ብአዴንን እንደ ኦህዴድ ማድረግ እንችላለንን?

Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዱዓለም)

ብአዴንን እንደ ኦህዴድ የአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ ማድረግ ይቻላል፤ ይገባልም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ። ይሄ በመሰረተ ሀሳብነት ችግር የለበትም። ችግሩ ግን ምን ያህል ከተጨባጩ ሀቅ ጋር ይገናኛል የሚለው ነው። ተጨባጩ ሀቅ ይሄ ነው። ኦሮሞ ከሞላ ጎደል አንድ ወጥ ብሄራዊ ስሜት እንዲያዳብር ተደርጓል። ኦነግ፣ ኦህዴድ፣ ኦፌኮ… ወዘተ ሆኖ ሊሰለፍ ይችላል። ሁሉም በኦሮሞ ብሄራዊ ጥያቄና ፍላጎት ላይ ልዩነት የላቸውም። የሚለያየው የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር እና አጀንዳውን ለማስፈጸም የሚጓዝበት ስልት ብቻ ነው። ላለፉት አምሳ ከምናምን አመታት የኦሮሞነት ስሜት ተሰርቶበታል። ስለዚህ ሁሉም ለዚህ ዋና የኦሮሞነት አስተሳሰብ ተገዥ ነው። በየትኛውም መንገድ ይሰለፍ ለብሄረተኝነቱ በታማኝነት ይቆማል። የኦሮሞን ፍላጎት ያውቃል። በየትኛውም አውድ ሆኖ ራሱን እንደ ኦሮሞ ይቆጥራል። በኦሮሞ ውስጥ እርሱ እዳለ ያውቃል። በዛ ላይ የኦሮሞን ካድሬዎች ለአማራ ማዳከሚያ በማለት ህወሀት ሲያጠናክራቸው ነው የቆየው። ስለዚህ የኦሮሞ ብሄረተኝነት በራሱ በብሄረተኝነቱ እድሜ ጠገብ ህዝባዊ ስሜት፣ በህወሀት እገዛ እና ውጭ ባሉት ልሂቃኑ ብርቱ እገዛ አንድ አይነት አስተሳሰብ ላይ ሊደርስ ችሏል። ስለሆነም በሁሉም ዘንድ የአካሄድ እንጅ የግብ ልዩነት የለም። ህብረ-ብሄራዊ ተብየ ድርጅቶችም አይገቡበትም። ህብረ ብሄራዊ ተብየ ድርጅቶች የማይገቡበት አጥር በመሆኑ የኦሮሞነት ፖለቲካዊ አመለካከቱና ብሄረተኛነቱ አይረበሽም።

ወደትግራይ ስንመጣ ሁኔታው ከኦሮሞው ብሄረተኝነት የበረታ ነው። ሁሉም ለትግሬ ብሄረተኝነት ታማኝ ዘብ ናቸው። በትግራይ ብሄራዊ ፍላጎትና የጥቅም ጥያቄ ላይ ሁሉም አንድ መስመር ላይ ናቸው። ሁሉንም ነገር ከትግራይ ጥቅም ብቻ መመልከት የሚያስችል የትግሬነት ብሄራዊ ታማኝነት አላቸው። አረና ሊሆን ይችላል፤ ህወሀት ሊሆን ይችላል፤ ነጻ ዜጋ ነኝ ሊል ይችላል፤ ህወሀት ያሳደደው ሊሆን ይችላል። ሆኖም በትግራይ ብሄረተኝነትና ጥቅምና ፍላጎት ላይ ልዩነት የላቸውም። ሁሉም የትግሬ ብሄረተኛነት የተባለ ጥላ ስር ይጠለላሉ። የትግሬም ብሄረተኛነት ህብረ-ብሄራዊ ተብየ ድርጅቶች በአጠገቡ ድርሽ የማይሉበት በብርቱ አጥር የታጠረ ነው። ስለሆነም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ብሄረተኛነቱን እያለመለመ ይገኛል።

ወደአማራ ስንመጣ በጣም ውስብስብና ከባድ ሆኖ እናገኘዋለን። እንዲያውም የአማራ ብሄረተኛነት እንደ ጣና በእምቦጭ የተወረረ እና አረሙን ለመነቃቀል ትግል እያካሄደ ያለ እንቅስቃሴ ነው። ዋና ዋና ችግሮቹም፡- ገና አንድ አይነት አማራዊ ስሜት ላይ አልተደረሰም። ኢትዮጵያዊነት ምሽግ የተደበቀው ከእውነት-ሸሽ ወገን እየጋለ ያለውን የአማራ ብሄረተኛነት ለማጥፋት ውሀ በባልዲ ይዞ ይዞራል። የዚህን ብሄረተኛነት አቀንቃኞች አንገት ለመቁረጥም ሰይፍ ይዞ ይዞራል። ባጭሩ የአማራ ብሄረተኝነት ከዚህ ወገን ከባድ ተጽእኖ ሲመጣበት ቆይቷል። በአማራ የህልውና ጥያቄ በማስታከክ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቃለሁ የሚል ወገን አለ። ይሄም እየጋለ ያለውን የአማራ ብሄረተኛነት ለማጥፋት የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። አማራነትን ከዘረኛነት ጋር በማዳበል ሲያወግዝ ይውላል። ይሄ ሁለቱ ወገን ለስሙ አማራ እያለ ይማል እንጅ አማራነትን አልተረዳም፣ የህዝቡንም ትክክለኛ ችግር አልተገነዘበም፤ ለአማራ ምን ማድረግ ነው የምትፈልገው ተብሎ ቢጠየቅ እንኳ መልስ የለውም። ምናልባት አማራን ተጠቅሜ ለኢትዮጵያ የሚበጅ የሆነ መልስ ቢጤ አለኝ ሊል ይችላል።

የአማራነት እንቅስቃሴ የህብረ-ብሄር ተብየዎች ባህላዊ ምሽግ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። አሁን አማራ የራሱን መንገድ መራመድ ሲጀምር ይሄ ወገን ያለ የሌለ ሀይሉን በመጠቀም ሊያጠፋው እየተረባረበ ይገኛል። ይሄም ቡድን የአማራን ብሄረተኛነት በብርቱው የተፈታተነ ጉዳይ ነው። አሁንም ገና ጫናው አልቀለለም። አማራው በራሱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ላይ በመመስረት የራሱ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያካሂድ ከሆነ ህብረ-ብሄራዊ ተብየው ወገን መድረሻ ማጣቱ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው በኦሮሞውም ሆነ በትግሬው ጉያ መጠለል አይችልም። ራሱን ችሎ ለመቆም ደግሞ አይችልም። ሁኔታው አይፈቅድለትም። እና በአማራ ላይ ጥገኛ ሆኖ በመኖሩ ይሄንን ወገን ከአማራ ትከሻ ላይ ማውረድ ቀላል ሆኖ አልተገኘም። አማራ እንደ ህዝብ የሚያደርገውን የህልውና ትግል የራሱ የፖለቲካዊ ትግል ህልውና ማክተሚያ አድርጎ በመውሰዱ (በእርግጥም ነው) በቀላሉ ሊላቀቅ አልቻለም። ህብረ-ብሄራዊ ተብየው ወገን የራሱን ፖለቲካዊ ህልውና ለማስቀጠል ነው የሚታገለው። ይሄ የፖለቲካዊ ህልውና ትግል ከአማራው የህይወት ህልውና ትግል ጋር ከባድ ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ብዙ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። የአማራ ብሄረተኝነት ከዚህ ወገን ጋር ገና ትግል ላይ ነው፤ ገና ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ይሄ ቡድን ቀላል የማይባል ሀይል አለው። የፖለቲካ ድርጅቶች አሉት፤ የፖለቲካ ድርጅቶቹም እንደ አሜባ ራሳቸውን በጎጥ ማህበራት ስም የማራባት አቅም አላቸው። በዚህም የአማራን ህዝብ ሲፈታተኑት ቆይተዋል። አሁንም እየተፈታተኑት ነው። ይሄ ቡድን ጠንካራ ሚዲያዎች አሉት። የኦሮሞና የትግሬ ብሄረተኞችም በስልት አማራን ለመጎተት ይጠቀሙበታል።

የአማራውን ቋንቋ ሌላው መናገሩም የአማራን ብሄረተኛነት ፈተና ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል። አማራ መስለው የሚያደናቅፉትን ሰዎች መለየት ከባድ ሲሆን ይስተዋላል። ይሄ ወገን ከተለያዩ አካላት ተልእኮ ይዞ የአማራ ማልያ ለብሶ መጫወት ቀላል ሲሆንለት ቆይቷል። የቋንቋውን ክፍተት በመጠቀም። የአማራነት ትግል ገና እነዚህን አራግፎ መጣል ይጠበቅበታል።

ሌላው ችግር ራሱ ብአዴን ነው። ብአዴን እንደ ድርጅት በዴሞክራሲያዉ ብሄረተኛነት የሚያምን ድርጅት ነው። የብአዴን ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኛነት ማለት አማራ ለራሱ የማይጠቅም፣ ህወሀትን የማይጎዳ አኩራፊ ብሄረተኛነት እንዲፈጥር እና እየቆዘመ እንዲኖር ያቀደ ነው። እውነተኛ የአማራ ብሄረተኛነት ሲመጣ ይሄ አማራን አዘናጊ ቡድን መርበትበቱ አልቀረም። ስለሆነም የአማራን እውነተኛ ብሄረተኛ በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ ብዙ እየሰራ ቆይቷል፤ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ወደአማራው ብሄረተኛነት ሰርጎ ለመግባትም ቀላል ሳይሆንለት አልቀረም። በተደጋጋሚም የአማራውን ብሄረተኛነት የራሱ አጀንዳ ማራገፊያ ሊያድረግ ሲሞክር ቆይቷል።

እንግዲህ ከላይ በተዘረዘረው ችግር ምክንያት የአማራ ብሄረተኛነት ትግሉ ከባድ ሆኖበት ይገኛል። ለዚህ ዋናው ምክንያት እንግዲህ ገና ህዝቡ በአንድ አስተሳሰብ ስላልቆመ ነው። እንደ ትግሬና ኦሮሞ በአንድ አስተሳሰብ እስከሚቆም ድረስ ገና ትግል ያስፈልጋል። በዚህም ሚዛን ብአዴንን አሁን መጠቀም አይቻልም። ብአዴን እንደ ድርጅት አሁንም የእውነተኛው አማራ ብሄረተኛነት ጠላት ነው። በውስጡ ያሉት አማራነታቸውን የሚወዱ ወጣቶችም አመርቂ ውጤት ማምጣት በሚችሉበት ይዘት ላይ አይደሉም። አሁን ባለው ሁኔታ መረጃ ከማቀበልና እውነተኛውን ብሄረተኛነት ውስጥ ለውስጥ ከማስረጽ የዘለለ ሚና የላቸውም። እነሱን ጥንካሬ እንዲኖራቸው ለማድረግ ደግሞ ጊዜና ትግል ያስፈልጋል። ቁንጮ ላይ ያለው የብአዴን አመራር በህወሀት ሳንባ እስከተነፈሰ ድረስ አሁን ለአማራ ሊጠቅም አይችልም።
ወጣቶቹ የብአዴን አመራር ደግሞ በብዙ አፈናና ክትትል የሚኖሩ በመሆኑ አሁን ውጤት ያለው ስራ ሊሰሩ አይችሉም። እናም በዚህ ጊዜ የአማራ ብሄረተኛነት ከብአዴን ጋር በጣምራ ይስራ ማለት ከባድ ስህተት ነው። ውጤቱ መጠለፍና መክሰም ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ከባድ አይደለም። ስለሆነም የአማራ ትክክለኛው ብሄረተኛነት ራሱን ማጠናከር፣ ብአዴንን ሰርጎ እንዳይገባበት መከላከል እና አጠቃላይ አማራዊ ስሜት መፍጠሩ ላይ ማተኮር ግድ ይለዋል። አደረጃጀቱ ሳይዘነጋ ማለት ነው። በዛ ላይ ብአዴንን በአደባባይ እንደግፍ ማለት ብአዴንን አምርሮ የሚጠላውን ወገን ማባረር ነው የሚሆነው። እናም በዚህ ሰአት ብአዴንን እንጠቀም ብሎ በአደባባይ መስበክ ህዝቡን ለሁለት ከመክፈል የዘለለ ሚና የለውም።

ምስጋናው አንዱዓለም