የወያኔ የሞት- ሽረት ካርድ !

Print Friendly, PDF & Email

የወያኔ የሞት- ሽረት ካርድ! pdf

ከጥንስሱ፣ ወያኔ ጠባብ ብሔርተኛ ድርጅት ነው። ተስፋፊ ነው። ዘረኛም ነው። ወያኔ ከጅምሩ ለትግራይ ሕዝብ ነፃነት የቆመ ድርጅት ሆኖ ሳለ፣በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ ተቀናቃኝ እንደሌለው ሲረዳ፣ከጠባቧ ትግራይ ይልቅ፤ ሊቀናቀነው የሚችል ኃይል እስከሌለ ድረስ፣ በታላቋ ኢትዮጵያ ስም ትግራይን የማልማት፤ የትግራይን ወጣት ትውልድ በትግራይ የበላይነትና በሁለንተናዊ መልኩ ለትግራይ የተፈጠረ ዜጋ አድርጎ ማሳደግ ዓላማው አድርጎ የተነሳ ድርጅት ነው።

ከዚያም አንፃር ላለፉት 27 ዓመታት የበላይነቱን በማስፈን በኢትዮጵያ ሕዝብ እና ንብረት ላይ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ የዘለቀ ድርጅት መሆን በቅቶዋል።

ይህን ዓላማው ዕውን ለማድረግም የተከተለው ሥልት በአገሪቱ በሕዝባቸው። ብዛት ከፍተኛ የሆኑትን ዐማራና ኦሮሞን ላይገናኙና ዓይንህ ለአፈር ተባብለው በአጥፊና ጠፊነት እንዲሰለፉ ማድረግ ነበር፣

ለዚህም የሀሰት ድርሳኑን በሻዕቢያው ሰላይ በተስፋዬ ገብረአብ አማክኝነት «የቡርቃ ዝምታ» የተሰኘ ድርሳን አስደርሶ፣ «አኖሌ» የተሰኘ መጭዎቹ የዐማራና የኦሮሞ ትውልዶች ጎን ለጎን መቆም እንዳይችሉ የሚያደርግ፣ «ዐማራው የኦሮሞ እናቶችን ጡት ቆርጧል የሚል ሀውልት» አቆመ።

ህዝቦችም ከመፈቃቀርና ተከባብረው ከመኖር ይልቅ መነጣጠልና መናቆር የዘወትር ሥራቸው አድርገው እንዲይዙት የሚያስችል የአስተዳደር ሥርዓት ዘረጋ። በዚህም የሥልጣኔ ተፎካካሪና አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ዐማራውንና ኦሮሞውን አይጥና ድመት በማድረግ ዘላለማዊ ጠላቶች እንዲሆኑ ብዙ ርቀት የተጓዘ የሤራ ድር ማድራቱን ማንም የሚያውቀው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ዐማራውን በዳይ ኦሮሞውን ተበዳይ በማስመሰልና ተበደለ ከሚለው ጎን በመቆም፣ ዐማራውን «ነፍጠኛ፣ ጨቋኝ፣ በዝባዥና ትምክህተኛ» የሚሉ የማጥላያ ስሞችን በመስጠት፣ ከቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጠለው። በአገሪቱም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ብሎም የጥቅም ተቋዳሽ እንዳይሆን በግልጽ ከለከለው። ያ አልበቃ ቢለው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሠርቶ የመኖር መብቱን ገፈፈው። ሀብት ንብረቱንም በመቀማት የዘር ማጥፉት ዘመቻ ከፈተበት።

የኢትዮጵያን ሕዝብ በአሠፋፈር፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በማኅበራዊ ፣ ሥነልቦና እና በታሪክ ያለውን ቁርኝትና አንድነት በቅጡ ለመረመረ ሰው ለትግራይ ሕዝብ ከማናቸው ኢትዮጵያዊ ዐማራው የቀረበ ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ መልኩ አንድና ልዩነት የሌለው መሆኑን ይረዳል።

ከሁሉም በላይ የጎንደርና የወሎ ዐማራ ለትግራይ ሕዝብ ከቅርበት ባሻገር የተጋባ፣ የተዋለደና አንድ ከመሆን አልፎ በሃይማኖቱ፣ በባሕሉ፣ በቋንቋው፣ በአለባበሱና፣ አመጋገቡ፣ ወዘተ ልዩነት አለው ሊባል የማይችል ህዝብ ነው።

ወያኔ ይህን ለመሰለና ዘመን ላስቆጠረ የሕዝብ አብሮነትና ትስስር ሳይጨነቅ፣ ዐማራው ለሥልጣኔ አስጊ ነው ከሚል ፍርሃቻ ተነስቶ ዝምድናውን እንኳን ቢንቅ ፤ «ከሩቅ ዘመድ፣ የቅርብ ጎረቤት መሻሉን» ባለመረዳት፣ ይልቁንም ዐማራውን በጠላትነት ፈረጀው ። በብዙ መልኩ ከሚርቀው የኦሮሞ ብሔር ጋር በፀረ-ዐማራነት ላይ የመሠረተ የፖለቲካ ጋብቻ ቀለበት አሰረ። ላለፉት ሃያ ሰባት የወያኔ አገዛዝ ዘመናት ዐማራውን በእርዳ ተራዳ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሰለባ አደረገው።

በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዐማራ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ አደረገ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዐማራ በራሱ የወያኔ ፓርላማ ተብየው የስታተስቲክ ባለሥልጣን የነበሩት ወይዘሮ፣ የ1999 ምርጫ ውጤትን ይፋ ሲያደርጉ ባቀረቡበት ሪፓርት መጥፋቱን አረጋግጠዋል።

ወያኔ ዐማራውን አግሎና በጠላትነን ፈርጆ ከኦሮሞ ጋር የተጎዳኘው ያለምክንያት አልነበረም። ዐማራው በተለይም ጎንደሬው፣ ለወያኔ ሰጥ ለጥ ብሎ ሊገዛለት የማይችልና እንዲያውም ለታላቋ ትግራይ ህልሙ ያለመሳካት ከፍተኛ መሰናክል የሚሆንበት እንደሆነ በመረዳቱ ነው። ስለሆነም በዐማራው ለዘመናት ተጨቁነዋል ወይም ተጨቁነናል የሚሉትን ብሔር/ ብሔረሰቦች በማደራጀትና አመራር በመስጠት በዐማራው ላይ ክንዳቸውን ማንሳት እንዳለባቸው ሰበከ። በተግባር መፈፅሙንም አረጋገጠ።

ከሁሉም በላይ «ላለቅስ ስል፣ ጪስ ወጋኝ» የሆነላቸውን የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች፣ ጠላትህ ዐማራው ነው፣ ልታጠፋው ይገባል በሚል በወታደራዊ ኃይል የታገዘ መጠነ ሠፊ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ በስፋት አሰራጨ።

ይህም ለዘመናት ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ እንደ ውኃሃና ወተት አንድ የሆኑትን ህዝቦች በግድ አንዱን ምረጥ እያለ ለዘመናት ተከባብሮ ፣ ተሳስቦ ለመኖር የፈጠረውን ግንኙነት ማፍረስ ተያያዘው። ያ ብቻ ሳይሆን በዐማራው ላይ ዘግናኝ የዕልቂት ዘመቻ እንዲከፈት አደረገ የበደኖ፣ አየርባጉጉ፣ የወተር፣ የአሰቦት ገዳም፣ በጥቅሉ በሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በከፋ፣ በኢሉባቡርና መሰል ክፍለሀገሮች በዐማራው ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የዚህ ዘረኛ ቅስቀሳ ውጤት መሆኑን ማንም የሚረሳው አይሆንም።

«ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለም እንደ አለቀሰ ይኖራል “ የሚሉት አባቶቻችን ብህል ዕውን ሆኖ፣ የጎንደርና የወሎ ከትግራይ ጋር በመልከዓምድር አቀማመጥ ኩታ ገጠም በመሆናቸው የሁለቱን ክፍለሀገር ለም ወረዳዎችና አውራጃዎች በመንጠቅ በየትኛውም ጊዜ የትግራይ አካል ሆነው የማያውቁትን ከትግራይ ጋር ቀላቀለ።

የጥንት አያት ቅድመ አያቶቹ ይኖሩበት ከነበረው መሬት ጎንደሬውንና ወሎየውን በማፈናቀል አገር አልባ አደረጋቸው ፣ ለችግር ዳረጋቸው ፣ አጋለጣቸው። ይህን አድራጎታቸውን የተቃወሙ ዐማሮችን በገፍ ገድለዋል ፣ አሰድደዋል የቀረውንም አምክነውታል።

ወያኔ ለብሔር/ ብሔረሰብ ዕኩልነት ቆሜአለሁ፣ ሁሉም በራሱ ልጆች ይተዳደራል ፣ ይዳኛል፣ እያለ ቢለፍም፣ አማራው ከሰፊው የአባቶቹ አገር ተገልሎ የበሬ ግንባር በምታክል ክልል ተወስኖ እናገኘዋለን። የሚገዛውም ቢሆን በኤርትራዊ በረከት፣ ስምዖን በትግሬዎቹ ሕላዊ ዮሴፍ፣ ካሣ ተክለብርሃን፣ ታደሰ ጥንቅሹ ወዘተ ነው።

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተባለው ድርጅት፣ ከላይ በተጠቀሱት ሰዎች የሚመራና ከኅብረ-ብሔራዊነት ወደ አንድ ብሔርተኛ ድርጅት በጠፍ ጨረቃ የተቀየረ የወያኔ ወዶ ገባ ፍጡሮች ስብስብ ነው። በነኝሁ አድርባዮች አማካኝነት፣ ታላቁን የትግራይ ረፐብሊክ የመመሥረትና የመስፋፋት አጀንዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የተመቻቸ መደላድል ሆነውለት ኖረዋል።

በዚህ የመስፋፋት ተግባሩም ከጎንደር ሠቲትን፣ ፀለምትን ወልቃይት ጠገዴንና ከፊል ታች አርማጭሆን ከወሎም ራያና ቆቦን ወደ ትግራይ እንዲጠቃለሉ በዐማራው ስም ፈቀዱ።

በብአዴን ጋሻ ጃግሬነትም በሌሎች ክልሎች ተግባራዊ ያልሆነ፣ ዐማራን ግን ጃርት እንደበላው ዱባ ብትክትክ ብሎ ርስ በራሱ እንዲፋጅ ለማድረግ፣ ከወሎ የከምሲ ዞን ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን፣ ከጎጃም አዊ ዞን ብሎ አገውኛ ተናጋሪዎችም፣ ጎንደር ውስጥ የቅማንት ዞን ብሎ ቅማንትኛን አደራጅቶ የዐማራው ጠላቶች ሆነው እንዲሰለፉ አድርጉዋቸል። የጎጃም አካል የሆነውን መተከልን ለቤንሻጉል-ጉምዝ ብለው ለከለሉት ክክል ተላልፎ እንዲሰጥ ፈቅደዋል።

የብአዴን ጉዳይ በዚህም አልተገታም። ከሰሜን ዞን የጎንደር ከተማን የትግራይ አካል ለማድረግ፣ ብሎም ጎንደር የሚባልን ክፍለ ሀገር ከኢትዮጵያ ካርታ እንዲጠፋ ለማድረግ የወያኔ የረዥም ጊዜ እቅዱ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጎንደር ከሱዳን ጋር የነበረውን ደንበርተኝነት አግዶ የትግራይ ወሰንተኛ እንዲሆን የታቀደው የታላቋ ትግራይ ግዛት መስፋፋት ዕቅድ በመጠናቀቅም ላይ ይገኛል።

ይህ ሕዝብን የናቀና ይሉኝታ ያጣ ስግብግብ እርምጃ ግፉ ከልክ በማለፉ ድርጊቱ እየተፈጸመበት ያለው ሕዝብ ዝምታውን ሰብሮ፣ ድምፁን ማሰማት እንዲጀምር ምክንያት ሆኖዋአል።

የሕዝቡም አፈናው አሻፈረኝ ብሎ ድምፅን ለማሰማት አደባባይ ላይ መውጣት ጀመረ። አፈናውን ጥሶና ገልብጦ በወጣበት ሰዓት ያሰማ የነበረው ድምፅ እንደ መረዋ ከአድምስ አድማስ በማስተጋባት ፣ የወያኔን የአገዛዝና የአፈና ሀይል እሳት እንደገባ ጅማት እያኮማተረው ይገኛል።

በጎንደር ሕዝብ ላይ ወያኔ የፈጸመው የግፍ ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ በፀረ-ኢትዮጵያ ፀረ-ዐማራ ኃይሎች ተደግፎና ተበራቶ ለሥልጣን የበቃውን የወያኔ መንጋ መግቢ መውጫ እያሳጣ ትግሉን ወደፊት ቀጥሉዋል።

እንቅስቃሴውም መጀመሪያ ጎንደር፣ ከዚያ ጎጃም፣ ሸዋና ወሎ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ሄደ። ሕዝባዊ እንቢተኝነቱም ፣ ራሱን በራሱ እያደራጀና በጎበዝ አለቆች እየተመራ አካባቢውን ከወያኔ አገዛዝ ነፃ እያወጣ መጥቶአል
። በሰሞኑ የሚታየው አገር አቀፍ ሕዝባዊ እንቢተኝነትና የአገዛዙ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናት አገር ጥለው መኮብለል ትግሉ ከምን ጊዜውም በላይ እየተጠናከረ መምጣት ያረጋገጠው ጉዳይ ነው።

ይህ ከጎንደር ያስተጋባው የአንድነት ጥሪ፣በኦሮሞ ሕዝብ ዘነድ ሙሉ ተቀባይነት በማግኘቱ ፣የኦሮሞ ወጣቶች«ጣና ኬኛ» በማለት በአገዛዙ ሆን ተብሎ ጣናን እንዲያደርቅ ዕድል የተሰጠውን እንቦጭ የተባለ የውኃ ጠር ለማጥፋት ጎጃም ገብተዋል።

ሟቹ መለስ ዜናዊ «የዐማራና የኦሮሞ ህዝቦች መልሰው ከተገናኙ ያን ጊዜ ሕወሓት ያልቅላታል፤ ድርጅቴ ያንጊዜ ያከትምላታል፤ ከማለቱም በላይ የሕወሓት ጥንካሬና የበላይነት መቀጠል በሁለቱ ነገዶች መፋታት ላይ የተመሠረተ ነው» ያለው ያለ ምክንያት እንደሆነ ዛሬ ደርሶ እያየነው ነው።

ዐማራውና ኦሮሞው በአንድነት ከቆሙ ወያኔ ከባሕር የወጣ ዓሣ ከመሆን የማያልፍ መሆኑን እኛ ሳንሆን፣ «ባለራዕዩ መለስ» አስቀድሞ የተናገረው ጉዳይ ነው። ይህ የዐማራና የኦሮሞ ብሄሮች አንድነት የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ፍፃሜ ከማብሰሩ በላይ በተጓዳኝ፣ ሰላሟና አንድነቷ የተረጋገጣባት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ብቸኛው ፍቱን መድኃኒት መሆኑን አሁን በተጨባጭ እያየን ነው።

ይህ እንቅስቃሴ ያሰጋቸው የወያኔ ጋሻ ጃግሬ የነበሩት የኦሕዴድ ሹም አባ ዱላ ገመዳና የአፈና መዋቅሩ መሪ ተዋንያን የነበሩት ጄኔራሎች ሥልጣን ከመልቀቅ እስከ ክዳት የደረሱ ርምጃዎችን እየወሰዱ እንዳሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሻ ምክንያቱ እስካሁን ምን እንደሆነ በግልጽ አይታወቅ እንጂ፣ የወያኔው ቀኝ እጅ የነበረው በረከት ስምኦን ፣ዐማራውን ለውርደት፣ ለስደት፣ ለሞትና ለሥቃይ ከዳረገ በኃዋላ የሥራ መልቀቂያውን አስገብቶ የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች አንዱ በሆነው ቨርጂኒያ እንደገባ ያልተረጋገጡ ምንጮች የሚያናፍሱት ጉዳይ ነው።

የነዚህ የወያኔ ፍጡሮች ከኃላፊነት መልቀቅና መክዳት፣ ሌላ ስውር ደባ ከሌለው በስተቀር የወሰዱት እርምጃ እሰየው ባያስብል መልካም ዜና እንደሆነ ይሰማናል። ነገሩን ግራ የሚያጋባ የሚያደርገው፣ ግን ወያኔ በባሕሪው እንኳን እንደዚህ ተገፍቶ ገደል ጠርዝ ላይ በቆመበተ ሰዓት ይቅርና በተረጋጋበት ጊዜ እንኳ ልዩነት የማስተናገድ ባህል የሌለው መሆኑ እየታወቀ፣ ዛሬ ከሥልጣን እንለቃለን፣ ኃላፊነቱን ተረከቡን የሚሉትን ጥያቄዎች በትዕግሥት የማስተናገዱ ጉዳይ እንዴት ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው።

ይሄ ሁሉ የሚሆነውም በአገዛዙ ቴሌቮዥንና ሬዲዎ፣ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁት አባ ዱላ ገመዳ ታይቶ በማያውቅ ድፍረት «በሕዝቤና በድርጅቴ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በዝምታ መመልከት አልችልም» ብለው መናገራቸው ጉድ ያሰኘ ያለ ጉዳይ ነው።

ይህንንስ እንዴት ሊል ቻለ ብለን ብንጠይቅ ከቶ የሚያስገርም አይሆንም። «ጠርጥር ፣ ከገንፎም አይጠፋም ስንጥር» ነውና የአባ ዱላ ድፍረት ነገር ሊኖራት እንደሚችል መጠርጠር ተገቢ ነው።

የኦሮሞው ፕሬዚዳንት የሆነው ለማ መገርሳም ቢሆን፣የወያኔው የደኅንነት ኃላፊው ጌታቸው አሰፋ ቀኝ እጅ እንደሆነ እየታወቀ የኦሮሞን ሕዝብና የኦሮሞ አክቲቮስቶችን ሰብስቦ በመስጠት ላይ ያለው መግለጫና የሚያደርገው ንግግር ከራሱ ታርቆና ከህሊናው መክሮ ያደረገው ከሆነ «አበጀህ፣ ጎበዝ» የሚያሰኝ ነው።

አንዳንዶች እንደሚሉ፣ የለማ ንግግር፣ ከራሱና ከኅሊናው ታርቆ ሳይሆን፣ ወያኔ ባላሰበውና ባልጠበቀው ጊዜ ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቢተኝነት የረዥም ጊዜ እቅዱን እንዳከሸፈበት ትገንዝቦ ቢያንስ የትግራይ ሪፐብሊክ እስኪያውጅና በኢትዮጵያም ቢሆን ሥልጣኑን ለሱ በሚያስተማምን እጅ ውስጥ የማስገባቱ ጉዳይ ዋናዉና አማራጭ እንደሌለው የተረዳበት ጊዜ ላይ በመድረሱም ነው።

ይህ ተረካቢ ሀይልም ነገ ለምትገነጠለው ትግራይ ዕውቅና የሚሰጥና በፊርማ የሚሸኝ በመሆኑ ሁነኛና ታማኝ ሰዎችን ማዘጋጀት ከመጠየቁም በላይ ሁሉንም ነገር ቦታ ቦታውን እስኪይዝ ድረስ የነደፈው እቅድ ሳይሆን አይቀርም ባይ ነን።።

እነኝህ አድርባዮች “ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ” እያሉ እስከ ጮሁ ድረስ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ቀቢፀ ተስፋ እንዳለውም ጥርጥር የለንም። ምንም ቢሆን ከጌታቸው አሰፋ መመሪያ ሳያገኝ አደረገው ማለት ከባድ ነው።

በተለይ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሠፊ ጊዜ ተሰጥቶት መነጣጠልና ልዩነትን ይሰብክ በነበረ የዜና አውታር፣ ስለአንድነት እና ኢትዮጵያዊነት እንደ አዲስ ፍልስፍና መስበኩ የሱም ወኔ ሆነ የወያኔ ሆደ ሰፊነት አዲስ ነገር ሆነውብን ብንጠራጠር ሊገርም አይገባም።

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የበረከት ልቀቁኝም ቢሆን ነገ የአንድነት ሰባኪ ወያኔንም አውጋዥ ሆኖ እንዲቀርብ ለማድረግ የተሸረበ ተንኮል ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ዘንድ ታማኒነትን ሊያገኝ ይችል ይሄናል ከሚል እሳቤ የተደረገ ስውር ሤራ ሊሆን እንደሚችል በታሳቢነት መያዙ ብልህነት ነው።

እኛም ቢሆን በታሪካችን ከዳተኛ ናፉቂዎች መሆናችን በታሪክ የታወቀ በመሆኑ ወያኔ ይህን ደካማ ጎናችንን ትስተዋለች ብሎ መገመትም የዋህነት ነው።

ወያኔ ይህን በአገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ቢቻል በጉልበት፣ ካልተቻለም በመለሳለስ በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል ያልሞከረው ጥረት የለም። በባሕር-ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ-ዘይት፣ በአምቦ፣ ወዘተ የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ለአሰቃቂ እስርና እንግልት ተዳርገዋል። የሕዝቡ ተዘዋውሮ የመሥራትና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ የዜግነት መብቱን ተነጥቆ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንዲውል ተደርጓል።

ይህ ሁሉ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ፣ «ምስማር ራሱን ሲመቱን እየጠነከረ ወደፊት እንደሚሄድ ሁሉ፣ የወያኔ የግፍና የጭካኔ እርምጃ ሕዝቡን የበለጠ ከማጠናከር አልፎ በአንድነት ለአንድነት እንዲቆም እንዳደረገው እያየን ነው። የግፉ መብዛት ሕዝቡን ማድረግ የፈለገው ከማድረግ ያገደው አንዳችም ነገር የለም። ወያኔም ትግሉን ወደኋሊት እንዲሄድ የሚስችል ተጽዕኖ መፍጠር አልተቻለውም። በአንፃሩ የተገፋና መከራው የበዛበት ሕዝብ መሪ ነን የሚሉትን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በቁማቸው እንደሚገንዛቸው በታሪክ የታየ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያም ነገ የሚታይ እውነታ መሆኑን ሕዝቡ እየወሰደ ያለው ሞትን በድፍረት የመጋፈጥ ድርጊት እያሳየ ነው።

ከዚህ ተነስተን የነአባ ዱላ፣ የነበረከት ስምዖን፣ ወዘተ ቲያትር ምን ሊሆን ይችላል? ብለን ብንጠይቅ፣ ይህ ሊሆን ይችላል ከሚል አንድ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን።

ይህም ወያኔ ሁለንተናዊ ፍላጎቱን ያለ አንዳች እንከን ለማሟላት የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ጥሩዋል። የሕዝቡን ኅሊና ሊቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት እስካሁን ድረስ ያልሞከረውን አዲስ ሙከራ ለመፈተሽ እንደተነሳሳ እንገምታለን። ይህም የአንድነት ሀይሉን ለአሸናፊነት ያበቃውን መፈክር መንጠቅ ነው። ከዚህ አስከፊ ውድቀቱ የቀሰመው ትምህርት ቢኖር የአንድነትና ኢትዮጵያዊነት አጀንዳን አሸናፊነትን ነው።

እሾህን በእሾህ ነው እንዲሉ ተቀናቃኞቹን መልሶ ማሽነፍ የሚችለው መፈክራቸውን በመቀማት ነው ብሎ እንዲያምን ተገዱዋል። ይህች ለክፉ ቀን ትሆነኛለች ያላትን የመጨረሻ ካርድ መምዘዝ የተገደደውም ሽንፈቱን ሙሉ በሙሉ በመቀበሉ ነው።

ከአንድነት ኃይሉ ጋር ያደረገው የሞት ሽረት ግብግብ ተሸናፊ መሆኑን ሳይወድ በግዱ ለራሱ መቀበል እንደተገደደ ሁሉ አንድ ብቸኛ አማራጭ የነበረችውን ካርድ ማለትም «የአንድነት እና የኢትዮጵያዊነት» ካርድ በመምዘዝ፣ ሌላ አዲስ ድራማ መጀመር ተገድዋል። ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት አድርባዮችም መድረኩ ላይ ለመጀመሪያው ትዕይንት የታደሙ ናቸው።

ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን በጎሣ ከፋፍሎ እንዳይገናኙ አድርጎ ለመግዝት የተሄደበት ጉዞ የማያዋጣ፣ እንደሆነና ወያኔ ከፋፈልኩዋቸው ያላቸው ህዝቦች ያላንዳች ሽማግሌ በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ነበረው አንድነታቸው በመመለሳቸውና አገዛዙ ገነባሁት ያለውን ሀሉ ከሥሩ የተናደበት በመሆኑ የሕዝቡን የአንድነት ጥያቄ እየተናነቀውም ቢሆን፣ ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ ለጊዜው ባለማግኘቱ ነው።

ለዚህም እንደ ለማ አይነቱን ሆነ ነገ በገፍ ከየ ካድሬ ማሰልጠኛው “በአዲሱ ርዕዮት” ሰልጥነው የሚወጡት ሁሉ አንድነትን እንዲሰብኩ ፍላጎቱ እንደሆነ ድርጊቱ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ይህ አዲስ አቋም በግልጽ ያልታወጀበትና በትግሬ-ወያኔዎቹ አንደበት ሊነገር ያልቻለበት ምክንያት ወያኔዎቹ ለዘመን የሰበኩት «የአማራና የሌሎች ብሄረሰቤች ጠላትነት » የሀሰት ድርሳን መሆኑን በተግባር በማየታቸው፣ ይህን ደፍረው ለመናገር ወኔ በማጣታቸው ነው።

በሌላ መልኩ ይህንንም አዲስ ቅጥፈት በወዶ ገቦቻቸው ማስነገሩ ከገቡበት የሀፍረት ጉድጓድ የሚያወጣቸው ስለመሰላቸውም እንደሆነ ይገመታል።

ይህ የአንድነት ጥያቄና አቋም የወያኔ ሊሆን ይችላል፣ ወያኔም ለኢትዮጵያ አንድነት ይቆማል ማለት፣ ሸንበቆ ያፈራል፣ በቁሎም ትወልዳለች፣ ገለባም ያብባል ማለት ይቀላል። የአንድነት ጥያቄ አስፈላጊነት በወያኔ ፍጡሮች፣ በወያኔው የመገናኛ ብዙኃን መነገሩ በራሱ፣የወያኔ አገዛዝ ከነከፋፋይ ፖሊሲው ግብአተ መሬት ለመግባት ጉድጓዱ የተማሰ፣ ልጡ የተራሰ መሆኑን አመላካች ነው።

ስለዚያም ይመስለናል የነአባ ዱላ ጉዳይ ሲነሳ «ጌታዋን የተማመነች በግ፣ ላቷ ውጭ ታድራል» የሚባለውን ተረት ያስታወሰን። ዋናው ጥያቄ ግን ጌታዋ ማን ነው ? የሚለው ነው። እየተጠናከረ የመጣው የኦሮሞ ሕዝብ ወይስ ገደል አፋፍ ላይ የሚገኘው ወያኔ።

ይህን ጥያቄ የሚፈታው ጊዜ ብቻ ነው። አባቶቻችን እንደሚሉት «ሽልም ከሆነ ይገፋል ዱባም ከሆነ ይጠፋል» ይሉናል።

የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም የተጎነጎነው ሤራ አስፈጻሚዎች በመሆናቸው ከወያኔ የደኅንነት ቢሮ «ኢትዮጵያዊነትን» እንዲሰብኩ ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆነ የአፈጻጸም ሂደቱ ያሳብቃል። ይህን ጉዳይ ለማራገብም ከየነገዱ የተመለመሉና የሰለጠኑ አዲስ ካድሬዋች ሊሰማሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የነአባ ዱላና የነለማ ዲስኩር ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ ከሆነና በራሳቸው አነሳሽነት ያደረጉት ሆኖ ከተገኘ ማናቸውም ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሜአለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት እሰይ ወሸኔ በማለት ሊደግፋቸውና ሊያበረታታቸው ይገባል።

ይህን ስንል ግን፣ እንኳን ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ብዙ ሸፍጦችና ክህደቶች ያስተናገደው ይህ ትውልድ ይቅርና ፣ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮአችን ተጠራጣሪዎች በመሆናችን ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ማየቱ ተገቢ ነው እንላለን። መጠራጠር በራሱ ክፋት የለውም። የመጠራጠሩ ምክንያት ዕውነቱን ከሀሰቱ፣ ምርቱን ከግርዱ፣ ስንዴውን ከእንክርዳዱ፣ ገብሱን ከጎሱ እስኪለይ ድረስ ሁኔታዎችን በጥርጣሬ ማየቱ ትክክልምና ተገቢም ስለሆነ ነው።

የሰሞኑን የነአባ ዱላና የነለማን ድርጊት የምንጠራጠረው፣ «እባብ ያየ በልጥ በረየ» እንደሚሉት ሁሉም እባብ መስለው ስለሚታዩን ጭምር ነው ። ያለፈው የፖለቲካ ተመክሮአችን ከባህላችን ጋር ተዳምሮ የተጠራጣሪነት ሥነ-ልቦና በኅሊናችን ውስጥ ሁነኛ ቦታ ይዞ ስለሚገኝም ጭምር ነው።

ከዚህም የተነሳ ብንጠራጠር ሊፈረድብን አይገባም። የፖለቲካ ሕይዎታችን በመጭበርበርና በመታለል መራር ሁነቶችን አሳልፈዋል። በዚህም የተነሳ እንደገና ተጨፈኑ እናሞኛችሁ የሚለን እንዲኖር አንሻም።

እነዚህ የኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች ከወያኔ ፍልጎት አፈንግጠዋል ብለን የገመትናቸው ሰዎች ከኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ውጭ ሆነው ወያኔን ከውድቀት ለመታደግ የሚሞክሩ አይመስለንም ያም ከሆነ፣ ከኦሮሞ ሕዝብ የበለጠ ጠላት አይኖራቸውም ባይ ነን።

የእኛንም ጥርጣሬ ትክክል ሆኖ ባናገኘው እንወዳለን። ስለሆነም ያሉንን ጥርጣሬዎች በምንደብቅበት ደብቀን ወይም ይዘን፣ የሰዎቹን እርምጃ በአግባቡ እየሰፈርን ያሉትን ሆነው እንዲገኙ በእኛም በኩል አስፈላጊውን እርዳታ፣ እገዛና ፣ ማበረታቻ ብንለግሳቸው ከወያኔ ጋር ተቆራኝቶ ዛሬ ልለይ ነገ እያለ ፈራ ተባ የሚለውን ቁጥሩ ብዙ የሆነ ኃይል የተቃዋሚው አጋር ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አለን።

በፖለቲካ ቋሚ ጥቅም እንጂ፣ቋሚ ጠላት የለም። ትግል ማለትም የጠላት የሆነውን ሁሉ የራስ ማድረግ ነው። በወያኔ አገዛዝ ልቡ የሸፈተውን የእኛ ማድረጊያው አንዱ ዘዴ እንደነ ለማ ያሉትን ለመቀበል ልባችን ክፍት ሲሆን ነው እንላለን።

ከዞብል !!!