ትግርኛ ቋንቋና ራያዎች ላይ እያሳደረው ያለው በደል

Print Friendly, PDF & Email

ሃምዚ ሃምዚ ብትይ መች ሰማሻለሁ
ባማርኛየ አውጊኝ እንጫወት እንደሁ።

(በEyasu Breneto)

Mengistu Zegeye በትግርኛው አገር እንደ ወላጆቹ በአማርኛ ጨፍሮ፡ በአማርኛ ዘፍኖ መምጣቱን አወጋን!! ክልል አንድ ራያ ላይ አማርኛ እየተናገሩ በትግርኛ መማርና መተዳደር ቅለቱና ክብደቱ መለኪያው ኪሎ ወይስ ሜትር? በአማራው ክልል አዲስ ሪፈረንደም የሚያዝ ልበ-ቡቡ መንግስት እነዚህን የኛን ወንድሞች ጉዳይስ በነካካ እጁ ቢቀባቸው ምን ይለዋል?? “ቋንቋ እና ትምህርት በራያ” በሚል ርእስ Eyasu Berento በ 15/06/2008 በዚህ የፌስቡክ ቀበሌ ትዝብቱን አካፍሎናል። የሃሳቡ መግቢያ ሰፋ ያለ ሰለነበር ቆርጨዋለሁ። እያ በጠቀሳቸው የራያ ቀየዎች የሚደርስባቸው በደል የውሸት እየኖሩ የእውነት የመሞትን ያክል እኩል ነው። እነዚህ አፋቸውም ልባቸውም አማርኛ የሆኑ የሰጋ ወንድሞቻችንንና ዜጎቻችንን በትግርኛ የቅኝ ግዛት ማነቆ ማበት በቁም ከመግደል በምን ይለያል? እያሱን ቀጥሎ አንብቡት!!

“በአንዳንድ የአማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ የሚኖሩ የራያ ታዳጊዎች ሁኔታ ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ አስገደደኝ። እኔ ተወልጄ ያደግሁበት የራያ ክፍል ማህበረሰቡ ሙሉ በሙሉ አማርኛ ተናጋሪ ነው። በሌሎቹ የራያ ቦታዎችም የራያ ህዝብ ትግርኛ (የራይኛ ዘዬ ያለው)፣ አፋርኛ፣ ኦሮምኛ (በጣም ቢመናመኑም)፣ አማርኛ (ከመደበኛው የጎጃም ወይም የጎንደር ዘዬ እና ይዘት የተለየ)፣ አገውኛ እና ሌሎች ቋንቋዎችን ተናጋሪ ነው። የማህበረሰቡ የኑሮ ዘይቤ ከፊል አርብቶ አደር በመሆኑ ከአፋሮች ጋር በክፉም በበጎም የመገናኘት ታሪክ ያለው ነው። በእርሻ ምርቱም ከትግራይ እና ከአማራ ክልል የሚመጡ “ዘመናዊ” ነጋዴዎች ጋር ይገናኛል። እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ የኑሮ ዘይቤ ያለው ሲሆን በዘመኑ የፖለቲካ ፍልስፍና (ፌደራሊዝም) አስተዳደር ራያ ራዩማ ለሁለት ተከፍሎ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች በወረዳነት ታቅፏል።

የራያን ታሪክ፣ ባህልና ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት በክብሮም አሰፋ “የራያ ህዝብ ታሪክ ና ባህል” (ርእሱን እርግጠኛ አይደለሁም ከሦስት ዓመታት በፊት ያነበብኩት) የሚለውን እና በዓለሙ ካሳ እና ሲሳይ መንግስቴ “የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄና የማእከላዊ መንግሥታት ምላሽ: ከአጼ ዮሃንስ፬ኛ እስከ ኢህአዴግ” የሚሉትን መጻህፍት እንድታነቡ እጋብዛለሁ።

ወደ ትምህርቱ እንምጣ። መንግስታችን ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው የልማት መርሃ ግብራት መካከል ትምህርት ቤቶችን መገንባት አንደኛው ነው። እናም በያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ በሚባል ሁኔታ በራያ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ትምህርት ቤቶች በዋናነት የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ በሁሉም (በከፊል ተብለው ከተገለጹት ውጭ) ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ፍጹም አማርኛ ተናጋሪ ከሆነው ማህበረሰብ የወጡ ናቸው። በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመግባቢያ (የመማሪያ) ቋንቋ ደግሞ ትግርኛ ነው። ትምህርት ቤቶቹን በመዘርዘር በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ችግር እና ህገ መንግስቱን እንዴት እየተገበርነው እንደሆነ የሚያሳይ የመወያያ ሃሳብ ለማቅረብ እወዳለሁ። ሁሉም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው አብዝሃኞቹ እስከ 8ኛ ክፍል። ያንዳንዶቹን ያሉበትን አካባቢስም እንጂ ሙሉ ስማቸውን አላውቀውም።

1. ቡታ መርፈታ
2. ኡላጋ
3. ኢዮብ (ባላ)
4. አድ አርባእቴ (አድ ነጮ)
5. ደረኢታ (በከፊል ትግርኛ ተናጋሪ)
6.ጉባጋላ
7. አዲስ ቅኝ ወይን ቃርሶሌ (በከፊል)
8. ቆጥቆጤ
9. ህብረት (በከፊል)
10. ኩቢ ድርባ
11. ዋጃ
12. ሰሌን ውሃ
13. ዲንጋ ቀበሌ
14. ጥሙጋ
15. አየር ማረፊያ(በከፊል)
16. ሃርሌ(በከፊል)
17. አላማጣ ያሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች (ከ4 ባላይ ናቸው- በከፊል)
18. ፋጫ (በከፊል)
19. ቂልጦ (በከፊል)
20. አሳዮ (በከፊል) ወዘተ ዝርዝሩን እናንተ ጨምሩበት። ሌላም አስተያየት ካላችሁ ለመታረም ፈቃደኛ ነኝ።

ከትምህርት ቤቶቹ መስፋፋት ጋር አንዲት ተቃርኖ ላክል እና ልለፍ። በተለይ በቡታ መርፈታ፣ ኡላጋ፣ ጉባጋላ፣ ቆጥቆጤ፣ ባላ፣አድነጮ እና ቂልጦ አካባቢ ያሉ ልጆች ሃይስኩል ለመማር ከ15 ኪሎሜትር በላይ መጓዝ ወይም ተከራይቶ ስንቅ ቋጥሮ መማር ይኖርባቸዋል። ቢያንስ ከ6 በላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጋቢ እያለ ባላ ላይ ሃይስኩል ባለ መከፈቱ ምክንያት ብዙዎቹ የድሃ ልጆች ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ ማየት የተለመደ ነው። ያካባቢው ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ይህችን ነገር ቢያስቡባት? እላለሁ።

እንግዲህ ከላይ የዘረዘርናቸው ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ ህጻናት የሚማሩ በትግርኛ ቋንቋ ነው። የዛሬን አያድርገውና ቀደም ባለው ጊዜ የነበርነው አብዝሃኛዎቹ ተማሪዎች ትምህርት ስንጀምር እድሜያችን ትልቅ ከመሆኑም በተጨማሪ ትምህርት ወዳድና በጉጉት የምንማር ስለነበርን በትግርኛ ቋንቋ የተጻፉርን መጻህፍት ትርጉሙ ቢከብደንም እንዳለ ሸምድደን (በነገራችን ላይ የራያ ልጆች ቀለሜዎች ናቸው የሚባል ሃሜትም ነበረ) እንይዘው ነበር። ፈተናውንም በቀላሉ ማለፍ እንችል ነበር። ያሆኖቹ ህጻናት ግን በዚህ የተሰላቸ ትውልድ የቋንቋው ባይተዋርነት ታክሎበት ብዙዎቹ እንዲሁ ለሪፖርት ሲባል ተገፍተው ያልፉና ከ8ኛ ክፍል በላይ መዝለቅ ከብዷቸዋል። ትግርኛን እንደ ቋንቋ ራሱን በቻለ ትምህርት የሚማሩ ሲሆን ከእንግሊዝኛ እና አማርኛ ውጭ ሁሉንም ትምህርቶች የሚማሩ በትግርኛ ቋንቋ ነው። እንዲያውም አንዳንዴ የቤት ሥራ ሲሰጠን ወጉ ደርሶን ወላጆቻችንን ስንጠይቃቸው “ልጄዋ ትግርኛ መች አውቃለሁ።” በማለት ይመልሱልን እንደነበር አስታውሳለሁ በተለይ ትግርኛን እንደ ቋንቋ ስንማር አንዳንድ ቅኔዎች፣ አባባሎችን፣ የዘፈን እና የለቅሶ ግጥሞችን፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ስንጠየቅ መመለስ ይከብደን እንደበር አይዘነጋኝም።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የትምህርትም ሆነ የስልጠና እድል ለማግኘት በምንወዳደርበት ወቅት ከእንግሊዝኛ፣ ሒሳብ እና ሥነ ዜጋ ትምህርቶች እኩል የትግርኛ ትምህርት ውጤትም እንደ መስፈርት የሚወሰድ ስለሆነ 10ኛ ያጠናቀቁ ያካባቢው ልጆች በትግርኛ ትምህርት ውጤት ብቻ እድሉን እንደሚያጡት ብዙ ምስክሮች ማግኘት አያዳግትም። እኔ ራሴ 10ኛ ክፍል ከ3.5 በላይ ውጤት ቢኖረኝም ከዝቅተኛ ውጤቶቼ አንዷ ትግርኛ ነበረች (ዛሬ ቢሆን ኖሮ አሳያት ነበር!) አንድ ገጠመኝ ላክልና ልቀጥል። አንድ ከምዕራብ ትግራይ የሄደ አስተማሪ “እንዴት ነው ተማሪዎቻችን ትግርኛው ይገባቸዋል?” ብዬ ለጠየቅሁት ጥያቄ ሲመልስልኝ “ባክህ ተገደን ነው እንጂ ልጆቹ አልቻሉትም። ይልቅ እኔን አማርኛ በደንብ እያስተማሩኝ ነው::” በማለት ነበር ከልቡ የመለሰልኝ። አንድ ኬንያዊ ጸሃፊ እና ፈላስፋ ስለ ኮሎኒያሊዝም ባተተበት ድርሳኑ “We are africans at home and european at school. That means we are bodyless minds at school and mindless bodies at home” በማለት ነበር ትምህርት ቤት ላይ በእንግሊዝኛ ለማሰብ መገደዳቸውና እና ማህበረሰባቸው ዘንድ ደግሞ ኬንያኛ የህይወት ምህዋራቸው እንዴት ሰዎቹ አፍርካ ውስጥ የሚኖሩ አውሮፓዊውን ጭንብል እንዲላበሱ ይደረጉ እንደነበር የገለጸው። የራያም ህጻናት ጉዳይ ይኸው ነው። ትምህርት ቤት ማይ፣ እንስሳ ዘቤት፣እንጨይቲ … እያሉ እንዲሸመድዱ ይደረጋል። ቤተሰቦቻቸው ጋር ደግሞ ከብቶቹን አሰማራ፣ ዉሃ ቅጂ፣ እንጨት ስበሪ እየተባሉ የህይወት መስተጋብራቸን ይመራሉ። ባጭር አማርኛ ትምህርት ቤት በትግርኛ ያስባሉ እቤት ባማርኛ ይኖራሉ ነው።

ታዲያ ያሆኖቹ መሪዎች እና ቀደምት ጓዶቻቸው መስዋእት የከፈሉለት፣ መንግሥት በህገ መንግሥቱ በግልጽ ያስቀመጠው (አንቀጽ 5፣ 39 ቁ. 2) የቋንቋ እኩልነት እና እያንዳድዱ ወገን በቋንቋው የመማር፣የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ መብት ወዘተ እዚያ ማህበረሰብ ዘንድ እንዴት መተግበር አልቻለም? ስንት ሃገርንና ወገንን የመጥቀም ተሰጥኦ ያላቸው ህጻናት በቋንቋ ምክንያት የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት በር ማንኳኳት ሳይችሉ ሲቀሩስ እንዴት የሚመለከተው አካል ችላ ሊል ይችላል?

እኔ ከዚህ በላይ የገለጽኩት ሃሳብ የተጋነነም የተኳሰሰም አይደለም። በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ ማለት ይቻላል። ግን እንዲሁ የተማሩ ነገር ግን ማንበብና መጻፍ የመይችሉ ልጆችን ማየት ምንኛ እንደሚያሳስብ የሚያውቀው ያውቀዋል። ከላይ ከተዘረዘሩት ትምህርት ቤቶች ባብዛኛዎቹ የስነ ጽሁፍም ሆነ ሌላ ጥበባዊ ሥራዎች የሚቀርቡት በአማርኛ ነው፣ ተማሪዎቹ ክፍል ውስጥ ጥያቄ የሚመልሱት በእናት ቋንቋቸው ነው፣ የሚያስቡት ባማርኛ ሆኖ ሳለ እንዲጽፉ የሚገደዱት ግን በትግርኛ ነው። ይህ ጉዳይ መፍትሄ እስካልተሰጠው ድረስ እዛ አካባቢ ያሚማሩ ተማሪዎችና ትምህርት “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ነው ተግባቦታቸው።

በሰለጠነ መንገድ ለሚደረግ ትችት፣ ማስተካከያ ወይም እርምት፣ ተጨማሪ ሃሳብ በሙሉ ልብ ለመቀበል ጸሃፊው ዝግጁ ነው። በማንኛውም ሃሳብ ሙሉ ሃላፊነቱን ይወስዳል።

***********

የራያ ትግርኛ (ራይኛ) Vs የራያ አማርኛ

(አማረ ጉበና)

በዚህ ሳምንት በዚሁ የፌስቡክ ገጽ ላይ አንዳንድ ወገኖች የራያ ትግርኛ ‘ራይኛ’ መባል የሚኖርበት ከሆነ የራያ አማርኛም ሌላ ስም ሊሰጠው ይገባል የሚል አራምባና ቆቦ የሆነ አይነት አስተያየት ሰጥተው አንብቤያለሁ:: የራያ ትግርኛ ወይም ራይኛ ከትግርኛ ቋንቋ ጋር ያለው ልዩነት በስፋቱ በተጨባጭ የሚታይ ስለሆነና ይህም ልዩነት በሁለቱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በቋንቋ እስካለመግባባት የሚያደርሳቸው እንደሆነ ይታወቃል።

በመሆኑም የራያ ትግርኛን ራይኛ ብለን ብንሰይመው ትክክለኛውን መጠሪያ አግኝቶ ራሱንም በቀጣይነት ለማሳደግ ያስችለዋል ሲባል እኮ የትግርኛ ቋንቋን በመጥላት ወይም ከትግርኛ ጋር በጨራሽ ላለመቀራረብ ተፈልጎ አይመሰለኝም። በሌላ በኩል የራያ አማርኛን ሌላ ስም ለመስጠት ከተፈለገም ልክ እንደ ትግርኛ ቋንቋ ሁሉ ከአማርኛ ጋር ያለው ልዩነት ተጨባጭና ሰፋ ያለ መሆኑን በምሳሌ አስደግፎ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይኸ ከሆነ ስያሜ መስጠቱ ቀላል ነገር ነው።

ከዛ ውጭ የራያ ትግርኛ ራይኛ ከተባለ የራያ አማርኛም ስያሜው ይቀየርና ሌላ ስም ይሰጠው የሚለው የመከራከሪያ ሀሳብ ጉንጭ አልፋ ሊሆን የሚችል ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል ውሀ የሚያነሳ ሆኖ አይገኝም።

የራያ አማርኛ ከአማርኛ የሚለይበት እና ራይኛ ከትግርኛ የሚለይበት መጠን የሰማይ እና የመሬት ያህል ርቀት እንዳላቸው መገንዘቡ ግን ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም:: ለዚህም ከታች በምሳሌዎች ተደግፎ የቀረበውን ሰንጠረዥ በሚገባ እንመልከት እና በሁለቱም ቋንቋዎች መካከል ያለውን የልዩነት ስፋት ለማየት እንሞከር።