በወያኔ አገዛዝ ብሔርህ ነው ዜግነትህ ተብሎ ተኮትኩቶ ያደገ ወጣት “ኢትዮጵያዊ” አይደለሁም ማለት ጀመረ!

Print Friendly, PDF & Email

ብሔርህ ነው ዜግነትህ ሲባል የኖረ ትውልድ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብሎ አረፈው፡፡ ይህ መንገዱ የት እንደሚያደርሰን ማሳያ ይመስለኛል፡፡

(ስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ)

የዩኒቨርሲቲ ምደባ ይፋ ሆኖ 400 ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ አይደለሁም በማለታቸው እንዳልተመደቡ ሰማን፡፡ እንግዲህ አስራ ሁለት ዓመት የደከመ ተማሪ እንዲህ ያለውን ቅጽ ሲሞላ የሚመጣበትን በደንብ የሚያጤነው ይመስለኛል፡፡

ግን አልፈራም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብሔሩ ከዜግነቱ በላይ እንዲደምቅ ሲነገረው ያደገ አዲሱ ትውልድ ነው፡፡ መንገዱን የት ድረስ እንደምንሄድበት ማሳያ ይመስለኛል፡፡

EBC ከላይ እንደዘገበው 400 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዜግነታቸው “ኢትዮጵያ” አይደለም ብለዋል።

ርቀቱንም ጥልቀቱንም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ አጋጣሚ ነው፡፡ መንግስት አራት መቶ አስራ ሁለት አመት ኢንቨስት ያደረገበት ተማሪ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ስላለ በምደባው አልተካተተም ብሎናል፡፡ ይሄም ቢሆን ግን ተጠያቂ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያዊ ያልሆነን ሰው አስራ ሁለት ዓመት አንድ ዜጋ የሚያገኘውን ጥቅም በመስጠት አስተምሮ አሁን ማግለል አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያዊ አይደለንም ቢሉ እንኳን ያጭበረበሩ የውጪ ዜጎች ተብሎ ክስ መከፈት አሊያም ልጆች ሆነው የተሳሳቱ ተብሎ መታለፍ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከትርኢቱ የምንማረው ነገር ግን አለ፡፡

የየክልሉን ህዝብ መዝሙር ሲዘመር ያደገ ትውልድ ሀገር የሚለውን ምሰሶ ልብ ሳይለው ዜግነት ምን እንደሆነ እስካይገባው፤ አሊያም እስኪጸየፈው ያደረሰውን ጉዳይ ልብ ብሎ መመርመር፡፡

ብሔርህ ዜግነት ነው ከተባለ ትውልድ ይሄን ማግኘት የተዘራውን የመሰብሰብ ያክል የማያሻማ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

ይልቁንስ ከዛሬዎቻችን ነገን እንይ፤ ነገን አለማየት የማንወዳቸው እና የማንፈልጋቸው ዛሬዎችን እያገናኘ አሸማቆናል፡፡

መስከረም ጠብቶም አዲስ ነገር መስማት ብርቅ አይደለም፡፡ አምና ያልነበረ አዲስ ነገር ዘንድሮ እየሰማን ጉዞ ቀጥለናል፡፡ ወንድማማች እስካንመስል የሚያጨካክነን፤ ታቦታቱን ሳይቀር በዘር ተከፋፍለን የጋራ ነገር ያሳጣን መንገዱ ይመስለኛል፡፡

እናም ተማሪዎቹ ኢትዮጵያዊ አይደለንም በማለታቸው የሚለው ቃል ዝም ብሎ የሚታለፍ አይደሉም፡፡

የሚያስደነግጥ ነው፡፡

ለምን ይሄን ማለት ፈለጉ?

ለምን ጨከኑ?

እንደማይመደቡ አሊያም ሌላ ርምጃ ሊኖር እንደሚችል እንዴት አላወቁም?

ተሳስተውስ ከሆነ ቅጽ አንብቦ መረዳት ያቃተውን ትውልድ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ እስከማድረስ የከሰረነው በምን ምክንያት ነው?

እንደኔ እንደኔ ልጆቹ የታሪክ መማሪያዎች፤ የጥያቄ መልስ መፈለጊያዎች መነሻ ይመስሉኛል፡፡ እናም ሀገርም ወገንም እኛም ራሳችንን እንጠይቅ፡፡

ምንጭ. DIRETUBE