በዛሬዋ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው … የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት

Print Friendly, PDF & Email

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የትግል ሥልት ስለዲሞክራሲ መስበክ ነው? ወይስ ስለኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ? ( pdf)

ቅጽ ፪ ቁጥር ፬ ማክሰኞ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፪ሺ፲ዓ.ም

ለዚህ ጥያቄ ሁነኛ መልስ ለመስጠት በቅድሚያ ዲሞክራሲና የኢትዮጵያ አንድነት አደጋላይ መውደቅ የሚሉትን ጽንሰ ሀሳቦች መረዳት፣ ለምንደርስበት መደምደሚያ ትክክለኛነት መቃረቢያ ይሆናል። ዲሞክራሲ ማለት በጥቅል አነጋገር የመስተዳድር (government) ሥርዓት የሆነና የመጨረሻው የፖለቲካ ሥልጣን የሕዝብ የሆነ ማለት ነው (Democracy: Asystem of government in which ultimate political authority is vested in the people.)ዲሞክራሲ የሚለው ቃል የተመሠረተው ከሁለት የግሪክ ቃሎች ሲሆን፣ እነርሱም «ዴሞስ»እና «ክራቶስ» የተባሉ ናቸው። ትርጉማቸውም «ዲሞስ» ሕዝብ ሲሆን፣ «ክራቶስ» ደግሞ ሥልጣን ማለት ነው። ከነዚህ ሁለት የግሪካ ቃሎች ተነስተን ዲሞክራሲ የሚለው ቃል ትርጉም፣ሕዝበ ሥልጣን ወይም ሥልጣን የሕዝብ የሆነበት ሥርዓተ መስተዳደር እንደሆነ እንረዳለን። ይህ ቃል ከክርስቶስ ልደፊት በፊት ከኖሩት የማኅበራዊ ሣይንስ ፈላስፋዎች እንደ ፕሌቶ ባሉት የተነገረና በተከታታይም ሲነገር የመጣ እንደሆነ ይታወቃል። የቃሉ ትርጉም በኅብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ከመንግሥት ጋር ተያይዞ እየዳበረና እየሠፋ የመጣ መሆኑም ግልጽ ነው። በመሆኑም ዲሞክራሲ የማያቋርጥ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት ሂደት እንጂ፣ ያንድ ወቅት ነባራዊ ሁኔታ ክስተት አይደለም። ሂደት ነው።

ዛሬ በምንገኝበት ነባራዊ የኅብረተሰብ ዕድገት ደረጃ ዲሞክራሲ ማለት የሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ የግለሰብ ነፃነት የሚጠበቅበት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ ባለሥልጣኖች በወቅታዊና ቀጥተኛ ምርጫ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት፣ የመምረጥ ሕጋዊ መብት ያላቸው ዜጎች በነፃ ፍላጎታቸው ከተወዳዳሪዎች መካከል እገሌ ወይም እገሊት ይወክለኛል/ትወክለኛለች ብለው ድምፃቸውን የሚሰጡበት ፖለቲካዊ ሥርዓት ነው። ይህ በአግባቡ እንዲከወን ደግሞ አስፈጻሚ አካሎች መኖርን የግድ ይላል። ለዚህ ዓይነቱ ሕጋዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖር የሚከተሉት ተቋሞች መኖርን ይጠይቃል። እነዚህም ነፃ የፍትሕ አካላት ማለትም ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ አቃቢ-ሕግ ከአስፈጻሚው አካላት ፍፁም ነፃ ሆነው ሕግና ኅሊናቸው ብቻ አዛዥ የሆኑበት አሠራር መኖር፣ ከማናቸውም የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች ተጽዕኖ ነፃ የሆኑ የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች መኖር፣ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ አካላት ተቋሞች መኖር ይጠይቃል። ከተቋሞቹ መኖር ጋር ዕኩል አስፈላጊ የሚሆነው የተቋሞቹ የሥራ ክንውን ሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ አመኔታ የጣለባቸው መሆንን ይጠይቃል። እነዚህ ደግሞ ባንድ ወቅት ተሟልተው የሚገኙ አይደለም። ተቋሞቹን ለመገንባትና የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘት ጊዜና ሕዝቡ ስለመንግሥት አሠራርና አደረጃጀት፣ ስለሕግና ሕጋዊነት፣ ወዘተ ንቃተ ኅሊናውን ማሳደግ ይጠይቃል። ይህ በራሱ ሂደት ነው። ስለሆነም ዲሞክራሲያዊ መስተዳደር ለመዘርጋት የማያቋርጥ ሂደትን መከተል የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ፣ በኢኮኖሚ መበልጸግንም የሚሻና ለዚህም ሕጋዊ ተጠያቂነትና ኃላፊነትን የሚሸከም አሠራርና ግንኙነት መዘርጋትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ሊጤን ይገባዋል።

ይህም ማለት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ ቅድሚያ የሚሰጠው፣ የተራዘመ ጊዜንና የሰከነ አመራርን፣ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሰላምን፣ መቻቻልና መከባበርን የሚሻው ዲሞክራሲ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲው የሚዘራበትና ተኮትኩቶ የሚያድግበት፣ በሂደትም ፋፍቶ የሚንሰራፋበት አገርና ሕዝብ ያሻዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች ማለትም፣ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሰላም፣ መቻቻልና መከባበር፣ መተሳሰብና አብሮነት፣ ከሁሉም በላይ የሕግ የበላይነት፣ ለዲሞክራሲያዊ መስተዳደር መመሥረት መሠረትና ቅድመ ሁኔታ የሆኑት ዲሞክራሲያዊ ተቋሞችና አሠራሮች በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፈጽሞ የሉም። ዘረኛው የትግሬ ወያኔ ቡድን ለዲሞክራሲያው መስተዳድር ጽኑ መሠረት የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና አብሮነት ስሜት፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የወል ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን አፈራርሶ ሕዝቡን በነገድ አቧድኖ ዓይና ነጫ፣ ንብና ጭስ አድርጎታል። የአገሪቱን ዓለም አቀፍ ድንበሯን አፍርሶ የነገዶች ደንበር አድርጎታል። የግዛት ወሰኗ ጠፍቷል። ከሁሉም በላይ በዘመን ፍሰት በአገሪቱ ግዛቶች በሥፋት ተሰራጭቶ የሚገኘውን የዐማራ ነገድ የሌሎች ነገዶችና ጎሳዎች አውራ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ፣ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ሰለባ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ዐማራው በየትኛውም የአገሪቱ አካል እንዳይኖር ከመከልከሉም በላይ በየትኛውም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲገለል ሆኗል። ይህን የነገዱን ማኅበራዊ ሰላምና በአገሩ ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት መብቱን የነፈገው በመሆኑ ጥያቄው የዲሞክራሲ ሳይሆን፣ የኅልውና እንዲሆን አስገድዶታል።

በሌላ በኩል ለመሬት ቅርምትና ዐማራውን ነጥሎ ለመምታት ያመቸኛል ሲል ወያኔ በተከተለው የስም የቋንቋ ፌደራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት፣ለዐማራው መምቻ እንዲሆን የታለመው ዓላማ የሌሎችንም ነገዶች ዕልቂት እየሆነ እያየን ነው። በጋምቤላ በኑየርና አኙዋክ ነገዶች ላይ የተፈጸመው የዘር ዕልቂት፣ በኦሮሞና በሶማሊያ ነገዶች መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በአዋሳ፣ በቴፒ፣ በመተከል፣በጠገዴ፣ ጠለምት፣ ወልቃይት፣ ራያና አዘቦ፣ ራያና ቆቦ፣ በጉጂና በደራሳ ወዘተ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው ዕልቂት አብሮነትንና መቻቻልን፣ ማኅበራዊ ሰላምና አንድነትን የሚያመለክቱ አይደሉም። ይህም ኢትዮጵያ አንድነቷ የተናጋ፣ ማኅበራዊ ሰላሟ በጽኑ የታመመ እንደሆነ በትክክል ያሳያል። ይህ ሁኔታ ካልተገታ፣ ኢትዮጵያ እንደአገር የመቀጠል ሁኔታዋ አስተማማኝ ነገር የለም።የሕዝቡ የአብሮነት ስሜት ትል የበላው አገዳ ሆኗል። የኢትዮጵያዊነት የወል ዕሴቶቻችን ባለፉት 26 ዓመታት ሆን ተብለው እንዲወድሙ ተደርገዋል። ከኢትዮጵያዊነት በላይ የነገዶች ማንነት በመሰበኩ ኢትዮጵያዊነት እንዲኮሰምን ተደርርጓል። ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ አገራዊነት ላይ የመበታተን አደጋ አርግዟል። ይህ መጥፎ የመበታተን ዳመና ወደ ዝናብነት ሳይለወጥና ምድር ሳይነካ በአየር ላይ እንዳለ እንዲበን የሚያደርግ የተቀናጀ የአገር አድን ሥራ ሊሠራ ይገባል። ይህ ሥራ ለዲሞክራሲ ሳይሆን፣ ለዲሞክራሲ ዘር መዝሪያ የሚሆን የአገር ኅልውና ትግል መሆን አለበት።

ስለሆነም በየትኛውም መልክ የተደራጁ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ለዚህ ፋታ ለማይሰጥ የአገር አድን ጉዳይ፣ ምክንያቶችን ሳያበዙ፣ ወደ መቃብር ጉዞ የጀመረው ወያኔ፣ እንደ እባብ አፈር ልሶ መልሶ ነፍስ ሳይዘራና አገራችን ሳይበታትናት ለኅልውናዋ ቀድመን እንድነደርስ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጥሪ ያቀርባል። የትግላችን ቅድሚያ አገር በማዳኑ ዙሪያ እንዲሆን በማድረግ፣ ለዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ ብልጽግናና ዕኩልነት ለተሰኙት ጥያቄዎቻችን የጋራ መቀመጫችንና የእኛነት መታወቂያ የሆነችው አገራችን ኅልውና በአስተማማኝ ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ የምናነሳቸው ሊሆኑ ይገባል። ጥያቄዎቹ የተረጋጋ ሰላምና የጠንካራ ተቋሞችን መኖር ይሻሉና!

ለጋራ አአገራችን ኅልውና መረጋገጥ፣ የጋራ ትግል ለነገ የሚባል አይሆንም!

መተባበር ያጠነክረናል፣ መለያየት ያዳክመናል!