በአማራነት እየተነሳ ያለው የዘር አደረጃጀት ለአ.ግ.7 በጣም አደገኛ ሁኔታ እየፈጠረ ነው!! ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

Print Friendly, PDF & Email

አርበኞች ግንቦት 7 የመከፋፈልና የመበተን አደጋ እንደገጠመው ሊቀመንበሩ ለደጋፊዎቹ በይፋ አረጋገጠ!!

(ክፍል 1)

የአርበኞች ግንቦት 7 የኤርትራው ጉባኤ የተሳካ እንደነበር የድርጅቱ አመራሮች ለሚደያ የተለያየ የሃሰት መግለጫ ሲሰጡ የሰነበቱ ቢሆንም የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሻዕቢያ ባለስልጣኖች በተገኙበት ከተለያዩ ሃገራት ለሰበሰባቸው ደጋፊዎቹ ብቻ አስመራ ከተማ በህግደፍ ጽ/ቤት ውስጥ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ ባካሄደው የመጀመሪያው ዝግ ስብሰባ ድርጅቱ ከፍተኛ የሆነ የመከፋፈል አደጋ እንደገጠመውና የነበረው ጥቂት ሰራዊትም እየተበተነ መሆኑን በማመን ለደጋፊዎቹ የይስሙላ ይቅርታ መጠየቁ ታውቋል።

ይህ የመጀመሪያው ስብሰባ በድርጅቱ ሊቀመንበር በዶ/ር ብርሃኑ የተመራ ሲሆን በስብሰባው ላይ ከተለያዩ ሃገራት ከመጡት የብርሃኑ ደጋፊዎች በተጨማሪ ግርማቸው የተባለው እና ሌሎች ኤርትራ የቆዩ ጥቂት የብርሃኑ ደጋፊዎችን ሚካኤል የተባለ የሻዕቢያ ተወካይ ከአጃቢዎቹ ጋር የተገኙ ሲሆን የድርጅቱ አመራር የነበሩት መአዛው ጌጡ፣ አሰፋ ማሩ (አመነሸዋ) እና ሩርጃባ አሰፋ ያልተገኙበት ስብሰባ ነበር ።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ በዚህ ስብሰባ ላይ ያለፉት ሁለት ዓመታት ጉዞን በተመለከተ ለተሰበሰቡት ደጋፊዎቹ በሰጠው ማብራሪያ፡-

– በእነ መአዛው ጌጡ የሚመራ አንጃ ተፈጥሮ ድርጅቱ ለሁለት እንደተከፈለ፣
– ጥንስሱ በኢንተርኔት አንመራም የሚል አቋም ሲያራምድ በነበረው በዘመነ ካሴ መጀመሩንና በውጭ ሀገር የሚገኙ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መከፈላቸውን፣
– ይህ የአርበኞች ግንባር አንጃ ብርሃኑ ነጋ አይመራንም የግንቦት 7 ተፅእኖ አንቀበለም የሚል አቋም በማንፀባረቅ ላይ እንደሚገኝ፣
– ችግሩን በተለያየ ጊዜ በሽምግልና ለመፍታት ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ መቅረቱን፤
– አንጃው በፈጠረው ችግር ሠራዊቱ በቡድንና በግል ወደተለያዩ አካባቢ መበተኑን እና ይህንንም ለማስተካከል የኤርትራ መንግሥት ባደረገው ድጋፍ ከቀሩት በጣም በጣት የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት ጋር ግምገማ መደረጉን፣ በግምገማውም

•  መአዛው ጌጡ ስልጣኑን ከብርሃኑ ነጋ ለመቀማት ያሴር እንደነበር ማመኑን፣
•  አሰፋ ማሩ (አመነሸዋ) እና ኑርጀባ የሚዋዥቅ አቋም እንደነበራቸው፣
•  አንድ አመራር ሊጠፋ ሲል በመያዙ እስከ አሁን መታሰሩን ገልጿል። (ይህ ግለሰብ በሻዕቢያ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ህይወቱ በአደጋ ላይ መሆኑ ተረጋግጧል።)

– ግምገማውን ተከትሎ ጉባዔ እንዲጠራ መወሰኑን፣ አንጃው ጉባዔው እንዳይሳካ የተለያዩ ሙከራዎች ቢያደርግም በሻዕቢያ ሙሉ ትብብርና ድጋፍ ለጉባዔው እለት መደረሱን ፣
– በዚህ ጉባዔ ላይ ከሠራዊቱ ውስጥ 50 የማይሞሉ አባላት እንደሚሳተፉ እነርሱም በአንጃው የተለያየ በደል (እስር፣ ግርፋት፣ ከባድ የጉልበት ሥራ ……) የደረሰባቸው በመሆኑ የተጎሳቆሉ መሆኑን፣
– ከአንጃው ጋር ትብብር ያደርጉ የነበሩት ሌሎች የአመራርና የሰራዊት አባላት በጉባዔው እንደማይሳተፉና ሐሬና ላይ ለብቻ ተነጥለው እንደሚገኙ (ታስረዋል ለማለት አልተፈለገም)፣
– መአዛው ጌጡ እና ቡድኑ ዘራፊና በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳታፊ መሆኑን ለዚህ የኤርትራ መንግሥት የተደበቁ በርካታ መሣሪያዎችና ገንዘብ እንዳገኘባቸውና በምርመራ ላይ መሆኑን በመወንጀል፣

የዚህ ሁሉ ችግር ዋና መነሻው የተበላሸ የአሰራር ባህልና ልምድ ካለው ጋር ራሱን የአማራ ወኪል ነኝ ከሚለው የሽፍቶች ስብስብ ከሆነው የአርበኞች ግንባር ጋር የተደረገው ውህደትና ውህደቱን ተከትሎ የአመራር ቦታ በአቅም ሳይሆን በኮታ መደልደሉ መሆኑን የገለፀው ብርሃኑ ነጋ በዚህ ለፈፀምነው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን በማለት መሬት ላይ በሌለ የሃሰት ወሬ ሲነዱ የከረሙት ከተለያዩ ሃገራት ወደ አስመራ የገቡት የድርጅቱ አባላት ኤርትራ ውስጥ በሚያጋጥማቸው ያልጠበቁት ሁኔታ እንዳይደናገጡ ከወዲሁ ለማረጋጋት ጥረት በማድረግ ለጉባኤው እንዲዘጋጁ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።

(ክፍል 2)

በአማራነት ዙሪያ እየተነሳ ያለው አሉባልታና የዘር አደረጃጀት ለድርጅታችን ህልውና በጣም አደገኛ ሁኔታ እየፈጠረ ነው !! ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ባለፈው የአርበኞች ግንቦት 7 ጉባኤ ዘገባችን አርበኞች ግንቦት 7 የገጠመውን የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ዋናው መንስኤ ከአርበኞች ግንባር ጋር ያለበቂ ጥናት የተደረገው ውህደት መሆኑን በመጥቀስ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ድክመቱን በአርበኞች ግንባር የአመራር አባላት ላይ ለማላከክ ጥረት እንዳደረገ መግፃችን ይታወሳል። በዚሁ ጉባኤ የተሳተፉት ምንጮቻችን አስመራ በዝግ ከተካሄደው የመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ቀጥሎ የነበረውን ሂደት በብዕራቸው የዘገቡልንን እንዳለ እንደሚከተለው አቅርበናል። በመጀመሪያው ቀን የአስመራ ዝግ ስብሰባ ብርሀኑ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ካብራራ በኋላ የነበሩትንና ያሉትን እንቅፋቶች ለማስወገድ አዲስ የሚግባባና የሚናበብ አመራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያለበለዚያ የአርበኞች ግንቦት 7 ውድቀት እውን እንደሚሆን፤ የሚመረጠው አመራርም በኤርትራ ጠቅልሎ መግባት የሚችል መሆን እንዳለበት የጉባዔው ዓላማም ይህ መሆን እንደሚገባው በማሳሰብ ለቀጣዩ ጉባዔ ደጋፊዎቹን ያዘጋጀበትን ስብሰባ በዚሁ መልኩ አጠቃለለ።

ከዚህ በመቀጠል ከውጭ ሀገር ከመጡት አባላት ጋር የሆቴል ክፍያን በተመለከተ “የትራንስፖርት እራሳችሁ ቻሉ የሆቴሉን ደግሞ እኛ እንችላለ”ን በሚል ከየሃገሩ ሲነሱ ቀደም ሲል ቃል ከተገባው ውጪ አስመራ ከገባን በኋላ የሆቴል ወጫችሁም እራሳችሁ ቻሉ የሚል ያልነበረ አዲስ ሃሳብ በመቅረቡ ለጉባኤ ከተለያየ ሃገር ተጠርቶ የገባው የድርጅቱ አባል ገና ከጅምሩ ከፍተኛ ተቃውሞ አነሳ። ሁኔታው ያላማረው የድርጅቱ ሊቀመንበር ከሻዕቢያ የቅርብ አለቆቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ እሺ መክፈል የምትችሉ ካላችሁ የአልጋ ወጪያችሁን እናንተ ራሳችሁ ብትሸፍኑ፣ የለም አንችልም የምትሉ ከሆነ ግን እኛው እንሸፍነዋለን የሚል ማስታረቂያ የሚመስል ሃሳብ በማቅረቡ ከውጪ የመጣው አባል ተከፋፍሎ በናይል፣ በኒያላና ሌሎች ሆቴሎች እንድናርፍ ተደረገ።

የሚያሳዝነው እነዚህ ሆቴሎች የኮኮብ ደረጃ የተሰጣቸው ቢሆንም በቀን አንድ የውጪ እንግዳ እንኳን የማይጎበኛቸው መሆናቸው ሲታይ ኤርትራ አፍሪካዊትዋ “ሰሜን ኮርያ” የሚል ስያሜ ማግኘትዋ ብዙም የሚገርም አይደለም። በማግስቱ ጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሰብሳቢው በሁለት አውቶቡሶች ተከፍለን እንድንሳፈር ከተደለደልን በኋላ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ራሱ መርጦ ከውጪ ሃገር ያስመጣቸው ደጋፊዎቹን እንኳን ማመን ባለመቻሉ ከሻዕቢያ በተሰጠው ቶዮታ ፒክ አፕ ተሳፍሮ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 የበላይ ተጠሪና የዶ/ር ብርሃኑ የቅርብ አለቃ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶችን በተመለከተ የሻዕቢያው ፈላጭ ቆራጭ መኮንን እንደሆነ የሚነገርለት ኮ/ል ፍጹም በሌላ ቶዮታ ፒክ አፕ መኪና ተሳፍረው ጉዞ ጀመርን።

በምዕራባዊ ኤርትራ ጋሽ ባርካ በአንድ ትምህርት ቤት መሰል ግቢ አውቶቡሶቹ ሲደርሱ ቁጥራቸው ከ50 የማይበልጡ እጅግ በጣም የተጎሳቆሉ ያደፈና የነተበ ልብስ የለበሱ የሀዘን ድባብ የሚታይባቸው ወጣቶች ሥርዓት በሌለው መንገድ ተሰልፈው ስናገኛቸው ሁላችንም ደነገጥን። ከፊታቸው ከወገቡ የጎበጠ እድሜው የገፋ ሽባባው የሚባል የቀድሞ የኢህአፓ አባልና ከአሜሪካ ድርጅቱን የተቀላቀለ ቆሞ የልጆቹን ሰልፍ ሲያተባበር ተመለክትን። የወጣቶቹን ሁኔታ የተመለከተው ሁሉም ከውጪ የመጣው ተሰብሳቢ በከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን ውስጥ ገብተን ሁላችንም ማልቀስ ጀመረን። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በዚህ ጉባዔ ላይ ከሠራዊቱ ውስጥ 50 የማይሞሉ አባላት እንደሚሳተፉ እነርሱም በአንጃው የተለያየ በደል (እስር፣ ግርፋት፣ ከባድ የጉልበት ሥራ የደረሰባቸው ናቸው በማለት አስመራ በተካሄደው የመጀመሪያው ቀን ዝግ ስብሰባ የተናገረው ይህንን ጉድ አይተን እንዳንደነግጥ አስቀድሞ ለማዘጋጀት የታቀደ እንደነበር የገባን ይህንን ከጠበቅነው በላይ የሆነው አሳዛኝ ትእይንት በአይናችን በብረቱ ካየን በኋላ ነበር።

እነዚህ ወጣት የኢትዮጵያ ልጆች በድርጅቱ ፕሮፖጋንዳ ተታልለው ኤርትራ ውስጥ እውነት ትግል ያለ መስሎዋቸው ከድርጅቱ ጎን ተሰልፈው ለመታገል ወደ ኤርትራ ከገቡ በኋላ ያለ በቂ የምግብ አቅርቦት በሻዕቢያ እርሻ በነፃ ሲሰሩ ከርመው ለጉባኤው ማድመቂያ ተብሎ ከየማሳው ተሰብስበው የመጡ መሆናቸውን ልጆቹ ራሳቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰማን።

ሽባባው ሰልፈኛውን ተጠንቀቅ ሲል ሁሉም ወጣቶች በጦር መሣሪያ ምትክ በእጃቸው በያዙት የተለያየ መጠን ያለው እንጨት ቀና በማድረግ መዝሙር መዘመር ጀመሩ። መዝሙሩን ከጨረሱ በኋላ ከውጪ ከመጣነው እንግዶች ጋር ሰላምታ የተለዋወጡ ሲሆን በቅርበት የመመልከት እድሉ ስናገኝ ወጣቶቹ ከማሳ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ከማይመች የማጎሪያ ካምፕ ለሰልፍና ለማስመሰል ቲያትር የመጡ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብንም። ከልጆቹ ጋር ተቀላቅለን በግል መነጋገርና ማውራት ስንጀምር ኤርትራ ውስጥ የአርበኞች ግንቦት 7 የሚባል ሰራዊት እንደሌለ፤ ብዙዎቹ በሃሬና እና አካባቢው በሻዕቢያ ወታደሮች ጥበቃና ቁጥጥር ታግተው እንደሚገኙ፣ እነሱም የእርሻ ሥራ በመስራት ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበረ ሲሆን አብዛኛዎቹ ወጣቶች የመአዛው ጌጡ አድናቂ መሆናቸውን ሲናገሩ መስማት ቻልን።

ከዚህ አሳዛኝ ትዕይንት በመቀጠል ከውጪ የመጣን የድርጅቱ አባላትና ወጣቶቹ ወደ ስብሰባው አዳራሽ እንድንገባ ሲደረግ መአዛው ጌጡ በኮሎኔል ፍጹምና ሚካኤል፣ በታጠቁ የሻዕቢያ ወታደሮች ታጅቦ ወደ አዳራሹ ሲገባ ተመለክትን። ሁኔታው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አስመራ ውስጥ አስቀድሞ እንደነገረንና ቀድሞ እንደተወራው አርበኛው መዓዛው ጌጡ በሻዕቢያ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ለማንም ግልፅ ነበር። ኑርጀባ አሰፋ እና አሰፋ ማሩ /አመነሸዋ/ ከነአምን ዘለቀ ጋር ተከታትለው ወደ ስብሰባው አዳራሽ ገቡ።

ተሰብሳቢው ቦታውን እንደያዘ የደርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመክፈቻ ንግግር አደረገ። በወቅቱ መአዛው ጌጡ ምንም ሳይናገር በማግስቱ ስብሰባው እንደሚቀጥል ተገልፆ በሜዳ የተዘጋጀልንን የምግብና የመጠጥ ግብዣ ተጀመረ። በግብዣው የመጠጥ ሃይል ዶ/ር ብርሃኑና እነ ኮሎኔል ፍፁም ሰክረው ህሊናቸውን ስተወ ሲወላገዱ የተመለከተው የድርጅቱ የዲያስፖራ አባል ያየውን ማመን አቃተው። የሻዕቢያ ሰዎች መአዛው ጌጡን ከተቀመጠበት በግድ አስነስተው ከብርሃኑ ጋር እንዲጨፍር ሲያደርጉ ለሚድያ ፍጆታ እንዲውል ሆን ተብሎ ታስቦበት የተካሄደ ድራማ እንደነበር የገባን ግን በኋላ ፎቶግራፉ በየሶሻል ሚዲያው ከተሰራጨ በኋላ ነበር።

በጉልበት ስራና በምግብ እጦት የተጎቆሳቆሉት ወጣቶቹ ከመጠጡ ትንሽ ከተጎነጩና ከሰከሩ በኋላ ያልጠበቅነው እና ሁላችንም ያሰደነገጠ ሁኔታ ተፈጠረ። ሁሉም በአንድነት መአዛው ጀግና ብርሃኑ ነጋ የሻዕቢያ ሙሽራ እያሉ ያለምንም ፍራቻ መጮህ ሲጀምሩ ሁላችንም ብርክ ያዘን። የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ነው ነገሩ። በማግስቱ የሻዕቢያ ሰዎች አስቀድመው ቦታቸውን እንዲይዙ ከተደረገ በኋላ አስቀድሞ አስመራ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ከተነገረን ውጪ ለይስሙላ ኑርጀባ አሰፋ የጉባኤው አዘጋጅ ተብሎ በመድረክ ላይ ቢቀመጥም ብርሃኑ ነጋ ከታች ሆኖ አጠቃላይ ሂደቱን በበላይነት ሲመራው ተመለክትን።

በዚህ ሁሉ ትእይንት ውስጥ መአዛው ጌጡ እጁን አፉ ላይ አድርጎ በመገረም ሲመለከት ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጉባዔው ሲከፈት የመጀመሪያ ቀን ከውጭ ሃገር ለመጣነው አባላት ያደረገውን ንግግር ለተሰብሳቢው ጆሮ በሚመጥን መልኩ በጽሑፍ በሪፖርት መልክ አቀረበ። ሪፖርቱ በዋናነት ባለፈው ሁለት ዓመት በአመራሩ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ምንም ሥራ ሳይሰራበት የባከነ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሁላችንም ማመን ያቀተንን ድርጅቱ የሚከተሉት ዋና ዋና ችግሮች እንዳሉበት ገለፀ፡-

– ለትግል የሚሆን በቂ ገንዘብ አለመኘቱን ፣
– የአልባሳት አቅርቦት፣ የቀለብ እጥረትና የጥራት ችግር መኖሩን ፣
– በጥይት እጥረት ስልጠና የወሰዱ የተኩስ ልምምድ አለማድረጋቸው፣
– የሠራዊቱ በተለያየ ምክንያት መክዳት (በፍርሃት፣ የመሣሪያ ፍቅር፣ ግዳጅ የለም ኩርፊያ፣ ግዳጅ ሲሰጥ ማፈግፈግ፣ ከትምህርትና ስልጠና መቅረት…..)
– ከኤርትራ የሚደረጉ ድጋፎች በምክትል ሊቀመንበሩ በኩል (መዓዛው ጌጡ መሆኑ ነው) ለሠራዊቱ አለመድረሱ፣
– ድርጅቱ ወደ ሃገር ውስጥ ገንዘብ ማስገባት አስቸጋሪ እንደሆነበት፣
– ድርጅቱ ከአገር ቤት ወያኔ የሚልካቸውን ሰርጎ ገቦች ፈፅሞ መቆጣጠር እንዳልተቻለ፣
– የመገናኛ ሬዲዮ ባለመኖሩ በስልክ የሚደረገው ግንኙነት እየተጠለፈ የድርጅቱ አባላት በወያኔ እየተያዙ መሆኑን፣
– ድርጅቱ የተቀናጀ እና ብቃት ያለው አመራር እንደሌለው ፣
– በአማራነት ዙሪያ በድርጅቱ ላይ እየተነሳ ያለው አሉባልታ እና ወደ ዘር አደረጃጀት ማዘንበል ወዘተ ለአርበኞች ግንቦት 7 ህልውና አደገኛ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን የሚገልፅ ይዘት ያለው ተስፋ አስቆራጭ ሪፖርት አቀረበ።

(ክፍል 3)

ሁሉም ነገር ወደ ደቡብ ጦር ግንባር!! – የአርበኞች ግንቦት 7 የአመራር አባላት የምርጫ ትዕይንት

በሁለተኛው ክፍል ያቀረብነው የአርበኞች ግንቦት 7 ጉባኤ ሪፖርታዥ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ድርጅቱ በውስጣዊ ችግር ተተብትቦ ላለፉት ሁለት አመታት ምንም የረባ ስራ ሳይሰራ ማሳለፉንና አሁንም የድርጅቱን ቀጣይ ህልውና የሚፈታተኑ እጅግ በርካታ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በማስመልከት ለጉባኤው ታዳሚ ያቀረቡትን ሪፖርት ይዘት ማስነበባችን ይታወሳል።

ባለፈው ባቀረብነው ሪፖርታዥ በገባነው ቃል መሰረት በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ምንጮቻችን ቀጣዩን የጉባኤው ሂደት (ትያትር) በተመለከተ በብዕራቸው የተረኩልንን እነሆ አቅርበናል። በክፍል ሁለት ሪፖርትዥ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የድርጅቱን ሁለት የችግርና ተስፋ አስቆራጭ አመታት ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ ጉባኤተኛው ድርጅቱ ገጠሙት በተባሉት ችግሮች ዙርያ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ሳይሰጥበት እንዲሁም መፍትሄ ይሆናል የሚላቸውን የበኩልን ሀሳብ ለማቅረብ እንኩዋን እድል ሳይሰጠው ወድያውኑ በኮሎኔል ፍፁምና በብርሃኑ ነጋ የተዘጋጀው የጉባኤ የመወያያ አጀንዳ ለቤቱ ቀረበ። በዚሁ መሰረት በሻዕቢያው ባለስልጣን በኮሎኔል ፍፁም ተዘጋጅቶ በድርጅቱ ሊቀመንበር በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለጉባኤው የቀረቡት አጀንዳዎች የሚከተሉት ነበሩ።

1. የንቅናቄውን ሰትራቴጂ መፈተሽና ማጽደቅ ፣
2. የንቅናቄውን መዋቅርን መፈተሽና ማጽደቅ፣
3. የንቅናቄውን መተዳደሪያ ህግ ላይ መወያየትና ማጽደቅ ፣
4. የሰራዊቱ ህገ ደንብ ላይ መወያየትና ማጽደቅ፣
5. የአመራር ምርጫ ማድረግ የሚሉ ናቸው።

ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 4 ድረስ የተዘረዘሩት አጀንዳዎች መጨረሻ በተራ ቁጥር 5 ላይ ለተቀመጠው ዋናው አጀንዳ ማጀቢያነት ከመቀመጣቸው በቀር ፋይዳ እንደሌላቸው ጉባኤተኛው ከአስመራ ጀምሮ ሲካሄድ ከከረመው ድራማ ለመገመት ብዙም አልተቸገረም። መጨረሻ ላይ ያረጋገጥነውም ይኸው በሚገባ የተቀነባበረው የነኮሎኔል ፍፁምና የዶ/ር ብርሃኑ ድራማ ነበር። ለማንኛውም በእያንዳንዱ አጀንዳ ዙርያ የተነሳው ሃሳብና የተደረሰው ውሳኔ ምን ይመስል እንደነበር እንደሚከተለው ቀርቧል።

አጀንዳ አንድ፡- የንቅናቄውን እስትራተጂ በተመለከተ የንቅናቄው ተልዕኮ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚፈጠርበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት መመስረት ሲሆን በስትራቴጂ ረገድ ይህ የትግል እስትራተጂ ሁለገብ ባህሪያት ያለው መሆኑ የሚታመንበት ቢሆንም ከዚህ የተሻለ የትግል ስትራቴጂ አለ የሚል ምክረ ሃሳብ ከጉባኤተኛው የሚቀርብ ከሆነ በዚያ ላይ ያተኮረ ውይይት ቢደረግ የሚል መሪ ሃሳብ ከድርጅቱ ሊቀመንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቀረበ። አስቀድመው በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተዘጋጁት የጉባኤው ታዳሚዎች በብርሃን ፍጥነት እጃቸውን በማውጣት “እስትራተጂው ወደ ድል የሚወስደን ብቸኛው እስትራተጂ በመሆኑ፤ ሁለገብ የትግል ስልት ሲባል ህዝባዊ ትግልና ህዝባዊ አመፅን (የትጥቅ ትግልን) አጣምሮ የያዘ ተመራጭ ስልት በመሆኑ ይህ ደግሞ አሁን ባለው ተሞክሮ ህዝባዊ አመፅ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነት ህዝባዊ ስለላንና ህዝባዊ አሻጥርን የሚያካትት ስለሆነ እስትራተጂው መቀጠል አለበት” በማለት በየተራ ተደጋጋሚ የሆነ ዲስኩር አሰሙ።

በማያያዝም “ለስትራቴጂው ተግባራዊነት ብቁ አመራር መፍጠር ብቻ ነው የሚያስፈልገው” በማለት እስካሁን ድረስ እስትራጂው ያሰገኘው ፋይዳና ጉዳት፣ ጠንካራና ደካማ ጎኑ ሳይገመገምና እስትራጂውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዱ የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦች ካሉ ከቤቱ እንዲቀርብና የጉባኤው ተሳታፊ እንዲወያይባቸው ሳይደረግ እስትራተጂው እንከን የለሽ ስለሆነ በነበረበት መቀጠል አለበት በሚል ባካሄዱት የንግግር ርብርብ እስትራጂው ያለምንም አይነት ውይይትና ማሻሻያ በዚያው እንዲቀጥል ፀድቋል ተባሎ ተወሰነ። በዚህ ውይይት ድራማው ያልገባቸው አንዳንድ የዋህ ተሳታፊዎች ስትራቴጂው በሃገር ውስጥ በዳር ሃገርና በውጭ ሃገር ያለውን ኃይል ሚና ማካተት የሚችል ነው ወይ? የሃገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍስ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ወይ? የሚሉና ሌሎችም አስተያየቶችና ጥያቄዎች ያነሱ ቢሆንም ሊቀመንበሩ ተጣድፈው መልስ በመስጠት በዚህ አጀንዳ ላይ የሚካሄደው ውይይት በአጭሩ ለመዝጋት ሲረባረቡ ለታዘበ ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶበት ባህር ተሻግሮ የመጣው ተሳታፊ ይህንን ድራማ ለማየት ነበር እንዴ የሚያሰኝ ነበር። ያልታደለች ሃገር ያልታደለ ህዝብ!! አልኩኝ በልቤ።

ይባስ ብሎ ለምን እንደታደሙ ያልገባቸው አንዳንድ ግልብ ዲያስፖራዎች ደግሞ በሃገራችን ውስጥ የብሔር ጥያቄ አለ ወይስ የለም? በሚል ላነሱት ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለና ጉዳዩ የገዥ ቡድኖች ፍላጎት እንደሆነ፣ የብሔር ጥያቄ አለ የምትሉ ሰዎች ካላችሁ ለጊዜው በጉዳዩ ላይ ከዚህ በላይ መሄድ አይኖርብንም፣ በዚህ አጀንዳ ላይ የሚካሄደው ውይይት መቆም አለበት። የዲሞክራሲ ጥያቄ ሲፈታ የብሔር ጥያቄም አብሮ ይፈታል በማለት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ውይይቱ በአጭሩ እንዲገታ በማድረግ በአጀንዳው ላይ የተካሄደው ውይይት በዚህ መልኩ እንዲዘጋ አደረጉ። ከዶ/ሩ ገፅታ ይነበብ የነበረው የቁጣ ስሜት ለተከታተለ ሰው በልባቸው ይህንን ጥያቄ የሚያነሱት የወያኔ ሰርጎ ገቦች መሆን አለባቸው ሳይሉ የቀሩ አይመስለኝም። አጀንዳ ሁለት፡- የንቅናቄውን መዋቅር በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7 አዲስ የተባለው መዋቅር በሊቀመንበሩ አማካይነት በፖወር ፖይንት ቻርት ለውይይት ቀርቦ ያለምንም አይነት ውይይትና ማስተካከያ ፀደቀ። በዚህ መሰረት የድርጅቱ አብይ መዋቅር ቀደም ሲል በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ተሰራጭቶ እንዳነበብነው ኤርትራ፣ ሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ተብሎ በ3 እንደተከፈለና የንቅናቄው ፅ/ቤትም በኤርትራ ውስጥ እንደሚሆን ተነገረን። ኤርትራ ውስጥ እንዲቀር የተወሰነበት አመራር ማን ይሆን? የሚል ሃይለኛ ስጋት የገባው ታዳሚው እርስ በርሱ መተያየት ጀመረ። በመቀጠል የንቅናቄው ሊቀመንበር፣ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ፣ የዲስፕሊንና ግልግል ኮሚቴ ከጠቅላላ ጉባዔ ሲመረጥ ከአሁን በኋላ ምክትል ሊቀመንበር የሚባል የሃላፊነት ቦታ አይኖረንም ተባለ። የምክትል ሊቀመንበርነቱን ቦታ አያስፈልግም የተባለው የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የነበረው መዓዛው ጌጡን ለማስወገድ ቢሆንም ዋና አላማው ግን የአርበኞች ግንባር ሰዎች የምክትልነት ቦታ ይገባናል የሚል ጥያቄ እንዳያነሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት ነበር።

ከዚህ ውጪ ራሳቸውን የድርጅቱ ምክትል ሊቃነመናብርት እንደሆኑ በየፊናቸው በሚድያ ሲነግሩን የከረሙት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት (እነ አበበ ቦጋለ፣ ነአምን ዘለቀ፣ ዶ/ር አዚዝ መሃመድ …ወዘተ ምን እንደተሰማቸው ባናውቅም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በዚህች በአጭር ጊዜ የኤርትራ ቆይታቸው የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ለድል ምን ያህል አሰፈላጊ እንደሆነ በእነ ኮሎኔል ፍፁም አማካይነት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምክር ወይም መመሪያ ቢጤ እንደተሰጣቸው የሚያጠራጥር አይደለም።

የኤርትራው መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ባስቆጠረው የትግልና የስልጣን ዘመናቸው እንደ ምክትል አምርረው የሚጠሉት የሃላፊነት ቦታ እንደሌለ ይነገርላቸዋል። ገና ያኔ በረሃ በትጥቅ ትግል ውስጥ የድርጅታቸው የሻዕቢያ ምክትል ሃላፊ በነበሩበት በነዚያ የመጀመሪያዎቹ አመታት ሳይቀር የምክትል መሪነት ቦታ ከድርጅቱ እንዲወገድ ሽንጣቸውን ገትረው ሲማገቱ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ የትግል ጓደኞቻቸው ያስታውሱታል ይላሉ፡። በድርጅቱ ውስጥ የመሪነት ስልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ የመጀመሪያው ተግባራቸው በሻዕቢያ ውስጥ ምክትል አመራር የሚባል የስልጣን እርከን እንዳይኖር ማድረግን እንነበር ያስታውሳሉ።

ኤርትራ ነፃነትዋን ከተጎናፀፈች በኋላም ቢሆን በመንግስት መዋቅራቸው ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚባል የስልጣን ቦታ እንዳይኖር በማድረግ እስካሁን ድረስ ሃገሪቱን በፈላጭ ቆራጭነት እየመሩ ብቻ ሳይሆን “የሰይጣን ጆሮ አይስማ እንጂ” ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እንደማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስጋ የለበሱ ሰው ናቸውና በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ አደጋ ምክንያት በህይወታቸው ላይ አንዳች አደጋ ቢያጋጥም ሃገሪቱን ያለ ህጋዊ ተተኪ መሪ እንድትቀር እድርገዋታል በማለት የሚያሙዋቸው ኤርትራውያን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ይባላል።

ከአርበኞች ግንቦት 7 ጠቅላላ ጉባዔ ቀጥሎ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚ እንደሚኖር፣ ምክር ቤቱ 30 ኤርትራ ውስጥ ከሚገኙ፣ 15 በውጭ ሃገር ከሚገኙ አባላት 8 ደግሞ ሃገር ውስጥ ከሚገኙ አባላት በድምሩ 53 አባላት እንደሚኖሩት፣ 10 ተጠባባቂም አብረው እንደሚመረጡ ተነገረን። በኑሮና በከባድ የጉልበት ስራ ተጎሳቁለው ያየናቸውን በቁጥር 50 የማይሞሉ ታጋዮችን ለመምራት 53 አዛዥ ጄኔራሎችን መምረጥ ማስፈለጉ የሚያሰገርም ነው። በማያያዝም ስራ አስፈፃሚው ሊቀመንበሩን ጨምሮ 13 አባላት እንደሚኖሩት 5ቱ (ሊቀመንበሩና 4 የየዘርፎቹ ኃላፊዎች) የስራ አስፈፃሚ ቋሚ ኮሚቴ እንደሚሆኑ ማብራሪያው ቀጠለ።

ከዚያ በኋላም ሁሉም ስራ አስፈፃሚዎች ተቀማጭነታቸው ኤርትራ ይሆናል በሚል የተወሰነ መሆነን የተነገረን ቢሆንም ዶ/ር ታደሰ ብሩ በሌለበትና አሁን ባለው ሁኔታ የእንግሊዝ መንግስት በመሰረተበት ክስ ምክንያት ወደ ኤርትራ መግባት እንደማይችል እየታወቀ “እንዲመረጥ” መደረጉን ጭምር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለጉባኤተኛው አሳወቁ። ውሳኔው አርበኞች ግንቦት 7 ከሰሜን ወደ ደቡብ ጦር ግንባር ጉዞ መጀመሩን የሚያበስር ዜና ነበር።

ይቀጥላል….

Source: http://www.ethiopatriots.com/