ኢረቻ 2010 በሸማ ደምቆ ዋለ!

Print Friendly, PDF & Email

በመጀመሪያ በዓሉን ለፖለቲካ ፍጆታና ለጥላቻ መዝሪያ ለማትጠቀሙበት የበዓሉ አክባሪዎች እንኳን አደረሳችሁ። ኢረቻን በተመለከተ መኩሪያ ቡልቻ የተሰኙ ሰው ayyantu.com ላይ የጻፉትን ረጅም ጽሁፍም አነበብኩ። በርካታ ጥያቄዎችን ግን መጠየቅ እሻለሁ።

ጥያቄ ፩

ለበዓሉ ድምቀት የዋለው ሸማ “የተጫነ” ወይስ የኦሮሞ?

ጸሐፊው ይህን አስፍረዋል…

የበዓሉ ተሳታፊዎችን በቀለማት ያሸበረቁ አልባሳትን ያያችሁ እንደሆነ በበዓሉ የኦሮሞ ብቻ የሆኑ እሴቶቻችን ሆን ተብሎ የተቀበሩበትን ድንጋይ ፈነቃቅለው እየወጡ እንዳሉ ያሳያል።

ተው እንጅ ጌታው? “ሸማ በላያችን ላይ ተጫነ” የትለው ንግግራችሁ የገደል ማሚቶ እኮ ገና አልጠፋም። ታድያ እንዴት ሆኖ ነው በኦፒዲኦ ባንዲራ “ያጌጠው” ሸማ uniquely Oromo የሚሆነው?? የዋለልኝ መኮነንን “ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የአማራ ባህል በግድ ተጭኗል” ብሎ ሸማን እንደምሳሌ መጥቀስን ተከትሎ በኦሮሞ ምሁራን ዘንድ የሚዘወተር ጉዳይ አለ፤ “አበሾች ሸማን በግድ ላያችን ላይ ጭነዋል” የሚል። ይህ በጽሁፍ ሰፍሮ በድምጽ ተቀድቶ ያለ ሀቅ ነው። ጥያቄየ ታድያ በባዕድ አገር ባንዲራ ያሸበረቀውን ሸማስ ማነው የጫነባችሁ? የሚል ነው።

የኦ.ፒ.ዲ.ኦ ባንዲራ 26 ዓመቱ ሲሆን ሸማ ግን ዕድሜው ከአማራ ዕድሜ ጋር ተቀራራቢ ነው። ታድያ ለዘመናት የነበረውን ሸማ በኦፒዲኦ/ኦነግ የሰንደቅ ቀለሞች ስለከለስከው ያንተ ይሆናል ወይ? አሁንም ሸማው ተጭኖብኛል የምትል ከሆነ የኦፒዲኦ /ኦነግ ባንዲራ ያለው ሸማም ተጭኖብሃል። ወላይታዎችን ውሰድ፤ ገዲዎችንም እይ። እነዚህ ሕዝቦች ሸማን በሚፈልጉት ቀለም፣ ዲዛይን ወርድና ስፋት ይጠቀማሉ፤ ተጫነብን ሲሉ ግን ሰምተን አናውቅም። የሸማ ልብስ ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት የተወሳሰብ የሽመና ጥበብን ይጠይቃል። የጥበቡ ባለቤት ታላቁና ጥበበኛው አማራ ነው። አማራ ያለውን ለሌሎች የሚያካፍል ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ሸማችን ሌሎች ወገኖች ቢለብሱት ቅር አንሰኝም። ያለበሰህን አካል ግን “በወጣ ይተካ” ብለህ ትመርቃልህ እንጅ ጫነብኝ አትልም። ጉዳዩ እዚህ ላይ አያበቃም። አሁን አሁን ጫኑብኝ ተረስታ “ሸማ ኬኛ” እየተባለ የቻይና ጀርሲ የአማራ ሆናለች። ይህ ግን አይሆንም! ሻማ የኛ ነው! ሌሎችን ግን አትልበሱት አንልም። በግድ አለበሱኝ የሚል አካል ካለም አጥቦና ተኩሶ እንዲመልስልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

ኢረቻ በዓል 2010 ዓ.ም

ጥያቄ ፪

እውን ኢሬቻ “Thanksgiving” ነው ወይ?? ከሆነ በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘት አይኖረውም?

ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተዘወተረ ያለ አንድ ነገር አለ። እሱም ኢሬቻን “the oromo version of Thanksgiving” የሚል። Thanksgiving ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው የፈረንጅ በዓል ሲሆን ክርስቲያን የሆነው ብቻ ያከብረዋል። ኢሬቻ “ባህላዊ” ከሆነ ሁሉም የዚያ ባህል ተጋሪ የሆኑ ህዝቦች ያከብሩታል (ሀይማኖትን ሳይለይ)፤ ባህላዊ ነው የሚባል ከሆን ግን the oromo version of Thanksgiving ሊሆን አይችልም። Thanksgiving ፈጣሪ ያለህን ሁሉ ባርኮ ስለሰጠህ በምትኩ የምትሰጠው የከበረ ምስጋና ነው። ኢሬቻ Thanksgiving ከሆነ ለምን ክርስቲያን ኦሮሞ፤ ሙስሊም ኦሮሞ፤ ዋቄ ፈታ ኦሮም በህብረት ያከብረዋል የኔ ጥያቄ ነው?

ጥያቄ ፫

“ከቅኝ ግዛት በፊት ኢሬቻ የክረምቱ ወራት መገባደዱን የሚያበስር ክብረ በዓል ነበር”

ጥያቄየ ታድያ ቅኝ ተገዝታችሁ ነበር ወይ? የሚል ነው! ከሆነ ከመቸ እስከ መቸ? በማን?

ከጽሁፉ ለመረዳት እንደቻልኩት ግን አሁንም ቅኝ ላይ እንደሆናችሁና ገዥዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው። ሰውየው በጽሁፉ ከቅኝ ግዛት በኋላ ባህሉ በቅኝ ገዥዎች እንዲጠፋ መደረጉንና ባለፉት 50 ዓመታት እንደገና ማቆጥቆጥ መጀመሩን ያትትና በ1903 ዓ.ም ሆራ ሀይቅ ላይ እሬቻ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሲከበር የሚያሳይ ፎቶ (captioned lakehora1903) ለጥፏል። ከፎቶው ጀርባ ብረት ለበስ ከባድ የጦር መሳሪያ አይታየኝም፤ በተሰበሰቡ የበዓሉ ታዳሚዎች አናት ላይም የጦር ሄሊኮፕተር ሲያንዣብብ አይታይም። በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተከወነ እንደነበረም ምስክር ነው ፎቶው። ታድያ 1903 ዓ.ም ከ50 በፊት ነው እንዴ? ፎቶውን አሁንም ደግሜ ደጋግሜ በደንብ አጤንኩት! ፈጽሞ በቅኝ ግዛት ላይ ያሉ ህዝቦች አይመስሉም። በቅኝ ግዛት ላይ ያለ ሕዝብ የራሱን ባህል አያከብርም። ይልቁን የቀኝ ገዥዎችን ባህል ተገዶ ይከውናል። ይህን አብዛኛው የአፍሪካ አገራት የነበራቸው ቅድመ-ቅኝ ግዛት ባህልና ወግ ቅኝ በነበሩበት ጊዜ እንዴት ተኖ እንደጠፋ ማየቱ በቂ ነው። ቅኝ ብትገዛ የምታከብረው ዓመታዊ የስፔንን ከበሬ ጋር ውጊያ እንጅ ኢሬቻን አይደለም። “ኢሬቻ አሁን ከቅኝ ግዛት ነጻ የምንወጣበትን ተስፋ የሚያሳየን ባህል ነው” ይለናል ጸሀፊው። ታድያ እኔ “መልካም ኢሬቻ” ብለው አግባብ ነው ወይ?

ኢረቻ በዓል በድሮ ግዜ

ጥያቄ ፬

“የአቢሲኒያ ነገስታትና ቀሳውስት በወረራ በያዙት መሬት ላይ ቤተ ክርስቲያን እያነጹ የኦሮሞን ሀይማኖት አስቀይረዋል፤ ማንነቱን አስረስተዋል”

የትኛውን መሬት ነው በወረራ የያዝነው? ፈጥጋርን? ባሊን? ደዋሮን? እናርያን?

ከወረራ በፊት አርሲ ፈጥጋር፤ ሐረርጌ ደዋሮ ባሌ ባሊ ተብለው ይጠሩ እንደነበር እኮ ሽ ከሚሊዮን ማስረጃ እና መረጃ አለን። ሌላው ቢቀር የግራኝ መሀመድ ጸሐፊ ትዕዛዝ ስለ ኦሮሞም ሆነ አሁን በጽሁፍህ ስለጠቀስከው እምነት አንዳች ነገር ያልጠቀሰው ለምን ይመስልሃል? መቸም በወቅቱ ባላንጣዎቹ ለነበሩት የክርስቲያን ነገስታት አድልቶ ነው እንደማትለኝ ተስፋ አለኝ። ሀቁ ወዲህ ነው! አሁን ተወረርኩ እያልክ የምትለፍፈው መሬትን ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በፊት አታውቀውም። ታሪክን እናውራ ካልን እኛን በሚመቸን መልኩ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያለን ታሪክ ብቻ ቆርጠን አንናገርም። ታሪክን በታሪክነቱ እንደወረደ እንናገራለን እንጅ። ነጭ አሜሪካውያን ከተለያየ የአውሮፓ ቦታዎች አሜሪካ መስፈር ሲጀምሩ ከቀያይ ህንዶች ዘንድ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር። መረር ያሉ ጦርነቶችም ተደርገዋል። በስተመጨረሻ ነጮቹ አሸንፈው አሜሪካን ሞሏት። ቀያይ ህንዶች አናሳዎች ሆኑ። ነጭ አሜሪካውያን ግን ቀያይ ህንዶችን ገልብጠው “ሰፋሪ” አይሏቸውም ነባር አሜሪካውያን (Native Americans) ነው የሚሏቸው። ተመሳሳይ ሁኔታ በአርጀንቲና አውስትራሊያ ካናዳ ብራዚል እና ሌሎች ቦቻዎች ተከውነዋል። ታሪኩን ግን ፈጽሞ አይክዱትም። በጸሐፊው እና መሰሎቹ ግን ተመሳሳይ ታሪክ እያላቸው ተገላቢጦሹን መናገር መርጠዋል። አፈታሪክ የታሪክ አንዱ አካል ቢሆንም በማንኛውም መመዘኛ ግን በጽሁፍ ከሰፈረ ታሪክ ጋር ሊወዳደር አይችልም። በሚገርም ሁኔታ ግን ጸሐፊው “According to Oral tradition; Oromo Oral literatures” እያለ የመከራከሪያ ነጥቦቹን ማስቀመጡ ነው።

ኢረቻ በዓል 2010 ዓ.ም

ጥያቄ ፭

“የኦሮሞ አገር (The Oromo Country)”?

ጸሐፊው ሙሉ ጽሁፉ ላይ “የኦሮሞ አገር” እያለ ጀምሮ “የኦሮሞ አገር” ጨርሷል። እዚህ ጋር ብዙ ጥያቄ አለኝ
“የኦሮሞ አገር” ወሰኑ ከየት እስከየት ነው? የኦሮሞ አገር ፕሪዚዳንቱ ማነው? “የአገሩ” የመንግስት መዋቅርስ አህዳዊ ነው ወይስ ፓርላመንታዊ? ይህ የተባለው “የኦሮሞ አገር” እንደተባለው ቅኝ ግዛት ላይ ያለ ከሆነ ቅኝ ከመያዙ በፊት ስሙ ማን ይባል ነበር። ስለዚህ አገርስ የታሪክ ድርሳናት ምን ይላሉ? ነገስታት ነበሩት? መልሱ ሌንጮ ለታ ያሰመረው ካርታ ነው ብትለኝ አልሰማህም። ሌንጮ ለታ ያቀለመውን “የኔ ነው” የሚል ሌላ አካል ካለስ? መልስ የሚሰጠኝ ባገኝ 15 ገጽ የሚረዝመውን የዶ/ር መኩሪያ ቡልቻ ጽሁፍ አንብቦ የጨረሰው ወፍራሙ ቆዳየ ያንኑ ለማንበብ ዝግጁ ነው።

ማሳሰቢያ

የየትኛውም ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓል ተቃዋሚ አይደለሁም። የምቃወመው የምናከብረው የኛ የምንለው በዓል ሲከበር የሌሎችን ጭቃ በቀባ መልኩ ሲሆን ነው። ዶ/ር መኩሪያ መሰረት የለሽ ጽሁፉን መሰረት ለማስያዝ መሰረታዊ የምንላቸውን ታሪካዊ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶቻችን ላይ በቀላሉ ሊታይ የማይችል የማጠልሸት ስራ ሰርቷል።

ምንጭ፡ ልሣነ ዐማራ- Amhara Press