የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 7

Print Friendly, PDF & Email

የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ንግድ በአስመራ… ( ክፍል 7, pdf)

በስድስተኛው ክፍል ያቀረብነው የግንት  7  የኤርትራ ጉባኤ ሪፖርታዥ ላይ ምንጮቻችን ከተለያዩ ሃገራት የታደሙ የድርጅቱ አባላት ይዘወት ስለገቡት ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም አስመራ በኢሳት ቢሮ ውስጥ ያለስራ ስለተቀመጡ የድርጅቱ ቅልቦች በብዕራቸው የተረከሉንን ማቅረባችን ይታወሳል።

ተከታዩን ሪፖርት ለማቅረብ በገባነው ቃል መሰረት አስመራ ውስጥ የሚገኙ የግንቦት  7  ከፍተኛ የአመራር አባላት በተለይ ደግሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆነው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአስመራ ከተማ ስለሚያካሄደው ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ የጥቁር ገበያ የንግድ እንቅስቃሴና ያለተቆጣጣሪ በመኝታ ቤቱ ውስጥ ስላከማቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላርና ዩሮ በተመለከተ የላኩልንን ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበናል።…

ኤርትራ ውስጥ በሚካሄደው “የአርበኞች ግንቦት 7” ጉባኤ እንዲሳተፍ በድርጅቱ ሊቀመንበር የተመረጥነው የዲያስፖራ አባላት ወደ አስመራ ከመሄዳችን በፊት ለእያንዳንዱ የውጪ አመራር የሚሆን በድርጅቱ በኩል ከሚመደበው ወጪ በተጨማሪ መጠባበቂያ የሚሆናችሁ የውጪ ምንዛሪ (ዶላር ወይም ዩሮ)  በርከት አድርጋችሁ መያዝ አለባችሁ የሚል መልእክት  “በታጋይ”  ቄስ ኤፍሬም ማዴቦ በኩል እስኪሰለቸን ድረስ በተደጋጋሚ ሲተላለፍልን ቆይቷል።

በዚህ መሰረት ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ጥቂት የዲያስፖራ አባላት በስተቀር አብዛኞቻችን በመሪዎቻችን  ለመወደስ  ስንል  የቤተሰቦቻችን  ጉሮሮ  በመዝጋትና  ከዘመድ  ቤተሰብ  በመበደር ለተለያየ ወጪና አስመራ ውስጥ የምንዝናናበት ከበቂ በላይ ሊባል የሚችል ዶላርና ዩሮ ይዘን ነበር ወደ አስመራ ያቀናነው።

ወድያውኑ አስመራ እንደገባን በኤርትራ ቆይታችን የሚኖሩንን ወጪዎች በተመለከተ ቄስ ኤፍሬም ማዴቦ ካረፍንበት ሆቴል ድረስ በመምጣት ከድርጅቱ ሊቀመንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተላለፈ መመሪያ  ነው  በሚል  “ለሆቴል፣  ለምግብና  ለተለያዩ  ጉዳዮች  የምታወጡት  ወጪ  መክፈል የምትችሉት በናቅፋ ነው። ናቅፋ ሆቴል ውስጥ ወይም በባንክ ምንዛሪ  በ  100  ዶላር  1500  ናቅፋ ነው። በህጋዊውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት ከፍተኛ ስለሆነ ሆቴል ውስጥ ወይም ባንክ ድረስ በመሄድ ዶላር መዘርዘር የለባችሁም፣ የኛ ታማኝ የሆነ ልጅ ይመጣል አንዱን ባለ አንድ መቶ ዶላር በ1900  ናቅፋ ይመነዝርላችኃል።”  በማለት በዶ/ር ብርሃኑ የሰጠውን ትዕዛዝ ቆፍጠን ባለ አነጋገር ገለፀልን።

በእርግጥ በኋላ ላይ አንድ መቶ ዶላር በጥቁር ገበያ የሚመነዘረው የናቅፋ መጠን ቄስ ኤፍሬም ከነገረን በላይ አንዳንድ ጊዜም እስከ  2500  ናቅፋ ድረስ የሚደርስ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በዚህ ስሌት መሪዎቻችን መጠጊያ ከሰጠቻቸው ድሃ ሃገር ኤርትራ ብቻ ሳይሆን ከኛም ምን ያህል ገንዘብ እንዳተረፉ ማስላት ይቻላል።

በክፍል ሁለት ሪፖርታዥ ላይ እንደገለፅኩት በድርጅቱ ከተገባው ቃል ውጪ የሆቴል ወጪውን ራሱ እንዲሸፍን የተነገረው የዲያስፖራ ታዳሚ  “ለግል ወጪያችን ከኪሳችን እንመነዝራለን። ነገር ግን በአስመራ ቆይታችን የሆቴልና የምግብ ወጪ ድርጅቱ ይሸፍናል ተብለን እዚህ ድረስ ከመጣን በኋላ ሃሳባችሁን እንዴት ትቀይራላችሁ?”  በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያቀርብ ቄስ ኤፍሬም ማዴቦ “የሆቴል ወጪ የሃገሪቱ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ሊሸፍንልን አልቻለም፣ በዚህ ምክንያት እናንተ እንድትሸፍኑ ነው የተወሰነው” በማለት የተለሳለሰ መልስ ለመስጠት ሞከረ። ይሁን እንጂ በተለይ ስማቸውን እዚህ ላይ ለመጥቅስ የማልፈልጋቸው ሁለት ዲያስፖራዎች በቂ ገንዘብ ያልያዝንስ ከየት አምጥተን  እንከፍላለን? የሚል  ሃይለኛ ተቃውሞ በማስነሳታቸው ቄሱ ስለ ዝርዝር ሁኔታው ብርሃኑን አነጋግሬ መልስ እሰጣችኋለሁ ወይም ደግሞ እሱ ራሱ መጥቶ እንዲያነጋግራችሁ አደርጋለሁ የሚል ምላሽ በመስጠት ሳይታሰብ ድንገት ከተፈጠረው ጭቅጭቅ አምልጦ ሄደ።

ከዚያ በኋላ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ተጠርቶ እኛ ድረስ በመምጣት “የምትችሉ የሆቴልና የምግብ ወጪያችሁን ራሳችሁ ሸፍኑ፣ አንችልም የምትሉ ካላችሁ ደግሞ እኛው እንሸፍናለን፣ ነገር ግን ስማችሁንና የመጣችሁበትን ሃገርና ከተማ በማስመዝገብ የፈለጋችሁትን ያህል ናቅፋ ድርጅቱ ያበድራቹኋል ወደየመጣችሁበት ስትመለሱ በምንሰጣችሁ አካውንት መሰረት ብድሩን ትመልሳላችሁ” የሚል ማብረሪያ በመስጠት ጉባኤው የሚካሄድበት ቦታ ከከተማ ውጪና ሆቴል የሌለው መሆኑ እየታወቀ  “ጉባኤው በሚካሄድበት ቦታ ግን የሆቴል ወጪያችሁን ሙሉ በሙሉ እኛ እንሸፍንልችኋለን አይዞአችሁ አታስቡ”  የሚል ንቀት አዘል ቀልድ እግረመንገዱን ጣል በማድረግ ወደመጣበት ተመልሶ ሔደ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ቄስ ኤፍሬም ማዴቦ ከአስመራ የኢሳት ቢሮ ቅልቦች አንዱ የሆነውን “የእኛ ልጅ” ተብሎ የተነገረን አብይ የተባለውን ወዳረፍንባቸው ሆቴሎች ይዞት በመምጣት ካስተዋወቀን በኋላ የሚመነዘሩ ዶላሮችና ዩሮዎች ለእሱ እንድንሰጥ ነገረን።

አብይ  የተባለው  የአስመራ  ኢሳት  ቢሮ  ተቀላቢ  ከመጣበት  ቅፅበት  አንስቶ  ዲያስፖራው (ላሜቦራው)  እየተግተለተለ ዶላሩንና ዩሮውን ለእሱ ለማስረከብ የነበረው ግፊያ ማየት ራሱን የቻለ ሌላ  አስገራሚ  ትዕይንት  ነበር።  ይሄ  የውጪ  ምንዛሪ  የማስረከብ  ሂደት  ጉባኤው  ተጠናቅቆ ከአስመራ እስከወጣንበት ቀን ድረስ የዘለቀ ሲሆን ከጉባዔው በኋላም ምፅዋና ሌሎች ከተሞች ለመዝናናት አቅም የነበራቸው የዲያስፖራው የጉባኤው ታዳሚዎች ይህን ህገወጥ አገልግሎት ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

በእርግጥ ይህ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ ንግድ ከኮሎኔል ፍፁም እውቀት ውጪ ሲካሄድ እንዳልነበረ ግልፅ ነው። ዶላርና ዩሮ በድብቅ መመንዘር ቀርቶ የግንቦት 7 አመራርን ጨምሮ እያንዳንዱ ዲያስፖራ ወደ መፀዳጃ ቤት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሳይቀር ከኮሎኔል ፍፁምና በህቡእ ካሰማራቸው ቁጥር ሰፍር የሌላቸው የህግደፍ ሰላዮች ቁጥጥርና ክትትል ውጪ እንዳልነበረ በግልፅ የሚታይ ነበር።  ህገወጥ የውጪ ምንዛሪ ንግዱ የሚካሄደው በኮሎኔል ፍፁምና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ምስጢራዊ ስምምነት መሰረት ስለመሆኑ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረንም።

ዶ/ር ብርሃኑ የአስመራ የኢሳት ቢሮ ቅልቦች አንዱ የሆነው አብይ ከዲያስፖራው (ላሜቦራው) የሰበሰበውን ዶላር እስኪያመጣለት ድረስ መኪናውን ለአብይ ሰጥቶ ማረፊያ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ከዚህ ህገወጥ የውጪ ምንዛሪ የሚያገኘውን ትርፍ እያሰላ በጉጉት ሲጠባበቅ ቆየ። አብይ ከዲያስፖራው የሰበሰበውን ዶላርና ዩሮው ምን ያህል እንደሆነ ከስር ከስር ለዶ/ር ለብርሃኑ በስልክ ሪፖርት ያቀርባል። ዶ/ር ብርሃኑ በቀረበለት የስልክ ሪፖርት መሰረት ማረፊያ ቤቱ ውስጥ ካስቀመጠው የኤርትራ ናቅፋ አስልቶ በማዘጋጀት ሲጠብቅ ከቆየ በኋላ አብይ ወደ ብርሃኑ ቤት በመሄድ ያዘጋጀለትን ናቅፋ በመረከብ እንደየ ሂሳባችን አምጥቶ አከፋፈለን።

አብይ በታማኝነቱ የተመረጠ ቢሆንም በዶ/ር ብርሃኑ መኝታ ቤት ውስጥ ምን ያህል ናቅፋና ዶላር እንደተከማቸ ለማወቅ የሚችልበት እድል እንዳይፈጠር ለጥንቃቄ ሲባል የሰበሰበውን ዶላርና ዩሮ ምን ያህል እንደሆነ ለዶ/ር ብርሃኑ አስቀድሞ በስልክ ሪፖርት ማድረግ አለበት። ዶ/ር ብርሃኑም ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ የናቅፋ ሂሳብ ለይቶና አስቀድሞ በማዘጋጀት እንደሚጠብቀው በአብይ ላይ ያላቸውን መንፈሳዊ ቅናት መደበቅ ያልቻሉት እነዚያ የአስመራ የኢሳት ቢሮ ቅልቦች ሲያሙት ድንገት ጆሮአችን ውስጥ ገብቷል።

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የቅርብ ታማኞቹ የሚባሉት ቄስ ኤፍሬም ማዴቦንና ነአምን ዘለቀን  እንኳን ሳያሳትፍ ምንም አይነት የሂሳብ ሰራተኛና የሂሳብ ተቆጣጣሪ  (ኦዲተር)  በሌለበት ከፍተኛ መጠን ያለውን ናቅፋና የውጪ ምንዛሪ በመኝታ ቤቱ ውስጥ አከማችቶ በመኖር ላይ መሆኑ ሌላው በአስመራ ቆይታችን የታዘብነው አስገራሚ እውነታ ነው። በእርግጥ በየጊዜው ከውጪ እየተሰበሰበ ለህዝባዊ  ትግሉ  እየተባለ  ከዲያስፖራው(ላሜቦራው)  የሚላከው  ገንዘብ  ለምን  ስራ  እንደዋለ ተቆጣጣሪ እንደሌለው ቀድሞውኑ ይታወቃል።

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ዶላር ጥቁር ገበያ የገባበት ዋናው ምክንያት አርበኞች ግንቦት 7 ኤርትራ ውስጥ ምንም አይነት ሰራዊት ሳይኖረው ለሰራዊቱ ቀለብና አንዳንድ ወጪዎች እየተባለ ከቅርብ የሻዕቢያ አለቆቹ ከነኮ/ል ፍፁም ጋር በመመሳጠር ከኤርትራ መንግስት የሚያገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ናቅፋ ለማከማቸት በመቻሉ ነው። በሃሰተኛ ስሌት ከኤርትራ መንግስት ለሰራዊት ቀለብ እየተባለ የሚመደበው በጀት ዴምህት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ አርበኞች ግንባር እና ሌሎችም ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚጠቀሙበት የተለመደ ስልት ነው ይባላል። በዚህ ህገወጥ ተግባር ኮ/ል ፍፁምን ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚከታተሉ

የሻዕቢያ ባለስልጣናት በጀቱን ከመንግስት ከማስፈቀድ ጀምሮ ወጪ እስከሚሆንበት ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የጥቅሙ ተካፋይ በመሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብትና ንብረት ማካበት የቻሉ ቱጃሮች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ናቅፋ የተባለው ይህ የኤርትራ ገንዘብ ከኤርትራ ውጪ ምንም አይነት ጥቅም የማይሰጥ በመሆኑ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በጥቁር ገበያ እየመነዘረ ዶላርና ዩሮውን ማጠራቀሙን ተያይዞታል። የሚያሳዝነው ነገር ግን ዶ/ር ብርሃኑ የራሱን ህገወጥ ድርጊት ደብቆ መአዛው ጌጡ እና ግብረ አበሮቹ በህገወጥ መንገድ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ አከማችተው በመገኘታቸው የኤርትራ መንግስት ምርመራ እያካሄደባቸው ነው በማለት የአርበኞች ግንባር አመራር አባላትን ለመወንጀል አለማፈሩ ነው።

ዶ/ር ብርሃኑ ለጉባኤ አስመራ ከገቡት ዲያስፖራዎች (ላሜቦራዎች) ከጥቁር ገበያው እጅግ ባነሰ ሂሳብ ገንዘባቸውን ሙሉጭ አድርጎ ከሰበሰበ በኋላ ኤርትራ ውስጥ ባለው የከፋ የኑሮ ሁኔታ ምክንያት የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሲሉ መንፈስን በሚሰብር አሳዛኝ ሁኔታ በየከተማው ጥጋጥግ ለዝሙት የተኮለኮሉት የአስመራ ወጣት ሴቶች በዲያስፖራው አባላት እንዲጎበኙና፣ በአረቄም እንዲራጩ ሲያደርግ መሰንበቱን ለታዘበ ማንም ሰው ምንም አይነት ማብራሪያና በረሃ መውረድ ሳያስፈልገው ኤርትራ ውስጥ ፀረ ወያኔ የሚባል ትግል የሌለና ተራ ውሸት መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል።

ይቀጥላል…..

*************

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 7

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 6

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 5

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 4

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 3

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 2

የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ክፍል 1