የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ሪፖርታዥ ክፍል አራት

Print Friendly, PDF & Email

የ”ስንብት ደብዳቤው” ሴራ እና የአርበኛ መዓዛው ጌጡ እምባና ለቅሶ

በሶስተኛው ክፍል ያቀረብነው የአርበኞች ግንቦት 7 ጉባኤ ሪፖርታዥ በኮሎኔል ፍፁም አዘጋጅነት በዶ/ር ብርሃኑ አቅራቢነት ለጉባኤው ተሳታፊዎች የቀረቡት አምስት የመወያያ አጀንዳዎችና ከእነዚህ መካከል በሁለቱ አጀንዳዎች ዙርያ በ”ውይይት” ሽፋን የተካሄደው ትያትር ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

በገባነው ቃል መሰረት በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ምንጮቻችን በቀሩት አጀንዳዎች ዙርያ የታዘቡትን ድራማ በተመለከተ በብዕራቸው የተረኩልንን እነሆ እንዳለ አቅርበናል፡፡ አጀንዳ ሶስት፡- የንቅናቄውን መተዳደርያ ህግ በተመለከተ የንቅናቄው መተዳደሪያ ህግ ባለበት እንዲቀጥል ከመድረኩ ሃሳብ ስለቀረበ ብዙ ውይይት አልተደረገበትም።

ህገመንግስትና ህግ በሌለበት፣ መሪው ራሱ ህግ በሆነበት ሃገር የሚካሄድ ጉባኤ በዚህ አጀንዳ ላይ መወያየቱ አስፈላጊም ጠቃሚም አልነበረም ብቻም ሳይሆን ያልታሰበ መዘዝም ሊያስከትል ስለሚችል እንዲሁ ያለ ውይይት አጀንዳው እንዲዘጋ ከመድረክ ሃሳብ መቅረቡ የሚያስገርም አልነበረም፡፡ አጀንዳ አራት፡- የሰራዊቱ መተዳደርያ ደንብ በተመለከተ በተለያዩ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ቢሆንም የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በምክር ቤቱ በድጋሚ ሊታዩ እንደሚችሉ በማመልከት አጀንዳው እንዲዘጋ አድርገው ደንቡ እንዲፀድቅ አደረጉ። ለነገሩ የሌለን ሰራዊት ለማስተዳደር ወረቀት ላይ በሰፈረ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ከዚህ በላይ መወያየቱና ጊዜ ማጥፋቱ አስፈላጊ አልነበረም፡፡

አጀንዳ አምስት፡- የአመራር ምርጫን በተመለከተ በዚህ አጀንዳ ዙርያ የተካሄደው ትዕይንት የጉባኤው ዋነኛ ኮሜዲ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንብንም፡፡ የአመራር ምርጫ ከመጀመሩ ከደቂቃዎች በፊት በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ተዘጋጅቶ በኮ/ል ፍፁም የፀደቀው መአዛው ጌጡን የሚመለከት “የስንብት ደብዳቤ” የጉባዔ አዘጋጅ ተብሎ በተሰየመው ግን ምንም ሚና ባልነበረው በኑርጀባ አሰፋ ተነበበልን።

የ”ስንብት ደብዳቤው” ሲነበብ ከአኛ ጋር እኩል ያዳመጠው አርበኛ መአዛው ጌጡ ከመድረኩ በታች ተቀምጦ በመገረምና በከፍተኛ የሃዘን ስሜት ተውጦ በእግሩ መሬት ሲቀበቅብ ኮ/ል ፍፁም ደግሞ ከመአዛው ፊት ለፊት ተቀምጦ አይኑን እያጉረጠረጠ ሲገረምመው ማየት የምር የሚያስፈራ ትዕይንት ነበር። በዚያች ቅፅበት የዋሁ መዓዛው ጌጡ በሻዕቢያና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሴራና ተንኮል በራሱና ለአመታት በመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አርበኞች ግንባር ላይ የተፈፀመበትን አይን ያወጣ ክህደት በአይነ ህሊናው እያሰበ በንዴትና በብስጭት ሲብከነከን እንደነበር ለመታዘብ የሚያስቸግር አልነበረም፡ “የስንብት ደብዳቤው” ዋነኛ ይዘት መአዛው ጌጡ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ እንደማይፈልግ የሚገልፅ ነበር።

ኑርጀባ ጽሁፉን አንብቦ እንደጨረሰ ቤቱ ውስጥ የነበሩት የአርበኞች ግንባር ታጋዮችና የአርበኛ መአዛው ጌጡ ደጋፊዎች በተፈፀመባቸው አይን ያወጣ ክህደት ማጉረምረም ቢጀምሩም በረሃብና በከባድ የጉልበት ስራ ከዛለው አንደበታቸው የሚወጣው የሰለለ የቅሬታ ድምፅ ወዲያውኑ “ዝለሉ ሲባሉ ምን ያህል” ለማለት በጥንቃቄ ተመርጠውና ተዘጋጅተው በመጡት የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ደጋፊ ዲያስፖራዎች እንደ ነጎድጓድ በሚያስገመግም ሃይለኛ ጭብጨባ ተውጦ ቀረ፡፡ በማስከተልም መአዛው ወደ መድረክ ወጥቶ ሃሳቡን እንዲገልፅ በድርጅቱ ሊቀመንበር በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ተጋበዘ፡፡

መአዛው በግድ መድረክ ላይ በመውጣት አንጀት በሚበላ እንባና ለቅሶ ታጅቦ እንዲህ ሲል ተናገረ “በ1996 ወደ ትግል ተቀላቀልኩ፣ በ2000 እና 2002 በሙሉ ድምፅ ተመርጬ በሊቀመንበርነት ድርጅቱን አገልግያለሁ፡፡ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ውህደት ሲፈፀም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆን ሃሳብ ያቀረብኩት እኔ ነኝ አሁን ግን ስልጣኔን ለወጣቶች አሳልፊ ሰጥቻለሁ፣ ተራ ታጋይ ሆኜ ለማገልገል ቃል እገባለሁ” አለ፡፡

ስልጣኑን እንደተረከቡት የተነገረን “ወጣቶች” ደግሞ በእድሜ ከአርበኛ መዓዛው ጌጡ ቢያንስ በእጥፍ የሚበልጡ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ ኤፍሬም ማዴቦና ሌሎች አዛውንቶች መሆናቸው ስናይ መሪዎቻችን ለጉባኤ ከሃገሩ በተሰበሰበው ዲያስፖራ ላይ ያላቸውን ከልክ ያለፈ ንቀት ምን ያህል ገደብ ያለፈ እንደሆነ በግልፅ የሚያሳይ ነበር፡፡

መዓዛው ጌጡ ስልጣኔን “ለወጣቶች” አሳልፌ ሰጥቻለሁ ብሎ ሲናገር “አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ” በሚለው የመሪዎቻችን ብልጣብልጥነት መድረኩ ላይ ወጥቶ ሲያለቅስ ከልቡ ግን እየሳቀ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም፡፡ አርበኛ መዓዛው ጌጡ ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር ከተነገረው ከዚህ ውጪ አንድም ቃል ቢናገር ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል አሳምሮ ያውቃል፡፡

ስልጣኑን ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለመቀማት ያሴር እንደነበር ማመኑን፣ ዘራፊና በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳታፊ እንደነበር፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግሥት የተደበቁ በርካታ የጦር መሣሪያዎችና ገንዘብ እንዳገኘበት እና በምርመራ ላይ የሚገኝ መሆኑን በአስመራው ዝግ ስብሰባ ላይ አስቀድሞ የተነገረን መሆኑን ስናስታውስ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና የሻዕቢያ ባለስልጣናት በአርበኛ መዓዛው ጌጡ ላይ ምን አይነት የተንኮል ሴራ እየሸረቡ እንደሆነ ለጉባኤተኛው ግልፅ ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ዶ/ር ብርሃኑ የማይፈልጉዋቸውን በተለይ የአማራ ተወላጅ የሆኑ አመራሮችን ሁሉ በዘዴ ያገለለ ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚል ስያሜ የተሰጠው የከፍተኛ አመራር ምርጫ ድራማ ተካሄደ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩ፣ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ….(ስራ አስፈፃሚ ደቡቦች) እንዲሁም ኑርጀባ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ በመሆን የደቡብ ቁጥርን በአንድ ከፍ የሚያደርግ “ምርጫ” ተካሄደ፡፡

በእርግጥ ኑርጀባ አሰፋ እንደማይፈለግ በአስመራው ዝግ ስብሰባ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፍንጭ የነገሩን ቢሆንም ምን እየታሰበለት እንደሆነ ስላልገባው ከምርጫ በኋላ ከስራ አስፈፃሚነት ስልጣን በመገፋቱ ምክንያት ደስተኛ እንዳልነበር አስተወለናል፡፡ ከዚህ የምርጫ ድራማ በኋላ በስራ አስፈፃሚነት

1. ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ/አስካዱ)     – ሊቀመንበር
2. ዶ/ር ታደሰ ብሩ/ሚያዝያ     – የሕዝባዊ እምቢተኝነት ዘርፍ ኃላፊ
3. ቸኮል ጌታሁን/አዳ     – የህዝባዊ እምቢተኝነት ምክትል ዘርፍ ሃላፊ
4. አብረሃም ልጅአለም     – የህዝባዊ እምቢተኝነት ምክትል ዘርፍ ሃላፊ
5. ኤፍሬም ማዴቦ     – የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ
6. ነአምን ዘለቀ     – የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ
7. አበበ ቦጋለ     – የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ
8. አስፋ ማሩ/አመነሽዋ     – ሕዝባዊ ተጋድሎ ዘርፍ አዛዥ
9. መሳፍንት አያሌው/ገበየሁ     – የሕዝባዊ ተጋድሎ ዘርፍ ምክትል አዛዥ
10. ታደለ ወንድም     – የሕዝባዊ ተጋድሎ ዘርፍ ምክትል አዛዥ
11. መኳንንት አበጀ     – ሴክሬታርያት
12. ጃንከበድ     – ምክትል ሴክሬታሪያት
13. መላኩ ተሾመ     – ምክትል ሴክሬታሪያት ሆነው ተመርጠዋል ተባልን።

አሁንም የጠላት የጥይት ማብረጃ ሆነው የተመደቡት የፈረደባቸው የአማራ ልጆች መሆናቸውን ከዝርዝሩ በቀላሉ ማየት የሚቻል ይመሰለናል፡፡

ለምክር ቤት ከውጭ ሃገር ተመርጠዋል ከተባሉት ደግሞ የሚከተሉት አባላት የስም ዝርዝር ተነገረን፤-

1. ዶ/ር ታደሰ ብሩ/ሚያዝያ
2. ዶ/ር አዚዝ መሃመድ/ማይክ አብርሃ
3. ነአምን ዘለቀ/መንግስቱ
4. አበበ ቦጋለ/ካለቤ
5. ታሜ
6. ብዙነህ ጽጌ/ውቤ
7. ርዕዮት …..ሴት
8. ፋሲካ ወልደሰንበት ….ሴት
9. ዶ/ር ሙሉዓለም አዳሙ/አስክፖት
10. መንገሻ ዳኜ/ ጃን አሞራ
11. ቸኮል ጌታሁን/አዳ
12. አሳይሽ…..ሴት
13. አምሳሉ ካሳው/ቬጄ
14. መቅደስ ተልአለ
15. ዶ/ር ገድሉ ……ተጠባባቂ
16. ዶ/ር አርአያ ….ተጠባባቂ
17. ሙሉነህ እዮኤል…..ተጠባባቂ ተደርገው ተመርጠዋል።

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ገና ወደ ኤርትራ ለመግባት ሲወስኑ ታግለውና ጥይት ተኩሰው ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ ሳይሆን በአማራ ታጋይ ልጆች ደም ተረማምደው ወደ ቤተመንግስት የመግባት ህልማቸውን ለማሳካት ነው በማለት ዶ/ሩን በቅርበት የሚያውቁዋቸው ሃቀኛ የአማራ ልጆች ሲያጠነቁቁ የነበሩ ቢሆንም አለመታደል ሆኖ ማንም የሰማቸው ሰው አልነበረም፡፡

ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ የግንቦት 7 ንቅናቄ እና ኢሳት ከምንም ተነስተው ለዚህ እንዲበቁ ከአማራው የተደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ በቀላሉ የሚገመት እንዳልነበረ ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ አንድም ወታደር ያልነበረው የግንቦት 7 ንቅናቄ መላው የአርበኞች ግንባር አመራርና አባል እየተቃወመ በሻዕቢያ ተፅእኖ ከአርበኞች ግንባር ጋር “ውህደት” እንዲፈጥር ከተደረገ በኋላ ያለበቂ ጥናት ከኤርትራ በየጊዜው እየተላኩ በብዙ መቶዎች የሚገመቱ የአማራ ወጣቶች የጠላት ጥይት ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ ማድረጋቸውን ሳያንስ አሁን ደግሞ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በሻዕቢያ ድጋፍ ጉልበታቸው የፈረጠመ መስሎ ሲሰማቸው ፀረ አማራነታቸውን ገሃድ በማውጣት የኢትዮጵያ ህዝቦች አርበኞች ግንባርን ህልውና የሚያጠፋ የመጨረሻውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ድፍረት ማግኘት መቻላቸው በጣም ያናድዳል፡፡

ይቀጥላል….

 

ከዚህ በፊት የነበሩትን የግንቦት 7 የኤርትራ ጉባኤ ሪፖርታዥ ክፍል 1፣ ክፍል 2 እና ክፍል 3 ከዚህ ላይ ያንብቡ  http://welkait.com/?p=10324