የወያኔ መንግስት የፓርላማ አፈ-ጉባዔ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው አባዱላ ገመዳ ከስልጣን ተነሳ!

Print Friendly, PDF & Email

የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በምህፃረ ቃሉ ኦህዴድ በመባል የሚታወቀውን የህወሃት ተለጣፊ ድርጅት ከመሰረቱት እና ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ አመራር ሲሰጡ ከኖሩት አንዱ የሆነው አባዱላ ገመዳ ነው። ህወሃት ጠፍጥፎ የፈጠራቸውን ድርጅቶችና መሪዎቻቸውን እንደ ቤት እቃ ሲፈልግ ስልጣን ይሰጣቸዋል፣ ሲፈልግ ደግሞ እንደ አሮጌ እቃ ወርውሮ ይጥላቸዋል። የአይናቸው ቀለም ካላማረው ደግሞ ወደ እስር ቤት ይወረውራቸዋል።

በዚህ ጽሁፍ ለመግለጽ የምንፈልገው ስለ አባዱላ ከስልጣን መባረ ወይም አለመባረር ሳይሆን የትግራይ ወያኔዎች ከተለጣፊ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኦሕዴድን እንዴት እንደፈጠሩት የቀድሞው የህወሃት መስራችና ከፈተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት የጻፉትን ለአንባቢያን ለማካፈል ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የአመሰራረት ታሪክ

የቀድሞው የህወሓት ከፍተኛ መስራችና ባለስልጣን የነበረው አቶ ገብሩ አስራት ከጻፉት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” ከሚለው መጽሃፍ ከገጽ 151 – 153 የተወሰደ

************

ህወሃት ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ግንባር ለመመስረት ፍላጎት ቢኖረውም ይህ ፍላጎቱ ሊሳካለት አልቻለም ነበር። በተለይ ከኦነግ ጋር ተቀራርበን ግንባር ለመመሥረት ያደረግነው ሙከራ ከሽፎ እንኳንስ ግንባር ልንመሠርትና ተባብረን ለመሥራት አልቻልነም ነበር። ከኢሕአፓና ከኢዴኅ ጋርም ቀድሞ ከነበረን ቁርሾና የዓላማ ልዮነት የተነሳ ግንባር ለመፍጠርም ይሁን አብሮ ለመሥራትም አልቻልነም ነበር።

በዚህ ሁኔታ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በተናጠል ጥረት ማድረግ ጀመርን። በእኛ መስፈርት ዴሞክራሲያውያን የምንላቸውን ኦሮሞዎች ከውጭ በማሰባሰብም ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሥርተው አብረን እንዲሠሩ ለማድረግ ሞከርን። ለውጭ ጉዳይ ክፍላችንም ከተሰጡት ተልእኮዎች አንዱም ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ኦሮሞዎችን መለየት የሚለው ነበር። ይህን ጥረታችንን የሚያዩና የቆየው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የለም የሚለውን አቋማችን የሚያውቁ አንዳንድ ታጋዮችም ያፌዙብን ነበር። ከነዚህ ከሚያፌዙብን አንዱ በደደቢት የህወሓት መሥራች አባል የነበረው አሁን በጀርመን አገር በስደት የሚኖረው ካሕሳይ በርሄ /ዶክተር ግንጽል / ነበር። ካሕሳይ በጀርመን የሕዝብ አደረጃጀት ሥራዎችን ይከታተል የነበረ ሲሆን ማሌሊት ከተመሠረት በኋላ ድርጅቱን ትቶ እዚያው አገር ይኖራል። በአንድ ወቅት የህወሓት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሲሠራ ከነበረው ነጋሽ ተኽሉ ጋር መንገድ ላይ ተገናኙና “ካሕሳይ እዚህ ምን እየሠራህ ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ካሕሳይም “አንድ ዴሞክራት ኦሮሞ ባገኝ ብዬ እየፈለግሁ ነው” ብሎ በፌዝ እንደመለሰለት ይነገራል።

ያሰብነው የኦሮሞ ዴሞክራቶችን በአውሮፓና በአሜሪካ የማሰባሰብ ዕቅዳችን ተግባራዊ ለማድረግ ሳንችል ከመላው አውሮፓ ፕሮግራማችንን የተቀበለው ነጋሶ ጊዳዳ ብቻ ነበር። በወቅቱ ዶክተር ነጋሶ ከዴሞክራትነት ዐልፎ ሶሻሊስት አቋሞችንም ያራምድ ስለነበር የማሌሊትን አቋሞችም ተቀብሏቸው ነበር። ከዚያም በላይ የኦሮሞ ጥያቄ ኦነግ ወይም ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶችና ልሂቃን እንደሚሉት የቅኝ ግዛት ጥያቄ ስለሆነ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነጻነት መፈታት አለበት የሚል አቋም አለነበረውም። አቋሙ ጥያቄው ምንም ይሁን ምን በመጨረሻ በሕዝበ ውሳኔ ሊፈታ ከቻለ ችግር የለውም የሚል ነበር። እንዲያውም ዶክተር ነጋሶ ከህወሓት ጋር ከመተባበሩ በፊት ለረጅም ጊዜ ያራመደውን አቋሙን ይዞ ከህወሓትና ከማሌሊት ጋር ተቀራርቦ ሲሠራ ቆየ።

በአውሮፓና በአሜሪካ ከኛ ጋር የሚስማሙ ኦሮሞዎችን ባለማግኘታችን ትኩረታችንን በሙሉ ወደ አገር ቤት አዙረን ዓይናችንን ሻዕብያ በገፍ ወደማረካቸውና መንገድ ሲያሠራቸው ወደነበሩት ኦሮሞ ወታደሮች ጣልን። ትግራይ ውስጥ ይማረኩና እጃቸውን ይሰጡ ከነበሩት ኦሮሞ ወታደሮች ውስጥም አንዲሁ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለመመሥረት ብቃት አላቸው ያልናቸውን እናፈላልግ ጀመርን። እንደ አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑት ወታደሮች ሻዕብያ የማረካቸውና በፈቃዳቸው እጃቸውን የሰጡት ኦሮሞ ወታደሮች በመጀመርያ የተቀላቀሉት ኅብረ ብሔር የሆነውን ኢሕዴንን ነበር። ሆኖም ኢሕዴን እንደ አገር አቀፍነቱ መላውን ሕዝብ ሊያደራጅና ሊያሰባስብ የሚያስችለው ብቃት አለነበረው። በዚህ ምክንያትና ስናቀነቅነው ለነበረው የብሔር መብት መከበር ለትግሉ ይበልጥ ዋስትና ይሰጣል የሚል እምነት ስለነበረንም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲመሠረት ከፍተኛ ፋልጎት ነበረን። ከዚህ የተነሣም ኢሕዴን ውስጥ ይታገሉ የነበሩትንና ገና አዲስ ሆነው የኦሮሞ ድርጅትን ለመመሥረት ፍላጎት የነበራቸውን ወታደሮች በማሰባሰብ አንድ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲመሠረት ጥረታችንን ቀጠልን። ይህንን መመሪያውንም ተግባራዊ እንዲያደርግ ክንፈ ገብረ መድኅን ተመድቦ ንቁና ዝግጁ የሆኑ ኦሮሞ ወታደሮችን በማነጋገር የተዋጣለት ሥራ ከመሥራቱም ባሻገር አየኦሮም ድርጅት ለመመሥረት የሚያስችል አንድ ቅድመ ሁኔታ በጭር ጊዜ ውስጥ አንዲሟላም ረድቷል።

የኦሮሞን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በማቋቋም ረገድ ግንባር ቀደም ከነበሩት መኻክ

1ኛ/ ኩማ ደመቅሳ /ታዬ/ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ፣
2ኛ/ ኢብራሂም መልካ ከድርጅቱ ተሰናብቶ አሁን በንግድ ሥራ ላይ የሚገኝ፣
3ኝ/ አባ ዱላ ገመዳ በአሁኑ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ
4ኛ/ ባጫ ደበሌ በጀኔራልነት ማዕረግ የመከላከያ አባል የነበረ አሁን በጡረታ የተገለል፣ ሊጠቀሱ ይችላሉ።

እነዚህና ሌሎች ምርኮኛ የነበሩትን በመሠብሰብ የፖለቲካ ድርጅት ለመሥረት በሚያስችላቸው አንቅስቃሴና በወታደራዊ ሥልጠና አንዲሳተፉ ተደርጓል።

እነዚህ የቀድሞው የደርግ ወታደሮች የፖለቲካ ፕሮግራምና የሕገ ደንብ ረቂቆችን ካዘጋጁ በኋላ ትግራይ ውስጥ ዓዴት በተባለው አክሱም አካባቢ በሚገኘው ስፍራ ዝግጅታቸውን ከጠናቀቁ በኋላ በ1982 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ውስጥ ደራ አካባቢ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን /ኦሕዴድ/ መመሥረታቸውን አወጁ። በእርግጥ የኦሕዴድ የፖለቲካ ፕሮግራም ከህወሓትና ከኢሕዴን የሚለይ አልነበረም። ኦሕዴድ በፕሮግራሙ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን በጠላትነት ፈርጆ ጥያቄ የብሔር ሆኖ እስከ መገንጠል የሚለውን መብት አካቶ ነበር። የኤርትራ ጥያቄም የቅኝ ግዛት ጥያቄ መሆኑን ተቀብሎ በዚህም ለስትራቴጂያዊ ግንባር የሚያበቃውን መስፈርት አሟልቶ ነበር። ይህ ክንውን ጎድሏል ያልነውን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ስላሟላ ግብችን እንደተሳካ ቆጥረነው ነበር።

የኦሕዴድ መመሥረትና ለትግል መዘጋጀት በወቅቱ የነበረውን የደር ሥር ዓት ለመደምሰስ እጅግ ጠቃሚ ነበር። ሆኖም ከሞላ ጎደል በምርኮኛ ወታደሮች የተቋቋመው ድርጅት የኦሮሞ ምሁራንን ባለማካተቱ ትልቅ ክፍተት ነበረው። ልሂቃኑ የሕዝብን ፍላጎት በመቀመርና በመግለጽ የማይተካ ሚና ስላላቸው እነርሱ ያልተሳተፉበት ፓርቲ ምስረታና መሪነት አጠራጣሪ መሆኑ አይቀርም። ሌላው ችግር ደግሞ የኦሕዴድ አባላት የተገኙት ማዕከላዊነትን ከሚያጠብቀው ከደርግ ወታደርዊ ተቋማት በመሆኑ በተቋቋመው ድርጅት ፀረ ዴሞክራሲዊ አዝማሚያ ሥር እንዲሰድ እርሾ ሊሆን መቻሉ የሚደቅነው አደጋ ነበረው።

********

የቀድሞው ኢሕዴን መስራችና ሊቀመንበር የነበረው አቶ ያሬድ ጥበቡ ደግሞ ስለ ኦህዴድ ጽንስ – ውልደትና – እድግት ያለውን የህይወት ታሪኩን እንዲያ ያብራራሉ።