብሔርተኝነትን ግን ተጨባጭና እዉነተኛ አድርጐ ያየ መሆኑን እናዉቃለን። የዚህ ነባር ተራማጅ ተብዬ አስተሳሰብ ርዝራዥ በተወሰኑ አማራን እንደ ነገድ ከጥፋት እናድን የሚል ይፋ አላማ ባላቸዉ አንዳንድ አክትቪስት ግለሰቦች/ስብስቦች ዘንድ ለየት ባለ አገባብ ዛሬም ይንጸባረቃል።

በዚህ፣ በጐ መንፈስ ቢኖረዉም ባመዛኙ ከታክቲካዊነት ባላለፈ የትግል አኪያሄድ፣ ባንዳፍታና በቀጥታ ተጨባጭ የሆኑ የአገርና የዘር ሁኔታዎች ላይ ተቻኩሎ ማተኮር ብሔራዊ ወይም ነገዳዊ ህልዉናችንን በጥልቀትም ሆነ በሙሉ ሁኔታዉ ለመጨበጥ አይረዳንም። በአገርም ሆነ በነገድ ደረጃ ህልዉናችንን ለራስ አድን ትግል በስልታዊ አስተዉሎ ማሰማራትና ማንቀሳቀስ አያስችለንም።

በኢትዮጵያዊነታችንም ሆነ በአማራነታችን ሕይወታችንን ከጥፋት የምናተርፈዉ እንግዲህ በታሪካዊ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ግብአቶች ህንፀት በተሟላ ማንነታችን እንጂ ዝምብለን በጐሣዊ ነጠላነት ወይም ክምችት አይደለም። አገራዊ/ነገዳዊ ተጐጂነታችንና መከራችን ላይ በማተኮር ብቻ ህልዉናችንን ብንጨብጠዉ ራስ አድን ሃይል አፍላቂነቱን፣ ተንቀሳቃሽ መንፈሱንና ተነሳሽነቱን እናሳጣዋለን። ባጭሩ ሙሉ ወርድና ስፋቱን እንነሳዋለን። ይህን እያደረግን ኢትዮጵያን እንታደግ፣ አማራን ከጥፋት እናድን ብለን መጮሁ ሩቅ አይወስደንም።

እርግጥ አማራዉ በቀጥታ ከገጠመዉ የህልዉና አደጋ በአስፈላጊዉ መንገድና አቅም ሁሉ ተከላክሎ ራሱን ማዳን አለበት። ይህን ለማድረግ መደራጀት እንደሚያስፈልገዉም ግልጽ ይመስለኛል። ስለዚህ ፍሬ ነገሩ ማህበረሰቡ ራሱን ከጥፋት ያድን አያድን ወይም ይደራጅ አይደራጅ አደለም። አንድ ዋና ጉዳይ የራስ አድን ትግሉ ምን አይነት ነገዳዊ፣ አካባባዊና አገራዊ አደረጃጀት ይከተላል ነዉ። ሌላ፣ ተያያዥ፣ ጉዳይ ደግሞ እነዚህን የተለያዩ ግን በከፊል ተደራራቢ የሆኑ የትግል እርከኖች ቅንብር የሚሰጥ ስልትና ንቅናቄ ምን ይመስላል ነዉ።

እነዚህን አይነት ጥያቄዎች በማንሳትና ተገቢ ትንተናዎች በማቅረብ የአማራዉን ህልዉና ተጋድሎ በስልት ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገርና ዘላቂ አቅጣጫ ማስያዝ ይቻላል። በድፍኑ ማህበረሰቡ በነገዱ ይደራጅ፣ ድርጅት ጉልበት ይሆነዋል፣ ጥቃቶች መከላከል ያስችለዋል እያሉ መቀጠል ግን ምንም ያህል የሃሳብ ክብደት ማንሳት የማይጠይቅና ትግሉን በተለመደ ዝቅተኛ የማንነት ፖለቲካ እርከን የሚያቆይ ይመስለኛል። ትልቁ የአማራ ማህበረሰብ ለደህንነቱና መዳበሩ ተሟጋች ነን ከሚሉ ግልሰቦችና ድርጅቶች ከዚህ የተሻለ ጥብቅና ይገባዋል፤ ይጠብቃልም።

አለበለዚያ ከታክቲካዊ ደረጃ ምንም ያህል በማይልፍ የዋህ ድርጅታዊነትና ተግባራዊነት በተጠመዱ እንቅስቃሴዎች ተወስነን ነገዳዊም አገራዊም ህልዉናችንን እናራቁታለን። አዉቀንም ይሁን ሳናዉቅ፣ በጐዉን የማይመኙልንን የዉስጥም የዉጭም ሃይሎች (በተለይ የሕወሓትና የሻቢያን) አጀንዳ አስፈጻሚ በሆነ “አማራነት” እና “ኢትዮጵያዊነት” እንቀጥላለን። በአገር ጉዳዮች ዉስጥ የነዚህን ሃይሎች የበላይ አድራጊ ፈጣሪነት ተቀባይነታችንን እናራዝማለን። ይህ አኳኋን ግን የአማራንም ሆነ የኢትዮጵያን ሙሉ ማንነት አይመጥንም።

ሆኖም እዚህ ላይ የምንረዳዉ አንድ ነገር አለ። ይኸዉም በሙሉነቱ አገራዊ ሕይወታችን የወያኔና ሻቢያ አገዛዞችና የነሱ ተቀጥላ ወይም ተጓዳኝ የሆኑ ወገኖች አላማዎች ማሳደጃ መሣሪያ ሆኖ የማይዘልቅ መሆኑን ነዉ። እርግጥ አገዛዞቹና ተባባሪዎቻቸዉ በፉክክርም ሆነ በትብብር ኢትዮጵያዊነትን በኢትዮጵያዊነት ስም አማራን በአማራነት ስም በተወሰነ (ፖለቲካዊ፣ ድርጅታዊ፣ ጐሣዊ፣ ወይም ቁሳዊ) ጥቅም መከታተያነት ታሳቢ አድርገዉ ከመጠምዘዝ አይቦዝኑም። ማለትም፣ ምንም እንኳን በኢትዮጵያም በኤርትራም ወቅታዊ የህዝብ እንቅስቃሴዎች እንደሚያሳዩት ሁኔታዎች ከቁጥጥራቸዉ እየወጡ ቢሆንም።

በዚህ አይነት ጥምዘዛ አገራዊ ሕይወታችን በወያኔና ሻቢያ ትግሬዎች የመኖር/አለመኖር አደጋ እንደተቃጣበት አይካድም። ጥምዘዛዉ አንድነታችንን አስጊ ሁኔታ ላይ እንደጣለ፣ ለኢትዮጵያዊነታችንና ለአማራ ነገዳዊ ማንነታችን በተጐጅነት ስሜት፣ በብሶት፣ በጭንቀትና ሲበዛ ተከላካይ በሆነ አቋም የመመከት አዝማሚያ የጣለብን መሆኑ የምናስተባብለዉ ነገር አይደለም። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊነት ያሉ የሌሉ የፖለቲካም የጐሣም ስብስቦችና የዉጭ ደጋፊዎቻቸዉ እንዳሻቸዉ ጨርሰዉ ሊቆጣጠሩት ወይም ሊያጠፉት የማይችሉ የራሱ ልዩ ሃይልና ተጽእኖ አለዉ። አገራዊ ህልዉናችን ጥንትም ሆነ ላለፉት አራት አስርተ አመታት የዉጭም የዉስጥም ጠላቶች ኢላማ የነበረዉ በዚህ የተለየ እዉንም እምቅም ጉልበቱና ተጽእኖዉ ነዉ።

ይህን ሃይሉን አገር ወዳድ እትዮጵያዊያን በደል ተቀባይና ለራስ አዛኝ በሆነ አሉታዊ ስሜት ሳንገታ በሃሳብ፣ ስልትና እንቅስቃሴ አፍላቂነት የራስ አዳኝ ትግል ቅርጽና አቅጣጫ ማስያዝ ይኖርብናል። ሃይሉ በባህል ማኅበረሰቦች ማንነቶች ድምምር ወይም በብቸኛ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት መንገድ ተደራሽና ተግባራዊ አይሆንም። ተግባራዊ የሚሆነዉ በታሪካዊ ስፋትና ጥልቀቱ፣ በምንኖረዉ የጋራ ብሔራዊ ልምድ እቅፉ ብቻ ነዉ።

3. ፖለቲካዉ ሃሳብን ከአገር ህልዉና በማራቅ (በማቃረንም) ይዘት የለሽ ቀኖና ያደረገ መሆኑ፦

ትላልቅ ሃሳቦች (ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ የሕግ በላይነት ወዘተ) ከተጨባጭ ሁኔታችን ተነስተዉ ብሔራዊ ልምዳችንን ሊያሳድጉ፣ ሊለዉጡና ሊያሻሻሉ ይችላሉ። ማድረግ የማይችሉት ታሪካዊ የአገርነት ባህላችንን ክደዉ ወይም አጣጥለዉ በንጹህ (ምክንያታዊ) እሳቤ በተገኘ “ፖለቲካዊ ማህበረሰብነት” መተካት ነዉ። ሃሳቦች በታሪክ ሂደት ከዳበረ ኢትዮጵያዊነት አካቶ ሲለዩ ወይም ሲርቁ የአገር አንቀሳቃሽነት፣ ለዋጭነትና አሻሻይነት መሠረታቸዉን ያጣሉ።

ይህ እጦታቸዉ በተራዉ ደግሞ አለም አቅፍ ሃሳቦቹን ወደ ኢትዮጵያ መሬት የወረደ ጽንሳዊም ተጨባጭም ይዘት ይነሳቸዋል። ተግባራዊ የሚሆኑት ከእዉን እሳቤ፣ ክርክር፣ ድርድርና ስምምነት በራቀና ገዢዉ ቡድን በብቸኝነት በሚቆጣጠረዉ ፎርሙላዊ የፖለቲካ ቃላት ዝዉዉርና ግዑዝ “ሥነ ሥርዓት” (lifeless ritual ) እንደሆነ የምናዉቀዉ ነገር ነዉ።

የዚህ አኪያሄድ መሠረታዊ ችግር በሁለት ጐኖች ይታያል። በአንድ ጐን የሃሳብን ጥራትና ሃቀኝነት ያጠፋል፤ ሃሳብ በአንጻር ነፃ ሆኖ አገርና ሕዝብ አገልጋይና አሻሻይ እንዳይሆን ያደርጋል። በሌላ ጐኑ ደግሞ አስተሳሰባችንን ከምንኖረዉ አገራዊ ልምዳችንና ከኢትዮጵያ ማህበራዊ እዉነታዎች ጋር በቅጡ ማገናኘት አያስችለንም። እንዲያዉም የፖለቲካ ሃሳቦችን የጋራ ብሔራዊነታችን አካላት ከማድረግ ይልቅ በአምባገነናዊነት እላያችን ላይ የጫነ ነዉ። በዚህ መንገድ ፈላጭ ቆራጩ ገዢ ወገን የኢትዮጵያን ተጨባጭ አገራዊ እዉንነት አሟሟቶ እንዳሻዉ በሚጠመዝዘዉ የማያዛልቅ አስመሳይ “እዉነታ” የተካ እንደሆነ ምንም ያህል ስዉር አይደለም።

ማጠቃለል፣ ነገደ ብዙዉ የጋራ ብሔራዊ ሕይወታችን ወይም ማኅበራዊ ኑሯችን በተወሰነ ሳይንሳዊ የሆነ (የተባለ) አቀራረብ የሚገለጽ ቅርጽ ሊይዝ ይችላል። በተቻኮለ ወይም ገራገር በሆነ ተግባራዊነት (naïve realism) በቀጥታና ባንዳፍታ የሚከሰት “መሬት ላይ ያለ መረጃ” ወይም ነገር ሆኖ/ተብሎ ይታይም ይሆናል። ግን በዚህ መልክ ተከሳችነት ካለዉ ግልብ እዉንነት ባሻገር ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር በምንኖረዉ ልምድ (lived experience) የፈጠርነዉ ጥልቅ ብሔራዊ እዉነታ እንዳለም እንረዳለን።

ብሔራዊ ባህላችን እርግጥ እዉነታን በጠቅላላ ወይም በፍጹም መጨበጥ አያስችለንም። እወነታ በጠቅሉ እንደ አገር ከምንኖረዉ ልምድ የተለቀና ይበልጥ የተወሳሰበ ነዉ። ነገር ግን ልምዱ በታሪካዊ ምንጩና ሂደቱ፣ በባህላዊ ክንዉኖቹ፣ እንዲሁም ዘመናዊ ሃሳቦችን ባካተተ ንቃተ ህሊናዉና ተንቀሳቃሽነቱ የራሳችንን ተመሳሳይ የማይገኝለት ልዩ አገራዊ ሕይወት (እዉነታ) መፍጠር አስችሎናል።

ይህ ከዉስጥ የሚያንቀሳቅሰን፣ የምናምንበትና በንቃት ታሳቢ የምናደርገዉም አገራዊ ሕይወት በብሔራዊ ስሜትና ትረካ ካልቃኘናቸዉ ወይም በቀጥታና ባንዴ ከሚታዩን ተፈጥሯዊ ነገሮች የላቀ እዉነታ አለዉ። ለምሳሌ መሬት፣ ተራራዎች፣ የማኅበራዊና መንፈሳዊ ኑሯችን ተቋማት በቅርቡ ታዪነትን ወይም የላይ ላይ እዉንነትን አልፈዉ የኢትዮጵያዊነትን ረጅም ሥር የሰደደ ታሪካዊ ህላዌ፣ አገራዊ ሕይወታችንንና ማንነታችንን፣ ገላጮች ናቸዉ።

To reach the writer: tdemmellash@comcast.net