ያ ትውልድና ይሄ ትውልድ ከአማራ አንጻር ሲፈተሽ!

Print Friendly, PDF & Email

(ጋሻው መርሻ)

በመጀመሪያ 60 አመት ሙሉ አማራ ላይ ጥላቻ ሲሰበክ፣ አማራ ሲገደል ዝምምምምም…..ምምምም….. ያለ ትውልድ አለ። ዝም ያለውማ እንዲያውም የተባረከ ነው። ጣልያንን እና መሰል ወራሪን ተዋግተው ያሸነፉ አባቶችን አዋክቦ ገደል የከተተ ክፍልም አለ። ይሄ ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው። አማራ ጠል የሆነ ልሂቅ አለ። ከዛ ትውልድ ውስጥ በኋላ እነ ፕሮፍ. አስራትን የመሳሰሉ ለየት ያሉ ሰዎች ተከስተው ነገር ግን በአብዛኛው አማራ ጠል-ልሂቅ ሴራ ተላልፈው ተሰጡ። አሁን ከዚህ አማራ ጠል ልሂቅ ጋር ግብግብ ገጥሞ የሚገኝ ወገኑን ወዳጅ ግዮናዊ ትውልድ አለ። በየቀኑ እየበረታ የሚሄድ። ግን ገና በቂ የቁሳቁስ ሀይል የሌለው ጀማሪ ነው። አንድ ወሳኝ ነገር ግን አለው። እውነትና ምንም ነገር ማድረግ የሚያሥችል ጉልበት! !

በዲያስፖራ ያሉትን የአማራ ጠል ልሂቃኑን ግብር ተመልከቱ። አማራ በተጨፈጨፈበት እና በታረደበት በማናቸውም ወቅት ጎላ አድርገው ድምጽ አሰምተው አያውቁም። እንዲያውም ሌሎች እንዳያሠሙ ለማፈን ይታትራሉ። ተረባርበው እርዳታ አሰባስበው አያውቁም። ካደረጉ እንኳ ለጭብጨባ የምትሆን መናኛ ነገር ቢያደርጉ ነው። ስለ አማራ ነፍስ በግልጽ አልተከራከሩም። ከአማራ ውጭ የሆነ ሰው አንድ ነገር ሆነ ሲባል ግን ለለቅሶ፣ ለሰልፍ እና ክስተቱን ለማውገዝ ሠባራ ወፍ አትቀድማቸውም። ኢትዮጵያ ገደል ገባች ብለው እሪታውን ያቀልጡታል። የአማራ ደም ግን መሬቱን አልፎ ጅረት ቢሠራ እንኳን አይታያቸውም። የአማራ ደም የሀገር ማያያዣ ሙጫ ይመሥላቸዋል። የቅርቡን እንኳ ተመልከቱ። በቅርቡ በተከሰቱ የተለያዩ የብሄር ግጭቶች ያለ የሌለ ሀይላቸውን አስተባብረው አማራ ላልሆኑት በሚሊዮን የሚሰላ ገንዘብ አድርሰዋል፣ በጅረት የሚሰላ እንባ አፍስሰዋል፣ በቡጢና ጥርስን በማንገራገጭ የሚሰላ ከፍተኛ ቁጣ ተቆጥተዋል። ድንኳን ተከራይተው ነጠላ ዘቅዝቀው ደረት ደቅተዋል። በሳምነቱ አማራ በገጀራ ታረደ ሲባሉ መጽሃፉም ቄሡም ዝም ጭጭ! በሸላቾቹ ፊት የሚነዳ በግን ያክል እንኳን አላዘኑለትም! በዲያስፖራ ያሉት አማራ ለሚታፈንበት ሚዲያና ድርጅት ገንዘባቸውን ይታለባሉ። ወንዱ ኪሡን ገልብጦ ለመለገሥ አያመነታም። ሴቷም መቀነት እንኳን ባይኖራት ቦርሳዋን ከእነ ዶላሩ ለመለገሥ አትነፍግም። የአማራ ገበሬ ለማንነቱ የሚያደርገውን ትግል ከህወሀት ጋር ተባብረው በጭካኔ ሲወጉ ለህዝቡ ማዘን የሚባል ነገር ለአፍታ እንኳ አይከሰትላቸውም። ለምን በሉ! በወያኔ ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ከተከሰሰ ድርጅት ነገር ግን በአማራ ምድር በሚደረግ ትግል ምንም አሻራ ከሌለው ድርጅት ጋር በመተባበር ወያኔው አማራን ለማጥቃት በራሱ አተረጓጎም ህጋዊ የሚመስል ሽፋን እንዲያገኝ ተባበሩት። ወትሮም አማራን ማጥቃት ቋሚ አላማው የሆነው የወያኔ ቡድን ይሄንን ምክንያት ሲያገኝ የተነሳውን የአማራነት ጥያቄ ከዚህ ከተፈረጀ ድርጅት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር በማዛነቅ ሥሙን እንኳን ሠምተውት በማያውቁት ድርጅት አባልነት እየከሠሠ የፈለገውን ለማድረግ እና የአማራን ትግል እውቅና ለመንፈግ እድል አገኘ። ይሄንን ሁሉ ያደረገው በዲያስፖራ የሚገኘው ወገን ባለው የሚዲያ ሀይል እና የገንዘብ ሀይል በመረባረብ ነው። የአማራ ገበሬን የእህል ክምር በማቃጠል የሸማቂ ኦፕሬሽን ሥኬት ከበሮ ተደለቀ። የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ ሆነ!!

አገር ቤት ወዳሉት ቀደምት ልሂቃን እና ባለሀብቶች ስንመጣ ከአማራ ውጭ ለሆኑት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሰጥተዋል። በስም እየተጠቀሱ ሚሊዮን ብሮች የሰጡ ባለሀብቶች እንዳሉ የሳምንታት ትዝታ ነው። አማራ ላይ አንዳች ሲደርስ ግን ጭጭ። የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ብሎም የአለም ብርቅ ሀብት የሆነው ጣና ሊጠፋ ጣር ውስጥ እያዩ ዝም! ጭጭ

ወደብአዴን እንምጣ። ብአዴንን አማራ አይደለም ብለን እንከራከራለን። በእርግጥ ከድርጊቱ አንጻር ስንመዝነው አማራ አይደለም። ግን ደግሞ የአንድ ዘመን አማራ ጠልና አድር ባይ ልሂቃን ትውልድ አካል ነው እንጅ አማራነት የለውም ለማለት ይቸግራል። ምክንያቱም ያደረጋቸውን ስንመለከት በውጭ ያለው ዲያስፖራ እና አገር ቤት ያሉት ቀደምት ልሂቃን እና ባለሀብቶች ከሚያደርጉት የተለየ አድርጓል ለማለት ስለሚያስቸግር። ለምሳሌ በሌላ አካባቢ በደረሱ የሌላ ብሄር ጉዳቶች በምክትል ጠ/ሚኒሰትርነት ደረጃ የተቀመጠው የብአዴን ሰው ሳይቀር ሄዶ ለቅሶ ደረሰ። ነገሩ ደመቀ ለምን ሄደ አይደለም! ይልቁንሥ ወደ ኢሉባቡር ሄድኩ ያለው የብአዴን ሰውም በገጀራ ስለታረዱት አማሮች ትቶ ሥለ ብሄር ብሄረሠቦች የፍቅር ድርሰት እያነበነበ ተመለሰ። እንዲያውም የሞቱት አማሮች ቁጥራቸው 3 ሥለሆነ ለቅሶም አይገባም አይነት አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ድሪቶውን ደረተ። አማራ በየትም የአገሪቱ አካባቢ ሲጨፈጨፍ ዝምም። ጭጭ!! ጣናን ያህል ሀብት ሊጠፋ እያጣጣረ እያየ ዝም! ! ጭጭ!!

ሲደመደም ብአዴንም ሆነ የተቀረው የ60ዎቹ ቅሪት አማራ-ጠልነት ማለትም ራስ-ጠልነት ባህርይ ይታይበታል። ቀድሞ ነገር ከኤርትራ፣ ከትግራይ እና ኦሮሞ ብሄርተኞች ጋር ሆኖ አማራ ጨቋኝ ነው በሚል የአባቶቹን ሀብት አዘረፈ። ወላጆቹን ገደለ፣ ዘረፈ፣ አዘረፈ። አደኸየና ጎዳና ላይ ጣለ። ይሄም ብዙ ምክንያቶች ሊሰጡት ይችሉ ይሆናል። አንዱ ግን አማራ ጨቋኝ ነው የሚለው ለ60 አመታት መድረክ ላይ ትኩስ ሆኖ የቆየው ፕሮፓጋንዳ እውነት ወደመምሰል ደረጃ ደርሶ አእምሮአቸውን አጥቦታል። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚለውን የናዚዎች ቲዎሪ ፕሩፍ አደረጉ ማለት ነው። በመሆኑም ተደጋግሞ በተጋቱት ፕሮፖጋንዳ ሆዳቸው ተወጥሮ በውስጣቸው የበደለኛነት ስሜት ፈጥሮባቸዋል። ያንን በውስጣቸው የተሸከሙትን በደል ያረሳሱ እየመሰላቸው አማራ ሲጠፋ ምንም አይመስላቸውም። አለፍ ሲልም ለመበደሉ ትክክለኛነት ምክንያት ሲደረድሩ ይገኛሉ። በአንጻሩ ሌላው ላይ ኮሽ ሲል ካሳ የካሱ እየመሰላቸው ቀድመው ይገኛሉ። የውስጣቸውን የበደለኝነት ስሜት ያራገፉ እየመሰላቸው። ታሪካዊና ፖለቲካዊ ንስሀ የገቡ እየመሰላቸው። በዛም በዚህም የተሰለፉት የአንድ ዘመን ትውልድ በመሆናቸው አንድ አይነት አስተሳሰብና ባህርይ ያሳያሉ። ያላቸው ልዩነት አንዱ ገዥ አንዱ ተቃዋሚ መሆናቸው ብቻ ነው። ስለሆነም አማራን በተመለከተ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት አንድ አይነት ነገር ነው። ለአማራ ባላቸው ጥላቻ ሲመዘኑ ብአዴንም ሆነ ሌሎች አንድ አይነት ናቸው። በአድር ባይነት እና አሽቃባጭነት ባህርይ ሲመዘኑ አንድ አይነት ናቸው። ስለዚህ ብአዴን አማራ አይደለም ብለን ካልን ዲያስፖራውም ሆነ አገር ቤት ያለው ቀደምት ልሂቅና ባለሃብትም አማራ አይደለም ማለት አለብን።

የአማራ ተስፋ አዲሡ ብሄርተኛ ትውልድ ነው! ለምሳሌ ሰሞኑን ከመቶ በላይ አማሮች በሸዋ፣ ኢሉባቦር እና ጉምዝ-ካማሽ በጥይት፣ በገጀራ እና በቀስት ሲገደሉ እና በአስር ሺህዎች ቤት ንብረታቸው ወድሞ ጫካ ውስጥ ሲወድቁ ከተለያየ አቅጣጫ የደረሰላቸውን እርዳታ ያሳዝናል። የለም ማለት ይቻላል!! በእኔና ጓደኞቸ በተከፈለተው አካውንት የገባው ገንዘብ መጠን እጅግ አስደንጋጭ ነው! ብቸኛ መዳኛ መፍትሄው የአማራ ብሄርተኝነትን መንከባከብ ብቻ ነው!

GashawMersha እንደከተበው።