እምቦጭን ነቅሎ እምቦጭን መትከል!

Print Friendly, PDF & Email

(ሰሎሞን ይመኑ)

#በፋሽስት ወያኔ በግፍ ለሞቱት ነፍስ ይማርልን።

እምቦጭ የጣና ሃይቅን የመኖር ህልውና እየተፈታተነ ያለ አደገኛ አረም ነው። የጣናን ውሃ መጦ በማድረቅ በውስጡ ያሉትን ውሃም አካለት አየር በመንፈግ አፍኖ የሚገድል አደገኛ አረም ነው።

ይህ አረም የህወኃት የስልጣን ሰረገላዎች የሆኑ አማራውን እንወክላለን የሚሉ የብአዴን ግዑዛን እምቦጮች ጋር ይመሳሰላል። እምቦጭ አላስፈላጊ አረም በመሆኑ እየተወገደ ነው። የብአዴን ግዑዛን እምቦጮችም ህዝቡን ደሙን በመምጠጥ ትንፍሽ አሳጥተው ከመጨረሳቸው በፊት ልንነቅላቸው ይገባል። የጣናን እምቦጭ ነቅለን የብአዴንን እምቦጮች ከተከልን አሁንም የአማራ ህዝብ በየቦታው መታረዱ ይቀጥላልና ሰሞኑን ለጣና እምቦጭ የሚተመው ወጣትም ሌላ የሚነቀል እምቦጭ እንዳለ ተነጋግሮ ሊሄድ ይገባል።

በኦሮሚያ ክልል በኢሉ አባቦራ ዞን ከዚህ በታች ያቀረብኩት የቪኦኤ ዘገባ ሰዎችን በማናገርና የክልሉን ባለስልጣናት በማናገር በሰሩት ዘገባ «የሌላ ብሔር ተወላጆች» የሚለው ዘገባ ስህተት ቢሆንም የሞቱት የአማራና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ናቸው በሚልም እንደገና የኦሮምያ ክልል የመንግስት ኮምኒኬሽን ሃላፊው ገልፀዋል። በግልፅ እንደሚታየውም ቪኦኤ 1500 የሚደርሱ የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸውና ቤታቸው መቃጠሉን የዘገቡት ዘገባ ህይወታቸውን ለማዳን ጫካ ውስጥ የደበቁትን የሰዎች ቁጥር ግን በምንም ሁኔታ ማወቅ እንደማይቻል መገመት ይቻላል።

VOA የዘገበው አሳሳቢው የቡኖ በደሌ ግጭት ዝርዝሩን ከዚህ በታች ያድምጡ።

ከጫካ ውስጥ ሁነውም ህይወታቸውን ለማትረፍ የድረሱልን ጥሪ በስልክ የሚደውሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ቤታቸው መቃጠሉን እና ንብረታቸው መዘረፉን እየገለፁ እያለ « የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ ጉዳት ደረሰ መባሉ የሚያሳዝን ሲሆን ጉዳት ለደረሰባቸውም አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ እንዳይደረግ ትልቅ እንቅፍትም ነው። አደጋው ሲደርስም እስካሁን ሁኔታውን ለማቆም የሚደረጉ ጥረቶች አለመኖራቸው ሌሎች ወያኔ የሚፈልጋቸው አይነት መጠነ ሰፌ ግጭት እንዳይኖር እሰጋለሁ።

የኦሮምያ ክልል ጥረት ምን ድረስ ነው?

ህወኃት ሰራሹ ኦፒዲዮ ከእምቦጩ ብአዴን አንፃር ከህወኃት ቀንበር ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም አሁን የደረሰውን እና እየደረሰ ያለውን የፋሽስት ወያኔ ሴራ ለመከላከል የሚያስችል ምንም አቅም እንደሌለው ግን ሃቅ ነው። ምክንያቱም ኦፒዲዮም የፋሽስት ወያኔ አንዱ ቅርንጫፍ በመሆኑ ብዙ የወያኔ ደህንነቶች በስሩ ተሰግስገው ይገኛሉና ትግሉ ቀላል አይሆንም። የዚህ ቀላል ማሳያም አደጋው በደረሰበት ወቅትና ቤቶቹ ሲቃጠሉ ከህዝብ ጎን እየቆሙ ነው የሚባሉት የኦሮምያ ክልል ልዩ የፖሊስ አካላት ምንም እርምጃ ሳይወስዱ ቁመው ሲያዩ እንደነበር የአይን እማኞች ገልፀዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ወያኔ ኦፒዲዮን እንደመሳሪያ ለመጠቀም በጣም ቀላል መሆኑን ያሳየን ሲሆን የክልሉ የኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋም ይህን ረብሻ የፈጠሩት የቀድሞ የኦፒዲዮ አባላት ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ነው ቢሉም ችግሩ እንዳለ ማሳያ ከሚሆን ውጭ ጉዳት ለደረሰባቸው በጫካ ለሚገኙት እና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው እየተደረገ ያለ ጥረት ግን እንደሌለ እያየን ነው። ይህ ደግሞ ሌላ ብጥብጥ ከማስነሳቱ በፊት የክልሉ መንግስት ግጭቱን መቆጣጠር ባይችል እንኳን ተጎጅዎችን ግን ወደ መኖሪያቸው በመመለስ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። ችግር ፈጣሪዎችንም ወደ ህግ ሊያመጣ ይገባል።

ከእምቦጩ ብአዴንስ ምን ይጠበቃል?

ሙሉ በሙሉ ለፋሽስት ህወኃት እጁን በመስጠት የወያኔን ህልውና በማረጋገጥ የሚታመነው ብአዴን እና ውስጡ እንደ መዥገር ለቅም የተሰገሰጉ ግኡዛን የአማራው በየቦታው መፈናቀልና መሞት ምንም የማያሳስባቸው ሰዎች እንደሆኑ አይተናል።

ለምሳሌ እስካሁን ድረስ በክልሉ ፕሬዝዳንት በኩል የተደረገ ጥረት አለመኖሩ አሁንም የወያኔ ቀንበርን መሸከም የሚከብደው ለህሊናው የሚኖር ሰው አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን እነ አቶ አለምነው መኮነንም ለዚህ ትግል ከፋሽስት ወያኔ ጎን የአማራውን ህዝብ ለማጥፍት እንቅልፍ የላቸውም።

የክልሉ የኮምንኬሽን ሃላፊ አቶ ንጉሱም በበኩላቸው የህዝብ ስቃይ የማይሰለቻቸው የፖለቲካ ቅልውጥና የለመዱ የወያኔ ሰው በመሆናቸውን በህዝብ ደም ቁማር እየቆመሩ ነው። የኦሮሚያ ክልል ሃላፊዎችም ሆኑ ቪኦኤ የሞቱ እና የተፈናቀሉ እንዲሁም ቤታቸው የተቃጠሉ መኖራቸውን እያረጋገጠ የብአዴን ወያኔዎች እነ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ግን ቁጥሩ ትንሽ እንደሆነ በመግለፅ የቁጥር ቁማር ይጫወታሉ።

ለመሆኑ ለብአዴን ግኡዛኖች

* ስንት ሰው ሲሞት ነው
* ስንት ሰው ሲፈናቀልና ስንት ሰው ቤቱ ሲቃጠል ነው አማራው ላይ ጉዳት ደርሷል ብለው የሚያምኑት?

ባጠቃላይ ለብአዴን እምቦጮች በሰው ልጅ ህይወት የፖለቲካ ቁማር መቀመር ትተው የደረሰውን ጉዳት በማመንና በግልፅ እውቅና በመስጠት ከኦሮምያ መሪዎች በመማር በፌድራል መንግስቱ ጫና በመፍጠር ባስቸኳይ ችግሩን ማስቆምና የተፈናቀሉ የሞቱ እንዲሁም ሃብት ንብረታቸው ተቃጥሎ ጫካ የገቡ ሰዎች አስፈላጊውን ካሳና መቋቋሚያ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረግና ለዚህም የሚረዳ የገቢ ማሰባሰቢያ ባስቸኳይ ተከፍቶ ያፈናቀላቸው ራሱ ፍሽስት ወያኔ አስፈላጊውን ክፍያ እንዲፈፅም አጋሩ እምቦጩ ብአዴን አለቃዎቹን እንዲለምን እና ወደ መፍትሔ እንዲመጣ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን አሁንም ጥቃቱ ቀጥሎ ህዝቡ ወደ ባሰበት እልቂት እንደሚገባ እንድታውቁት እና በዚህ እልቂትም ዋጋችሁን የምትከፍሉ እንደሆነ እንዲታወቅ። የህዝብ ድምፅ ሰሚ ሲያጣ አለኝ የሚለውን ሁሉ እንደሚጠቀም አሳይቷችኋልና አሁንም ህዝቡ ውስጥ ያለው እረፍት ማጣት እናንተን እረፍት ለማሳጣት ሁሌም ዝግጁ ነው። ህዝብ ሁሌም ያሸንፍልና።