የወሎ ጉዳይ!!

Print Friendly, PDF & Email

(Damtew Neftegnaw )

ትንሽ ስለወሎ ላዉጋችሁ።

እንደሚታወቀው የወሎ ህዝብ ዘር ሃይማኖት ሳይለየው ከሁሉ ጋር ተዋዶ እና ተዛምዶ የሚኖር ህዝብ ነው። ወሎ ትግራይ ቢሆን ኖሮ በዚህ የፍቅር እና ተሳስቦ መኖር ባህሉ በዩኔስኮ በተመዘገበ ነበር። የወሎ ሙስሊሞች የአዝእርት በአል እያሉ የጊዮርጊስን እና የአቦ ባእላትን ያከብራሉ። ጸበል ይጸበላሉ። የወሎ ክርስቲያኖች መስጂድ ያሰራሉ። ከሰው ጋር ከተጣሉ በሸህ ተማምለው እርቅ ያወርዳሉ።

1. ወሎ እና ህወሃት

ይህ ከሁሉም ዘር እና ሃይማኖት ጋር በፍቅር እና በሰላም የሚኖርን ህዝብ ህወሃት እንድህ እንድህ አድርጎ በድሎታል ብሎ ለመዘርዘር መጸሃፍ ካላሳተምኩ በዚች አጭር ጽሁች መዘርዘር አዳጋች ነው። ወሎ ላሊበላን እና ግሸን ማርያምን የመሳሰሉ ድንቅ የቱሪስት ሃብት ይዛ ለምን አስፓልት አልተሰራም ሲባል “ህዝቡ በአዉሮፕላን እንድጠቀም ለማበረታታት ነው” የሚል አሳፋሪ አስተዳደር ያላት ወሎ፣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር መልካም ስም ከነበራቸው ተቋማት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማእከል ለምን ተደካመ ሲባል ይህን ጥያቄ ደግመህ ካነሳህ ትታሰራለህ የሚል የክልል አስተዳደር የሚመራት ወሎ፣ በመንግስቱ ሃ/ማርያም ዘመን የነበሩት ደኖች ተራቆቱ እንክብካቤ ይደረግላቸው ሲባል ዛፎቹን ቆርጣችሁ ለማገዶ እንጨት ተጠቀሙ የሚል ሃገር መሪ አዝላ የምትኖር ወሎ፣……. በእንድህ አይነት ሁኔታ ከእንግድህ ምን ይጠየቃል? ምንስ መልስ አለና? እንደው መንግስትስ እረስቶናል ግን እንደ አላሙድን ያሉ ልጆቻችንስ ለምን ችላ አሉን የሚል ጥያቄ በተለይም ወልድያ አካባቢ ይዘወተራል እና እሱን እንመልከት።

ቆንጆዎቹ የወሎ እህቶቻችን

2. ወሎ እና አላሙድን

መቸም በወሎ ምድር እንደ አላሙድን ያለ አወዛጋቢ ግለሰብ የለም ብል ግነት አይሆንም። ብዙ ደጋፊ, ብዙ ተቃዋሚ። በተለይ ወልዲያ አካባቢ የአላሙድን የቅርብ ዘመዶች ስለሚኖሩ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል። በርግጥ ግን አላሙድን ያስተማረችዉን ወልድያን እረስቷታል? እስኪ በአፋችን ምራቅ እስኪሞላ ድረስ ሲያስጎመጁን የነበሩትን የአላሙድን የወሎ/ወልድያ እቅድ በትንሹ ላጫውታችሁ።

ሸህ አላሙድን የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቱን የተማረበትን በወልድያ ከተማ የሚገኘዉን የእትጌ ጣይቱ ት/ት ቤት አሳድሳለሁ አለ። የወልድያ ልጆች ት/ት ቤታችን በዘመናዊ መልኩ ሊሰራ ነው ብለን ፈነጠዝን። ደስታችን ግን ዘላቂ አልነበረም። በቀናት ልዩነት ዉስጥ “ለታሪክ ተቆርቋሪው” መንግስታችን እንድህ አለን፡ “ታሪካዊ ት/ት ቤት ስለሆነ ታሪኩን ለማስቀጠል ሲባል መታደስ የለበትም” ። የጉድ ሃገር ታሪክን ለማስቀጠል ሲባል ት/ት ቤቱ በአናታችሁ ላይ ይፍረስ እንጂ አይታደስም!? ድንቄም የታሪክ ተቆርቁሪ፡፡

እሺ ታድያ ልጃችን የለገሰዉን ገንዘብ ምን ልታደርጉት ነው? የሚል ጥያቄ ተነሳ። አላሙድንም አንደ ነይቱ ብያለሁ እና ለወልድያ ከተማ የወስጥ ለዉስጥ መንገድ 12ኪ.ሜ እሰራለሁ አለ። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው። ወልድያ ዉስጥ 12ኪ.ሜ የዉስጥ መንገድ, ዘመናዊ ስፓልት! ደስ ሲል! በእኛ ሰፈር ሁሉ ይገባል ማለት ነው! ከእንግድህ ወደ መልካ ቆሌ ት/ት ቤትም ይሁን ወደ መልካ ቆሌ ወህኒ ቤት ስንሄድ ጭቃ የለም ማለት ነው እያልን ፈነጠዝን። 12ኪ.ሜ እያሰብን 12 አመት ሞላን። ቄሱም ዝም መጸሃፉም ዝም።

መቸም የወሎ ህዝብ ሁሉን በትግስት ማሳለፍ ያዉቅበታል አሁንም በትግስት ሲጠብቅ መንገዱ ተረስቶ ሌላ ቃል ተገባለት። የወልድያ ከተማ ከንቲባ እንድህ አለ፡ “የከተማችን እንቁ ልጅ ሸህ ሁሴን አሊ አላሙድን በጀነቶ በር የቆርቆሮ ፋብሪካ ሊያስገነባ ነው።” ህዝቡ በደስታ ፈነደቀ። እንደዉም ይሄኛዉ የስራ እድል ስለሚፈጥር ጥሩ እቅድ ነው። የእስካሁኑን ሊክሱን ነው ተባለ። አመታት ተጠበቀ አሁንም ወፍ የለም።

ደጉ የወሎ ህዝብ አሁንም በተስፋ ይጠብቃል። እንድህ እንድህ እያለ ምርጫ 97 ደረሰ። የአላሙድንም ጉዳይ በወሎ በተለይም በወልድያ እና አካባቢዋ ትልቅ የመከራከሪያ አጀንዳ ሆነ ። ምርጫው ሲቃረብ የዞኑ አስተዳደሮች (እራሳቸውን ያስተዋወቁን የብአደን ተጠሪ በለው ነው ፡) ) ሰበሰቡን። እንደተጠበቀው የአላሙድን ጉዳይ ከታዳሚወች ተጠየቀ። ከእትጌ ጣይቱ እስከ የዉስጥ ለዉስጥ መንገድ፣ ከቆርቆሮ ፋብሪካ እስከ አምቡላንስ በልጃችን የተገባዉ ቃል የት አደረሳችሁት? መልሱ አስቂኝ ነበር፡ ይህ የግል ባለሃብት (private) ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን በቅርቡ መቻሬ ሜዳ ላይ (አሁን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተሰራበት) የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንደሚከፍት መረጃው አለን አሉን። ዛሬ ላይ ይህ ቃል የተገባ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ትግራይ ላይ ተገንብቷል።

3. ምርጫ 97፣ ትግሬ እና ወሎ

የወልድያ ከተማን አንድ ቀን ትግሬወች የእኛ ናት እንደሚሉ ስጋት ያደረብኝ በምርጫ 97 ነው። በወቅቱ በቅንጂት የወጣት ክንፍ እንቀሳቀስ ነበር እና ብአደን ወልድያ ላይ ሰልፍ በጠራበት ቀን እንድህ የሚል መመሪያ ተሰጠን። “ዛሬ ብአደን ሰልፍ ስለጠራ እና ሆን ብለው ሰልፉ በእኛ ቢሮ በኩል እንድያልፍ ስላደረጉት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳታደርጉ የምርጫ ምልክታችሁን ይዛችሁ ከቢሮ ፊት ለፊት መቆም ትችላላችሁ።” ….. ሰልፉ ተጀመረ። ሰልፈኛው ወደ እኛ እየቀረበ መጣ።
የማየዉን ነገር ማመን አቃተኝ። ከገመትኩት በላይ እጂግ በጣም ብዙ ሰው ወጣ። ሰልፈኛዉ እኛ ጋር ደረሰ። አሁንም በጣም ግራ ገባኝ። ሰልፈኛው ዘፈን፣ ጭፈራ፣ ዳንኪራ ያቀልጠዋል። ሁሉም ነገር በትግርኛ። ሁሉም አለባበስ የትግሬ!! እንዴ ? ወልድያ ነው ያለነው አይደል? አልኩት ጓደኛየን!! ዝም አለኝ!! እኔምልህ ይህ ሁሉ ትግሬ እዚች የኛ ወልድያ ከተማ ላይ ነው ሚኖረው? አልኩት መልስ አልሰጠኝም። እረ ቆይ “ሰልፍ የጠራው ብአደን ነው ህወሃት?” “ወልድያ ላይ የሚወዳደረው ብአደን ነው ህወሃት?”

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወልድያን የብሄር ሁኔታ ማስተዋል ጀመርኩ። ለካ የኛዋን ወልድያ እነሱ ናቸው የሚኖሩባት። ለካ የእትጌ ጣይቱዋ ወልድያ የነዜናዊ አስረስ ልጆች መፈንጫ ሆናለች። የሚገርመው አሁን ላይ ሳስታዉስ ለምን እንደሁ ባላቅም ከትግራይ ክልል መጥተው ወልድያ ሃይስኩል የሚማሩ ልጆች ነበር። ከተማዉን እማ ተዉት። የወልድያ ፋይናንሺያል ሴንተር (financial center) የሆነችዉ አድያጎ ብትሄዱ አማርኛ እንደ እንጀራ ይርባችኋል። ሁሉም የንግድ ቦታወች የትግሬወች ናቸው። ከመናሃሪያ እስከ ፒያሳ ብትሄዱ ከትናንች የሃገር ልብስ ሱቆች ጀምሮ እስከ ወርቅ ቤቶች ድረስ መገበያያው ትግርኛ ነው። እንደው ሌላዉን ተውት እና ምስኪኑ የወሎ ህዝብ ከከተማዋ ጫፍ ተወርዉሮ በቲንፋዝ እና ጎንደር በር ሲኖር መሃል ከተማ ላይ ቤት ሰርተው የሚኖሩት እነሱው ናቸው።

4. ወሎ እስከ አሰብ ወይንስ ትግሬ እስከ አላ ዉሃ ?

እኔ የታሪክ ባለሙያ አይደለሁም። እንደው እንደሆቢ አንዳንድ መጽፋፎችን ከማንበብ እና ከአባቶቻችን በማገኘው መረጃ ግን የወሎ ግዛት እስከ አሰብ ወደብ እንደነበር እሰማለሁ። የሰሞኑ ትግሬወች ደግሞ የለም የእኛ ድንበር እስከ አላ ዉሃ (ወልድያ አካባቢ የሚገኝ ወንዝ) ነው ሲሉ እሰማለሁ። መቸም ይህ ሁሉ ጥረት በግማሽ የወሰዱትን የራያ መሬት ለማጠቃለል እንደሆን ግልጽ ነው። ይህን ለማሳካት ደግሞ እየሄዱበት ያለው መንገድ እጂግ አደገኛ ነው እና ሊታሰብበት ይገባል። እስኪ በዝርዝር እንየው:

የመጀመሪያው ሙከራ በትሮይ ፈረሳቸው በብአደን ነው። ብአደን በወሎ ህዝብ ላይ የሚያደርሰዉን በደል መዘርዘር ለቀባሪዉ ማርዳት ነው ። ከ230 አመት በላይ እድሜ ያላት የወልድያ ከተማ እና ከወልድያ በ50ኪ.ሜ ርቀት የምትገኘው የራያ ቆቦ ከተማ ዛሬ ላይ በዉሃ እጥረት, በመብራት መቆራረጥ, በአስተዳደር በደል ህዝቡ ተማሯል። ይህን በደሉን የትግሬ ጎረበቱ ጋር ሲያወራ እንድህ የሚያደርገን እኮ ብአደን ነው! ብአደኖች እኮ የጎጃም እና የጎንደር ስብስቦች ናቸው። እስኪ ባ/ዳርን ተመልከት ? ለምድን ነው ወልድያን የረሷት የሚል መርዛማ መልክት እየተሰራጨ እንደሁ ስንቶቻችን እናዉቅ ይሆን?

ይህን የሚያጠናክረው እና ሆን ተብሎ እየተሰራበት እንደሁ የሚያሳየን ደግሞ የራያ ቆቦ እና የራያ ዘቦን ከተሞች ማነጻጸር ነው። በትግራይ ስር የተጠቃለለው ራያ ዘቦ ከአማራ ክልል አዋሳኝ ከተሞች የተሻለ ተጠቃሚወች ናቸው። በአቅራቢያቸው የሚገኙ የራያ ቆቦ ነዋሪወች ደግሞ ጤናቸዉን እንኳን መጠበቅ አቅቷቸው በተላላፊ በሽታ እያለቁ ነው። ህዝብ አቤቱታ ሲያሰማ የሚሰጠው መልስ ደግሞ “ብአደን ጎጃምን እያለማ እናንተን እረስቷችኋል” የሚል ነው። ይህ ሆን ተብሎ አማራን መከፋፈል እና ወደ ትግራይ ብትጠቃለሉ የተሻለ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ ለማለት ነው።

አማራ ሆይ በተባበረ ክንድ ወሎን እናድን!