የወያኔ ስትራተጂ የተጎለጎለ ልቃቂት!

Print Friendly, PDF & Email

(ከተስፋዬ መኮንን)

ሀገራችን ኢትዮጵያ እውነትም ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ከመስቀልኛ መንገድ ላይ ቁማለች። ይህ መስቀልኛ መንገድ አንዱ የሚወስዳት ወደ መበታተን ሌላው ወድ ህዝብ አንድነትና መልካም የሽግግር ዘመን ውስጥ ሊከታት የሚችል ጎዳና ነው። በሁለቱም አማራጭ ጎዳናዎች ጀርባ የቆሙ ሀይሎችን መዳሰስ አስፈላጊ ነው።

1. ወደ መበታተን ጎዳና የሚወስዷት ሀይሎች። እነዚህ ሀይሎች የመንግስት ሀይልን የተቆጣጠረውን የወያኔ ትግሬን፣ የሱ ሰራሽ የሆኑ የጎሳ ድርጂቶችን፣ ከውጪ ሀገራት ውስጥ የተጠለሉ የተገንጣይ ግንባሮችን፣ ባካባቢ የሚገኙ ኤርትራን፣ የአራብ ሀገራትን፣ ለአጭር ጊዜ ጥቅም የታወሩ የምእራብ ሀገራትን ያካትታል። ይህ ሀይል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የማይገፋ ጎራ እንደ ነበር የታወቀ ነው። ይሁንና ከሁለት አመታት በፊት የጀመረው የነቃ አመራር አልባ ነገር ግን የቆረጠ የህዝብ ትግል ባደራሰብት ምት ይህ አይነኬ መስሎ ቁሙ የነበር ሀይል እተተፍረከረከ ነው።

የዚህ የውስጥ የጸረ ኢትዮጵያ ግንባር መስራች፣ አስተባባሪና መሪ የሆነው የትግሬ ወያኔ የተነሳበት እስትራተጂክ ግቡ ላይ ሳይደርስ በጊዜ እየተቀደመ ነው። ዛሬ ባላቋረጠው የህዝብ ትግል ምክንያት “ጊዜ” ለወዳጅም ለጠላትም ወሳኝ አሉታዊ ሚናውን እየተጫወተ መሆኑ የሚታይ ነው። በተለይም የትግሉ ፍጥነትና ሂደት ወያኔ ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ እንደሆነበት የሚታይ ነው። የወያኔ ትግሬን ስትራተጂዎችን ዘርዘር አድርጎ ማየት ይጠቅማል። ዋና የስትራተጂው ግብ የትግራይ ሪፑብሊክን እውን ማድረግ ነው። እዚያ ለመድረስ ስልቶቹ ምንድናቸው?

(ሀ) በኢትዮጵያ ላይ የዘረጋውን ግዛቱን በተቻለ መጠን ረጅም አመታትን የሚያስቆጥር እንዲሆን በማድረግ ትግራይን በኢኮኖሚ መገንባት፣ የአማራውን ህዝብ በማጥፋት ሂደቱ እርምጃው ዝግመታዊና የውጪ ረዳቶቹን የሚያጋልጣቸው እንዳይሆን በጥንቃቄ መምራት፣ በመጨራሻም በእልቂት ጎዳና ውስጥ የከተተውን ህዝብ መሬት በመንጠቅ ከሰሜን እስከ ደቡብ ምእራብ የሚደርስ መሬትን ለታላቋ ትግራይ ማድረግ ናቸው።

(ለ) ሌላው ለነገዋ ነጻ የትግራይ ሀገር የውስጥና የውጭ ደህንነቷ መሰረት የሆነ ከአካባቢ ሀገሮች ጋር በጸር ኢትዮጵያ ጥቅም የሚያስተሳስራትን የውጪ የግኑኝነት መመሪያዋን ማራመድ ነው። የዚህ የውጪ ግኑኝነቷ መመሪያ ያካባቢ ምሶሶው ከሱዳን ጋር የጀመረችው ግኑኝነት ነው። የግኑኝነት መሰረቱ ለሁለቱም የጸር ኢትዮጵያ አቋማቸው መመሪያቸው ነው። ሌላው ከኤርትራ ጋር ወደፊት ከበቀልተኛው ኢሳያስ ሞት በኈላ ወያኔ መራሽ የሆነ መንግስት ኤርትራ ላይ በማቆም የትግራይ ትግርኝን መንግስት በመመስረት ለትግራይ የባህር በር የማስገኘት ስልት ነው። ከምእራቡ ዓለም ጋር ያለውን ግኑኝነቱን እንዳይደፈርስ ያዘዙትን የሚሰራ የአካባቢ ጃስ ሲሉት እየሄደ የሚናከስ ውሻ ሁኖ ማገልገል ነው።

(ሐ) በመሰረተው የጎሳ መንግስት ውስጥ በጸረ አማራና በጸረ ኢትዮጵያ መአድ ዙሪያ ያቋቋማቸው ድርጂቶች ውስጥ ኦህዴድ የተባለውን በማጎልበት ለነገው የነጻነት ቀን የሸኝ ደብዳቤ ጸሀፊነት ማብቃት ነው።
ይህ ታላቅ እቅድ እውነትም ረጅም ጊዜንና ለሁለት የትግሬ ትውልድ የተሰጠ ስራ ነበር።

ዛሬ በህዝቡ ግፊት እንደ ልቃቂት የተጎለጎለው ይህ የወያኔ እስትራተጂ ነው። እንደተጀመረ ሳያልቅ የቀረ ቤት። በዚህ የወያኔ ጎራ ተሰልፎ የነበረው ወያኔ ሰራሽ ድርጂት ሁላ በትግሉ ምት ውስጠ መሰንጠቅ ደርሶበታል። የጎጥ አጥሩ እየተነቃነቀ ነው። ህዝብ ለህዝብ በተለያየ መንገድ በትግሉ መስክ እየተገናኘና እየተናበበ ነው። ይህ ለዋናው የወያኔ ስትራተጂ ግብ መምቻ ሁኖ የተቀመጠውን የከፋፍለህ ግዛውን ሴራ በተግባር እየበጣጠሰው ነው። የህዝቡ ትግል መፈክሮች ወያኔ ይሂድ ነው። አንከፋፈልም ነው። ይህ ሀያል የህዝብ የትግል ጥሪ ለወያኔ ግብአተ መሬት አብሳሪ መሆኑ በራሱ የመጨራሻው ደወል ነውና በትግሬው ድርጂትም ውስጥ መሰንጠቅ መድረሱ አይቀሬ ነው። አክራሪው የትግሬ አመራር እጁን ይሰጣል ብሎ ማለም የማይሆን ነው። ባህሪያቸውም አይፈቅድም። ለዘመናት ባባቶቻችን ከኋላችን የተገነቡ የአንድነት ድልድዮችን አፍርሰዋል። ይህን በሚገባ ያውቁታል። እናም ካላቸው የኢትዮጵያ ጥላቻ አኳያ የሚሆነው ባወጣው ያውጣው ብለው መገንጠልን ያውጃሉ። የሸኝ ደብዳቤ ሰጭ ግን እንደሚያስፈልግ ይረዳሉ። ከሰሞኑ የመጨረሻ ለመሰንበት ከሚያደርጉት ሙከራቸው የምንረዳ ይህንን ነው።

ምንድነው የመጨረሻ ሙከራቸው ? እንደ ታቀደው ለረጅም ጊዜ መግዛት እንደማይችሉ ተረድተዋል። መሄዳቸው ካልቀረ አካሄዳቸውን “ህጋዊ” እንዲሆን ለማድረግ የመጨራሻ ቀን ትግል ማድረግ ነው። ይህም ሙከራ የሚያካትተው ትግሬ ወያኔ ስልጣኑን ለፈጠረው አጋር ድርጂት ኦህዴድ ማስረከብና ከሱ የስንብት ደብዳቤ ማግኘት ይሆናል። እንደሱማሌ ላንድ ቆሞ ቀር ሁኖ ላለመቅረትና የኤርትራን የሽኚት ታሪክ ለመድገም ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ በህዝብ ትግል ግፊት ለሁለት በመሰንጥቅ አደጋ ውስጥ የወደቀውንና በአባዱላ ሲገነባ የመጣውን “ሲፍቁት ኦነግ” የተባለውን መልሶ በሁለት እግሩ እንደገና ለመገንባት የሚደረግ ጊዚያዊ የጥገና ስራ ነው። ለዚህ ተግባር ነባሩን የወያኔ ቀኝ እጅ የሆነውን አባዱላን መላካቸው ነው። አባ ዱላ ለማወናበጃነት እንዲጠቅመው የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የምትሆነው “መንግስት ለህዝቤና ለድርጂቴ የሚገባቸውን ክብር አልሰጠም” ይምትለዋን እንዲጠቅምባት ፈቅዶ የላከው ወያኔ ነው። እስር ቤቱን ኦሮሞ ያደረገው እሱ እንዳልነበር! ግድያና ሰቆቃ በሱ እንዳልተጀመረ! አጭር ተልእኮው በኦህዴድ ውስጥ የተነሳውን እኔነኝ ባይነትና የህዝቡን ትግል በማፈን ኦህዴድን ወደ ኦነግ የቀረበና ከመገንጠል ዓላማ ጋር የሚተሻሽ የስልጣን ባለቤት ማድረግና የወያኔ ሸኝ መሆን ነው። አዲስ አበባን “ፊንፊኔ” ብሎ በዋና ከተማነት፣ ከተሳካም የኦህዴድ ጭንብል አጥልቆ ኦነግ የሚመራው ሌላ የብሄረሰቦች ግንባር መንግስት መመስረት፣ ካልሆነም መገንጠል ለአባዱላ የህልሙ እውነታ ይሆናል። ተቀባይነት እንዲኖረውና ትግሉም ተዳፍኖ ለወያኔ መፈናፈኛ ጊዜን እንዲያስገኝ ወያኔ በሱማሌ ሽፋን የሚያካሄደውን ወረራና እልቂትን ያቆማል። የአባዱላ የስራ ፍሬ ሁኖ እንዲታይ ማድረግ ይሆናል።

ከዚሁ ጋር ለወያኔ ጊዜ መግዣ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ከያዙት የመንግስት ስልጣን እየለቀቁ ወደ ድርጂታቸው እንዲመለሱና የማረጋጋትና የማፈን ስራ እንዲሰሩ የሚደረጉ፣ እጃቸው በደም የተበከሉትንና ወደፊት ከማለት ሌላ አማራጭ የሌላቸውን አዛውንት “ታጋዮቻቸውን” እንደሚያሰማሩ ልንጠብቅ ይገባል። በረከት ስምኦንንም ከዚሁ ካአባዱላ አረጋውያን “ታጋዮች” ተልእኮ አኳያ የምንመድበው ይሆናል። በትግል ሞገድ እየተናወጠች ያለችን መርከብ እየዘለሉ የሚሄዱት እበላ ባዮች እንጆ በይዎች፣ ዘራፊዎች፣ ገዳዮች፣ ዘር አጥፊዎች የነበሩት አይሆኑም። እነዚህ እስከመጨረሻዋ የትግል ቀን ድረስ ህዝቡን ቁመው የሚፋለሙን ናቸው።

ከዚህ የጸረ ኢትዮጵያ ጎራ በተቃራኒ የቆመው ሰፊ፣ ያልተያያዘ፣ የመመናበብ ችግር ያለበትና በመጠላለፍ አፍራሽ ተግባር ውስጥ የወደቀው “ተቃዋሚ” በሚል የሚታወቀው ነው። የከማን አንሼ የስነልቡና የበላው ሀይል የበላይነቱን በመያዙ ለመሰባሰብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቀና አመራር አልባ የሆነ ሰፊ ሀይል ነው። ይህ ሀይል ከውስጡ በብዙ ክፍልፋይ የተተበተበ ነው። የአንድነት ድርጂት ብሎ ካዲስ አበባ ቢሮው ለመውጣት ከወያኔ ፈቃድ የሚጠብቅ ነው። ላለፉት 60 ዓመታት በመገንጠል ልክፍት የተያዘው ልክፍቱን ለዛሬው ልጆቹ ያወረሰበት ሁኔታ ጎልቶ የሚታይበት ሌላው ነው። አዲስ የአድርባይ ሀይል እንደ ፖለቲካ አዝማሚያ በግልጽ ወጥቶ የመቧደንን አካሄድ እያምታታ፣ የትግል ሂደቱ ላይ አለመተማመን እንዲፈጠር ማድረግና ያልዋለበት ቦታ ደራሽ፣ ያልዋለበት የጦር ሜዳ ላይ ድል አፋሽ እየሆነ መድረኩን ለመያዝ የሚያደርገው እርባና ቢስ ትግል የሚካሄደው በዚሁ የተቃዋሚ ተብዬ ጎራ ውስጥ ነው።

ባንድ በኩል ያለ በቃ መሪ በመግፋት ላይ ያለ የህዝብ ትግል በወያኔ ስትራተጂ ላይ የፈጠረው መመሰቃቀል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በህዝብ ወገኖች በኩል ተሰባስቦ የበቃ ድርጂት ለመፍጠር አለመቻል ምክንያት ሀገራችን የምትሄድበትን አቅጣጫ መምረጥ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ወድቃ መስቀልኛ መንገድ ላይ መቆሟ አደጋውን ሀያል ያደርገዋል። ይህ አደጋ በምን ይገለጣል? ልክ እንደ 83 ዓ.ም. በውጪ ሀይሎችና በአክራሪ ሀይሎች መሀል በሚደረግ ድርድር ይሆንና ውሳኔውም የኢትዮጵያን እንደ ሀገር መኖር የሚፈታተን ውሳኔን የሚያስከትል፣ የአፍሪካ ቀንድን መልካ ምድራዊና ፖለቲካዊ አቀማመጥን የሚሽር አዲስ አቀማመጥን እውን የሚያደርግ ሊሆን እንደ ሚችል መተንበይ ይቻላል። ይህ እርምጃ ለውጪ ተስፋፊዎች እንደሚበጅ፣ ለውስጥ ተገንጣይ አጋሮቻቸው የሚስማማ ነው ቢባልም ለመላው የአካባቢ ህዝቦች የማያልቅ ጦርነትን የሚጋብዝ መሆኑንም እያወቁ አያደርጉትም ማለት አይቻልም። ይህንን አደጋ እንዴት መታደግ ይቻላል? ይቻላል። የሚቻለው ግን በአንድና በአንድ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ነው።

በተቃዋሚ ሀይሎች ዙሪያ ያለ ግን በአንድ ግንባር ያልተሰባሰበው ሀይል በውጪው የወያኔ ደጋፊ መንግስታትና በሀገር ቤት በሚደረገውም የህዝብ ትግልም ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ሀይል ሁኖ መውጣት ሲችል ነው። ይህ ሁኔታ እውን ይሆን ዘንድ እያንዳንዱ ድርጂት “ፕሮግራሜ ” የሚለውን ለጊዜው ከሳጥኑ ከቶ እናት ኢትዮጵያን እናድን ብሎ መነሳት ይኖርበታል። እናም የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ የሽግግር ጊዚያዊ መንግስት የሚመሰረትበትን ጉባኤ ባስቸኳይ የሚጠራ የጋራ ኮሚቴ መመስራት የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል። ለዚህ ዋሽንግተን የተሰባሰበ ተቃዋሚ የመጀመሪያውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል። በጥቂት ግለሰቦች ሊጀመር ይችላል። ያወኩሽ ናኩሽን አመለካከታችንን ለዚች አጭር የታሪክ ወቅት ስንል ለመያዝ እንሞክር። አገራችን ለወደቀችበት ነብስ ግቢ ነብስ ወጪ ቀን ስንል ይህንን ኋላ ቀር አመለካከታችን እንጥል ዘንድ እንማጸናለን።

እናት ሀገራችንን ለመታደግ ድርጂታችንንም እራሳችንንም አሳልፈን እንስጥ!!

መግቢያ ሀገራችንን እናድን!!