ህወሀት በሞተር ዘይት ቅየራ ላይ!

Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዱዓለም)

በመጀመሪያ የህወሀት መሰረታዊ ባህርይና አላማ የመለወጥ አዝማሚያ አላሳየም። ይሄውም ህወሀት የትግራይን ህዝብ ነጻ ለማውጣት የተመሰረተ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ገና ከጅምሩ የትግራይ ህዝብ ነጻ እንዲወጣ የተፈለገው ከኢትዮጵያ ኢምፔሪያሊስት መንግስት (አሁን የሌለ)፤ ከትግራይ ኢትዮጵያኒስት መሳፍንት (አሁን የሌሉ)፤ ከጨቋኟ የአማራ ብሄር እና የአማራው ነው ተብሎ ከታሰበው ኦሮቶዶክስ ሀይማኖት ነው። ህወሀት የትግራይን ህዝብ ከእነዚህ ወገኖች ነጻ ለማውጣት ሲያቅድ ዋና አላማው አድርጎት የተነሳው የትግራይን ሪፑብሊክ መመስረት ነበር። በጊዜው የኢትዮጵያኒስት ትግሬዎች ተጽእኖ በማየሉ እና ዋና አጋዣቸው የነበረው ሻዕብያ እናንተ ቅኝ ስላልተገዛችሁ ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የምትታገሉበት ምክንያት የለም፤ የእናንተ ብሄራዊ ጭቆና ስለሆነ ከብሄራዊ ጭቆና ነው ነጻ መውጣት ያለባችሁ፤ አለበለዛ የኤርትራን የቅኝ ተገዥነት ጥያቄና ትግል ታደበዝዛላችሁ የሚል አቋም ስለተያዘባቸው አቋማቸውን ለጊዜውም ቢሆን በሰነድ ደረጃ ለውጠዋል።

ሆኖም አቋማቸውን በሰነድ ደረጃ ቢቀይሩም የትግራይ ነጻ መንግስትነት አስተሳሰብ በአመራርና ታጋዮቹ ዘንድ ያልተጻፈ ህግ ሆኖ ቆይቷል። ያ ያልተጻፈ ህግም እስከአሁን ድረስ በልዩ ልዩ መንገዶች እየተንጸባረቀ ነው። በተለያዩ አለማቀፍ መስሪያ ቤቶችና ድረገጾች እውቅና እንዲያገኝ የተደረገው ካርታ፣ የአማራን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብቶች በትግራይ ሀብትነት ማስተዋወቅ የመሳሰሉት የ1967/8ቱ የተጻፈ ሰነድ ነገር ግን በኋላ የተቀየረ ሰነድ ሌላኛ የወረቀት ስራ መገለጫዎች ናቸው። ዞሮ ዞሮ ህወሀት ኢትዮጵያኒስት ትግሬዎችንና መሳፍንቶቻቸውን አጥፍቷል፤ በምትኩም ከትግሬነት እና ትግራዊነት ውጭ ሌላ አለም ያለ የማይመስለው ህዝብ መፍጠር ችሏል። የኢትዮጵያ ኢምፔሪያስት መንግስት ብሎ የከሰሰውን መንግስት ራሱ ተቆጣጥሮ ለትግራይ አጎብዳጅ መንግስት አድርጓል፤ የኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ቅርስ በመዝረፍ፣ ደህና አባቶችን በማጥፋት የአገዛዙ ጭካኔ ባራኪ በሆኑ ካድሬዎች ሞልቷል፤ በዚህመ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህዝባዊ ጫና ፈጣሪነት ባዶ አድርጓል። ይሄም ሁሉ ሆኖ ህወሀት የትግራይ ነጻ አውጭነት ስምና ግብሩን አልለወጠም። በኢትዮጵያ ውስጥ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣም ፍላጎት አላሳየም። አማራና የአማራ የሆነው ነገር ሁሉ ላይ ይዞት ከተነሳው እኩይ አላማ አንድ መስመር እንኳ ፈቀቅ የማለት አዝማሚያ አላሳየም።

“ታዲያ ምን ቀረ?” ከተባለ የትግራይ ህዝብ ገና ሙሉ በሙሉ ነጻ አልወጣም። የትግራይ ህዝብ ነጻ አልወጣም ማለትም ለመጨረሻው ነጻነት የሚያስፈልጉት ነገሮች ገና አልተሟሉም ማለት ነው። የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጣ የሚባለው ምን ምን ነገሮች ሲሟሉ ነው?

1) አማራ በስነህዝብ ብዛት አናሳ ቁጥር ሆኖ ለተስፋፊዋ ትግራይ ምንም አይነት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስጋት የማይሆንበት፤

2) ለኢትዮጵያ መልሶ አንድነት ግንባታ ሌላውን ህብረተሰብ ማስተባበር እንዳይችል ማህበራዊ መሰረት መናድና መሳሳት ሲረጋገጥ ናቸው።

3) አማራ አናሳ ቁጥር እንዲሆን የተለያዩ ስልቶችን መተግበር።

ከእነዚህም፡-

ሀ) የስነህዝብ ቅነሳ ፖሊሲ በአማራ “ክልል” በገፍ መተግበር፤

ለ) የጤና ጥበቃ ማሽቆልቆልና ቀላል ህመሞች ገዳይ ሆነው ህዝቡን እንዲቀንሱት ማድረግ፤

ሐ) በልዩ ልዩ ሰበቦች መግደል፤

መ) አማራን ከኢኮኖሚውና ፖለቲካዊ መድረክ ገለል በማድረግ ለድህነትና ስራ አጥነት ማጋለጥ እና በዚህም ሳቢያ በገፍ እንዲሰደድና የህዝብ ቁጥሩ እንዲመናመን ማድረግ፣

ሠ) ሌላ ክልሎች በሚል ማፈናቀልና መጨፍጨፍ በዛውም የህዝቡን ቁጥር መቀነስ፤

ረ) የዚህ ጥቅል ውጤትም (በተለይ በከተማው) የትዳር አጋር ምስረታን እድሜ በማራዘም የህዝቡ ቁጥር ላይ ቅነሳ እንዲያሳይ ማድረግ፤

ሰ) አማራ የሚኖርባቸውን ነባር ቦታዎች ወደትግራይ እና ሌላ ክልሎች ቀምቶ በመከለል በቀጥታ የህዝቡን ቁጥር የሚቀንስበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና የመሳሰሉት ናቸው።

4) አማራውን በሁሉም ብሄሮች የተጠላና ሁሉም ጦር የሚመዝበት ማድረግ። በዚህም አማራ ለነጻቱም ሆነ ለምንም አይነት ለውጥ እንደልቡ መንቀሳቀስ የማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ ማድረግ፤

5. ትግራይ በሀይልና ኢንዱስትሪ ራሷን የቻለች መሆን። ትግራይ ከራሷ የሐይል ምንጭ አመንጭታ የኢንዱስትሪ ምርትን ለማምረት የሚያስችል እድል የላትም። ስለሆነም አንድ ዘዴ መዘየድ አለበት። እርሱም ቤኒሻንጉል ጉምዝን (የጎጃም ክፍል መተከልን) ለብቻው በመከለል የአባይ ግድብን መገንባት እና ያንን አካባቢ የትግራይ አካል በማድረግ
ለወደፊቷ ትግራይ ጠቃሚ ግብአት ማግኘት፡-

ሀ) ከግድቡ የሚገኝን ሀይል ለትግራይ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት ማዋል።

ለ) ግድቡን ለጅኦ-ፖለቲካዊ አገልግሎት በማዋል ትግራይን በግብጽ፣ ሱዳን እና ኤርትራ ሞገስ ያላት አገር ማድረግ።

ሐ) በዚህ ግድብ ሰበብ ከሰሜን ሱዳን ጋር አማራን ድንበሩን መቁረጥ። የመተማን፣ የአርማጭሆን፣ የሁመራን መሬት ወደትግሬ መወሰድና የተቀረውም ለሱዳን መሰጠት እንዲሁም ቅማንትን እንደመተላለፊያ ኮሪዶር ለመጠቀም እየተሰራ ያለው ወደዚህ የሚያመራ ነው።

መ) በዚህ ኮሪዶርና በግድቡ ሳቢያ ትግራይን ከደቡብ ሱዳን ጋር አጋር አገር ማድረግ። በዚህም የአማራን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን የኦሮሞና የደቡብ ኢትዮጵያ ሁኔታዎች በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል። በደቡብ ሱዳን ውስጥ ትግል የሚደረግበትንም በር ይዘጋል።

እንግዲህ ከአንድ እስከ አምስት የተዘረዘሩትን ነገሮች ህወሀት አሁንም እየሰራ ነው። በእነዚህ አቋሞቹ ላይ ለውጥ አላሳየም። በእነዚህ አቋሞች ላይ ለውጥ አለማሳየቱ ደግሞ ህወሀት እቅዱን ለማሳካት ሌላ አካሄድ እየተከተለ ነው ማለት ነው። ዋና አቋሞቹን በተለያዩ ዘዴዎች ማስቀጠል። ህወሀት ላለመለወጡ ተጨማሪ ማስረጃዎች፡-

ሀ) የትግራይ ህዝብ በአማራ ላይ ለአርባ አመት የተጋተውን ጥላቻ በማጠናከር ላይ መሆኑ፤

ለ) በብሄሮች መካከል ግጭት የመፍጠር አዝማሚያው ጊዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ያለ መሆኑ

ሐ) ለፖለቲካዊ መድረክ ሙሉ በሙሉ ዝግ ሆኖ የግላጭ ጠብመንጃ አገዛዝ ማስፈኑ፤

መ) የትግራይ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተገነባለት የጥላቻ ግድግዳ በመፍረስ ፈንታ የበለጠ እንዲጠብቅ እየተደረገ መሆኑ፤

ሐ) የአማራን መሬቶች የወሰደውን አለተጠያቂነት ይዞ ለመቅረት እና ሌላም ለመውሰድ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ መሆኑ፤

መ) የአማራን ወጣት ያሰራውን በመፍታት ፋንታ በገፍ እያሰረና እየገደለ መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እንግዲህ ከላይ የተገለጸውን የህወሀት እቅድ ለማስፈጸም የኢትዮጵያን መንግስት ለረዥም ጊዜ በመቆጣጠር የትግራይን ወደአገርነት የሚያመራ መሰረተ ልማት መዘርጋት፣ አማራውን በተዘረዘረው መሰረት አናሳ ህዝብ ማድረግ፣ እና ትግራይ በአለም አቀፍ መድረክ እውቅና የምታገኝበትን መንገድ በኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ማካሄድ ዋና ዋና መሳሪያዎች ናቸው። ይሄ እንዲሆንም የኢትዮጵያን መንግስታዊ ስልጣን ለረዥም ጊዜ መቆጣጠር አለባቸው (በእነሱ ቋንቋ መቶ አመት የሚሉት)። ኢትዮጵያን ረዥም ጊዜ መግዛት እና የወደፊቷ ትግራይ ሪፑብሊክ ማብቀያ መደብ ለማድረግ ግን ሁለት ነገሮች በነበሩበት መቀጠል ነበረባቸው፡-

ሀ) አማራ ብሄረተኛ ሳይሆን፣ ሳይሰባሰብ ለመቶ አመት ተበታትኖና ተዳክሞ መቆየት አለበት፤

ለ) የኦሮሞ ህዝብ በየጊዜው የኩርፊያ ፖለቲካ ሰለባ በመሆን ለችግሩ ቀጥተኛ ተጠያቂ ያልሆኑ አማራና ነገስታቱን የተመለከቱ ተረቶች ላይ ተንጠላጥሎ መቆየት አለበት፤

እዚህ ላይ ህወሀቶች አንድ ያልታያቸው ሀቅ እንደነበር ግልጽ ነው። አማራ አሁን ባለበት ሁኔታ ወደብሄረተኛ እንቅስቃሴ ይገባል ብለው ያሰቡ አይመስልም። እነሱ እንደመሰላቸው አማራ የራሱን ፖለቲካዊ ግብ ይዞ ይነሳል፣ እንደ አማራ የፖለቲካ፣ የታሪካዊ መሬት ባለቤትነት፣ የማንነት እና መሰል ጥያቄ አሁን እያደረገ ባለው ሁኔታ ያነሳል ብለው አላሰቡም። እናም ለመቶ አመት ያቀዱት እቅድ ገና 25ኛው አመት ላይ እያለ ያልታሰበው የአማራነት እንቅስቃሴ በድንገት ከባድ ጥያቄዎችን አዝሎ ተነሳበት። አማራ ነኝ ማለት እንደሆነ ነገር ይቆጠር የነበረበት ጊዜ አብቅቶ አማራነትን መግለጽ ኩራት እየሆነ መጣ። ከዛም አልፎ ህዝቡ ግልጽ የሆነ የአማራነት ትግል ውስጥ ገባ። ህወሀት በህይወት ዘመኑ ሊመልሳቸው የማይቻለውን ጥያቄዎችም ያዘንብበት ያዘ። እናም ድንገተኛው የአማራነት መነሳሳት የህወሀትን ቀመር አዛባ። ህወሀት ቀድሞም ያላሰበው አደጋ ስለሆነ የአማራን ብሄረተኝነት የሚገታበት የተዘጋጀ ስልት ጠረጰየዛው ላይ አልነበረውም። ከዛም የተነሳ በዚህ ሶስት አመት ውስጥ ቀመሩ ሁሉ ተምታቶበት ውሉን ስቶ ይገኛል። በዚህ በአማራነት እንቅስቃሴ የተነሳም ይሄ ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ ጨምድዶ ይዞ የትግራይን ዘላቂ ግብ ማሳካት የሚለው ነገር ችግር ላይ ወደቀ።

የአማራው መነሳት ለኦሮሞው ትግልም ጉልበትን ሰጠው። በዚህም የተነሳ የኦሮሞ ትግል ህወሀት ቀድሞ ካቀደው አድማስ ተሻግሮ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆነ። ለምን ቢባል ኦሮሞ በአንድ ሰው እድሜ የሚለካ ብሄረተኝነት ውስጥ ያለፈ ህዝብ ነው። በዚህም አንድን ነገር ከሆነ አቅጣጫ ሰምቶ ትእዛዝ ለመፈጸም በነቂስ መውጣት ይችላል። እስካሁን የታየውም ያ ነው። ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በአሁኑ ሰአት መሪ ወይም ተቆጣጣሪ ድርጅቶች እንኳ ባይኖሩት እንዲሁ ለህወሀት በቀላሉ የሚገዛ ሊሆን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የኦሮሞ ህዝብ ትግል በአጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ግቡን ለመቆናጠጥ አቅም ቢያጥረው እንኳ የህወሀት የገንዘብ ምንጭነቱን ንብረት በማውደምና የሰጋት ክልል በማድረግ ህወሀት ላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ማድረስ ችሏል። ያለ ኢኮኖሚያዊ ሀይል ደግሞ የህወሀት ፖለቲካ ምውት መሆኑ ይታወቃል። እናም የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ የድርጅት አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ የህዝብ አጀንዳ ሆኗል። ይሄ ደግሞ በቀላሉ የሚሸነፍ አይመስልም። ባጭሩ የዚህ አማራና ኦሮሞ ሁኔታ ድምር ውጤት የህወሀትን እድሜ ከታቀደው በ75 አመት እንዲመሽበት አደረገው።

እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የሞተር ዘይት ለውጥ የማድረጉ አስፈላጊነት። ህወሀት እስካሁን በመጣበት መንገድ ለመቀጠል አይችልም። ፈጥኖ መሽቶበታል። ፖለቲካዊ ሞገሱ ተገፏል። የደህንነትና የወታደር አቅሙ ግን አልተነካም። ያንን የሚነካ ተገዳዳሪ ሀይልም የለም። የደህንነት ሀይሉና ወታደራዊ ተቋሙ በአሁኑ ሰአት ሊንኮታኮት የሚችለው በኢኮኖሚና ፖለቲካው መስክ አክሳሪ የሆነው የህዝብ ተከታታይ ቁጣና አልፎ አልፎ አመጽ ሲመታው ነው። ይሄ ደግሞ በሁለቱ የህወሀት የኢኮኖሚ መሰረት በሆኑት ክልሎች ማለትም በአማራና በኦሮሞ ለአመት ተኩል በላይ ቀጥሏል። የኦሮሞው በግላጭ እየገፋ ሲሆን የአማራ ብሄረተኝነት ደግሞ የጀማሪነት ስህተቶቹን በማረም ውስጥ ለውስጥ ዝግጅት እያደረገ፣ አማራዊ ማንነቱን እያጸና እና በየእለቱ እየተጠናከረ ነው የመጣው። ይሄም አንድ ቀን ማለዳ ህወሀትን ቁርስ ሊያደርገው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። በተለይ የአማራ ብሄረተኝነት ከህዝቡ ሀቀኛ በደልና ግፍ እንዲሁም የህልውና ስጋት ላይ የተወለደ በመሆኑ ጥያቄው እጅግ መሰረታዊ፣ ሀይሉ አስፈሪ እና ታሪካዊ ሁነቱም መሰረት የሚሰጠው ለህወሀት ከባድ አደጋ ነው።

እናም ህወሀት ረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ እንዲቆይ ይሄ የአማራነት እንቅስቃሴ በምንም ስልት መቀልበስ አለበት። ይሄን ለመቀልበስ ደግሞ ህወሀት የአንድነት ዘማሪ መሆን አለበት። ይሄንን በማድረጉም ሁለት ነገሮችን ይለውጣል፡-

1) አማራ ጠቅላይ-አግላይ፣ ብዝሀነትን የማይቀበል፣ ኢትዮጵያዊነትን ሌላው ላይ አስገድዶ የሚጭን፣ ትምክህተኛ እየተባለ በኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነቱ ሲመታ ቆይቷል። ሆኖም ከሶስት አመት ወዲህ ወደአማራ ብሄረተኝነት እንቅስቃሴ መግባቱ እነዚህን የመመቻ ካርዶች ሁሉ አቃጥሎ ህወሀትን ባዶ ጥፍሮቹን የሚያወናጨፍ ምክንያት አልባ አሮጌ ጅብ አድርጎታል።

2) በዚህም ምክንያት ህወሀት የይስሙላ አንድነት ዘማሪ መሆን አለበት። ይሄንን በማድረጉም፡-

ሀ) አንድነት ሲባል ልቡ ወከክ የሚለው አማራ ተታሎ ብሄረተኝነቱን ይተውልኝና እንዳቀድኩት ተጨማሪ 75 አመታት ገዝቸ የትግራይን ቋሚ እቅድ አሳካለሁ ብሎ ያስባል።

ለ) ህወሀት የይስሙላው አንድነት ፊታውራሪ በመሆን አማራን በጸረ አንድነትና በብሄረተኛነት (ጠባብ ብሄረተኝነትም ሊለው ይችላል) ሰበብ መወንጀልና መምታት ይችላል። በዚህ በአዲሱ ስሌት ህወሀት ራሱን የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ ወኪል አድርጎ በመቁጠር አማራን ጸረ አንድነት (ኦሮሞንምጭም) አድርጎ ፈርጆ ካሁን ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ይመታል፤ ወይም የመምቻ ምክንያት ያበጃል ማለት ነው። በዚህም አንድ ፖለቲካዊ የመታገያ ካርድ አገኘ ማለት ነው።

የእነዚህ የሁለቱ ድምር ውጤትም የአማራ ብሄረተኝነት ተገትቶ እና ህወሀት አዲስ የአንድነት ዘማሪ ነጠላ ተከናንቦ ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ በመግዛት የተለመውን የታላቋ ትግራይ ግብ እውን ያደርጋል ማለት ነው።
———

የሞተር ዘይት ለውጡ የአሁን ጊዜ መገለጫዎች

የአንድነት መዝሙሩን ካልተጠበቀ አቅጣጫ ማሰማት። ለዚህ ያው እንግዲህ ሁሉም እንደሚያውቀው ከኦህዴድ አካባቢ እንዲዘመር ማድረግ ነበር፤ እየሆነ ያለውም ያው ነው። በዚህም ብአዴንን አጋር አድርጎ የይምሰል አንድነት መገንባት። እየሆነ ያለው ማለት ነው። አሁን በብአዴን እና በኦህዴድ መካከል እየተደረገ ያለውን እውነተኛ ሂደት ለመረዳት አስቸጋሪ የሚመስሉ ነገሮች አሉ። ምናልባት በምእራባዊያን ዘንድ ታማኝ ወኪል የሆነው ህወሀት ከአዛዦቹ ጥገናዊ ለውጥ እንዲያደርግ ተመክሮ ይሆናል። ይሄም ከራሱ ከህወሀት የረዥም ጊዜ እቅድ ጋር በተሳሰረ መልኩ የሚፈጸም ስለሆነ አስቸጋሪ አይደለም። በዛም አለ በዚህ ህወሀት ምን አልባት ኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር ለማስቀመጥ አስቦ ሊሆን ይችላል። ያ ቀጣይ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር ደግሞ በአማራ ህዝብና (በህወሀቱ ስሪት ብአዴን) ተአማኒነት እንዲያገኝ ያስፈልጋል። ለዛ ደግሞ ብቸኛው መንገድ የአንድነት መዝሙር ቀድሞ መዘመር ነው። ካሁኑ እንዲህ አይነት ዝግጅት ከተደረገ ደግሞ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር በሚሾምበት ጊዜ በአማራም በኦሮሞም ያለው ህዝባዊ ግለት ይበርዳል ተብሎ ታስቦ ይሆናል።

አንድ ነገር መሰመር ያለበት ግን የኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር ቢመጣም ከሀይለማርያም የተለየ ሚና እንደማይኖረው ነው። ምክንያቱም እንደ ደኢህዴን ሁሉ ኦህዴድ በመላው ኢትዮጵያም ሆነ በአለም ዙሪያ አይደለም ከህወሀት የሚወዳደር ጫማው ስር የሚጠጋ የደህንነት መዋቅር የለውም፤ ይሄንን የህወሀትን መረብ አልፎ ሊዘረጋም አይችልም። ህወሀት የደህንነት እና የጦር ሰራዊት መሰረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ውስጥ የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታ ለኦህዴድ ቢሰጥ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። በአንጻሩ የኦሮሞን ተቃውሞ ዝም ለማሰኘት እና የአማራውን ወገን ለማዘናጋት ይጠቅማል። ያ ደግሞ ለህወሀት ከሞተር ዘይት ለውጥ በኋላ ተጨማሪ እድሜን እና ራሱን ለማስተካከል ታካይ እድልን ከመፍጠር የዘለለ ሚና የለውመ። ስለሆነም አሁንም ዋናው ተዋናይ ህወሀት ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው። እንዲያውም ህወሀት የኦህዴድን ሰው ጠቅላይ ሚንስትር በማድረግ ከቻለ ትልቅ የፖለቲካ ስኬት ነው።

በመጨረሻም መዘንጋት የሌለበት ሀቅ ሸክላ ሰሪ በሸክላው ላይ ሙሉ ስልጣን ያለው መሆኑ ነው። እንዴት እንደሰራኸው የምታውቀውን ሸክላ እንዴት እንደምታሰራውና እንዴት እንደምትሰብረው ሙሉ እውቀቱ አለህ። የኦህዴድም ሆነ የብአዴን ባለስልጣናት አይደለም ፖለቲካዊ አካሄዳቸው እስትንፋሳቸው ራሱ በህወሀት የደህንነት አካል መዳፍ ስር ነው። (ለቀልድ ያህል፡- ለመሆኑ ለማ መገርሳን ይዞ ባህር ዳር የሄደው አውሮፕላን አብራሪ ኦህዴድ ይሆን?) በተጨማሪም ገዱ አንዳርጋቸው እና የተቀሩት ክበቦቹ ለአማራ ህዝብ ጥቅም ሊቆሙ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ቢፈልጉ እንኳ አይችሉም። ግጨውን ተደብቆ በአሳቻ ሰአት ፈርሞ የሰጠ ብአዴን መቸም ያለ ህወሀት ፈቃድ ከኦህዴድ ጋር አስረሽ ምችው ሊደነክር እንደማይችል መገመት ከባድ አይደለም።

እናም አሁን እየሆነ ያለው በህወሀት ቀማሪነት የሚካሄድ የህወሀት “ግራንድ ዲዛይን” ነው፤ እየሆነ ካለው ሁሉ አንዳች ስንኳ ከህወሀት እቅድና ፈቃድ ውጭ የሆነ ነገር የለም ለማለት ያስደፍራል። ይህ የግል አስተያየት ትክክል ነው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ስህተት ያለባቸው አረፍተ ነገሮችን ያካተተ የማይሆንበት እድልም የለም። በዛም አለ በዚህ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ለአሁኑ ግን ህወሀት የሞተር ዘይት እየቀየረ ነው ብሎ መደምደም የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነን። ምናልባት ጥልቅ ተሀድሶ የተባለው እውነተኛ ባህርይም አሁን እየተካሄ ያለው ሊሆን ይችላል……